በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር በተግባር የታየበት ረጅምና አድካሚ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ፍቅር በተግባር የታየበት ረጅምና አድካሚ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ፍቅር በተግባር የታየበት ረጅምና አድካሚ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

ሂውስተን ክሮኒክል የተባለው ጋዜጣ አዘጋጅ የሆኑት ሪቻርድ ቫራ በቀላሉ የሚገረሙ ዓይነት ሰው አይደሉም። ባለፈው ዓመት ግን በጣም የሚያስገርም ሁኔታ አጋጥሟቸው እንደሚከተለው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸው ነበር:- “እንደዚህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይቼ አላውቅም! ይህ የማይታመን ነገር ነው!” በዩናይትድ ስቴትስ፣ ቴክሳስ ውስጥ የሚገኘው የሂዩስተን ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሊ ፒ ብራውንም እንደዚያው ተሰምቷቸው ነበር። እንዲህ ብለዋል:- “ያከናወናችሁትን በሂዩስተን የሚኖር ሁሉም ሰው ቢያየው ደስ ይለኝ ነበር። በጣም የሚደነቅ ተግባር ነው።” ሁለቱ ሰዎች እየተናገሩ ያሉት ስለምን ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች በሂዩስተን ከተማ ስላከናወኑት የመልሶ ማቋቋም ተግባር ነበር። በዚህ የመልሶ ማቋቋም ተግባር ምን ተከናውኗል? የመልሶ ማቋቋም ሥራ ያስፈለገው ለምን ነበር? ሥራውን ይህን ያህል አስገራሚ ያደረገውስ ምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት እስኪ ታሪኩን ከመነሻው ጀምረን እንመልከት።

ከዚህ ቀደም ሆኖ የማያውቅ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ

ሰኔ 2001 መግቢያ ላይ የቴክሳስ ደቡብ ምሥራቅ ሜዳማ አካባቢ አሊሰን የሚል ስያሜ በተሰጠው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተመታ። ዓርብ ሰኔ 8 የጣለው ዶፍ ዝናብ በ24 ሰዓት ውስጥ በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በትልቅነቱ አራተኛ ደረጃ የሚይዘውን የሂዩስተንን ከተማ 1 ሜትር ያህል ከፍታ ባለው ጎርፍ አጥለቀለቀው። * በጥቂት ሰዓት ውስጥ የውኃው ከፍታ ጨምሮ ወደ ሱቆች፣ ቢሮዎችና በአሥር ሺህ ወደሚቆጠሩ ቤቶች መጉረፍ ጀመረ። በከተማዋ ዙሪያ ባሉት መንገዶች ላይ እንደ ፈረሰኛ ወንዝ የሚፈሰው ውኃ ማለፊያ አጥተው የቆሙትን ትናንሽና ትላልቅ መኪናዎች ሸፈናቸው። የእሳት አደጋ መኪናዎችና ሌሎች የእርዳታ መኪናዎች እንኳን በጎርፍ የተጥለቀለቁትን መንገዶች አቋርጠው ማለፍ አልቻሉም። ሄሊኮፕተሮችና ትላልቅ የወታደር መኪናዎች የሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ተሰማሩ።

በመጨረሻም ሰኞ ሰኔ 11 ሰማዩ ሲጠራ አሊሰን በሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ታወቀ። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑትን ጄፈሪ ግሪን የተባለ ክርስቲያን ሽማግሌና ፍሬዳ ዊሊስ የተባለችውን የባለቤቱን እህት ጨምሮ ሃያ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። * ከዚህም በላይ 70,000 በሚጠጉ ቤቶች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ይህም እስከ ዛሬ በአንድ ትልቅ ከተማ ላይ ከደረሱት የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ የከፋው ሆኗል። እንዲያውም አሊሰን ወደ 5 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ንብረት በማውደም በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ አውዳሚ እውሎ ነፋስ ሆኗል።

