መጠነ ሰፊ አሳዛኝ ክስተት
መጠነ ሰፊ አሳዛኝ ክስተት
ኤሪክ ከተወለደ ስድስት ወሩ ነው። * ክብደቱና ቁመቱ ሲታይ ግን ገና የአንድ ወይም የሁለት ወር ሕፃን ነው የሚመስለው። በጣም ቀጭን ከመሆኑ የተነሳ እግሮቹና እጆቹ ያበጡ ሲሆን ፊቱም ትልቅና ክብ ነው። መልኩ አመድ የመሰለ፣ ፀጉሩ የተሰባበረና ወዝ የሌለው ሲሆን ቆዳውን ደግሞ ቁስል ወርሶታል እንዲሁም በጣም ይነጫነጫል። ሐኪሙ የኤሪክን ዓይን ሲመረምር የዓይኑ ሕዋሳት በቀላሉ ሊቀደዱ ስለሚችሉ በጣም መጠንቀቅ አለበት። የኤሪክ የአእምሮ እድገትም የተገታ ይመስላል። የሚያሳዝነው እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በዚህ ልጅ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ ነው።
“በዓለም ዙሪያ ከሚሞቱት ሕፃናት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚሞቱት በዚሁ ሳቢያ ሲሆን ጥቁር ሞት ተብሎ የሚታወቀው ተላላፊ በሽታ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ካለበት ጊዜ ወዲህ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መቅሰፍት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ተላላፊ በሽታ አይደለም። ቢሆንም የአካል ጉዳት ያለባቸውን፣ በተደጋጋሚ በበሽታ የሚጠቁና ለትምህርት እጦት የተጋለጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሁሉ ይነካል። ሴቶችንና ቤተሰቦችን አልፎ ተርፎም የመላውን ኅብረተሰብ ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል።”—የዓለም ሕፃናት ሁኔታ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት
እነዚህ ቃላት የሚገልጹት የትኛውን በሽታ ነው? የዓለም ጤና ድርጅት “ድምፅ አልባው አደጋ” ብሎ የሰየመውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በተለይም ደግሞ የፕሮቲንና የኃይል ሰጪ ምግብ እጥረት ነው። ይህ አሳዛኝ ክስተት ምን ያህል ተስፋፍቷል? የዓለም ጤና ድርጅት “በየዓመቱ ከሚሞቱት 10.4 ሚልዮን ሕፃናት ውስጥ ቢያንስ ግማሽ የሚሆኑት የሚቀሰፉት” በፕሮቲንና በኃይል ሰጪ ምግብ እጥረት መሆኑን አስታውቋል።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደ ቫይታሚንና ማዕድን ያሉ አንድ ወይም ከዚያ በላይ አልሚ ንጥረ ምግቦችን ከማጣት አንስቶ ከመጠን በላይ መወፈርና ሌሎችም ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሥር የሰደዱ የሕመም ዓይነቶችን ያጠቃልላል። የሆነ ሆኖ “ለሕልፈተ
ሕይወት በመዳረግ ረገድ አቻ ያልተገኘለት ችግር የፕሮቲንና ኃይል ሰጪ ምግቦች እጥረት ነው” በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ይናገራል። ዋና ሰለባዎቹም ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሕፃናት ናቸው።እስቲ ለአንድ አፍታ በመግቢያችን ላይ ስለተጠቀሰው ኤሪክና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ እየተሰቃዩ ስላሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት አስብ። ለደረሰባቸው አሳዛኝ ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እነሱ ባይሆኑም የችግሩ ሰለባ ከመሆን ግን አላመለጡም። ስለ ሕፃናት አመጋገብ ያጠኑ ኪኦርኬና ታውሴንት የተባሉ አንዲት ሴት “እየተሰቃዩና አሳዛኝ መዘዙን እያጨዱ ያሉት ለችግሩ ተጠያቂ ባይሆኑም ከሁሉ የበለጠ ተጠቂዎቹ ግን እነሱ ናቸው” በማለት ለንቁ! ተናግረዋል።
አንዳንዶች ይህ ሁሉ ችግር የተከሰተው ለሁሉም የሚዳረስ በቂ ምግብ ባለመኖሩ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። በተቃራኒው ግን የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው “በዛሬው ጊዜ የምንኖረው ምርት በተትረፈረፈበት ጊዜ ነው።” በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች የሚበቃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የሚተርፍ ምግብ አለ። ከዚህም በላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን መከላከል በጣም ቀላልና ብዙ ወጪ ሳይጠይቅ ሊፈወስ የሚችል ሕመም ነው። ሐቁ ይህ መሆኑን ስትገነዘብ በጣም አታዝንም?
የሚጠቁት እነማን ናቸው?
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሕፃናት ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ችግር አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ሐምሌ
2001 ባቀረበው ሪፖርት ላይ “የተመጣጠነ ምግብ እጥረት 800 ሚልዮን በሚሆኑ ሰዎች ላይ አስፈሪ ጥላ አጥልቶባቸዋል። ከነዚህም ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።” ይህ ማለት ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ከስምንት ሰዎች አንዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይሠቃያል ማለት ነው።በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚገኘው በእስያ በተለይም በደቡባዊና ማዕከላዊ ክልሎች ሲሆን በመቶኛ እጅ ሲሰላ ግን ከፍተኛው ረሃብተኛ ሕዝብ የሚገኘው በአፍሪካ ነው። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ቀጣዩን ደረጃ የሚይዙት በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን የሚገኙ አንዳንድ ታዳጊ አገሮች ናቸው።
የበለጸጉ አገሮችስ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነፃ ናቸውን? አይደሉም። የዓለም ምግብ ዋስትና ማጣት 2001 የተሰኘው ዘገባ እንደገለጸው በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች 11 ሚልዮን ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ በማጣት ይሠቃያሉ። ከዚህም በተጨማሪ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ካሉት የዓለም ሕዝቦች ውስጥ 27 ሚልዮን የሚሆኑት የሚገኙት በኢንዱስትሪ በመበልጸግ ላይ ባሉ አገሮች በተለይ ደግሞ በምሥራቅ አውሮፓና በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ነው።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይህን ያህል አሳሳቢ ችግር የሆነው ለምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ ለማሻሻል ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? ምድራችን ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነፃ የምትሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይዳስሳል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 ስሙ ተለውጧል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በቂ የምግብ አቅርቦት የሌለባቸው አገሮች
ከፍተኛ ችግር ያለባቸው
መካከለኛ ችግር ያለባቸው
አነስተኛ ችግር ያለባቸው
ችግር የሌለባቸው ወይም በቂ መረጃ ያልተጠናቀረባቸው
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሱዳን የእርዳታ እህል ለማግኘት ሲጠባበቁ
[ምንጭ]
UN/DPI Photo by Eskinder Debebe