ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ የተጣለልኝ መሠረት
ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ የተጣለልኝ መሠረት
ኧርነስት ፓንዳቹክ እንደተናገረው
የተወለድኩት በካናዳ በምትገኘው በሣር የተሸፈነ ሜዳ በተንጣለለባት በሳስካቼዋን ክፍለ ሀገር ነው። በ23 ዓመቴ ወደ አፍሪካ የሄድኩ ሲሆን በዚያም ለ35 ዓመታት በሚስዮናዊነት አስደሳች ሕይወት አሳልፌያለሁ። ሕይወቴ ወደዚህ አቅጣጫ ያዘነበለው እንዴት ነበር? በአጋጣሚ አይደለም። እስቲ ልንገራችሁ።
የመጀመሪያው ቤታችን ቤተሰባችንን ከኃይለኛው የክረምት ቁር ለመከላከል ያህል ከአጣና፣ ከጭቃና ከሣር እንደነገሩ የተሠራ ነበር። በ1928 ከዘጠኝ ልጆች ውስጥ አብዛኞቻችን ከመወለዳችን በፊት ወላጆቻችን ቤታችን ድረስ መጥቶ ከነበረ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ተቀብለው ነበር። በቀጣዩ ረዥም ክረምት በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን አጠኑ። የጸደይ ወራት ሲገባ እውነትን እንዳገኙ እርግጠኞች ሆነው ነበር። ያገኙትን እውቀት ለወዳጅ ዘመዶቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን በተለይም ለእኛ ለልጆቻቸው ይነግሩን ነበር።
እኔ የተወለድኩት በ1931 ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አምስቱ ወንድሞቼና እህቶቼ ተወለዱ። ቤተሰባችን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ የማንበብና የማጥናት ልማድ ነበረው። ጧት ጧት አንድ ላይ እናሳልፍ የነበረው ጊዜ አሁን ድረስ አይረሳኝም። አባቴ የየዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውይይት ይመራ የነበረ ሲሆን እንግዶች በሚኖሩበት ጊዜም እንኳን ይህ ልማድ አይቋረጥም ነበር። አባቴና እናቴ እንዲሁም ታላላቆቼ በየተራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያነብቡ ነበር።
አባታችን ማንበብና መጻፍ ያስተማረን ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንሶችን በመጠቀም እንዴት ምርምር ማድረግ እንደምንችል አሳይቶን ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ እምነታችንን ለሌሎች ለማስረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደምንጠቀም ተማርን። እነዚህ አስደሳች ውይይቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በሚገባ ለማስተዋል እንድችል ረድተውኛል። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሜ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ትክክል እንዳልሆኑ ማስረዳት ቻልኩ። ነፍስ ሟች እንደሆነች፣ ሲኦል መቃጠያ ቦታ እንዳልሆነ፣ አምላክና ኢየሱስ እኩል እንዳልሆኑ ወይም የሥላሴ ክፍል እንዳልሆኑ ማስረጃ እየጠቀስኩ ማስረዳት ጀመርኩ።—መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ ዮሐንስ 14:28
አባቴና እናቴ ምሳሌ በመሆን ጭምር ያስተምሩን የነበረ ሲሆን በሰዎች ዘንድ የማይወደድ ቢሆንም እንኳን ትክክል
ለሆነው ነገር እንድንቆም ያበረታቱን ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እነርሱ ትንባሆ አጭሰው የማያውቁ ከመሆኑም በላይ ትንባሆ ሰውነትን እንደሚያረክስና በትምህርት ቤት እንድናጨስ ተጽዕኖ እንደሚደረግብን አስቀድመው ያስጠነቅቁን ነበር። አባቴ “አናጨስም ስትሉ ሴታ ሴት ትባሉ ይሆናል። ግን እንዲህ የሚላችሁን ሰው ‘ሴታ ሴት ማን ነው? የትንባሆ ተገዢ የሆነው? ወይስ ትንባሆ የማያጨሰው?’ ብላችሁ ጠይቁት” በማለት የነገረንን አስታውሳለሁ።በ11 ዓመቴ ደግሞ በልጅነቴ ያገኘሁትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥልጠና ተግባራዊ አደርግ እንደሆነና እንዳልሆነ የተፈተንኩበት ሌላ ሁኔታ አጋጠመኝ። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ስለነበር በትምህርት ቤት ለባንዲራ ያለንን ታማኝነት እንድንገልጽ ይጠበቅብን ነበር። ይህ የጣዖት አምልኮ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተረድቼ ስለነበር እንዲህ ባለው ሥነ ሥርዓት እንደማልሳተፍ ገለጽኩ። በዚህም ምክንያት ለስድስት ወራት ከትምህርት ቤት ተባረርኩ።
