ከጉልበተኝነትና ከጥቃቱ መገላገል
ከጉልበተኝነትና ከጥቃቱ መገላገል
‘ጉልበተኝነት አብሮ የሚወለድ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ የሚለመድ ባሕርይ ነው። በልምድ የመጣ ነገርን ደግሞ መተው ይቻላል።’—ዶክተር ሳሊ መርፊ
ጉልበተኛውም ሆነ ተጠቂው ሁለቱም እርዳታ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ጉልበተኛው ኃይል ሳይጠቀም ከሌሎች ጋር በሰላማዊ መንገድ መግባባትን መማር ያስፈልገዋል። ጉልበተኞች የሚያስቸግሩት ሰው ደግሞ ከችግሩ የሚገላገልበትን ዘዴ መቀየስ ያስፈልገዋል።
ብዙውን ጊዜ ጉልበተኛው ከሌሎች ጋር በሰላማዊ መንገድ መግባባት ስለማያውቅ የሚያስፈራራቸውን ሰዎች ስሜት ሳይረዳ ይቀራል። በተገቢው መንገድ ሐሳቡን እንዴት መግለጽ እንደሚችል እየተከታተለ የሚያስተምረው ሰው ያስፈልገዋል። ቴክ አክሽን አጌንስት ቡሊይንግ የተሰኘው መጽሐፍ “ጉልበተኞች አዲስ ባሕርይ እንዲያዳብሩ እስካልተማሩ ድረስ ዕድሜ ልካቸውን ጉልበተኞች እንደሆኑ ይኖራሉ። የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና በሥራ ቦታ የበታች ሠራተኞችን ያስቸግራሉ።”
ልጆች ጉልበተኞች እንዳይሆኑ መርዳት
ልጆች አዛኝ እንዲሆኑ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን የኋላ ኋላ ጉልበተኞች እንዳይሆኑ ለመከላከል ይረዳል። በአንዳንድ አገሮች የሌላን ችግር እንደራስ አድርጎ እንዴት ማየት እንደሚቻል የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ዓላማውም ልጆች ገና ከአምስት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ የሌሎችን ስሜት የሚረዱ እንዲሆኑና ሰዎችን በደግነት እንዲይዙ ማስተማር ነው። የዚህ ሥልጠና ውጤት ገና በአኀዛዊ መረጃ የተደገፈ ባይሆንም እንኳ ገና ከጅምሩ ይህን
ትምህርት ያገኙት ልጆች ካላገኙት ይልቅ ሰላማዊ እንደሆኑ የሚጠቁም መረጃ ተገኝቷል።ወላጅ ከሆንክ እንዲህ ያለውን ማሠልጠኛ መስጠቱን ለትምህርት ቤቶች ብቻ መተው የለብህም። ልጅህ ጉልበተኛ እንዳይሆን ከፈለግህ ሌሎችን በክብር እንዴት መያዝ እንዳለበት በቃልም ሆነ በተግባር ማስተማር ያስፈልግሃል። ለዚህ ምን ሊረዳህ ይችላል? በዚህ ረገድ ብዙም ትኩረት አልተቸረውም እንጂ ግሩም የሆነ የማስተማሪያ መሣሪያ ተዘጋጅቶልሃል። እርሱም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ስለ ጉልበተኝነት ምን አመለካከት እንዳለው በግልጽ ያስተምራል። አምላክ ጉልበተኝነትን በጣም ይጸየፋል! መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ “ዐመፃን የሚወዱትን . . . ነፍሱ ትጠላቸዋለች” ይላል። (መዝሙር 11:5 አ.መ.ት) ከዚህም በላይ አምላክ እየተፈጸሙ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ይመለከታል። አምላክ እስራኤላውያንን “ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው” ግፈኞች የተሰማውን ሐዘን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮታል። (መሳፍንት 2:18) በማን አለብኝነት ተነሳስተው ደካማና ረዳት የሌላቸውን ምስኪኖች ያጠቁ ሰዎችን አምላክ የቀጣባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ።—ዘጸአት 22:22-24
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሌሎችን ችግር እንደ ራስ በመመልከት ረገድ ከሁሉ የላቀ ሊባል የሚችል መመሪያ ይዟል። ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ልጆች ወርቃማ ሕግ ተብሎ የሚታወቀውን ይህን መመሪያ እንዲቀበሉ ማለትም እንዲወዱትና በሥራ እንዲያውሉት ማስተማር ቀላል አይደለም። ትንንሽ ልጆች በተፈጥሯቸው ራስ ወዳዶች ስለሆኑ ይህን ለማድረግ ጥሩ ምሳሌ መሆንን፣ ቁርጠኝነትንና ጥረትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጥረት ሊደከምለት የሚገባ ነው። ልጆችህ ደጎችና ለሰው የሚያዝኑ እንዲሆኑ ከተማሩ ጉልበተኝነትን ይጸየፉታል።
