በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች የቆዩ ሃይማኖቶችን እየተዉ ያሉት ለምንድን ነው?

ሰዎች የቆዩ ሃይማኖቶችን እየተዉ ያሉት ለምንድን ነው?

ሰዎች የቆዩ ሃይማኖቶችን እየተዉ ያሉት ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት እናስተምራለን የሚሉ ሃይማኖቶች ወደ 1.7 ቢልዮን የሚደርሱ ተከታዮች አሏቸው። የክርስትና ተከታዮች ቁጥር እንደ ቡዲዝም፣ ሂንዱኢዝም እና እስልምና ካሉት ትልልቅ ሃይማኖቶች እንኳን ሳይቀር እንደሚበልጥ ይነገራል። ይሁን እንጂ የክርስቲያን አገር በሚባሉ በርካታ አገሮች ሕዝቡ ቀስ በቀስ ከሕዝበ ክርስትና ጉያ ሾልኮ በመውጣት ላይ መሆኑን አንዳንድ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደ አብያተ ክርስቲያናት መሄድ እየተዉ ነው። የዓለም የግብረ ገብ ጥናት ፕሮጀክት ዲሬክተር የሆኑትና በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በምርምር ሥራ ላይ የተሠማሩት ሮናልድ ኤፍ ኢንገልሃርት ሃይማኖት በበለጸጉት አገሮች የሚጫወተው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ እንደመጣ ተናግረዋል። ባይብል ሪቪው የተሰኘው መጽሔት እኚህ ሰው የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ከማሽቆልቆሉም በላይ የላቲን አሜሪካ አገሮች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸውን ነፍስ ከጥፋት ለማዳን ሚስዮናውያንን እየላኩ ነው።” በተለይ በሰሜን አውሮፓ በሚገኙ አንዳንድ አገሮች ውስጥ “በሃይማኖት ላይ የደረሰው ውድቀት” አስደንጋጭ መሆኑን አክለው ተናግረዋል። በኖርዌይና በዴንማርክ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር 5 በመቶ ብቻ ሲሆን በስዊድን 4 በመቶ፣ በሩስያ ደግሞ 2 በመቶ ብቻ ነው።

በጀርመን የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከ1984 እስከ 1993 ባሉት ዓመታት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከተመዘገቡት አማኞች መካከል አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር ከ25.3 በመቶ ወደ 19 በመቶ አሽቆልቁሏል። በ1992 እሁድ እሁድ በሚካሄዱት የአምልኮ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ፕሮቴስታንቶች ቁጥር 4 በመቶ ብቻ ነበር። በ1999 ደግሞ “ከአሥር ጀርመናውያን መካከል በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄደው አንዱ ብቻ” እንደነበረ ክርስቺያኒቲ ቱዴይ ዘግቧል።

ዘ ጋርዲያን የተባለው ጋዜጣ በብሪታንያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን የአማኞች ቁጥር አስመልክቶ ሲናገር “በክርስትና ታሪክ እንዲህ ያለ አስከፊ ሁኔታ ተከስቶ አያውቅም” ብሏል። በተጨማሪም “ቀሳውስት ከ1950-2000 ያለውን ግማሽ ምዕተ ዓመታት ያህል እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ዘመን ገጥሟቸው አያውቅም” ሲል አክሎ ገልጿል። ጋዜጣው በታላቋ ብሪታንያ ያለውን የሃይማኖት ሁኔታ በተመለከተ የወጣን አንድ ልዩ ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ አረጋውያንም በተደራጁ ሃይማኖቶች ላይ ያላቸው እምነት እየተዳከመ ነው። “አረጋውያን ዕድሜያቸው እየገፋ በሄደ መጠን በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት እየጠፋ መጥቷል። እየተመናመኑ ለመጡት ጉባኤዎቻችን የጀርባ አጥንት ሆነው የኖሩት አረጋውያን ናቸው ብለው የሚያምኑት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ የብሪታንያ አብያተ ክርስቲያናት በቅርቡ በተደረጉ ጥናቶች የተረጋገጠው ይህ አዝማሚያ በጣም እንደሚያስደነግጣቸው የታወቀ ነው” ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።

ከአውሮፓ ውጪ ባሉ አገሮችም እንዲህ ዓይነት አዝማሚያዎች እየታዩ ነው። ለምሳሌ ያህል አልበርታ ሪፖርት የተሰኘው የካናዳ ጋዜጣ በካናዳ “በታወቁ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የታቀፉ እምነቶችና የአምልኮ ዓይነቶች ከፍተኛ ውድቀት” እንደገጠማቸውና “አንድ በግልጽ የታወቀ ሃይማኖት ከመከተል ይልቅ ራሳቸው ስለ አምላክ የሚሰማቸውን የግል አመለካከትና አስተሳሰብ መከተል የሚመርጡ ካናዳውያን ቁጥር በሦስት እጥፍ ልቆ እንደተገኘ” ገልጿል።

ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥርዓቶች ላይ መገኘታቸው በመንፈሳዊ እንዳበለጸጋቸው ወይም መንፈሳዊ እውቀት እንደጨመረላቸው ሆኖ አይሰማቸውም። መክሌንዝ የተባለው የካናዳ መጽሔት እንዳለው ከሆነ በአንድ የሂንዱዎች የጸሎት ሥፍራ የተገኙ አይሁዶችና ካቶሊኮች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “አሰልቺ የሆኑት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ልባችንንም ሆነ ስሜታችንን ሊነኩት አልቻሉም” ብለዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ለብዙ ዓመታት አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ከኖሩ በኋላ ‘ከቤተ ክርስቲያን ያገኘሁት ትምህርት ምንድን ነው? ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል?’ ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ ተገድደዋል። ግሬግ ኢስተርብሩክ የተባሉት ደራሲ እንደገለጹት “በዘመናችን በምዕራቡ ዓለም ዋነኛው ችግር በቁሳዊ ድህነት ምትክ በሠፊው ተንሰራፍቶ የሚገኘው መንፈሳዊ ድህነት” መሆኑ እምብዛም አያስደንቅም።

አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምእመናን የሚገኙባቸው ብዙ አገሮች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄድ ሁሉ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት በታማኝነት አጥብቆ ይከተላል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል ዚ ኤጅ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ እንደገለጸው በምዕራቡ ዓለም “ሃይማኖታቸውን አጥብቀው የሚከተሉ ክርስቲያኖች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። በብዙዎቹ የአፍሪካ፣ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ብዙ ሰዎች ከክርስትና መጋረጃ በስተጀርባ ባዕድ የሆኑ የጎሳ እምነቶችን ወይም አምልኮዎችን በመከተል ላይ ናቸው። እነዚህ እምነቶች ከክርስትና ትምህርቶች ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸውና የሚጋጩ ከመሆናቸውም በላይ ከበርካታ ዓመታት በፊት የተተዉ ናቸው።”

ብዙ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን አብያተ ክርስቲያናትን ጥለው እየወጡ ያሉት ለምንድን ነው? ትልቁ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሃይማኖትን እንዳሰቡትና እንደጠበቁት ሆኖ ስላላገኙት ነው።

ሃይማኖት ያስመዘገበው መጥፎ ታሪክ

ዘ ጋርዲያን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በ20ኛው መቶ ዘመን በሙሉ ከፋሽዝም ጋር በማበር መጥፎ ታሪክ አስመዝግባለች። በስፔይን ከተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ለጄኔራል ፍራንኮ ያቀረበችውን ውዳሴና በቅርቡ ጄኔራል ፒኖሼን ለመርዳት ያደረገችውን ጥረት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።” ዘ ጋርዲያን አክሎ ሲናገር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሮማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ፓየስ አሥራ ሁለተኛ “በአይሁዶች ላይ የደረሰውን የጅምላ ጭፍጨፋ በይፋ ማውገዝን የመሰሉ ከባድ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ ኃላፊነቶችን በመሸሽ ከ[ሂትለር] ጋር ስምምነት ላይ መድረስን መርጠዋል” ብሏል።

ዚ ኤጅ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ክርስትና በብዙ ሁኔታዎች እንደ ቃሉ ሆኖ አልተገኘም። ክርስቲያኖች ለሌሎች ሰላምና አንድነት ሊያስገኙ ቀርቶ የራሳቸውን የውስጥ ሰላምና አንድነት እንኳ መጠበቅ አልቻሉም። ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መመለስ በሚል ሽፋን የተካሄዱት ከፍተኛ ዘረፋና ወረራ የተፈጸመባቸው በርካታ ጦርነቶች ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ናቸው። እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ከሁሉ ይበልጥ ጎልተው የሚታዩ የክርስቲያን ባሕርያት ናቸው ይባል ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ባሕርያት ለማንጸባረቅ ይጥራሉ የሚባሉት ሰዎች ክርስቲያን ካልሆኑት ሰዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ተጠራጣሪዎችና ለተስፋ መቁረጥ የተጋለጡ ሆነዋል። የሚያሳዩት ፍቅርና ደግነትም ከሌሎች ያልተለየ ሆኗል። . . . አይሁዶች በጅምላ እንዲጨፈጨፉ ያደረገችው የክርስቲያን አገር ነች። በጃፓን ላይ የአቶሚክ ቦምብ በመጣል ከፍተኛ ሽብር የለቀቀችውም የክርስቲያን አገር ነች።”

አንዳንዶች ሕዝበ ክርስትና ከረጅም ዘመን አንስቶ ጠንቃቃነትን፣ መንፈሰ ጠንካራነትን፣ ልከኝነትንና ፍትሕን የመሳሰሉ ባሕርያትን ስታስተምር ኖራለች ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዚ ኤጅ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በአውስትራሊያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የምድርን የተፈጥሮ ሀብት ሊያገኙ ከሚገባቸው ድርሻ በላይ የሚጠቀሙ ሲሆን የራሳቸውን የስስት ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ደካማ በሆኑ የጎረቤት አገሮች ላይ የሚፈጸመውን ብዝበዛ፣ ጭቆናና የተፈጥሮ ሀብት መመናመን አሁንም ድረስ በቸልታ በመመልከት ላይ ናቸው።”

ዚ ኤጅ የሕዝበ ክርስትናን የወደፊት ዕጣ በተመለከተም እንዲህ ብሏል:- “ጤናማና የተስተካከለ ድርጅታዊ መዋቅር እስካልኖረ ድረስ ክርስትና ባለፉት መቶ ዘመናት በኅብረተሰቡ ላይ የነበረውን ሥልጣን መልሶ ማግኘት አይችልም። ይህ እንደ ሰዉ አመለካከት ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ክርስትና በመጪዎቹ ዓመታት ይህን እውነታ መጋፈጡ የማይቀር ነው።”

የተደራጁ ሃይማኖቶች እንዲህ ያለ ብልሹ ሁኔታ የገጠማቸው በመሆኑ ብዙዎች ከአብያተ ክርስቲያናት እየራቁ ነው። ይሁን እንጂ አማራጭ ብለው የያዙት ነገር ፍላጎታቸውን በሚገባ ሊያሟላላቸውና መፍትሔ ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የተንዛዙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የብዙዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያሟሉ አልቻሉም

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቆዩ ሃይማኖቶች ጦርነቶችንና ጨቋኝ የፖለቲካ መንግሥታትን የሚደግፉ በመሆናቸው ብዙዎች እየተዉአቸው ነው

[ምንጭ]

ፎቶ:- age fotostock