የሆነ ሆኖ ከጊዜ በኋላ ትምህርቴን ጨረስኩና በመጋቢት 1947 ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅሁ። ከስድስት ወራት በኋላ አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ ሆንኩ። በመጀመሪያ በደቡባዊ ሳስካቼዋን ሠፊ ክልል ለሚኖሩ ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች እመሠክር ነበር። በበጋ በፈረስ እጓዝ የነበረ ሲሆን በቀዝቃዛው ክረምት ደግሞ ካቡስ ብለን በምንጠራው በፈረስ የሚጎተት ጋሪ እጠቀም ነበር። ለሙቀት የከሰል ምድጃ ስለምጠቀም ጋሪው እንዳይገለበጥ መጠንቀቅ ነበረብኝ።
የአካባቢው ነዋሪዎች የሚቀረቡና እንግዳ ተቀባዮች ነበሩ። ከሰዓት በኋላ እቤታቸው ከሄድኩ ብዙውን ጊዜ እንዳድር ይጋብዙኝ ነበር። ከእነሱ ጋር በማድርበት ጊዜ የምናደርጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶች በጣም ያስደስቱኝ ነበር! ከእነዚህ አንዱ የፒተርሰን ቤተሰብ ነው፤ ከዚህ ቤተሰብ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ስንወያይ ካደርን በኋላ ምሥራቹን የተቀበሉ ሲሆን አርልና እናቱ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
በኩቤክ ማገልገል
በ1949 በኩቤክ ክፍለ ሀገር በሚደረገው የስብከት ሥራ እንዲረዱ ለአቅኚዎች ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ሰጠሁ። ከምዕራብ ካናዳም 200 የሚሆኑ አቅኚዎች እንዲሁ ራሳቸውን አቅርበው ነበር። የአገልግሎት ምድባቸውን ለመቀበል በመስከረም ወር ሞንትሪያል ከተማ ደረሱ። ጊዜው ኩቤክን ከይሖዋ ምሥክሮች ለማጥራት ቃል ገብቶ የነበረው ካቶሊኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪስ ዱፕሌሲ በሥልጣን ላይ የነበረበት ወቅት ነበር።
እነዚያ ጊዜያት ሥራ የበዛባቸውና አስደሳች ቢሆኑም ፈታኝ ሁኔታዎችም ነበሩባቸው። ፈታኝ ከሚባሉት ሁኔታዎች መካከል ፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር፣ እስራትና የሕዝብ ረብሻ እንዲሁም አክራሪዎች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን ለማቋረጥ የሚፈጥሩት ረብሻ ይገኙበታል። እንዲህ ዓይነቱ ተቃውሞ ግን እንድፈራ ወይም አምላክን ከማገልገል ወደ ኋላ እንድል አላደረገኝም። ወላጆቼ ትክክል የሆነውን ነገር እንድወድና ኢየሱስ በትንቢት የተናገረለት ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ ተቃውሞ ቢኖርም መከናወኑ እንደማይቀር ጽኑ እምነት እንዳዳብር አድርገው ነበር።—ማቴዎስ 24:9, 14
በኩቤክ በነበርኩበት ጊዜ ኤሚሊ ሆውሪሽ ከተባለች ከሳስካቼዋን የመጣች ታማኝ አቅኚ እህት ጋር ተገናኘን። ጥር 27, 1951 ከተጋባን ጀምሮ ኤሚሊ ታማኝ የሥራ ባልደረባዬና የብርታቴ ምንጭ ሆናልኛለች። በአገልግሎቱ ይበልጥ በተሟላ መልኩ ለመካፈል ግብ ስለነበረን ሚስዮናውያን
ለወራት በሚሰለጥኑበት በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተን ለመማር አመለከትንና ተቀባይነት አገኘን። በየካቲት 1953 ከ20ኛው የጊልያድ ክፍል ተመረቅን።ወደ አፍሪካ ለመግባት የሚያስችለንን የይለፍ ወረቀት በመጠባበቅ ላይ ሳለን በካናዳ ውስጥ በአልበርታና በኦንታሪዮ ያሉ ጉባኤዎችን እንድንረዳ ተጋበዝን። በዚያ ጊዜ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው የምንሄደው በሕዝብ መጓጓዣ ነበር። ስለዚህ ኑሯችንን ቀላል ማድረግንና ጓዛችንን በአንድ ሻንጣ መሸከምን መማር ነበረብን። ከጥቂት ወራት በኋላ የጉዞ እና የይለፍ ወረቀታችንን ስናገኝ አሁን ዚምባብዌ ተብላ ወደምትጠራው የቀድሞዋ ደቡባዊ ሮዴዢያ ጉዞ ጀመርን።
