በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈረስ በልጓም እንደሚገራ አንደበትን መግራት

ፈረስ በልጓም እንደሚገራ አንደበትን መግራት

ፈረስ በልጓም እንደሚገራ አንደበትን መግራት

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን “ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 21:31) ፈረሰኛ ወታደሮች ከረጅም ጊዜ አንስቶ በጦርነቶች ላይ ድል ለመቀዳጀት ጠቃሚ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ከጥንት ጀምሮ ወታደሮች የፈረሶችን ጉልበት ለመቆጣጠር ልጓም ተጠቅመዋል።

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ልጓም “እንስሳው አፍ ውስጥ የሚገባው ብረት እንዳይወጣ የሚይዝና ሰውየው ፈረሱን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ከጠፍር የሚሠራ ትጥቅ ነው” በማለት ይገልጻል። የጥንት ልጓም በዚህ ዘመን ካለው እምብዛም የማይለይ ሲሆን ፈረስን ለመግራት ብሎም ለመጋለብ በጣም አስፈላጊ ነው።

የሰሎሞን አባት ንጉሥ ዳዊት “በልባብና በልጓም ካልተገሩ በቀር፣ ወደ አንተ እንደማይቀርቡት፣ ማስተዋል እንደሌላቸው፣ እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ” ብሎ በተናገረ ጊዜ የልጓምን ጠቃሚነት በተዘዋዋሪ ጠቅሷል። (መዝሙር 32:9) ፈረስ ከተገራ በኋላ የማይከዳ ወዳጅ ይሆናል። ታላቁ እስክንድር ቢዩሳፈለስ ለተባለው ፈረሱ ከነበረው ፍቅር የተነሳ አንዲትን የሕንድ ከተማ ለመታሰቢያነት በፈረሱ ስም ሰይሟታል።

ሰዎች ለብዙ ዘመናት ፈረስን በመግራት ረገድ ቢሳካላቸውም ፍጹም ያልሆነውን ሥጋቸውን መግታት ግን አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ እንዲህ ብሏል:- “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2) በእርግጥም ሰውን የሚያቆስል ወይም የሚጎዳ ሳይታሰብ የተነገረ ቃል ከአፌ ወጥቶ አያውቅም ሊል የሚችል ማን ይኖራል?

ታዲያ ‘ማንም ሰው ሊገራው የማይችለውንና’ አስቸጋሪ የሆነውን ምላሳችንን ለመግራት መጣጣር የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 3:8) ሰዎች ፈረስን ለመግራት ጊዜና ጉልበት የሚያጠፉት የተገራ እንስሳ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው። በተመሳሳይም አንደበታችንን በገራነው ወይም በተቆጣጠርነው መጠን የዚያኑ ያህል ጠቃሚ ይሆናል።

በአሳቢነት የተነገሩ ቃላት ወዳጆቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንንና ዘመዶቻችንን ሊያጽናኑና ሊያበረታቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 12:18) እንዲህ ያሉ ቃላት አብረውን ያሉ ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ ይረዷቸዋል። ያልተገራ ምላስ ግን ችግር ያስከትላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምላሱን የሚቈጣጠር፣ ራሱን ከመቅሠፍት ይጠብቃል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 21:23) ምላሳችንን በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ በሆንን መጠን ራሳችንንም ሆነ የሚያዳምጡንን እንጠቅማለን። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የሚገርመው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው” በማለት ክርስቲያኖች አነጋገራቸውን ከአምልኮታቸው ነጥለው ማየት እንደማይኖርባቸው ይናገራል።—ያዕቆብ 1:26

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቁ እስክንድር

[ምንጭ]

Alinari/Art Resource, NY