አካባቢውን እንደ ጎርፍ ያጥለቀለቁ ፈቃደኛ ሠራተኞች

ሰዎች በሁኔታው በጣም ተደናግጠው ነበር። አንድ የእርዳታ ሠራተኛ እንደተናገረው “አልጋቸውና ምንጣፋቸው በውኃ ርሶ እንዲሁም የልጅነት ፎቶግራፎቻቸውና የልጆቻቸው ፎቶግራፎች በውኃው ተወስደው ነበር።” በሂዩስተን አካባቢ ከሚኖሩት ከ16,000 ከሚበልጡት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ ንብረታቸውን አጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡባቸው ስምንት የመንግሥት አዳራሾችና በመቶዎች የሚቆጠሩ የምሥክሮቹ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንዶቹ ቤቶች ብዙ ሴንቲ ሜትሮች ከፍታ ባለው ውኃ የተጥለቀለቁ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ውኃው እስከ ጣሪያቸው ድረስ ሞልቶ ነበር። በአጠቃላይ ከ80 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ብቻቸውን አልተተዉም። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች አካባቢውን እንደ ጎርፍ አጥለቀለቁት። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

በሂዩስተን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ሽማግሌዎች ውኃው መጉደል ከመጀመሩም በፊት ለሥራ ተሰማርተው ነበር። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ስልክ እየደወልንና ቤታቸው እየሄድን ጠየቅናቸው። በዚያም የጉዳቱን መጠን ለመገመት ቻልን። ሰኞ ሰኔ 11 የተጎዱትን ሰዎች ስም፣ ምን ያህል ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸውና የጉዳቱን ልክ የሚያሳይ የተሟላ ሪፖርት አጠናቅረን ነበር። ከዚያም ሪፖርቱ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተላከ።” ከጥቂት ቀናት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሂዩስተን የሚገኙ ስምንት ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ያቀፈ አንድ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አደራጀና ለመልሶ ማቋቋሙ ሥራ የሚሆን ገንዘብ ሰጣቸው። የኮሚቴው ኃላፊነት ምን ነበር? ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ስሜታዊ ድጋፍ መስጠትና ከ700 የሚበልጡትን የፈራረሱ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች መጠገን ነበር።

በ2001 በሂዩስተን የተቋቋመው የዚህ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ‘ይህንን ግዙፍ ሥራ ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ጥያቄ ከፊታቸው ተደቅኖባቸው ነበር። ለመነሻ የሚሆን እቅድ ለማውጣት በጣም እያመሹ ይሠሩ የነበረ ሲሆን በሂዩስተን ዙሪያ ካሉት ከ160 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችም እርዳታ ጠየቁ። የኮሚቴው ሊቀ መንበር “ወንድሞች ያሳዩት የትብብር መንፈስ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር” ብሏል። “ከ11,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ችሎታቸውን በነጻ ለመስጠት ፈቃደኝነታቸውን ገለጹ።”

ሻጋታውና ፈቃደኛ ሠራተኞቹ

የጎርፍ መጥለቅለቁ ከደረሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በውኃ የራሱ ምንጣፎችንና ቁም ሣጥኖችን፣ የተበላሹ ወለሎችንና ግድግዳዎችን እንዲሁም ከጥቅም ውጭ የሆኑ በሮችንና ጎርፉ ያበላሸውን ማንኛውንም ነገር አንስተው በማውጣት ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች መጠገን ጀመሩ። አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ “እኛን ያሳሰበን የቤቶቹ መጠገን ብቻ ሳይሆን የወንድሞቻችን ጤንነት ጭምር ነበር” ብሏል። ከግድግዳዎቹና ከቁም ሣጥኖቹ ጀርባ መርዛማ ሻጋታ በቀላሉ ሊፈጠር ስለሚችል በመጀመሪያ ቤቶቹ በመድኃኒት መጽዳት ነበረባቸው።

