የረዥም ጊዜ ምኞቴ ተሟላልኝ
የረዥም ጊዜ ምኞቴ ተሟላልኝ
ሉቺያ ሙሳኔት እንደተናገረችው
በሰሜን ምዕራብ ኢጣሊያ ጠረፍ፣ በስዊስ አልፕስ እና ፈረንሳይ በሚገኘው ሞንት በላንክ በሚባለው እውቅ ተራራ አቅራቢያ ቫሌ ደአኦስታ የምትባል አንዲት ራስ ገዝ ክፍለ አገር ትገኛለች። በ1941 በዚህች ክፍለ አገር ቻላንት ሴንት አንሰልሜ በምትባል ትንሽ መንደር ተወለድኩ።
የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ስሆን አራት ታናናሽ ወንድሞች ነበሩኝ። እናቴ ጠንካራ ሠራተኛና ቀናተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበረች። አባቴም ያደገው ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ከእህቶቹ መካከል ሁለቱ መነኮሳት ነበሩ። ወላጆቼ እኔን ለማሳደግና ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። በምንኖርበት አካባቢ ትምህርት ቤት ስላልነበረ 11 ዓመት ሲሞላኝ ወላጆቼ መነኮሳት በሚያስተዳድሩት አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቡኝ።
እዚያም ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ጨምሮ የላቲንና የፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ተማርኩ። ከዚያም 15 ዓመት ሲሞላኝ አምላክን እንዴት ማገልገል እንደምችል በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ይህንንም ምኞቴን ለማሳካት ገዳም ከመግባት የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ተሰማኝ። ይህም እናቴ ያለ እኔ እርዳታ ብቻዋን ሆና ወንድሞቼን እንድታሳድግ ስለሚያደርጋት ወላጆቼ ይህን ሐሳቤን አልወደዱልኝም ነበር። ወላጆቼ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ጥሩ ሥራ ይዤ በገንዘብ እንደምረዳቸው ተስፋ አድርገው ነበር።
የወላጆቼ ሁኔታ ቅር ቢያሰኘኝም የሕይወትን ዓላማ ማወቅና ለአምላክ የመጀመሪያውን ቦታ ሰጥቼ መኖር ፈልጌ ነበር። በዚህም የተነሳ በ1961 ወደ አንድ የሮማ ካቶሊክ ገዳም ገባሁ።
በምንኩስና ያሳለፍኩት ሕይወት
የመጀመሪያዎቹን ወራት የቤተ ክርስቲያኒቱን መመሪያና ደንብ እያጠናሁና በገዳሙ ውስጥ አንዳንድ የጉልበት ሥራዎችን እየሠራሁ አሳለፍኩ። ነሐሴ 1961 የምንኩስና ትምህርት መማርና የተለመደውን የመነኮሳት ልብስ መልበስ ጀመርኩ። ከዚያም በእናቴ ስም ኢኔስ ተብዬ እንድጠራ ሐሳብ አቀረብኩ። አዲሱ ስሜ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እማሆይ ኢኔስ በሚለው ስሜ መጠራት ጀመርኩ።
አብዛኞቹ አዳዲስ መነኮሳት በገዳሙ ውስጥ የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎች የሚሠሩ ቢሆንም የተሻለ የትምህርት ደረጃ ስለነበረኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኜ ተመደብኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ በነሐሴ 1963 በአኦስታ፣ ኢጣሊያ የሚገኘው የሳን ጁሴፔ ገዳም አባል ለመሆን የምንኩስና ቃለ መሃላ ፈጸምኩ። ከዚያም ገዳሙ ለተጨማሪ ትምህርት ሮም ወደሚገኘው የማሪያ ሳንቲሲማ አሱንታ ዩኒቨርሲቲ ላከኝ።
በ1967 ትምህርቴን ጨርሼ ወደ አኦስታ ከተመለስኩ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመርኩ። በ1976 የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሆኜ ተሾምኩ። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪና በቫሌ ደአኦስታ ራስ ገዝ ሥር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቦርድ አባል ብሆንም አንዳንድ ክፍሎች ገብቼ አስተምር ነበር።