ከአፍሪካ ኑሮ ጋር መላመድ
አፍሪካ በደረስን በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ በዚምባብዌ፣ በቦትስዋና እና (አሁን ዛምቢያ በምትባለው) በሰሜናዊ ሮዴዢያ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድንጎበኝ ተመደብን። በጊልያድ ትምህርት ቤት ሳለን የተመደብንበትን አገር ኑሮ ከትውልድ አገራችን ጋር እንዳናወዳድር እንዲሁም ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ከተሞክሮው አንድ ጠቃሚ ነገር የሚገኝ መሆኑን እንድናስታውስ ማበረታቻ ተሰጥቶን ነበር። እንደዚህ ያለው ጥበብ ያዘለ ምክር አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል ረድቶናል። አሁንም ቢሆን እኔና ኤሚሊ “ማንኛውንም አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀሙበት፣ ዳግመኛ ላይገኝ ይችላልና” በሚለው አባባል እንስማማለን።
ከቦታ ቦታ የምንጓጓዘው በተገኘው ሁሉ ማለትም በባቡር፣ በአውቶቡስ፣ በጭነት መኪና ወይም በብስክሌት ነበር። ይህ በጣም አድካሚ ቢሆንም “ማንኛውንም አጋጣሚ በሚገባ ለመጠቀም” የነበረንን ቁርጥ አቋም የሚፈታተኑ ሌሎች ሁኔታዎችም ነበሩ። ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ኤሚሊ በአካባቢው በነበረው ሕግ ምክንያት የተለያዩ ጎሳዎች ወደሚኖሩባቸው ክልሎች አብራኝ መሄድ አትችልም ነበር። በመሆኑም ከተጋባን ገና ሁለት ዓመት ብቻ ቢሆነንም ባለቤቴን ብዙውን ጊዜ አንድም የይሖዋ ምሥክር በማይኖርባቸው በባቡር ሐዲድ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች እየተውኩ ለመሄድ ተገድጄ ነበር። የኤሚሊ እምነት፣ ድፍረትና ቆራጥነት ይበልጥ እንድወዳትና እንዳደንቃት ያደረገኝ ከመሆኑም በላይ በእነዚህ አካባቢዎች የመንግሥቱ ምሥራች ፍሬ እንዲያፈራ አስችሏል።
ኤሚሊ በአካባቢው ካሉ ነዋሪዎች አንዱ ጋር ታርፍና እኔ እስክመለስ ድረስ በዚያ ለሚገኙት ሁሉ ምሥራቹን እየሰበከች ትቆያለች። አንዳንድ ጊዜ አንድ ወር ሙሉ ብቻዋን ታገለግል ነበር። በይሖዋ ኃያል ክንድ ላይ የነበራት ትምክህት ብርታትና ጥበቃ ያስገኘላት ሲሆን አገልግሎቷም ፍሬ አፍርቷል። በአንድ ወቅት ሪታ ሃንኮክ የተባለች ሴት ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥሩ ምላሽ ሰጠች፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ባለቤቷም እውነትን ተቀብሎ ታማኝ ወንድማችን በመሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በክርስቲያን ሽማግሌነት አገልግሏል። በዛሬው ጊዜ ኤሚሊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ዘሮች ከዘራችባቸው ከተሞች በአንዳንዶቹ ፈጣን እድገት የሚያደርጉ ጉባኤዎች አሉ።
የአፍሪካውያን እንግዳ ተቀባይነትና የፈጠራ ችሎታ
በእነዚያ ሁሉ ጊዜያት እኔ በማገለግልባቸው ክልሎች ያሉት ምሥክሮች ለይሖዋ ድርጅትና ለተጓዥ ወኪሎቹ የነበራቸው ከፍተኛ አድናቆት በጣም ይነካኝ ነበር። እነዚህ አፍቃሪ ክርስቲያን ወንድሞች ጥሩ እንክብካቤ ያደርጉልኝ ነበር። ሰኞ በመጣ ቁጥር ከአንዱ የመሰብሰቢያ ቦታ ወደ ሌላው የምጓዝ ሲሆን የሚዘጋጅልኝ ማረፊያ በሳስካቼዋን የነበረውን ቤታችንን የሚያስታውሰኝ አዲስ የተሠራ የሣር ጎጆ ነበር። የምተኛው አንሶላ በተነጠፈበት 30 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ባለው የሣር ፍራሽ ላይ ነበር።