ለተጠቂዎች የሚሆን እርዳታ
በጉልበተኞች መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች በተለይ ደግሞ ትናንሽ ልጆች ሚዛናቸውን መጠበቅ ያስቸግራቸዋል። አንድ ጉልበተኛ የሚያስቸግርህ ምናልባት ሊያናድድህ ፈልጎ ይሆናል። ይህን የሚያደርገው ስትናደድ አለዚያም ስትፈራ ማየት ስለሚፈልግ ሊሆን ይችላል። ከተናደድክ ወይም ካለቀስክ እንዲሁም ከተጎዳህ ወይም ከፈራህ ጉልበተኛው የልብ ልብ ይሰማዋል። ስለዚህም እየደጋገመ ሊያናድድህ ይሞክራል።
ታዲያ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት። ምክሩ በዋነኝነት ለልጆች የተጻፈ ቢሆንም መሠረታዊ ሐሳቡ ጉልበተኞች ለሚያስቸግሯቸው ትልልቅ ሰዎችም ይሠራል።
▪ ተረጋጋ። አትናደድ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል። (መዝሙር 37:8) ከተናደድክ ጉልበተኛው እንዲቆጣጠርህ ፈቀድክለት ማለት ነው። በተጨማሪም የምት ጸጸትበትን ነገር ልታደርግ ትችላለህ።—ምሳሌ 25:28
▪ የበቀልን ሐሳብ ከአእምሮህ አውጣ። ብዙውን ጊዜ በቀል የሚወልደው በቀልን ነው። ምንም ቢሆን በቀል ጥሩ ውጤት አያስገኝም። በ16 ዓመቷ አምስት ልጃገረዶች ተባብረው የደበደቧት አንዲት ልጅ እንዲህ ትላለች:- “በልቤ ‘ቆይ ላግኛቸው’ ብዬ አሰብኩ። እኔም ከጓደኞቼ ጋር ሆንኩና ሁለቱን ደበደብኳቸው።” ውጤቱስ ምን ሆነ? “የባዶነት ስሜት ተሰማኝ” ትላለች። ከዚያ በኋላ ባሕርይዋ የባሰ ተበላሸ። “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስታውስ።—ሮሜ 12:17
▪ ነገሩ እየከረረ ከመጣ ቶሎ ብለህ ከአካባቢው ሽሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው” ይላል። (ምሳሌ 17:14) ከሁሉ የሚሻለው ከጉልበተኞች መሸሽ ነው። ምሳሌ 22:3 “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” ይላል።
▪ ጉልበተኛው እየተከታተለ የሚያስቸግርህ ከሆነ ማነጋገር ያስፈልግህ ይሆናል። ረጋ የምትልበትን ጊዜ ምረጥና ጉልበተኛውን ፊት ለፊት እያየህ ጠንከር ባለ ሆኖም በተረጋጋ መንፈስ አነጋግረው። በሚያደርገው ነገር እንደማትደሰትና የጉልበተኝነት ድርጊቱ የሚያስቅ ሳይሆን የሚጎዳ እንደሆነ ንገረው። ስትናገር የስድብና የዛቻ ቃላት አትሰንዝር።—ምሳሌ 15:1
▪ ጉልበተኛው እያደረሰብህ ስላለው ችግር ለአንድ ለሚያስብልህ ትልቅ ሰው ተናገር። ችግሩን ለይተህ በመጥቀስ እርዳታ እንዲያደርግልህ ጠይቀው። ለአምላክም በጸሎት ንገረው። ይህም ግሩም የሆነ የእርዳታና የመጽናኛ ምንጭ ሊሆንልህ ይችላል።—1 ተሰሎንቄ 5:17
▪ ዋጋ ያለህ ሰው መሆንህን አስታውስ። ጉልበተኛው ምንም ዋጋ እንደሌለህና በክብር ልትያዝ የሚገባህ እንዳልሆንክ ሊያሳምንህ ይፈልጋል። ፈራጅህ ግን እርሱ ሳይሆን አምላክ ነው። አምላክ ደግሞ በእያንዳንዳችን ውስጥ መልካም ነገር ያገኛል። እንዲህ ያለ ጠባይ በማዳበሩ ዋጋ ቢስ የሆነው ጉልበተኛው ራሱ ነው።
ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ጠብቁ
ወላጆች ልጆቻቸው ጉልበተኞችን መቋቋም እንዲችሉ ገና ከትንሽነታቸው ጀምረው ሊያዘጋጁአቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ልጆቹ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዴት ማሳየት እንደሚችሉ በሠርቶ ማሳያ አሠልጥኗቸው።
ቀጥ ብሎ መቆም እንኳን አንዳንድ ጉልበተኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያደርግ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ዓይን ዓይኑን ማየት፣ ዘና ብሎ መቆምና በድፍረት ፈርጠም ብሎ መናገርም ሊረዳ ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው ከጉልበተኞች እንዲሸሹ እንዲያስተምሯቸውና በትምህርት ቤቱ የሚያስተምር መምህርም ይሁን ወይም ሌላ እምነት የሚጣልበት አዋቂ ሰው ልጆቻቸውን እንዲከታተልላቸው እንዲያደርጉ ተመክረዋል።