በውስጤ የነበረው ዋነኛው ፍላጎት ድሆችን መርዳት ነበር። ድሆች በጣም ያሳዝኑኝ ነበር። ለሞት በሚዳርግ ህመም የተያዙትንና ተንከባካቢ ቤተሰብ የሌላቸውን ሰዎች መርዳትን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ ፕሮግራሞችን አደራጅቻለሁ። የስደተኞች ልጆችን ለማስተማር የሚያስችል ፕሮግራምም አዘጋጅቼ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሥራና ቤት በማፈላለግ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ ድሆችን እረዳ ነበር። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ መመሪያ አክብሬ ለመኖር የተቻለኝን ሁሉ አደርግ ነበር።
በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ያላትን እምነት ጨምሮ ሥላሴና ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ያሉ ትምህርቶችን ተማርኩ። በጊዜው የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት የሌሎች ሃይማኖቶችን እምነት መቀበልንና ተቻችሎ አብሮ መኖርን ይደግፍ ነበር።
አእምሮዬን የሚረብሹ ጉዳዮች ተፈጠሩ
ሆኖም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረጉ አንዳንድ ነገሮች ይረብሹኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል ከጥምቀት በፊት ወላጆችና ልጆች የጥምቀትን ትርጉም በተመለከተ በቂ እውቀት ማግኘት ይጠበቅባቸው ነበር። ሆኖም ብዙዎቹ ለመማር ፈቃደኞች ያልነበሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለማጥናት ምንም ዓይነት ጥረት አያደርጉም። ከዚህም በላይ አንዳንዶች በአንዱ ደብር ለጥምቀት ተቀባይነት ሳያገኙ ከቀሩ ወደ ሌላኛው ደብር ሄደው ይጠመቁ ነበር። ይህ ለእኔ ትርጉም የለሽና ግብዝነት ነበር።
አንዳንድ ጊዜ በጣም ይገርመኝና አብረውኝ ያሉትን መነኮሳት “በሌሎች እንቅስቃሴዎች ከምንካፈል ይልቅ ወንጌሉን መስበክ አይገባንም?” ብዬ እጠይቃቸዋለሁ። “መልካም ሥራ መሥራትም በራሱ ስብከት ነው” በማለት ይመልሱልኛል።
ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአቴን ለመናዘዝ ወደ ቄስ መሄድ እንዳለብኝ የሚገልጸው ሥርዓትም ፈጽሞ ልረዳው የማልችለው ልማድ ነበር። ይህን የመሰሉ የግል ጉዳዮቼን እኔው ራሴ ለአምላክ መንገር አለብኝ የሚል እምነት ነበረኝ። እንዲሁም ጸሎትን ማጥናትና በቃል መድገም ልቀበለው የማልችለው ልማድ ነበር። ጳጳሱ ፈጽሞ አይሳሳቱም የሚለውን ትምህርት መቀበልም ይከብደኝ ነበር። በመጨረሻም ስለ እነዚህ ጉዳዮች የራሴን እምነት ይዤ በሃይማኖቴ ውስጥ መኖር እችላለሁ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።
መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ የነበረኝ ምኞት
ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት የነበረኝ ከመሆኑም በላይ መጽሐፉን በደንብ ለማወቅ እፈልግ ነበር። ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ወይም የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ በሚሰማኝ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አነብባለሁ። በገዳሙ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የማይሰጥ ቢሆንም በግሌ አነብብ ነበር። በኢሳይያስ 43:10-12 ላይ ይሖዋ አምላክ “እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ በጣም ይነካኝ ነበር። እርግጥ ነው በወቅቱ የጥቅሱ ትርጉም አልገባኝም ነበር።
በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ሮም በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ በቫቲካን ድጋፍ ለአራት ዓመታት ሃይማኖታዊ ትምህርት ተከታትዬ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መማሪያ መጽሐፍ አድርገን አንጠቀምበትም ነበር። ወደ አኦስታ
ከተመለስኩ በኋላ በአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ኮንፈረንሶች ላይ እንዲያውም ካቶሊክ ያልሆኑ ሌሎች ድርጅቶች በሚያዘጋጅዋቸው በርካታ ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጉጉቴን ይበልጥ አቀጣጠለው። ስለ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ እናስተምራለን በሚሉ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ብዙ የሐሳብ አለመግባባት ይታይ ነበር።ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መቅሰም
በ1982 አንዲት የይሖዋ ምሥክር ማኅበራዊ አገልግሎት ወደምሰጥበት ማዕከል መጣችና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልታወያየኝ ሞከረች። በወቅቱ ሥራ በዝቶብኝ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ስለመማር የተናገረችው ሐሳብ ትኩረቴን ሳበው። “እባክሽ የምሠራበት ትምህርት ቤት ነይና በሚኖረኝ ነፃ ጊዜ እንነጋገራለን” አልኳት።
ሴትየዋ ብትመጣም በፕሮግራሜ ውስጥ ምንም ዓይነት “ነፃ ጊዜ” አልነበረኝም። በዚህ ወቅት እናቴ ካንሰር አመማትና ፈቃድ ወስጄ እርሷን ማስታመም ጀመርኩ። እናቴ ሚያዝያ 1983 ከሞተች በኋላ ወደ ሥራዬ ተመለስኩ። ሆኖም በዚህ ወቅት ከምሥክሮቹ ጋር ተጠፋፍተን ነበር። ብዙም ሳይቆይ በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልታነጋግረኝ ወደ እኔ መጣች። በዚህ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የራእይን መጽሐፍ በግል ማንበብ ጀምሬ ስለነበር “ራእይ ምዕራፍ 14 ላይ የተጠቀሱት 144,000 ሰዎች እነማን ናቸው?” ብዬ ጠየቅኳት።
ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚል ትምህርት ተምሬ ስለነበር ከእነዚህ ጥሩ ሰዎች መካከል 144,000 ሰዎች ተለይተው ለብቻቸው እንዲኖሩ መደረጉ አልዋጥልሽ አለኝ። ‘እነዚህ 144,000 ሰዎች እነማን ናቸው? ሥራቸውስ ምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። እነዚህ ጥያቄዎች አእምሮዬን እረፍት ነሱት። ምሥክሯ በተደጋጋሚ እቤቴ ብትመጣም ልታገኘኝ አልቻለችም።
ከጊዜ በኋላ ምሥክሯ አድራሻዬን ማርኮ ለሚባል የጉባኤዋ ሽማግሌ ሰጠችው። እርሱም የካቲት 1985 አገኘኝ። ሥራ በዝቶብኝ ስለነበር ብዙም መነጋገር አልቻልንም። ስለዚህ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን። ከጊዜ በኋላም እርሱና ባለቤቱ ሊና አዘውትረው እየመጡ መጽሐፍ ቅዱስን እንድማር ይረዱኝ ጀመር። ብዙም ሳይቆይ እንደ ሥላሴ፣ ነፍስ አትሞትምና የሲኦል እሳት የመሳሰሉት የካቶሊክ መሠረታዊ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንደሌላቸው ተረዳሁ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ጀመርኩ
የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት አዳራሾቻቸው በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ በተገኘሁ ጊዜ ሁሉም ነገር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሚደረገው ፍጹም የተለየ እንደሆነ ተረዳሁ። በስብሰባዎቻቸው ላይ መዝሙር የሚዘምሩ አንድ የተለየ የመዘምራን ቡድን የለም። ከዚያ ይልቅ ሁሉም ተሰብሳቢዎች ይዘምሩ ነበር። እንዲሁም በስብሰባው ላይ ሁሉም ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። መላው ድርጅት “በወንድሞች” እና “በእህቶች” የተገነባ እንደሆነ አስተዋልኩ። እርስ በርስ ይተሳሰቡ ነበር። ይህ ሁሉ በጣም ነካኝ።
