ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ቆሻሻን ወደ ወርቅ መለወጥ
በጃፓን የሚገኝ አንድ የማዕድን ኩባንያ ውድ ማዕድናት ለማግኘት የሚያስችል ቀላልና አትራፊ ዘዴ አግኝቷል። በአኪታ የሚገኝ ማቅለጫና ማጣሪያ ኩባንያ የማዕድን ጉድጓድ በመፈለግ ብዙ ጊዜና ገንዘብ ከማባከን ይልቅ በተጣሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ኮምፒውተሮች ውስጥ የሚገኙትን ውድ ማዕድናት አቅልጦ ማውጣት መጀመሩን የቶኪዮው አይ ኤች ቲ አሳሂ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። የኩባንያው ፕሬዚዳንት እንዳሉት “የባትሪዎቹ ክብደት ሳይታሰብ አንድ ቶን ከሚያክል ተንቀሳቃሽ ስልክ በርካታ መቶ ግራም የሚመዝን ወርቅ ማግኘት ይቻላል።” ከተለመደው የማዕድን አወጣጥ ጋር ሲወዳደር የዚህ “የከተማ ማዕድን” ውጤት ከማዕድን ጉድጓዶች ከሚገኘው ማዕድን በአሥር እጥፍ ይበልጣል። ከዚህም በላይ ከተንቀሳቃሽ ስልኮች ውስጥ ወርቅ ማውጣት መሬት ቆፍሮ ከማውጣት ጋር ብዙም ልዩነት ስለሌለው አዲስ ዓይነት መሣሪያ ለማቆም ተጨማሪ ገንዘብ ማውጣት አያስፈልገም።
በእረኝነት ሥራ የተሰማሩ ላማዎች
የሰሜን አሜሪካ ከብት አርቢዎች በጎቻቸውን በላማዎች ማስጠበቅ ጀምረዋል። የካናዳው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል እንዳለው ላማዎች “አብረዋቸው ለሚውሉት እንስሳት ከፍተኛ ቅርበት ይሰማቸዋል።” የማስጠንቀቂያ ድምፅ በማሰማት፣ በጎች እንዳይበታተኑ በመጠበቅ፣ ያልተፈለጉ እንግዶችን በማባረርና ነጣቂ አራዊትን በመራገጥ መንጎችን በትጋት ይጠብቃሉ። እንዲያውም አንዳንድ ገበሬዎች ከእረኛ ውሾች ይልቅ ላማዎችን ይመርጣሉ። ምክንያቱም ላማዎች የውሾቹን ያህል ብዙ ገንዘብ አያስወጡም። በተጨማሪም “ላማዎች ከበጎቹ ጋር ሣር ግጠው አብረው ስለሚያድሩ ለእነርሱ ሲባል የሚወጣ ወጪ እንደሌለና ዕድሜያቸውም ከእረኛ ውሾች በጣም እንደሚበልጥ” ጋዜጣው ገልጿል። ላማዎች ያሉት አንድ ካናዳዊ በግ አርቢ “ምንም ወጪ አያስወጡም፣ ደግሞም አይጮሁም” በማለት ተናግሯል።
ሕፃናት ለውትድርና እንዳይመለመሉ እገዳ ተደረገ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የካቲት 12, 2002 ያወጣው የዜና ዘገባ “በዓለም ላይ ለሰብዓዊ መብት መደፈር ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ የሆነውን ልጆችን በውትድርና የማሰማራት ተግባር ለማስወገድ አሥር ዓመት የፈጀ ዓለም አቀፋዊ ትግል ከተደረገ በኋላ ዛሬ ይህን ምልመላ የሚያግድ ስምምነት ጸድቋል” ይላል። ይህ በ96 አገሮች የተፈረመው አስገዳጅነት የሌለው ስምምነት “18 ዓመት ያልሞላው ማንኛውም ሰው የመደበኛ ሠራዊት አባል ሆኖ እንዲመለመል እንደማይገደድና ማንም ሰው በገዛ ፈቃዱ ለውትድርና የሚመለመልበት የመጨረሻው አነስተኛ ዕድሜ 16 ዓመት እንዲሆን ይደነግጋል።” “ባሁኑ ጊዜ ግማሽ ሚልዮን የሚደርሱ ልጆች 85 በሚሆኑ አገሮች ውስጥ የመንግሥት መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የሌሎች ታጣቂ ቡድኖች አባላት ሆነው በማገልገል ላይ እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህ መካከል ከ300, 000 የሚበልጡት በ35 አገሮች በሚካሄዱ ቀጥተኛ ውጊያዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው።” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንተርኔት ዜና አገልግሎት እንዳለው ከሆነ ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ብዙዎቹ ታፍነው የተወሰዱ ሲሆኑ “ለማምለጥ ቢሞክሩ ይደበደባሉ ወይም ይገደላሉ። በተለይ ሴቶች ልጆች ብዙ ጊዜ ተገድደው ስለሚደፈሩ ለበለጠ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።”
የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ጥሩ አካላዊ እንቅስቃሴ ነው