የጉልበተኝነትን ጠባይ ማስወገድ የሚጀምረው ቤተሰብን በማስተማር ነው። ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ የሚያሳልፉ፣ በጥሞና የሚያዳምጧቸውና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለማወቅ የሚጥሩ ወላጆች ልጆቻቸው ለእነሱ ውድ እንደሆኑና እንደሚደሰቱባቸው እንዲሁም ማንኛውንም ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ዝግጁ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። በልጆች አስተዳደግና በእኩዮች የሚደርሱ ችግሮች ላይ ጥናት ያካሄዱ ብዙ ባለሞያዎች ወላጆች ልጆቻቸው ስለ ራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው እንዲረዷቸው ይመክራሉ። ልጆች ስለ ራሳቸው እንዲህ ዓይነት ጤናማ አመለካከት መያዛቸው በጉልበተኞች ዒላማ ውስጥ እንዳይገቡ ይረዳል።
ከመናገር የሚበልጥ ነገር ማድረግም ያስፈልጋል። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሌሎችን እንዴት በክብር እንደሚይዝ መማርና የሰውን ችግር እንደ ራስ አድርጎ የመመልከት ባሕርይን መኮትኮት ያስፈልገዋል። ስለዚህ በቤትህ ውስጥ ምንም ዓይነት የጉልበተኝነት ባሕርይ እንዲኖር አትፍቀድ። ቤትህ አክብሮትና ፍቅር የሰፈነበት ማረፊያ እንዲሆን አድርግ።
ጉልበተኞች የማይኖሩበት ጊዜ
መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለመጉዳት ነው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 8:9 NW) መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ ታሪክ የሚገልጸው በዚህ መንገድ ነው። በእርግጥም ጉልበተኞች የሰው ልጆችን ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲያሠቃዩ ኖረዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።”—መክብብ 4:1
አምላክ በዓለም ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጉልበተኝነት ድርጊት በሙሉ ስለሚመለከት እየተገፉ ላሉት ሰዎች ይራራላቸዋል። ታዲያ የሚያደርገው ነገር ይኖር ይሆን? እንዴታ! በሚክያስ 4:4 ላይ የሰጠውን የሚከተለውን ተስፋ ልብ በል:- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”
ይህ ተስፋ ሲፈጸም ዓለም ምን ልትመስል እንደምትችል እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። ሌሎችን እያስፈራራ የሚኖር ጉልበተኛ አይኖርም! ይህ የሚያስደስት አይደለም? አምላክ ይህን ተስፋ ከመስጠት የሚበልጥ ነገርም አድርጓል። አሁንም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመላው ዓለም በመሰጠት ላይ ነው። ይህም አበረታች ውጤት እያመጣ ነው። በዚህ ትምህርት የሚካፈሉ ሁሉ ዕብሪተኛ የሆነ ጠባያቸውን ትተው ሰላማዊና ሌሎችን በክብር የሚይዙ እንዲሆኑ እየተማሩ ነው። (ኤፌሶን 4:22-24) በቅርቡ የዚህ ወደር የለሽ ትምህርት ውጤቶች በምድር በሙሉ ይዳረሱና የጉልበተኝነት ችግር ለዘላለም ይወገዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገቡት የአምላክ ተስፋዎች እውን ይሆናሉ። በዚያን ጊዜ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ከጉልበተኞች በጸዳ ዓለም ውስጥ በመኖር ይደሰታል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጉልበተኛ መሸሽ አያሳፍርም
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ማንኛውንም ዓይነት ጉልበተኝነት እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ይማራሉ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ልጆቻችሁ ጠንከር ባለ ሁኔታ ሆኖም በዘዴ መናገር እንዲችሉ አስተምሯቸው