በዚህ ወቅት ስብሰባ እሄድ የነበረው የመነኩሲት ልብስ ለብሼ ነበር። አንዳንዶች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ መነኩሲት ሲያዩ በጣም ይገረሙ ነበር። በፍቅር በተሳሰረ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ በመግባቴ ደስታና እርካታ ተሰማኝ። እንዲሁም በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ እከተላቸው የነበሩት አብዛኞቹ መመሪያዎች ከአምላክ ቃል ጋር ፈጽሞ እንደማይጣጣሙ አስተዋልኩ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች የተለየ ልብስ እንዲለብሱ አያዝዝም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የሥልጣን ተዋረድ መጽሐፍ ቅዱስ በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ስለሚያገለግሉ ትሁት ሽማግሌዎች ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነበር።
ይህን ሁሉ ሳውቅ የቆምኩበት መሬት የከዳኝ መስሎ ተሰማኝ። ላለፉት 24 ዓመታት የተጓዝኩበት ጎዳና ውሸት ነበር ብሎ መቀበሉ በጣም ከበደኝ። ሆኖም እውነትን እንዳገኘሁ ሆኖ ተሰማኝ። በ44 ዓመቴ አዲስ ሕይወት የመጀመሩ ሐሳብ በጣም አስፈራኝ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት ማየት ከጀመርኩ በኋላ በጨለማ መደናበሬን የምቀጥለው ለምንድን ነው?
ከባድ ውሳኔ
ከገዳም ከወጣሁ ምንም ዓይነት ቁሳዊ ነገር እንደማይኖረኝ አውቃለሁ። ሆኖም ዳዊት ጻድቃን ‘እንደማይጣሉና ዘራቸውም እህል እንደማይለምን’ የተናገራቸውን ቃላት አስታወስኩ። (መዝሙር 37:25) በተወሰነ ደረጃ እንደምቸገር ባውቅም በአምላክ ላይ በመታመን ‘የምፈራው ለምንድን ነው’ ብዬ አሰብኩ።
ቤተሰቦቼ እንዳበድኩ ሆኖ ተሰማቸው። እንደዚያ ማሰባቸው ቅር ቢያሰኘኝም “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ትዝ አሉኝ። (ማቴዎስ 10:37) በተጨማሪም ወንድሞችና እህቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይሰጡኝ የነበረው ማበረታቻ በእጅጉ አጠናከረኝ። የመነኩሲት ልብስ ለብሼ በመንገድ ላይ ስሄድ ያገኙኝ ሁሉ መጥተው ሰላም ሳይሉኝ አይሄዱም ነበር። ይህም ይበልጥ እንድቀርባቸውና የዓለም አቀፉ ቤተሰብ አባል እንደሆንኩ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
በመጨረሻም ወደ ገዳሙ እመምኔት ሄድኩና ከገዳም ለመውጣት የወሰንኩበትን ምክንያት አስረዳኋት። ይህን ውሳኔ እንዳደርግ ያነሳሱኝን ምክንያቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላሳያት ብፈልግም “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ካስፈለገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ እጠራለሁ” በማለት ፈጽሞ ልትሰማኝ እንደማትፈልግ ነገረችኝ።
ያደረኩት ውሳኔ ያላስደነገጠው ሰው አልነበረም። አንዳንዶች መባለግ ጀምራለች እንዲሁም አብዳለች እያሉ ያወሩብኝ ጀመር። ሆኖም የሚያውቁኝ ሁሉ ውንጀላው ውሸት እንደሆነ ያውቁ ነበር። አብረውኝ ይሠሩ የነበሩ ሁሉ አመለካከታቸው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። አንዳንዶች የወሰድኩት እርምጃ ድፍረት የሚጠይቅ እንደሆነ አውቀዋል። ሌሎች ደግሞ የተሳሳተ መንገድ እንደመረጥኩ ሆኖ ስለተሰማቸው እንዲሁም የምጎዳ መስሏቸው አዘኑልኝ።
