በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጨው እያስከተለ ያለው ከባድ ችግር

ጨው እያስከተለ ያለው ከባድ ችግር

ጨው እያስከተለ ያለው ከባድ ችግር

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጨው ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። አንድ በመቶ የሚሆነው የሰውነታችን ክፍል ጨው ከመሆኑም በላይ በምግባችን፣ በመድኃኒቶች ውስጥና በከብቶች መኖ ውስጥ ይገኛል። በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1,900,000,000 ኩንታል ገደማ ጨው ጥቅም ላይ ይውላል። * ሆኖም ይህ ጠቃሚ የሆነና ተትረፍርፎ የሚገኝ ንጥረ ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታማ በሆኑ አንዳንድ የእርሻ ቦታዎች ላይ ከባድ ችግር እያስከተለ ነው።

በዓለም ዙሪያ ከሚመረተው እህል መካከል 40 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው ወደ 15 በመቶ በሚጠጋ የመስኖ እርሻ ላይ ነው። እርግጥ ነው፣ መስኖ ጠፍ የነበረ መሬት እንዲለማ ያደርጋል። በአንጻሩ ግን መሬቱን ቀስ በቀስ የሚያበላሽ የጨው ዝቃጭ እንዲጠራቀም ምክንያት ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት በመስኖ ከሚለሙ እርሻዎች ግማሽ የሚያህሉት ጨው እየተጠራቀመባቸው በመሆኑ ምክንያት ምርታማነታቸው በጣም ቀንሷል። የሚገርመው ነገር በየዓመቱ የስዊዘርላንድን የቆዳ ስፋት ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ መሬት ጨዋማ ይሆናል እንዲሁም ውኃ አቁቶ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል!

ታዋቂ የአፈር ምርምር ሳይንቲስት የሆኑት ዳንኤል ሂሌል፣ አውት ኦቭ ዚ ኧርዝ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል:- “ባለፉት ዘመናት የነበሩት ሥልጣኔዎች እንዲወድቁ ትልቁን ሚና የተጫወቱት ሰው ሠራሽ ችግሮች በሙሉ በዘመናችንም እየተከሰቱ ነው። . . . እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ እየተከሰቱበት ያለው ሁኔታ ከየትኛውም ጊዜ የከፋ ነው።” የጨው መጠን መጨመር የሚያስከትለው የምርት መቀነስ ዩናይትድ ስቴትስ በዓመት አምስት ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ እያደረጋት እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና አውስትራሊያ ከሁሉም ቦታዎች በበለጠ በዚህ ችግር የተጠቃች አህጉር ነች።

ነጩ ሞት

በምዕራብ አውስትራሊያ በየሰዓቱ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክል ስፋት ያለው ትልቅ የስንዴ ማሳ በጨው ክምችት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። የኮመንዌልዝ የሳይንስና የኢንዱስትሪ ምርምር ድርጅት (ሲ ኤስ አይ አር ኦ) አባል የሆኑት ዶክተር ቶም ሀተን “ከገጠሙን አካባቢያዊ ችግሮች ሁሉ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ይህ ጉዳይ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም” ብለዋል።

መሪ-ዳርሊንግ ሸለቆ ተብሎ የሚጠራው የምሥራቅ አውስትራሊያ ዋነኛ የእርሻ ክልል ለጨው ክምችት በእጅጉ የተጋለጠ ቦታ ነው። ሸለቆው ፈረንሳይና ስፔይን ተዳምረው የሚኖራቸውን ስፋት የሚያክል ቦታ የሚሸፍን ከመሆኑም በተጨማሪ አውስትራሊያ በመስኖ ከምታለማው መሬት ውስጥ ሦስት አራተኛው የሚገኘው በዚህ ሥፍራ ነው። ይቺ አህጉር ግማሽ የሚያህለውን የእርሻ ገቢዋን የምታገኘው ከዚህ ሸለቆ ነው። የዚህ ዋነኛ የእርሻ መሬት የደም ስሮች የሆኑት መሪና ዳርሊንግ የሚባሉት ወንዞች በርካታ ቦታዎችን ለማልማት ያገለግላሉ፤ እንዲሁም ሦስት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች የሚጠጡትን ውኃ የሚያገኙት ከእነዚህ ወንዞች ነው።