ቤት ማጽዳት፣ የመስኮት መስታወት መወልወልና የሕፃናት ጋሪ መግፋት ለጤንነት እንደሚጠቅም አካላዊ እንቅስቃሴ ሊቆጠር ይችላል? በቅርቡ በአውስትራሊያ በሚገኘው በኩዊንስላንድ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ መልሱ አዎን የሚል ነው። ተመራማሪዎቹ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ላሏቸው ሰባት እናቶች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የኦክስጂን ፍጆታቸውን የሚለካ መሣሪያ እንዳደረጉላቸው ዘ ካንቤራ ታይምስ ያወጣው ሪፖርት ይገልጻል። ተመራማሪዎቹ እንዳሉት “አንዳንዶቹ የቤት ውስጥ ሥራዎች የጤና ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል እንቅስቃሴ የሚጠይቁ እንደሆኑ የጥናቱ ውጤት ያመለክታል።” ፕሮፌሰር ዌንዲ ብራውን “የሴቶቹ የቤት ውስጥ ሥራ የሚጠይቀው ጉልበት ፈጣን የሆነ የእግር ጉዞ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም ዋና ከሚጠይቀው ጋር ተመጣጣኝ ነው ለማለት ይቻላል” ሲሉ መናገራቸውን ሪፖርቱ ዘግቧል። ብራውን “ጥናቱ ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ሙሉ ቀን ላይ ታች ሲሉ የሚውሉት ሴቶች በቂ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ናቸው ማለት እንደማይቻል ያመለክታል” ብለዋል።
መድኃኒቶችና አረጋውያን
ዴር ሽፒገል የተባለው የጀርመን የዜና መጽሔት “ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋውያን በአማካይ ሦስት ዓይነት መድኃኒቶች የሚወስዱ ሲሆን ይህም ከዚህ በሚያንስ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ከሚወስዱት መድኃኒት በሦስት እጥፍ ይበልጣል” ብሏል። “ይሁን እንጂ የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ዓይነት በጨመረ መጠን [የመድኃኒቶቹ] እርስ በርስ የመጋጨትና በዚህም ምክንያት ለሚመጡ ተጓዳኝ ችግሮች የመጋለጣቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል።” ሌላው ተጨማሪ ችግር ደግሞ “ብዙውን ጊዜ ሐኪሞች . . . ዕድሜ እየገፋ በሄደ መጠን በሽንት አማካኝነት የሚካሄደው የሰውነት ቆሻሻ የማስወገድ ሂደት እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ” በመቅረታቸው የተነሳ የሚመጣ ነው። በዚህ ምክንያት መድኃኒቶቹ በሰውነት ውስጥ ሊጠራቀሙ ይችላሉ። ስለዚህ “ለ40 ዓመት ሰው ትክክለኛ መጠን የሆነ መድኃኒት የ70 ዓመቱን ሰው በዝቶበት ሊመርዘው ይችላል” በማለት ዴር ሽፒገል ያብራራል። “ብዙ አረጋውያን ደግሞ በቂ ውሃ ባለመጠጣት ሁኔታውን ያባብሳሉ።” በቂ ፈሳሽ አለማግኘት በራሱ የሕመም ማስታገሻና የደም ግፊት መድኃኒቶች የሚያስከትሉትን
ዓይነት ተጓዳኝ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እንደ መፍዘዝ፣ ግራ መጋባትና ማዞር የመሰሉት የሕመም ስሜቶች አብዛኛውን ጊዜ በእርጅና የሚሳበቡ ይሁኑ እንጂ በመድኃኒቶች ምክንያት የሚመጡ ሊሆኑ ይችላሉ።“ለጉዲፈቻ” የተዘጋጁ አያቶች
በስፔይን አንዳንድ ቤተሰቦች ዘመድ የሌላቸውን 66 አረጋውያን ተቀብለው ለማኖር ዝግጅት እንዳደረጉ ኤል ፓይስ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። “የዚህ ፕሮግራም ዓላማ . . . ብቻቸውን መኖር የማይችሉ አረጋውያን ወደ ጡረታ ቤት ከመግባት የተለየ አማራጭ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው” ይላል ጋዜጣው። አረጋውያኑን ለመቀበል ማመልከቻ ካቀረቡት መካከል ኑሯቸውን አረጋዊ ከሆነ ሰው ጋር ለመካፈል የፈለጉ በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ባልና ሚስት ይገኙበታል። ትናንሽ ልጆች ያሏቸው ሌሎች ቤተሰቦች እቤታቸው እንደ አያት የሚሆንላቸው ሰው ቢኖር እንደሚወዱ ተናግረዋል። አረጋውያኑን የተቀበሉት ቤተሰቦች የገንዘብ ድጎማ የሚያገኙ ቢሆንም “ለመቀበል የሚያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት ገንዘቡ አይደለም” ይላሉ የፕሮግራሙ ዲሬክተር የሆኑት ማሪሳ ሙኞዝ ካባሌዬሮ። “ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ብለው ቢሆን ኖሮ አረጋውያንን መንከባከብ በጣም አድካሚ በመሆኑ ወዲያው ይሰላቹ ነበር።”