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የፌደራሉ የድንገተኛ አደጋ ተቆጣጣሪ ቢሮ (ፌማ) ተብሎ የሚጠራው ከአደጋዎች ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን የሚከታተል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጉዳት ሳይደርስባቸው ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ከዚያም በፌማ ሥልጠና ያገኘ እያንዳንዱ ምሥክር አሥር ፈቃደኛ ሠራተኞችን ይዞ አደጋ ወደ ደረሰባቸው ቤቶች በመሄድ የተበከለውን ቤት እንዴት በሚገባ ማጽዳት እንደሚቻል ያሳያቸዋል። በቀጣዩ ቀን ሥልጠና ያገኙት አሥሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በተራቸው ከእነርሱ ጋር ሌሎች አሥር ሰዎች ይዘው ይሄዳሉ። አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ እንዳለው “በጥቂት ቀናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ ሥራ እንዴት መከናወን እንዳለበት ተማሩ።” ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ብዙ ስለነበሩ እየተሰራጨ የነበረውን ሻጋታ መቆጣጠር ቻሉ። ቀን ቀን ጡረታ የወጡ ሠራተኞችና ትምህርት ቤት በመዘጋቱ በእረፍት ላይ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ሲሠሩ ይውላሉ። ማታ ደግሞ ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች በእነርሱ ቦታ ተተክተው ሥራውን ይቀጥላሉ። በዚህ መንገድ በስድስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተበክለው የነበሩት ሁሉም ቤቶች ሙሉ በሙሉ ጸዱ።

አንድ ዋና ማዕከልና ሰባት ንዑስ ጣቢያዎች

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ከፍተኛ መጠን ያላቸው የግንባታ ዕቃዎች ገዛ። ሆኖም ይህ ሁሉ ዕቃ የት ሊቀመጥ ነው? የኮሚቴው ቃል አቀባይ እንዲህ ይላል:- “የአንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ችግራችንን ሲሰማ 5,000 ስኩዌር ሜትር ስፋት ያለው መጋዘን በነጻ እንድንጠቀምበት ሰጠን!” መጋዘኑ የግንባታ እቃዎችን ለማስቀመጫ ብቻ ሳይሆን ለቢሮነት ሊያገለግል የሚችል ቦታም ነበረው። መጋዘኑ ብዙም ሳይቆይ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ፈቃደኛ ሠራተኞች ቀንና ማታ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ የሚሠሩበት የመልሶ ማቋቋም ሥራው ዋና ማዕከል ሆነ።

አደጋው ሰፊ አካባቢዎችን የሚሸፍን በመሆኑ በሰባት የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ሰባት ንዑስ ጣቢያዎች ወይም የአካባቢ የእርዳታ ጣቢያዎች ተቋቋሙ። ቅዳሜና እሁድ ላይ እያንዳንዱ ንዑስ ጣቢያ በፈቃደኛ ሠራተኞች ይጥለቀለቅ ነበር። (“የእርዳታ ጣቢያዎች” የሚለውን ሳጥን ተመልከት።) ከፈቃደኛ ሠራተኞቹ መካከል አብዛኞቹ ከዚህ ቀደም በዚሁ አካባቢ የመንግሥት አዳራሾች ሲገነቡ አብረው ሠርተዋል። እንዲያውም በሉዋሲና፣ አርካንሳስ፣ ኦክላሆማና ቴክሳስ ከሚገኙ 11 የተለያዩ የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች የተውጣጡና የግንባታ ችሎታ ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች በሥራው እገዛ አድርገዋል። * በእያንዳንዱ ጣቢያ ውስጥ አናፂዎች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ ቧንቧ ሠራተኞችና ሌሎች የግንባታ ሙያ ያላቸው ሠራተኞች ቀዳሚ ሆነው እየሠሩ ሌሎቹን አሠልጥነዋል።—“የሥልጠና ፕሮግራሞች” የሚለውን ሳጥን ተመልከት።

እቅድ ማውጣትና መረጃ ማሰባሰብ

ፈቃደኛ ሠራተኞቹ የግንባታ ሥራቸውን የሚያከናውኑት ደረጃ በደረጃ ነበር። የግንባታ ቁሳቁሶችን በአራት ዙር ወደየቤቶቹ ከወሰዱ በኋላ እያንዳንዱን ቤት በሦስት ቅዳሜና እሁዶች ውስጥ ጠግነው ለመጨረስ የሚያስችላቸው እቅድ ወጥቶ ነበር። በዚህ መንገድ የመልሶ ማቋቋም ሥራው በስድስት ወራት ገደማ ይጠናቀቃል።

እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚቴው ዝርዝር ጉዳዮችን የሚቆጣጠር፣ የዕቃ ግዢ፣ የዕቃ ማስቀመጫ እና የዕቃ ማጓጓዣ ክፍልን ጨምሮ 22 ክፍሎችን አቋቋመ። ሁሉም ክፍሎች ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ኮምፒውተር ውስጥ ባስገቡት መረጃ ይጠቀሙ ነበር። የጥገና ሥራው ከመጀመሩ በፊት ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ለአሥር ቀናት ያህል አስፈላጊ መረጃዎችን ኮምፒውተር ውስጥ አስገቡ። አንድ የዜና ዘገባ እንደገለጸው “ከፍተኛ የሆነ መረጃ የማሰባሰብ ዘመቻ ነበር።” ሆኖም በእነዚህ አስር ቀናት ውስጥ ብዙ አስፈላጊ መረጃዎች ተሰብስበው ነበር። ኮምፒውተሩ 11,000 የሚያህሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች መቼ እንደሚመጡ፣ ምን ዓይነት ሙያ እንዳላቸው እንዲሁም ከእነርሱ ጋር እንዴት መገናኘት እንደሚቻል ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ ምን ያህል ጥገና እንደሚያስፈልግ፣ የግንባታ ፈቃዱን ዓይነትና ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች በተመለከተ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ይህ የመረጃ ስብስብ “የመልሶ ማቋቋም ሥራው እምብርት” የሚል ስም ተሰጥቶታል።

በአመስጋኝነት መንፈስ ተሞልተዋል

ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች ሻጋታ ከጸዳና እርጥበቱ ከደረቀ በኋላ የግንባታ ባለሞያ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ እያንዳንዱ ቤት እየሄዱ የጉዳቱን መጠን መገምገም ጀመሩ። ቃል አቀባዩ እንደተናገረው “እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን የምስማር ብዛት እንኳ ሳይቀር ያሰሉ ነበር።” አክሎም “በእርዳታ የተገኘውን ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ ማባከን አልፈለግንም” ብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ደግሞ ከከተማው ባለሥልጣናት አስፈላጊውን የግንባታ ፈቃድ አወጡ።

ቀጥሎም በአደጋው የተጎዱት ቤተሰቦች ወደ መጋዘኑ እንዲመጡ ተደረገና እዚያ ካለው ምንጣፍ፣ ቁምሳጥን፣ የወለል ንጣፍና ሌሎች ቁሳቁሶች መካከል የጠፋባቸውን ንብረት የሚተካ ዕቃ እንዲመርጡ ተጋበዙ። በጎርፍ መጥለቅለቁ የተጎዱት ሰዎች የተደረገላቸውን ነገር ሲመለከቱ በጥልቅ በመነካታቸው ባብዛኛው ያለቅሱ ነበር። በኢንሹራንስና በሌሎች መንግሥታዊ ፖሊሲዎች ረገድም ባለሞያ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች በአደጋው ለተጎዱት ሰዎች ምክር ለገሷቸው። ከዚያም ቤቶቹ የሚጠገኑበት ፕሮግራም ወጣ፤ ጥገናውን የሚያከናውነው ቡድን የግንባታ ቁሳቁሶች በሚያስፈልገው ቀን ትላልቅ መኪና ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ያመጡላቸው ነበር። ቤቱ እየተጠገነለት የነበረ የአንዲት እህት ባል ለሚስቱ እንዲህ ብሏታል:- “ወንድሞችሽ የሚደነቁ ናቸው። አንደኛው ቡድን ሲሄድ ሌላኛው ወዲያው ይተካል። ልክ እንደ ንብ ነው የሚሠሩት!”