ሐምሌ 4, 1985 ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለቀቅሁ። የይሖዋ ምሥክሮች የዚህ ዓይነት እርምጃ የወሰዱ ሌሎች ሰዎች ምን እንደደረሰባቸው ስለሚያውቁ ለደህንነቴ በማሰብ ለአንድ ወር ያህል ደበቁኝ። ያለሁበት ድረስ መጥተው ወደ ስብሰባ ይወስዱኝና መልሰው ቤት ያደርሱኛል። ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ ከዓይናቸው ዞር አልኩ። ከዚያም ነሐሴ 1, 1985 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በአገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።
በዚያው ወር መጨረሻ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘቴ ለመገናኛ ብዙኃን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቅቄ እንደወጣሁ ስላረጋገጠላቸው ታሪኬን መዘገብ ጀመሩ። ታኅሣሥ 14, 1985 ስጠመቅ የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያና ጋዜጣ በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ ሁሉም ሰው እንዲያውቀው ለማድረግ ታሪኬን እንደገና ማሰራጨት ጀመሩ።
ገዳሙን ለቅቄ ስወጣ በእጄ ላይ ምንም አልነበረኝም። ሥራ፣ ቤት ወይም የጡረታ አበል አልነበረኝም። በዚህም የተነሳ አንድ ዓመት ለሚያህል ጊዜ የአካል ጉዳተኛ የነበረችን አንዲት ሴት የመንከባከብ ሥራ ሠራሁ። ሐምሌ 1986 አቅኚ ሆኜ ሙሉ ጊዜዬን በአገልግሎት ማሳለፍ ጀመርኩ። አዲስ የተቋቋመ አነስተኛ ቡድን ወደሚገኝበት አካባቢ ተዛውሬ መኖር ጀመርኩ። እዚያም ትምህርት ቤት ያገኘሁትን እውቀት በመጠቀም በግሌ ቋንቋና
ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመርኩ። ይህም ፕሮግራሜን እንደ ሁኔታው ማስተካከል እንድችል ረድቶኛል።ውጭ አገር ሄዶ ማገልገል
አሁን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስላወቅኩ ይህን እውነት የተቻለኝን ያህል ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ፈለግኩ። ፈረንሳይኛ መናገር ስለምችል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ወደሚነገርበት አንድ አፍሪካ አገር ሄጄ ለምን አላገለግልም ብዬ አሰብኩ። ሆኖም በ1992 እኔ ከምኖርበት አገር ብዙም በማትርቀው በአልባኒያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ነፃነት አገኙ። በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ ኢጣሊያ ከሚገኙ አቅኚዎች መካከል የተወሰኑት እዚያ ሄደው እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ከእነዚህ አቅኚዎች መካከል እኔ ባለሁበት ጉባኤ የሚገኙት ክርስቲና እና ፋዚዮ ይገኙበታል። ወደ አልባኒያ ሄጄ እንድጠይቃቸውና በዚያ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረቡልኝ። ጉዳዩን በጸሎት በጥንቃቄ ካሰብኩበት በኋላ በ52 ዓመት ዕድሜዬ በአንጻራዊ ሁኔታ ደህንነት ያለበትን አካባቢ ትቼ ፈጽሞ ወደማላውቀው አገር ሄድኩ።
ይህ የሆነው መጋቢት 1993 ነበር። እንደደረስኩም ከትውልድ አገሬ ብዙም ወደማይርቅ አካባቢ እንደመጣሁ ባውቅም ሌላ ዓለም ውስጥ የገባሁ ሆኖ ተሰማኝ። ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በእግራቸው ሲሆን የሚግባቡትም ለእኔ ባዕድ በሆነ በአልባኒያ ቋንቋ ነው። አገሪቱ ታላላቅ ለውጦችን ያካሄደች ሲሆን ብዙ የፖለቲካ ሥርዓት ተፈራርቆባታል። ሆኖም ሕዝቡ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ጥማት ስለነበረው ማንበብና ማጥናት ይወድዱ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመንፈሳዊ ፈጣን እድገት የሚያደርጉ መሆናቸው እንድደሰትና ከዚህ አዲስ አካባቢ ጋር ቶሎ እንድላመድ ረድቶኛል።