የሚያሳዝነው ግን ከዚህ ዋነኛ የእርሻ ቦታ 2,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚያህለው መሬት በጣም ጨዋማ ሆኗል፤ ከዚህም በተጨማሪ ሳይንቲስቶች ወደ 10,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ጨዋማ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። በመሪ እና በዳርሊንግ ወንዞች እንዲሁም የእነዚህ ገባር በሆኑት ወንዞች ውስጥ ያለው የጨው መጠን በመጨመሩ በአንዳንድ ቦታዎች ውኃውን ለመጠጥነት መጠቀም የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። በወንዞቹ ዳርቻ ያለው ለም የነበረ ቦታ የጨው ቅርፊት እያበጀና ጥቅም አልባ ረግረግ መሬት እየሆነ ነው። ገበሬዎች ይህንን ክስተት ነጩ ሞት ይሉታል።

ነገር ግን አደጋ የተደቀነበት የእርሻው መሬት ብቻ አይደለም። የሲ ኤስ አይ አር ኦ አባል የሆኑ ሳይንቲስቶች እንደገለጹት በተከሰተው የጨው ክምችት ሳቢያ በአውስትራሊያ የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። እንዲሁም ሁኔታው አሁን ባለው መልኩ ከቀጠለ በመሪ-ዳርሊንግ ሸለቆ ከሚገኙት የወፍ ዝርያዎች መካከል ግማሽ የሚያክሉት በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ሊጠፉ ይችላሉ። ይህንን አካባቢያዊ ቀውስ ያስከተለውን አርቆ ለማሰብ ያለመቻል ችግር እስኪ እንመልከት።

ጨዉ ከየት መጣ?

ሳይንቲስቶች በአውስትራሊያ ያለው አብዛኛው ጨው በብዙ ሺህ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከውቅያኖስ ተንኖ በጉም ውስጥ ተከማችቶ ከቆየ በኋላ በዝናብ አማካኝነት ወደ የብስ እንደተሸጋገረ ይገምታሉ። ሌላው ግምት ደግሞ ጨዉ በአንድ ወቅት የአህጉሯን የተወሰኑ ክፍሎች ሸፍነው የነበሩ የአንዳንድ ባሕሮች ዝቃጭ ነው ብለው ያምናሉ። ዝናብ ጨዉን እያጠበ ወደ ስረኛው የአፈር ንጣፍ ካስገባው በኋላ ቀስ በቀስ በዚህ ጨዋማ የአፈር ንጣፍ ስር ውኃ መጠራቀም ጀመረ።

ከጊዜ በኋላ ወደ ምድር ውስጥ ከ30 እና ከ40 ሜትር በላይ ስሮቻቸውን መስደድ የሚችሉ ባሕር ዛፍና ሌሎች ተክሎች አህጉሯን ሸፈኗት። እነዚህ ተክሎች መሬት ውስጥ የገባውን አብዛኛውን የዝናብ ውኃ መጥጠው በቅጠሎቻቸው አማካኝነት ወደ ላይኛው የአፈር ንጣፍ ይመልሱታል። ይህም የከርሰ ምድር ውኃ በጣም ጥልቀት እንዲኖረው አደረገ። ነገር ግን አውስትራሊያ እንድትበለጽግና እንድታድግ ያስቻለው የአውሮፓውያን የእርሻ ዘዴ ደን መመንጠርን የሚጨምር ነበር። እነዚህ ረጃጅም ስሮች ያሏቸው ዛፎች ከልክ በላይ በመጨፍጨፋቸውና የመስኖ ልማት በጣም በመስፋፋቱ የከርሰ ምድር ውኃ ወደ ላይ ከፍ ማለት ጀመረ። ይህም ለረጅም ጊዜያት በምድር ውስጥ በጣም ጠልቆ ይገኝ የነበረው ጨው እየሟሟ ለም ወደሆነው አፈር እንዲወጣ አደረገ።