ለእያንዳንዱ ቤት መሠረታዊ የጥገና ሥራዎች ለማካሄድ ሦስት ቅዳሜና እሁዶች ገደማ ፈጅተዋል። የኮሚቴው ሊቀ መንበር እንደተናገረው “አንዳንድ ጊዜ ግን አምስት ከዚያም አልፎ ስምንት ሳምንት ፈጅቷል።” አብዛኛውን ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ያረጁ ግድግዳዎችን በሚያድሱበት ጊዜ ግድግዳዎቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆን አለመሆናቸውን ያረጋግጣሉ፤ የተበላሸው የግድግዳ ክፍል በደንብ ሳይስተካከል ማደስ አይጀምሩም። አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ እንዲህ ብሏል:- “አንዳንድ ጊዜ የግድግዳዎቹ መሠረት በምስጥ ተበልቶ እናገኛለን፤ ስለዚህ መጀመሪያ ምስጦቹን እናጠፋለን። ቋሚዎቹን ለማስተካከል ብዙ መሥራት ቢያስፈልገንም ቤቶቹን ጥሩ አድርገን አድሰናቸዋል።” ቤቱ በጎርፍ የተጎዳበት አንድ ወንድም በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ ለአንድ ጎብኚ “ቤቴ ስገዛው ከነበረው ይልቅ አሁን የተሻለ ሆኗል!” ብሎታል። ቤታቸው የተጠገነላቸው ብዙዎችም ልክ እንደ ሩዲ ተሰምቷቸዋል።

በፍጥነት ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ምግቦች

ለፈቃደኛ ሠራተኞቹ ምግብ ለማቅረብ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ የመንግሥት አዳራሽ ጀርባ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ምግብ ማዘጋጀትና ማከፋፈል ጀመሩ። በመላ አገሪቷ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ማቀዝቀዣዎችን፣ የዕቃ ማጠቢያ ማሽኖችን፣ ምድጃዎችንና ሌሎች የወጥ ቤት እቃዎችን ለገሱ። ሁልጊዜ ቅዳሜና እሁድ 11 የወጥ ቤት ሠራተኞችና 200 ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚህ ቦታ በሺህ የሚቆጠር ምግብ ያዘጋጃሉ። ይህንን ዝግጅት በኃላፊነት የሚቆጣጠረው ፈቃደኛ ሠራተኛ እንዲህ ብሏል:- “ለ19 ዓመታት ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሚሆን ምግብ አዘጋጅተናል፤ እንዲህ ያለ ግዙፍ ሥራ ግን ከዚህ ቀደም ገጥሞን አያውቅም።”

የተዘጋጁት ምግቦች በ120 ትላልቅ የዕቃ መያዣ ሣጥኖች ውስጥ ይከተታሉ። እነዚህም ቆመው በሚጠብቋቸው 60 መኪኖች ላይ ከተጫኑ በኋላ ወደ ሁሉም ጣቢያዎችና ወደ ዋናው ማዕከል ይላካሉ። በዚህ መሃል በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ እየሠሩ ካሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዱ ወደ ተመደበበት ጣቢያ ይሄድና ለቡድኑ የሚሆን ምግብ ይወስዳል። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በሚጠግኑት ቤት ውስጥ ምሳቸውን ይበሉና ወዲያው ወደ ሥራቸው ይሰማራሉ።

ጥረቱ ተሳካ!

በመጨረሻም ሚያዝያ 2002 ላይ 11,700 የሚያክሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች ካከናወኗቸው የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሁሉ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደውን ሥራ አጠናቀቁ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በሥራው ላይ 1,000,000 ሰዓታት ያሳለፉ ሲሆን በአጠቃላይ 723 ቤቶችንና 8 የመንግሥት አዳራሾችን ጠግነዋል አሊያም እንደገና ገንብተዋል። ቤቱ በጎርፍ የተጎዳበት አንድ ወንድም ዓይኖቹ እንባ አቅርረው የተናገራቸው የሚከተሉት የምስጋና ቃላት የብዙዎቹን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነበር:- “ይሖዋንና እርዳታ ያበረከቱልንን ፈቃደኛ ሠራተኞች በሙሉ ላመሰግን እወዳለሁ። አፍቃሪ በሆነ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መገኘት ምንኛ የሚያጽናና ነው!”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 የኒው ዮርክ፣ የሎስ አንጀለስና የቺካጎ ከተሞች በሕዝብ ብዛት ከሂዩስተን ይበልጣሉ። በሂዩስተን ከተማ 3,500,000 ገደማ ሕዝብ የሚኖር ሲሆን በትልቅነቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ከምትገኘው ከሊባኖስ ይበልጣል።