በ1993 ወደ ዋና ከተማዋ ቴራን ስደርስ በአልባኒያ አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ሲሆን በመላው አገሪቱ የሚገኙት ምሥክሮች ከ100 ብዙም አይበልጡም ነበር። በዚያ ወር በቴራን ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ 585 ሰዎች ተገኝተው 42 ተጠምቀዋል። ምንም እንኳ ቋንቋው ባይገባኝም ምሥክሮቹ ሲዘምሩ መስማትና ፕሮግራሙን በትኩረት ሲከታተሉ መመልከት ልብን ደስ የሚያሰኝ ነበር። በሚያዝያ ወር በተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይም 1,318 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በአልባኒያ የሚደረገው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገት ማድረግ የጀመረው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነው።
አራተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የቤቴ በረንዳ ላይ ሆኜ ከተማዋን ቁልቁል እየተመለከትኩ ‘ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች ምሥራቹን የምናዳርሰው መቼ ይሆን?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። ይሖዋ አምላክ ሥራውን አከናውኖታል። ዛሬ በቴራን 23 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚገኙ ሲሆን በመላው አገሪቱ ደግሞ 2,846 ምሥክሮች፣ 68 ጉባኤዎችና 22 ቡድኖች አሉ። በጥቂት ዓመት ውስጥ እንዲህ ያለ እድገት መገኘቱ በጣም የሚያስደንቅ ነው! በ2002 በተደረገው የመታሰቢያው በዓል ላይ ደግሞ 12,795 ሰዎች ተገኝተው ነበር።
አልባኒያ በቆየሁባቸው አሥር ዓመታት 40 ሰዎች ለጥምቀት እንዲበቁ የመርዳት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በአቅኚነት ወይም በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ላይ ናቸው። ባለፉት ዓመታት በአልባኒያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ እንዲያግዙ ከኢጣሊያ ስድስት የአቅኚዎች ቡድን ተልኮ ነበር። ለእያንዳንዱ ቡድን ለሦስት ወር የሚቆይ የቋንቋ ኮርስ የተሰጠ ሲሆን የመጨረሻዎቹን አራት ቡድኖች የማስተማር መብት አግኝቻለሁ።
ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቅቄ እንደምወጣ ጓደኞቼ በሰሙ ጊዜ የተሰማቸው የመደነቅ ስሜት በጣም ከፍተኛ ነበር። ሆኖም ባሳለፍኳቸው በእነዚህ ዓመታት ተረጋግቼና በሰላም እንደምኖር ሲመለከቱ አመለካከታቸው እየተስተካከለ መጥቷል። አሁን ድረስ መነኩሲት የሆነችው የ93 ዓመቷን አክስቴን ጨምሮ ቤተሰቦቼ ጥሩ ድጋፍ ያደርጉልኛል።
ይሖዋን ካወቅኩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ይሖዋ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ተንከባክቦ ይዞኛል! ወደ ድርጅቱም መርቶኛል። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ድሆችን፣ የተጨቆኑትንና ችግረኞችን ለመርዳት የነበረኝን ምኞትና አምላክን ሙሉ በሙሉ ለማገልገል የነበረኝን ጉጉት አስታውሳለሁ። ይሖዋ የረዥም ጊዜ መንፈሳዊ ምኞቴን ስላሟላልኝ ከልብ አመሰግነዋለሁ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናኋቸው የአልባኒያ ቤተሰብ አባላት መካከል አሥራ አንዱ ተጠምቀዋል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናኋቸው ከእነዚህ የአልባኒያ ሴቶች መካከል ብዙዎቹ አሁን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው