ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
የውሾችን ቋንቋ መረዳት?
አንድ የጃፓን አሻንጉሊት አምራች ድርጅት የውሾችን ጩኸት ወደ ሰው ቋንቋ ይለውጣል የተባለ መሣሪያ እንደሠራ የጃፓን ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ ዘግቧል። መሣሪያው ውሻው አንገት ላይ የሚታሰር ማይክሮፎን ሲኖረው ውሻው የሚያሰማውን ጩኸት ወደ ትንሽ የሬዲዮ መቀበያ መሣሪያ ያስተላልፋል። የመቀበያ መሣሪያው የውሻውን ጩኸት ከመረመረ በኋላ ወደ ስድስት የስሜት ዓይነቶች ይለውጣል ተብሏል። እነዚህም የስሜት ዓይነቶች ተስፋ መቁረጥ፣ ቁጣ፣ ደስታ፣ ሐዘን፣ ፍላጎትና ማስገደድ ናቸው። የምርመራው ውጤት በሬዲዮ መቀበያው ሰሌዳ ላይ የሚታይ ሲሆን “በጣም ደስ ብሎኛል!”፣ “እስቲ እንጫወት!” እና “በጣም ያናድዳል!” እንደሚሉ ያሉ ሐረጎች ይነበባሉ። አምራቹ ድርጅት በጃፓን አገር ብቻ 300,000 የሚያክሉ መሣሪያዎችን እንደሸጠ ሲገልጽ የአንዱ መሣሪያ ዋጋ 800 ብር ገደማ ነው። በደቡብ ኮሪያና በዩናይትድ ስቴትስ መሸጥ ሲጀምር ደግሞ ጠቅላላ ሽያጩ አንድ ሚሊዮን እንደሚደርስ ተስፋ አድርጓል።
ገዳይ የሆኑ ፌስታሎች
በመላው ዓለም በየዓመቱ 100,000 የሚያክሉ አጥቢ እንስሳት፣ አእዋፍና ዓሦች የተጣለ ፌስታል በመብላት ወይም በፌስታል ታፍነው እንደሚሞቱ ይገመታል። በአውስትራሊያ ብቻ በየዓመቱ ሸማቾች 6.9 ቢሊዮን የሚያክሉ ፌስታሎች የሚጠቀሙ ሲሆን ይህም እያንዳንዱ ሸማች በአማካይ 360 ፌስታሎች ይፈጃል ማለት ነው። ከእነዚህ መካከል 25 ሚሊዮን የሚያክሉት ፌስታሎች ቆሻሻ ሆነው ይጣላሉ። የሲድኒው ሳንዴይ ቴሌግራፍ በ2002 መጨረሻ ላይ በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለመቀነስ የአውስትራሊያ የገበያ አዳራሾች የተለመዱትን የፕላስቲክ ከረጢቶች ሊበሰብሱ ከሚችሉ ጥሬ ዕቃዎች በሚሠሩ ከረጢቶች እንደሚተኩ ዘግቧል። አዲሶቹ ከረጢቶች በመልካቸውም ሆነ በልስላሴያቸው ከፌስታሉ የማይለዩ ሲሆኑ የተሠሩትም ከካሳቫ ከሚገኝ ስታርች ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ከረጢቶች በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በስብሰው ይጠፋሉ። ፕላኔት አርክ የተባለው የአካባቢ ደህንነት ተሟጋች ማኅበር ሊቀ መንበር የሆኑት ፖል ሸንስተን “በአውስትራሊያ በቀላሉ የሚበሰብስና በዋጋውም ከተለመደው ፌስታል ጋር የሚመጣጠን ሆኖ ያገኘነው ይህን ከረጢት ነው” ብለዋል። አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው “81 በመቶ የሚያክሉ ገበያተኞች በቀላሉ ሊበሰብሱ በሚችሉ ከረጢቶች መጠቀም አለብን ብለው በጥብቅ ያምናሉ።”
ለሃይማኖት ፍላጎት የለኝም
አሳሂ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ “ጃፓናውያን የጊዜያችንን አስጨናቂ ሁኔታዎች ለመቋቋም በሚጥሩበት ጊዜ ለሚያጋጥሟቸው ጥያቄዎችና ችግሮች መልስ ለማግኘት የሃይማኖትን እርዳታ የሚፈልጉ አይመስልም” ይላል። “የምታምንበት ሃይማኖት ወይም አንድ ዓይነት እምነት አለህ? ወይም ለሃይማኖት ፍላጎት አለህ?” የሚለው ጥያቄ ከቀረበላቸው ወንዶችና ሴቶች መካከል የአዎንታ መልስ የሰጡት 13 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ተጨማሪ 9 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችና 10 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ “አነስተኛ ፍላጎት” እንዳላቸው ተናግረዋል። “በተለይ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ለሃይማኖት ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት 6 በመቶ ብቻ ናቸው” በማለት ጋዜጣው