የቤት ውስጥ አምባጓሮ በአውሮፓ
የአውሮፓ የሥራና የማኅበራዊ ጉዳይ ኮሚሽነር የሆኑት አና ዲያማንቶፑሉ “ከአውሮፓ አምስት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ ውስጥ ከባሏ ወይም ከወንድ ጓደኛዋ ጥቃት ይደርስባታል” ብለዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን የኃይል ድርጊት በተመለከተ በስፔይን ተደርጎ በነበረው የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ዲያማንቶፑሉ እንዳመለከቱት “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ15 እስከ 44 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች መካከል በካንሰር፣ በወባ፣ በመኪና አደጋ ወይም በጦርነት ከሚሞቱት ወይም የአካል ጉዳት ከሚደርስባቸው ይልቅ በወንዶች ጥቃት ምክንያት የሚገደሉትና የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ይበልጣሉ።” በዩናይትድ ኪንግደም “በየሦስት ቀኑ አንዲት ሴት ቤት ውስጥ በሚፈጠር አምባጓሮ ምክንያት ስትሞት በአየርላንድ ደግሞ በሰው ተገድለው ከሚሞቱት ሴቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው የሚያልፈው በባሎቻቸው ወይም በወንድ ጓደኞቻቸው ነው።” በአውስትራሊያም ለሞንድ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው “ከግማሽ የሚበልጡት የፍቺ ጥያቄዎች የሚቀርቡት ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ በሚፈጽሙት የኃይል ድርጊት ምክንያት ነው።”
ሕፃናት ውኃ ውስጥ ሰጥመው እንዳይሞቱ መከላከል
ሃብታም በሚባሉ 26 አገሮች ውስጥ ከ14 ዓመት በታች የሚገኙ ልጆችን ለሞት የሚዳርገው ሁለተኛው ምክንያት ውኃ ውስጥ መስጠም እንደሆነ የቀድሞው ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል ሪፖርት አድርጓል። ጆርናሉ እንዳለው “ጨቅላ ሕፃናት በቤት ውስጥ (አብዛኛውን ጊዜ በባኞ ገንዳ ውስጥ)፣ ድክ ድክ የሚሉ ልጆች ደግሞ በቤት አጠገብ በሚገኝ የመዋኛ ገንዳ ወይም ኩሬ ውስጥ፣ ትልልቅ ልጆች ደግሞ በሐይቆች ወይም በወንዞች ሊሰጥሙ ይችላሉ።” እንዲህ ያለውን አደጋ ለመከላከል ሊቃውንት የሚከተለውን ምክር ይሰጣሉ:- ሕፃናት በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ወይም በማንኛውም የተጠራቀመ ውኃ አጠገብ በሚሆኑበት ጊዜ ዓይናችሁ ከእነርሱ ላይ አይነቀል። በአትክልት ቦታ የሚገኝ ኩሬ ወይም የመዋኛ ገንዳ ካለ በቀላሉ መግባት እንዳይችሉ እጠሩት። ሕፃናት ብቻቸውን ወይም ሰው በማይኖርበት ቦታ እንዲዋኙ አትፍቀዱ። አፍ ለአፍ ገጥሞ የማስተንፈስ ዘዴ ተለማመዱ።
ፍግና በመድኃኒት የማይደፈሩ ጀርሞች
“የአውሮፓ መስኮች ለከብቶች በሚሰጡ አንቲባዮቲኮች በከፍተኛ ደረጃ ተበክለዋል” በማለት ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። በአውሮፓ ኅብረትና በዩናይትድ ስቴትስ የከብቶችን እድገት ለማፋጠንና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል ከ10, 000 ቶን የሚበልጡ አንቲባዮቲኮች ለከብቶች ይሰጣሉ። “ይሁን እንጂ በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት በእነዚህ የከብት መድኃኒቶች አጠቃቀምና አንቲባዮቲክ የማይደፍራቸው ሰዎችን የሚያሳምሙ ጀርሞች እየበዙ በመሄዳቸው መካከል ዝምድና አለ” ይላል መጽሔቱ። ኒው ሳይንቲስት “ለማዳበሪያነት በማሳዎች ላይ በሚበተነው ፍግ ውስጥ የሚኖሩት መድኃኒቶች የምንመገበውን ምግብና የምንጠጣውን ውኃ እንዲሁም የምንመገባቸውን እህሎች ይበክላሉ” ብሏል።