መኪናህን ስትጠግን አደጋ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ
መኪናህን ስትጠግን አደጋ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ
ኬቨን የመኪናውን ዘይት እንዴት እንደሚቀይር በልምድ ያውቃል። የመኪናውን ዘይት ማፍሰሻ ብሎን እንዴት እንደሚፈታ ያውቃል። አንድ ጊዜ ግን ብሎኑን ለመፍታት መፍቻውን በኃይል ሲገፋ መፍቻው ከብሎኑ አናት ላይ አፈትልኮ ወጣ። የኬቨን እጅ ሹል ብረት ላይ አረፈና መዳፉ መሰፋት እስኪያስፈልገው ድረስ ተሰነጠቀ።
ጪ ለመቀነስ ብለውም ሆነ በሌላ ምክንያት እንደ ኬቨን መኪናቸውን ራሳቸው የሚጠግኑ ሰዎች ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የጥገናና የእድሳት ዘዴዎችን ማወቅ ሌሎች በርካታ ጥቅሞችም አሉት። ካቲ የምትባል ሴት “አንድ ጊዜ ረዥም ጉዞ ላይ እንዳለሁ መኪናዬ ተበላሸች” ትላለች። “መኪናዬን መጠገን ለምጄ ስለነበር ብልሽቱን አስተካክዬ መንገዴን ቀጠልኩ።”
ወምናልባት አንተም መኪናህን ማደስና መጠገን ብትችል ትወድ ይሆናል። ሆኖም መኪናህን በምትጠግንበት ጊዜ አደጋ እንዳይደርስብህ ጥንቃቄ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?
አርቀህ አስብ!
ከሁሉ በላይ ቅድሚያ መስጠት የሚኖርብህ ለደህንነትህ ነው። * በኬቨን ላይ ከደረሰው አደጋ መረዳት እንደምንችለው በጠባብ ቦታ በምትሠራበት ወይም አንድ ነገር ለማከናወን ኃይል በምትጠቀምበት ጊዜ በቀላሉ በራስህ ላይ ጉዳት ልታደርስ ትችላለህ። ጉዳት እንዳይደርስብህ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ትችላለህ? ብሎን በመፍቻ በምታጠብቅበት ጊዜ መፍቻው በደንብ መግባቱንና ብሎኑን መያዙን አረጋግጥ። ‘መፍቻው ቢያፈተልክ እጄ የሚያርፈው የት ነው?’ ብለህ አስብ። ጓንት ማድረግ ወይም እጅህ ላይ ጨርቅ መጠቅለል በመጠኑም ቢሆን ሊከላከልልህ ይችላል። ኃይልህን መቆጣጠር እንድትችል መፍቻውን ከመግፋት ይልቅ ወደ ራስህ ሳበው። በተመሳሳይም የጠበቀ ብሎን በምትፈታበት ጊዜ በአንድ ጊዜ ከአንድ አራተኛ ዙር በላይ ለማዞር መሞከር የለብህም። እነዚህ የጥንቃቄ ሕጎች ሁልጊዜም መከበር የሚገባቸው ናቸው። በመቻኮል ወይም በመጣደፍ ችላ ልትላቸው አይገባም!
አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚፈጠረው አንድ መሣሪያ ወይም መፍቻ ከተሰራበት ዓላማ ውጭ እንዲያገለግል ሲደረግ ነው። ለምሳሌ ቶም የመኪናውን ካንዴላ ለመቀየር በጣም ተቸግሮ ነበር።
ለምን? መፍቻው አጭር ስለነበረ ከመጀመሪያው ካንዴላ እያፈተለከ ይወጣ ነበር። በመጨረሻ ቶም መፍቻው ላይ ማስረዘሚያ አደረገበት። ከዚያም የመጀመሪያውን አንድ ካንዴላ ለመለወጥ ከወሰደበት ጊዜ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የቀሩትን አምስት ካንዴላዎች በራሱ ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርስ መለወጥ ቻለ። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ትክክለኛውን መሣሪያ ወይም መፍቻ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው።መኪናህ ሥር ተኝተህ ስትሠራ ወይም ከመኪናህ ሥር ሆነህ ወደ ላይ አንጋጠህ ስትመለከት ባዕድ ነገር ዓይንህ ውስጥ ሊገባ ይችላል። እንዲህ ያለውን አደጋ እንዴት ማስወገድ ይቻላል? ከአሥር ዓመት በላይ በመካኒክነት የሠራው ሾን “የዓይን መከለያ መነጽር አድርጉ” ይላል። በማከልም “በምሠራበት ጋራዥ እንዲህ ያለውን የዓይን መከለያ መነጽር ማድረግ ግዴታ ነው” ብሏል። በተጨማሪም እንደ ባትሪ አሲድ ያለ አደገኛ ፈሳሽ ባለበት አካባቢ በምትሠራበት ጊዜ የዓይን መከለያ መነጽር ማድረግ ይኖርብሃል።