^ አን.5 በጄፈሪና በፍሬዳ የቀብር ንግግር ላይ 1,300 ጓደኞቻቸው ተገኝተው ነበር። ይህም የጄፈሪ ሚስትና የፍሬዳ እህት የሆነችውን አቢጌይልን በእጅጉ አጽናንቷታል።

^ አን.15 የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴ የይሖዋ ምሥክሮችን የመሰብሰቢያ አዳራሾች ይሠራል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የእርዳታ ጣቢያዎች

ዕለቱ ቅዳሜ ጠዋት 1:00 ሰዓት ሲሆን ቦታው ደግሞ በሰሜናዊ ምሥራቅ ሂዩስተን የሚገኘው የእርዳታ ጣቢያ ቁጥር 4 ነው። የመንግሥት አዳራሹ እርስ በርስ እያወጉና እየተሳሳቁ ቡናቸውን በሚጠጡና ዶናታቸውን በሚበሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ተሞልቷል። አንዳንዶቹ እዚህ ለመድረስ ከሚኖሩበት ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በመኪና ተጉዘዋል። ልክ 1:30 ሲሆን ጭውውቱ ቀስ በቀስ እረጭ እያለ ሄደና የጣቢያው የበላይ ተመልካች የዕለቱን ጥቅስ ማድረግ ጀመረ። ከዚያም ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ወደየሥራ ቦታቸው ከመበተናቸው በፊት እሁድ ከጠዋቱ 1:30 ላይ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንደሚኖርና ሁሉም በእንግሊዝኛ አሊያም በስፓኒኛ ሐሳብ መስጠት እንደሚችሉ ተናገረ። ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የተላከውን ሰላምታ ሲያቀርብ ሁሉም ሞቅ ባለ ጭብጨባ ሰላምታውን መቀበላቸውን ገለጹ።

ቀጥሎም የጣቢያው የበላይ ተመልካች የመልሶ ማቋቋም ሥራው ምን ያህል እየተከናወ እንዳለ ከተናገረ በኋላ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ላሳዩት የትብብር መንፈስ አመሰገናቸው። ከዚያም “እዚህ ካለነው መካከል ዛሬ ሥራ ያልተሰጠው ወይም የት ሄዶ እንደሚሠራ የማያውቅ አለ?” ሲል ጠየቀ። እጁን ያነሳ ማንም ሰው አልነበረም። “ስንቶቻችሁ እዚህ ለመመገብ አስባችኋል?” በዚህ ጊዜ ሁሉም እጁን ሲያወጣ አዳራሹ በሳቅ ተሞላ። በመጨረሻም ጸሎት ከተደረገ በኋላ 250 የሚያክሉት ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ ፈቃደኛ ሠራተኞች አድካሚ ወደ ሆነው ወደ ቀኑ ሥራቸው ተሰማሩ።

በሌሎቹም ስድስት የእርዳታ ጣቢያዎችና በዋናው መጋዘን ተመሳሳይ ሁኔታ ይከናወናል። በዚህ ጊዜ በዋናው ወጥ ቤት የሚሠሩ ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ምግብ በማዘጋጀት ሥራ ተጠምደዋል፤ በምሳ ሰዓት በመላው ሂዩስተን ከ2,000 የሚበልጡ ረሃብ የሞረሞራቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ይጠብቋቸዋል!

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሥልጠና ፕሮግራም

በመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴው ወቅት በግንባታ ሥራ ሞያ ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ሌሎችን አሰልጥነዋል። አንዳንዶቹ ቤቶችን በመርዝ እንዴት ማጽዳት እንደሚቻል ሥልጠና ሲሰጣቸው ሌሎች ግድግዳዎችንና ቁም ሳጥኖችን እንዴት መግጠም እንደሚቻል ተምረዋል። ሌሎች ደግሞ ቤት መለሰንና ቀለም መቀባት ተምረዋል። እነዚህ ባለሞያ ሰዎች የሚሰጡት ሥልጠና በቪድዮ ከተቀረጸ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ለማሠልጠን ወደ ሌሎች ጣቢያዎች ይላክ ነበር። አንድ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው አባል “በእነዚህ የሥልጠና ፕሮግራሞች አማካኝነት ከፍተኛ ጥራት ያለው የጥገና ሥራ ማከናወን ችለናል” ብሏል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለሙያዎች ሥልጠና ሲሰጡ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“እውነተኛው የአምላክ ሥራ”

የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው አባል የሆነ አንድ ወንድም “የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን የአምላክ ሥራ እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እውነተኛዎቹ የአምላክ ሥራዎች ለእነዚያ ሁሉ ወራት እዚህ የሠሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። የወንድማማች ማኅበራችን በጣም የሚደነቅ ነው!” ብሏል። በዚህ የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ወቅት 2,500 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ቅዳሜና እሁድ ለሥራ ይመጡ ነበር። የኮሚቴው ሊቀ መንበር እንዲህ ብሏል:- “ሳይከፈላቸው ለመሥራት የሚመጡት እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች እስከዛሬ ድረስ በይሖዋ ምሥክሮች ከተከናወኑት ሁሉ አቻ በማይገኝለት በዚህ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለመካፈል ሲሉ ቀደም ብለው ያወጡትን የሽርሽር ፕሮግራም ሰርዘዋል፣ የቤተሰብ ፕሮግራሞቻቸውን ለውጠዋል እንዲሁም ሌሎች የግል ጉዳዮቻቸውን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል።”

ረዘም ያለ ጊዜ በወሰደው በዚህ የመልሶ ማቋቋም ዘመቻ መሳተፍ መሥዋዕትነት ጠይቋል። ሥራው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ እገዛ ያደርግ የነበረ አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ በሳምንት ውስጥ ለ50 ሰዓታት ሰብዓዊ ሥራ ይሠራ ነበር። ሆኖም በየሳምንቱ በመልሶ ማቋቋሙ ሥራ ላይ 40 ሰዓታት ያህል ያሳልፍ ነበር። “ይሖዋ ኃይል ሰጥቶኛል” ይላል። “አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች ‘ይከፈልሃል?’ ብለው ይጠይቁኛል። ‘ምንም ያህል ገንዘብ ቢከፈለኝ እንዲህ ልሠራ አልችልም’ በማለት እመልስላቸዋለሁ።” በሉዊሲያና የሚኖር አንድ ቤተሰብ ሳምንቱን ሙሉ በሰብዓዊ ሥራ ካሳለፈ በኋላ ቅዳሜና እሁድ በመልሶ ማቋቋም ሥራው ለመካፈል ሲል ደርሶ መልስ 800 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር። ብዙዎቹ ከጠዋት እስከ ማታ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። በአንድ ጉዞ ብቻ ከሰባት እስከ አሥር ሰዓት በመኪና ተጉዘው ወደ ቦታው የሚደርሱ 30 ባለሞያ ፈቃደኛ ሠራተኞች:- “ምንም አይቆጨንም!” ብለዋል። ሌላዋ ፈቃደኛ ሠራተኛ ከሰዓት በኋላ 9:30 ላይ ከሥራ ከወጣች በኋላ በዋናው ማዕከል እስከ ምሽቱ 4:00 ድረስ ትሠራ ነበር። ቅዳሜና እሁድም ትሠራ ነበር። “የሚክስ ሥራ ነው” ብላለች።

በእርግጥም እነዚህና ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ይህንን ተግባር ማከናወን የቻሉት የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነው የወንድማማች ፍቅር ስላላቸው ነው። (ዮሐንስ 13:35) የሂዩስተን ከተማ ከንቲባ ዋናውን ማዕከል ከጎበኙ በኋላ ለምሥክሮቹ እንዲህ ብለዋቸዋል:- “አምላክ እንድናከናውን ያዘዘንን መሥራት እንዳለባችሁ ታምናላችሁ። እምነታችሁን በተግባር እየገለጻችሁ ነው።”

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰኔ 9, 2001 የሂዩስተን ከተማ በጎርፍ ተጥለቀለቀ

[ምንጭ]

© Houston Chronicle

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንገዶች በውኃ ተጥለቀለቁ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውኃው ወደ ቤቶቹ ጎረፈ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ካገለገሉት በሺህ ከሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ጥቂቶቹ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጥ ቤቶቹ ሩብ ሚልዮን የሚያክል ምግብ አዘጋጅተዋል!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

NOAA