በእነዚህ አካባቢዎች የጉባኤ ስብሰባዎች በአብዛኛው የሚካሄዱት ጫካ ውስጥ ነበር። በስብሰባው ላይ የሚገኙት ወንድሞች ለጥላ እንዲሆኑ ትላልቅ ዛፎችን አስቀርተው ቁጥቋጦውን ይመነጥራሉ። ከዚያም ለመቀመጫ የሚሆኑ የሣር እስሮች በመደዳ ይደረደራሉ። በመጨረሻም የተመነጠረው ቦታ ዙሪያውን በሣር ይታጠራል። ተፈጥሯዊ ውበት በተላበሱት በእነዚህ የመሰብሰቢያ ቦታዎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለጆሮ በሚጥም ዜማ ይሖዋን ሲያወድሱት ልዩ ስሜት ይሰማኝ ነበር።
የማይረሳ ተሞክሮ
በአንድ ወቅት ጌዴዎን ዜንዳ ከተባለ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሚተዳደሩ የሚስዮን ትምህርት ቤቶች ዋና ተቆጣጣሪ ከነበረ ሰው ጋር ተገናኘሁ። ጌዴዎን የዩኒቨርሲቲ ሥልጠናውን ጨምሮ መደበኛ ትምህርቱን የተከታተለው በቤተ ክርስቲያኗ አማካኝነት ነበር። ይሁን እንጂ አጥጋቢ መልስ ያላገኘላቸው በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች ነበሩት። ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎቹን እንድመልስለት ከእሱና ከበርካታ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር እንድገናኝ ጠየቀኝ። በዚህ ስብሰባ ላይ የትምህርት ቤቶቹን ተቆጣጣሪዎች፣ ርዕሳነ መምህራንንና አስተማሪዎችን ጨምሮ 50 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የመራው
ጌዴዎን ሲሆን ሥርዓት ባለው መንገድ ርዕስ በርዕስ ተወያየን። በእያንዳንዱ ርዕስ ላይ ለ15 ደቂቃ ያህል ከተናገርኩ በኋላ ጥያቄዎች ይጠይቁኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለብዙ ሰዓታት የዘለቀ ውይይት አደረግን።በውጤቱም ጌዴዎንና ቤተሰቡ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የሥራ ባልደረቦቹ ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል። በዚህ ምክንያት የአካባቢው ጳጳስ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከሚተዳደሩት የትምህርት ተቋማት በሙሉ አባረሯቸው። ቢሆንም ሁሉም በዚህ ሳይበገሩ ይሖዋን ማገልገላቸውን ጸንተው የቀጠሉ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ አቅኚዎች ሆነዋል።
አስደናቂው ፊልም ያስገኘው ውጤት
በ1954 የይሖዋ ምሥክሮች የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ በእንቅስቃሴ ላይ የተሰኘውን ተንቀሳቃሽ ፊልም አዘጋጅተው ነበር። በቀጣዩ ዓመት አንዲት ሴት ከባሏ ጋር የተለያዩ ጎሳዎች ወደሚኖሩባቸው ክልሎች እንዳትሄድ የሚከለክለው ሕግ ተነሳ። በዚህም ምክንያት ኤሚሊ ወደ እነዚህ ክልሎች አብራኝ መሄድ ጀመረች። በዚህ ጊዜ በአካባቢው ላሉት የጎሳ ማኅበረሰቦች ሁሉ ፊልሙን ማሳየት እንድንችል አንድ ተሽከርካሪ፣ ጄኔሬተርና የፊልም ማሳያ ፕሮጄክተር ተሰጥቶን ነበር። አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚያ ቀደም ፊልም የሚባል ነገር አይተው ስለማያውቁ የምናሳየው ፊልም የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ፊልሙ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ባለው ትልቅ ማተሚያ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዴት እንደሚዘጋጁ የሚያሳይ ነበር።
በተጨማሪም ፊልሙ ከዓለም ዙሪያ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች በ1953 በኒው ዮርክ፣ ያንኪ ስታዲየም ተሰብስበው በአንድነት አምልኳቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳይ ነበር። እነዚህ አፍሪካውያን ከዚያ ቀደም እንዲህ ያለ ሁሉንም ዘሮች ያቀፈ አንድነትና ፍቅር የሚታይበት ስብሰባ አይተው አያውቁም ነበር። ብዙ የዚምባብዌ ቤተሰቦች ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመሰብሰብ ተነሳስተዋል። ፊልሙ ያለውን ትምህርታዊ ጠቀሜታ የተገነዘቡ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ርዕሳነ መምህራን ለተማሪዎቻቸው እንድናሳይላቸው የሚያቀርቡት ጥያቄ ይጎርፍ ነበር።