አክሏል። ዓመታዊው ጥናት ከጃፓናውያን ወንዶች መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት ከሴቶቹ ደግሞ 76 በመቶ የሚሆኑት ስለማንኛውም ዓይነት ሃይማኖት ወይም እምነት ደንታ እንደሌላቸው አረጋግጧል። ጃፓናውያን ለሃይማኖት ያላቸው ፍላጎት በ1978 የተደረገ ተመሳሳይ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ካስገኘው ውጤት በግማሽ ቀንሷል። በአጠቃላይ ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት በዕድሜ ጠና ያሉት በተለይም ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው ናቸው።
ጭንቀት ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተዛማጅነት አለው
ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት “የዓለም ጤና ድርጅት በ2020 የመንፈስ ጭንቀት በመላው ዓለም ከልብ በሽታ ቀጥሎ ሁለተኛው የጤና መታወክ ምክንያት ይሆናል” ብሏል። ይህ ከባድ የሆነ የጤና ችግር “ሙሉ በሙሉ ሥነ ልቦናዊ” እንደሆነ አይታሰብም። በብሔራዊ የአእምሮ ጤና ማዕከል የኒውሮኢንዶክሪኖሎጂ ኃላፊ የሆኑት ፊልፕ ጎልድ “የመንፈስ ጭንቀት ሁሉንም ሌሎች በሽታዎች ሊያባብስ የሚችል ብቸኛው መላውን ሰውነት የሚነካ ችግር ነው” ብለዋል። እንዲያውም የመንፈስ ጭንቀት እንደልብ በሽታና ስኳር በሽታ ለመሰሉት የጤና ችግሮች መንስዔ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች “የልባቸው የመለጠጥ ችሎታ አነስተኛ በመሆኑ ሰውነታቸው የሚጠይቀውን የደምና የኦክሲጅን ፍላጎት የማሟላት አቅም እንደሚያንሰው” ጥናቶች አመልክተዋል። በተጨማሪም “የተጨነቀ አእምሮ ብዙ ጉልበት ያስፈልጋል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ይህ ደግሞ ሰውነት ኮርቲዞል የተባለውን ሆርሞን እንዲያመነጭ ስለሚያዝ በደም ውስጥ የሚኖረው የስኳር መጠን ከፍ ይላል።” በተጨማሪም በመንፈስ ጭንቀትና በኦስትዮፖሮሲስ (አጥንትን የሚጎዳ በሽታ) እንዲሁም በካንሰር መካከል ተዛማጅነት እንዳለ ተስተውሏል። የመንፈስ ጭንቀቱን ማከም በእነዚህ የጤና እክሎች ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችል እንደሆነ ለማወቅ ጥናቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።
ትዳርና ልብ
የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ “የአንድ ሰው የትዳር ሁኔታ ከልብ ቀዶ ሕክምና ቶሎ በማገገም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥናቶች አመልክተዋል” ብሏል። በዩናይትድ ስቴትስ፣ የፔንስልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጀምስ ኮይን ጥሩ ትዳር አንድ በሽተኛ ሕመሙን አሸንፎ ቶሎ እንዲያገግም የሚገፋፋው ምክንያት እንዲኖረው ሲያደርግ “መጥፎ ትዳር ግን ትዳር ከሌለውም የባሰ ጉዳት ሊያስከትል” እንደሚችል ተናግረዋል። ዶክተር ኮይንና ከእርሳቸው ጋር የሚሠራው የጥናት
ቡድን በባልና ሚስቶች መካከል የሚፈጠረውን ጭቅጭቅ በቪዲዮ ከቀዱ በኋላ ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር የሚጣሉ የልብ ሕመምተኞች አምርረው ካልተጣሉት በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመሞት አጋጣሚያቸው በእጥፍ በልጦ መታየቱን ተገንዝበዋል። በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሊንዳ ዌት ጥሩ ትዳር ለጥሩ ጤና አስተዋጽኦ በማድረግ ረገድ “ጥሩ አመጋገብ ከመከተል፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግና ካለማጨስ ጋር ሊመደብ ይችላል” ከሚል ድምዳሜ ደርሰዋል።ፈገግታ ያለው ኃይል
ቭፕሮስት የተባለው መጽሔት በክራኮቭ፣ ፖላንድ የሚገኘው የያጌሎንያን የማኅበረሰብ ጥናት ተቋም ስላደረገው ጥናት ሲዘግብ “ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት ፊታቸውን ከሚያጨፈግጉ ሰዎች ጋር ለንግድም ሆነ ለሥራ ጉዳይ መገናኘት እንደማይፈልጉ ሲገልጹ 69 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ጋር መወዳጀት እንደማይችሉ ተናግረዋል” ብሏል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ሐዘንተኛ ሰዎች በውስጣቸው አንድ የደበቁት ነገር አለ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ሕዝብ ፊት የሚቀርቡ ሰዎች ይህን ካወቁ ረዥም ጊዜ የሆናቸው በመሆኑ “ፖለቲከኞች፣ የንግድ ሰዎች፣ ዘፋኞች፣ የቴሌቪዥን አስተዋዋቂዎች እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነትና የሽያጭ ሠራተኞች ፈገግታ አይለያቸውም” ብሏል ቭፕሮስት። በተጨማሪም ፈገግ በምንልበት ጊዜ ወደ አንጎላችን የሚደርሰው ደም ስለሚጨምር ጥሩ ስሜት እንደሚሰማን ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። በንግድ ሥራ የተሰማራች አንዲት ሴት “ደስ ባላለኝ ጊዜ እንኳን ፈገግ ለማለት እሞክራለሁ። ፈገግ በምልበት ጊዜ በውስጤ ለውጥ ይሰማኛል። በእርግጥ ስሜቴ ይሻሻላል” ስትል ገልጻለች።
ባዕድ ቋንቋ መማር
ባዕድ ቋንቋ መማር ትፈልጋለህ? ፖራድኒክ ዶሞቪ የተባለው የፖላንድ መጽሔት የሚከተለውን ምክር ይሰጣል። “መሳሳትና አዲስ ቋንቋ መማር ፈጽሞ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች ናቸው። አዲስ ቋንቋ ለመቻል የመጀመሪያው እርምጃ ይህን ሐቅ መቀበል ነው።” ከዚህም በተጨማሪ “ግምታዊ ሙከራ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል።” አንድ ነገር እንዴት እንደሚነገር ካላወቅን “አንጎላችን ያመጣልንን በግምት ለመናገር እንገደዳለን።” ይህ ደግሞ ብሳሳትስ በሚል ፍርሃት ዝም ከማለት ይሻላል። መጽሔቱ “የችግራችን ምንጭ ፍርሃት ወይም እፍረት መሆኑን ብዙ ጊዜ አንገነዘብም” ይላል። “እነዚህን ድክመቶች መወጣት ከቻልን ፈጣን እድገት እንደምናደርግ አያጠራጥርም።” በተጨማሪም ጥሩ አስተማሪ ፍርሃትን ለማሸነፍና ፈጣን እድገት ለማድረግ ሊረዳ ይችላል።
የጠፉ ዘመዶች
በመላው ዓለም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በጦርነት ወይም በሕዝባዊ ግጭት ምክንያት የጠፉ ዘመዶቻቸው የት እንደደረሱ አያውቁም። በቅርቡ በጀኔቭ፣ ስዊዘርላንድ “የጠፉ ሰዎች” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተደረገ አንድ ጉባኤ ላይ ዘመዶቻቸው የጠፉባቸው ሰዎች ስለሚያጋጥማቸው ችግር ውይይት እንደተደረገ ፍራንክፉርተር አልገማይነ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የጠፉ ሰዎች ፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት ሶፊ ማርቲን እንደሚሉት ከሆነ “ጦርነቱ ካበቃ ከብዙ ዓመት በኋላ እንኳን እነዚህ ቤተሰቦች ከሥጋት አይላቀቁም።” አብዛኛውን ጊዜ ዘመዶቻቸው የጠፉባቸው ቤተሰቦች “በተረጋጋ አእምሮ ኑሯቸውን መምራት ወይም ሐዘናቸውን መርሳት ያቅታቸዋል።” አብዛኛውን ጊዜ ጎራ ለይተው ይዋጉ የነበሩ ወገኖች የጠፉ ሰዎችን ፈልጎ በማግኘት ረገድ ለመተባበር ፈቃደኛ አይሆኑም። ችግሩ አቅም ማጣት ሳይሆን የፈቃደኝነት ጉድለት ሊሆን ይችላል። አንድ ባለሞያ እንደጠቆሙት የጠፉ ሰዎች ስለሞቱበት ሁኔታ መግለጽ በጦርነቱ ጊዜ የተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶችን ይፋ ሊያወጣ ይችላል።