ከመኪናህ ሥር ገብተህ በምትሠራበት ጊዜ ሁሉ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ ክሪክ ወይም ማንሻ ወይም ተቆፍሮ በሲሚንቶ በተጠናከረ ጉድጓድ ተጠቀም። በክሪክ ላይ ብቻ የቆመ መኪና ሥር ፈጽሞ አትግባ። የአንዳንድ መኪኖች የተጠቃሚ መመሪያ መኪናውን በጥሩ ሁኔታ ደግፎ ለማቆም ክሪኩ የት ቦታ መደረግ እንደሚኖርበት ያመለክታል። ይሁን እንጂ አንድን አልፈታም ብሎ ያስቸገረ ብሎን በኃይል ለማስለቀቅ የሚደረግ ትግል
መኪናውን ከክሪኩ ወይም ደግፎ ከያዘው ሌላ ነገር ላይ እንዲንሸራተት ሊያደርገው ስለሚችል ተጠንቀቅ።ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግ
አንዳንዶቹ የመኪናህ ክፍሎች በጣም ሊግሉ ስለሚችሉ ከነካሃቸው ያቃጥሉሃል። ለምሳሌ በራዲያተሩ ውስጥ ያለው ውሃ ሞተሩ ከጠፋ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንኳን ትኩስ ሆኖ ሊቆይ ይችላል። ስለዚህ ራዲያተሩን በባዶ እጅህ ለመንካት እስከምትችል ድረስ ሳይቀዘቅዝ ክዳኑን ለመክፈት አትሞክር። በአንዳንድ መኪኖች ላይ የራዲያተሩ ማራገቢያ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ሲሆን ሞተሩ ከጠፋ በኋላ እንኳን ማንም ሳይነካው በራሱ ሊነሳ ይችላል። ጉዳት እንዳይደርስብህ ሥራ ከመጀመርህ በፊት ማሳ የሚሆነውን ሽቦ ከባትሪው ላይ አላቅ።
መኪናህን በምትሠራበት ጊዜ በተለይ ሞተሩ በመሥራት ላይ ከሆነ ማንኛውንም ቀለበትና ጌጥ ከእጅህ አውልቅ። ቀለበቶችና ጌጦች ከመኪናው ክፍሎች ጋር ሊያያዙ ወይም ሊጠላለፉ ከመቻላቸውም በላይ ከኤሌክትሪክ ሽቦዎች ጋር ኮንታክት ሊፈጥሩ ይችላሉ! ያልተሰበሰበ እጅጌ፣ ከረባት፣ ሻሽ ወይም ረዥም ፀጉር ከተንቀሳቃሽ የመኪና ክፍሎች ጋር ሊጠላለፍ ይችላል።
ሥራዬን ጨርሻለሁ ብለህ በምታስብበት ጊዜ እንኳን ልትረሳው የማይገባ አንድ መመሪያ አለ። አንድ በጣም ሥራ የሚበዛበት ጋራዥ የጥገና አማካሪ “ሁልጊዜ የሠራኸው ሥራ በትክክል መሠራቱን ለሁለተኛ ጊዜ አረጋግጥ” ብሏል። በመቀጠል “አንድ ጊዜ አንድ መካኒክ ፍሬን ከሠራ በኋላ ይህን ሳያደርግ ቀረ። ፍሬኖቹ የማይዙ በመሆናቸው መኪናው እስከ ጠረጴዛዬ ድረስ ዘው ብሎ ገባ!” ይላል።
ድንገተኛ ሁኔታ ሲፈጠር
አንድ ቀን ቶም መኪናው ከመጠን በላይ እንደጋለች ተመለከተ። አንድ ቱቦ ፈንድቶ ኖሮ በራዲያተሩ ውስጥ ያለው ውሃ ፈስሶ አልቋል። ቶም መኪናው ውስጥ ያስቀመጠውን የኤሌክትሪክ ፕላስተር አውጥቶ በተቀደደው ቱቦ ላይ ከጠመጠመ በኋላ ውሃና የበረዶ መከላከያ ኬሚካል ራዲያተሩ ውስጥ በመጨመር ጊዜያዊ ጥገና ሊያደርግ ችሏል። ከዚያም ወደ መለዋወጫ ሱቅ በመኪናው ሄዶ አዲስ ቱቦ ገዛ። የቶም ተሞክሮ ለጥገና የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን መኪና ውስጥ መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።