አንድ ምሽት ላይ ወንድሞች ፊልሙን እንዳሳይ ከእንቅልፌ ቀሰቀሱኝ። አምስት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ፊልሙን ለማየት ብዙ ሰዓታት ተጉዘው እንደመጡ ስመለከት በጣም ተገረምኩ። በዚያ አካባቢ ፊልሙን ሳሳይ እንደነበረ ሰምተው የመጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ፊልሙን አይተው ወደየቤታቸው ሲሄዱ ደግሞ ሌሎች 300 ሰዎች መጡ። ስለዚህ ለእነዚህም ፊልሙን አሳየሁ። ፊልሙ አብቅቶ ሰዎቹ ሲሄዱ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሆኖ ነበር። በ17 ዓመታት ውስጥ በዛምቢያ ብቻ ይህንን ፊልም ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አይተውታል።
አዲስ ምድብ በአፍሪካ
በዚምባብዌ ከአምስት ዓመት ተኩል በላይ ካገለገልን በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተዛወርን። ይህም አፍሪካንስ የተባለውን ቋንቋ መማር ይጠይቅብን ነበር። ከጊዜ በኋላም ሴሱቱና ዙሉ የተባሉትን ቋንቋዎች ተማርን። የአምላክን ቃል በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማር መቻላችን በአገልግሎቱ ያለንን ውጤታማነት ከፍ ያደረገልን ከመሆኑም ሌላ አንድን ጠቃሚ ነገር ማከናወን የሚያስገኘውን እርካታ እንድናጣጥም አድርጎናል።
በ1960 መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያም ለቀጣዮቹ 27 ዓመታት በሌሶቶ፣ በናሚቢያ፣ በደቡብ አፍሪካና በስዋዚላንድ እንዲሁም በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ባሉት አሴንሽንና ሴንት ሄሌና ደሴቶች በስፋት ተጉዘናል። ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለማገልገል በጠቅላላው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘናል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸውም እንኳን ያሳዩት እምነትና ታማኝነት ፈጽሞ ተስፋ እንዳንቆርጥ ብርታት ሰጥቶናል።
ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ዳግማዊ ሶቡዛ በሞቱበት ጊዜ እምነታቸውን ለመካድ ፈቃደኞች ካልነበሩ የስዋዚላንድ ምሥክሮች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። እንዲህ ያሉ ትልቅ ባለ ሥልጣን ሲሞቱ በሚደረገው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተካፋይ ለመሆን እምቢ በማለታቸው ምክንያት ከሥራቸው ከመባረራቸውም በላይ የዜግነት መብታቸውን ሁሉ ተገፍፈው ነበር። ለዓመታት ብዙ ግፍና መከራ ቢደርስባቸውም እምነታቸውን
አልካዱም። እንደዚህ ካሉ የሚደነቁ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር መተዋወቅና መነጋገር መቻል ይሖዋን ምንጊዜም እንዳመሰግነው የሚገፋፋኝ ታላቅ መብት ነው።ከባሕር ወለል በላይ 3,000 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው በሌሶቶ፣ ሞክሆትሎን መንደር አቅኚ ሆኖ የሚያገለግል ፊልሞን ማፋሬካ የተባለ ወንድም ነበረ። መጓጓዣ ስላልነበረ እሱ፣ ሚስቱ፣ ሁለት ልጆቹና አራት የጥምቀት እጩዎች ከባሕር ወለል በላይ 1,000 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኝ ቦታ ወዳደረግነው ትልቅ ስብሰባ ለመድረስ 100 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል። አብዛኛው መንገዳቸው ቁልቁለት ቢሆንም አቀበት ቁልቁለቱን መውጣት መውረድ እንዲሁም በርካታ ጅረቶችንና ወንዞችን ማቋረጥ ነበረባቸው።
