“የተለያየ ድምፅ የሚያወጣው ከበሮ”
“የተለያየ ድምፅ የሚያወጣው ከበሮ”
ሴኔጋል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“የሚያስገመግም፣ የሚያንሳጥጥ፣ የልቅሶ እንዲሁም የኡኡታ ዓይነት ድምፅ ያሰማል። ያንሾካሹካል እንዲሁም ይዘፍናል። . . . እነዚህን ሁሉ ድምፆች የሚያወጣው በተለያየ መልክ የሚሠራው ከበሮ ነው።” የዚህን ጸሐፊ ትኩረት የሳበው ምንድን ነው? ጄምቤ ተብሎ የሚጠራው የአፍሪካውያን ከበሮ ነው።
ጄምቤ በአንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ ጎሣዎች ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው የሙዚቃ መሣሪያ ነው። ጄምቤ በአንድ መንደር ውስጥ ከሚፈጸሙ የተለያዩ ክስተቶች ጋር በተያያዘ ይሠራበታል። ለምሳሌ ያህል በሠርግ፣ በሐዘን፣ ልጅ ሲወለድ፣ በበዓል ቀን፣ በመከር ወቅትና ሌላው ቀርቶ አዲስ ልብስ ሲገዛ እንኳ በጄምቤ የተለያየ ዜማ ይሰማል።
ጄምቤ በተለያየ ቅርፅና መጠን ይሠራል። በማሊ፣ በሴኔጋል፣ በቡርኪና ፋሶና በጊኒ ያለው የጄምቤ አሠራር የተለያየ ነው። ይህ የሙዚቃ መሣሪያ የሚሠራው ውስጡ ከተቦረቦረ ድፍን ግንድ ነው። አንዳንዶቹ ከበሮዎች እምብዛም ያልተጋጌጡ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን በሚያምር መንገድ የተቀረጹ ናቸው።
ግንዱ ውስጡ ከተቦረቦረ በኋላ ጥሩ ችሎታ ያለው ከበሮ ሠራተኛ ድንቅ የሙዚቃ መሣሪያ አድርጎ ይሠራዋል። በመጀመሪያ፣ ግንዱ ተፈላጊውን ድምፅ ለማውጣት የሚያስችለውን ትክክለኛ ቅርፅ እስኪይዝ ድረስ እየጠረበ፣ እየፋቀና እያለሰለሰ ያስተካክለዋል። ባለሞያው የከበሮውን የውስጠኛ ክፍል የቴምር ዘይት ከቀባው በኋላ እንዲደርቅ ፀሐይ ላይ ያስቀምጠዋል። ይህም እንጨቱ እንዳይሰነጠቅ ይረዳል።
የጄምቤው አናት ከፍየል ቆዳ ይዘጋጅና በክብ ሽቦ ላይ ተወጥሮ በተቦረቦረው እንጨት ላይ ይደረጋል። ከዚያም በሲባጎ እየተወጠረ በሌላኛው ጫፍ ላይ ካሉ ሁለት ክብ ሽቦዎች ጋር ይታሰራል። ባለሞያው ሲባጎውን የሚወጥረው ምን ያህል ነው? ይህ በሚፈልገው የድምፅ ቃና ላይ የተመካ ነው። ሠራተኛው ከበሮውን በሚቃኝበት ጊዜ የሚችለውን ዜማ ለመጫወት እየሞከረ በትክክለኛው መጠን መወጠሩን ያረጋግጣል።
ጄምቤ አፍሪካውያንንም ሆነ ሌሎች ጎብኚዎችን የሚመስጥ ድምፅ አለው። በእርግጥም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ከበሮ መቺዎች ሲጫወቱ የመስማት አጋጣሚ ብታገኝ “የተለያየ ድምፅ የሚያወጣው ከበሮ” ፈጽሞ ከአእምሮህ አይጠፋም።