መኪና በምትነዳበት ጊዜ ላልተለመደ ዓይነት ድምፅ ወይም ሽታ ንቁ ሁን። ኢቮን ከመኪናዋ ሞተር ያልተለመደ ዓይነት ሽታ ሲወጣ ተሰማት። ባሏ ኮፈኑን ከፍቶ ሲመለከት ከራዲያተሩ ላይኛ ክፍል በአንዲት ትንሽ ቀዳዳ የበረዶ መከላከያ ፈሳሽ ፊን ብሎ ሲወጣ ተመለከተ። መኪናው ከመጋሉ በፊት ችግሩ ስለታወቀ ኢቮንና ባሏ መኪናቸውን እየነዱ ጋራዥ ለማድረስ ችለዋል።
መኪናህ አውራ ጎዳና ላይ ተበላሽቶ ቢቆም ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ መኪናህን በተቻለ መጠን ከመንገድ ለማራቅ ሞክር። ተሳፋሪዎች፣ በተለይም ሕፃናት ቀበቷቸውን እንዳሠሩ መኪናው ውስጥ መቆየት ይገባቸዋል። ከመኪናህ ወጥተህ መቆም ቢኖርብህ በተቻለ መጠን ከተላላፊ ተሽከርካሪዎች ራቅ። የማስጠንቀቂያ መብራቶችን አብራ። የመኪና ችግር እንዳጋጠመህ ለማመልከት የመኪናህን ኮፈን ክፍት አድርገህ ተወው። በተጨማሪም ሌሎች የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ልትጠቀም ትችላለህ።
የመኪናህ ባትሪ ከሞተብህ በሌላ መኪና ባትሪ ረዳትነት ለማስነሳት ትመርጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከባትሪ ውስጥ በቀላሉ በእሳት ሊያያዝ የሚችል ጋዝ እንደሚወጣ አትዘንጋ። የኤሌክትሪክ ብልጭታ ሊያቀጣጥለው ስለሚችል ባትሪው ፈንድቶ መርዛም አሲድ ሊረጭብህ ይችላል። ስለዚህ አንተም ሆንክ የሚረዳህ ሰው ባትሪዎቹን እንዴት እንደምታገናኙ እርግጠኛ ካልሆናችሁ የሚረዳችሁ ሰው እስኪመጣ ጠብቁ።
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መኪና መጠገን ከባድ ሥራ ነው። መኪናህን የምትጠግነው ድንገተኛ ችግር አጋጥሞህም ሆነ የተለመደ እድሳት ለማድረግ ምንጊዜም ራስህን ከጉዳት መጠበቅ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን አስታውስ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሠራው ሥራ ከሆነ የመኪናውን የጥገና መመሪያ አንብብ ወይም በቂ ልምድ ያለው ሰው እንዲረዳህ ጠይቅ። የመኪናህ አሠራር የተራቀቀና የተወሳሰበ ከሆነ አስፈላጊው መሣሪያና ልምድ ያለው መካኒክ ጋር ወስደህ ብታስጠግነው የተሻለ ይሆናል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚፈጠረው አንድ መሣሪያ ወይም መፍቻ ከተሠራበት ዓላማ ውጭ እንዲያገለግል ሲደረግ ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
በመኪናህ ውስጥ ልትይዛቸው የሚገቡህ ነገሮች
▪ ትርፍ ጎማና ክሪክ
▪ ባትሪ ማገናኛ ሽቦ
▪ የማስጠንቀቂያ መብራት
▪ መፍቻዎችና የዓይን መከላከያ መነጽር
▪ የእጅ ባትሪ
▪ መጠባበቂያ ዘይት፣ ውሃ፣ የበረዶ መከላከያ ወይም የፍሬን ዘይት
▪ የኤሌክትሪክ ፕላስተር
▪ ትርፍ ፊውዝ
▪ መጎተቻ ካቦ (ማሳሰቢያ:- በአንዳንድ አገሮች መኪናህን መጎተት የሚችለው ፈቃድ ያለው ጎታች ብቻ ነው)
▪ መፍቻዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ የሚያስችል ሣጥን
ተጨማሪ የጥገና መሣሪያዎችን መያዝ ትፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ የመንገድ ላይ ድንገተኛ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ አንዳንድ የመኪና ክበቦች ባለቤቱ ሊጠግን ሙከራ ያደረገባቸውን መኪናዎች ለመጠገን ፈቃደኛ አይሆኑም። የመኪና ክበብ አባል ከሆንክ እንዴት ያሉ ጥገናዎች እንደሚፈቀዱ አጣራ።