ከስብሰባው በኋላ ወደቤታቸው ሲመለሱ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተሰኘውን መጽሐፍ መቶ ቅጂ ተሸክመው ሄዱ። መጽሐፎቹን የያዙት በሞክሆትሎን ላሉት ሰዎች ለመስጠት ብለው ነበር። ነገር ግን በመንገዳቸው ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ስላጋጠሟቸው ወደ መንደራቸው ሳይደርሱ መጽሐፎቹ አለቁባቸው። እኔና ኤሚሊ እንደ ፊልሞንና ሚስቱ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ያላቸውን ቅንዓትና ለአምላክ የማደር ባሕርይ በዓይናችን የማየት አጋጣሚ ማግኘታችንን እንደ ትልቅ መብት እንቆጥረዋለን።
አንዳንድ ጊዜ እንደ ኮብራ ያሉ መርዛማ እባቦች፣ ደራሽ ውኃና ሌሎችም አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ነበር። እንደነዚህ ያሉ አጋጣሚዎች በጊዜው አስፈሪ ቢሆኑም በይሖዋ አገልግሎት ካገኘነው በረከትና ደስታ ጋር ሲወዳደሩ ከቁም ነገር የሚገቡ አይደሉም። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ተምረናል።
ኤሚሊ ከባድ የጤና ችግር ባጋጠማት ጊዜ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድንወጣው ይሖዋ ጥበብ ሰጥቶናል። የአመጋገብ ለውጥ ማድረጋችንና በንጽሕና ረገድ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳችን ቶሎ እንድታገግም ረድቷታል። አንድን አነስተኛ የጭነት መኪና ከላይ ሽፋን በማልበስ ከቦታ ወደ ቦታ በምንጓዝበት ጊዜ ለኤሚሊ ተስማሚ መጠለያ ያዘጋጀን ሲሆን ከጊዜ በኋላ ጤንነቷ እየተሻሻለ ሄደ።
ወደ ካናዳ መመለስ
ማራኪ በሆነችው አፍሪካ በሚስዮናዊነት ለ35 ዓመታት ካገለገልን በኋላ በ1988 ካናዳ ተመደብን። ከዚያም በ1991 እንደገና በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ጀመርኩ። ከስምንት ዓመታት በኋላ በአንጎል ውስጥ የደም መርጋት በሽታ አጋጠመኝ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ እንቅስቃሴዬ በእጅጉ ቢገደብም አሁንም በካናዳ፣ ኦንታሪዮ በምትገኘው ለንደን ከተማ ውስጥ ካሉት ጉባኤዎች በአንዱ ሽማግሌ ሆኜ በማገልገሌ ደስተኛ ነኝ።
ከ56 ዓመታት በፊት በደቡባዊ ሳስካቼዋን በፈረስ እየተጓዝኩ በአቅኚነት ያገለገልኩበትን ጊዜ ዛሬ መለስ ብዬ ሳስታውስ እርካታ ይሰማኛል። አባታችን መንፈሳዊ ሰዎች እንድንሆንና ያለ አንዳች ፍርሃት ለእውነትና ለጽድቅ እንድንቆም ሳያሰልስ ስላስተማረን በጣም አመስጋኝ ነኝ! የሕይወትን ዓላማ እንዳውቅ ያስቻለኝን የአምላክን ቃል አስተምሮኛል። ይህ ውርሻ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ጠቅሞኛል። ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኩትን ሕይወት ይህ አሮጌ ዓለም ሊሰጠው በሚችለው በምንም ነገር ፈጽሞ አልለውጠውም።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1949 ዘጠኝ ልጆችን ያቀፈው ቤተሰባችን፤ እናቴ የመጨረሻውን ልጅ ይዛ፣ እኔ ደግሞ ከእሷ ኋላ ቆሜ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአገልግሎቴ እንድጠቀምበት የሠራሁት “ካቡስ” ተብሎ የሚጠራው ጋሪ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኩቤክ ሲሰብኩ የተያዙ ሴቶች
[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1954 በዚምባብዌ እነዚህን የበላይ ተመልካቾች በማስተማር ተካፍያለሁ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤሚሊ ከህመሟ እስክታገግም የምታርፍበትን ይህን ተንቀሳቃሽ መጠለያ ሠራን
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ ከኤሚሊ ጋር የተነሳነው ፎቶ