ለጨው ክምችት ምክንያት የሆኑት ችግሮች

በመሪ-ዳርሊንግ ሸለቆ በማሳዎች ላይ ውኃ ለተወሰነ ጊዜ እንዲተኛ በማድረግ የሚካሄደው የመስኖ ልማት አካባቢው ምርታማ እንዲሆን ቢያስችልም የከርሰ ምድር ውኃ ወደ ላይኛው የመሬት ክፍል በፍጥነት ከፍ እያለ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል። ጨዋማው የከርሰ ምድር ውኃ ወንዞች ውስጥ በመግባት ንጹሑን ውኃ በከለው። ይህም የወንዙን ውኃ ጨዋማ ስላደረገው ሌላ ችግር ተፈጠረ። ይህ ጨዋማ የወንዝ ውኃ በመስኖ አማካኝነት ወደ እርሻ መሬቶች ተመልሶ ስለሚገባ ችግሩ እንዲህ ባለ የማያቋርጥ ዑደት እየተባባሰ ሊሄድ ችሏል።

ይሁን እንጂ የከፋ ጉዳት እያስከተለ ያለው፣ የመስኖ መስመር ባልተዘረጋበት ደረቅ የመሬት ክፍል ላይ እየተፈጠረ ያለው የጨው ክምችት ነው። ሸለቆው ውስጥ የነበሩት ረጃጅም ስሮች ያሏቸው ዛፎች በሙሉ ተመንጥረው፣ ጥቂት ሜትሮች ብቻ ስራቸውን በሚሰድዱ የግጦሽ ተክሎችና በዓመት በሚደርሱ ሰብሎች ተተክተዋል። ቀደም ሲል ዛፎቹ ይመጥጡት የነበረው የዝናብ ውኃ አሁን የተክሎቹ ስሮች ሊደርሱ ወደማይችሉበት ርቀት ሰርጎ ይገባል።

ሳይንቲስቶች እንደገመቱት በዚህ ምክንያት ረጃጅም ስሮች ያሏቸው ዛፎች በነበሩበት ጊዜ ወደ ከርሰ ምድር ከሚገባው ውኃ ከ10 እስከ 100 እጥፍ የሚበልጥ መጠን ያለው ውኃ ይሰርጋል። ስለዚህ ባለፉት መቶ ዓመታት በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ወደ ምድር ውስጥ ሰርጎ የገባ ሲሆን ይህም በመሪ-ዳርሊንግ ሸለቆ ያለው የከርሰ ምድር ውኃ ከ60 ሜትር በላይ ወደ ላይ ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል። ይህም ጨዋማ የሆነው ውኃ ከላይኛው የአፈር ንጣፍ ጥቂት ሜትሮች ብቻ ርቆ እንዲገኝ በማድረጉ ገበሬዎች እህል ለማምረት ተቸግረዋል።

ለም የነበሩ የእርሻ ቦታዎች አሁን አጥጋቢ ምርት አይሰጡም። የጨው ቅርፊት መታየት ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በቅርብ ያለው ጨዋማ የሆነው የከርሰ ምድር ውኃ በትነት መልክ ወደ ላይ ይወጣ ነበር። ቀደም ሲል በእነዚህ ቦታዎች ይበቅሉ የነበሩት ሰብሎች ችግሩን መቋቋም ችለው ነበር፤ ሆኖም ወደ ላይኛው የመሬቱ ክፍል የሚወጣው የጨው መጠን እየጨመረና እየተጠራቀመ ሲመጣ አፈሩ ለምነቱን አጣ።

የመስኖ መስመር ባልተዘረጋበት መሬት ላይ የሚከሰተው የጨው ክምችት የሚጎዳው በግብርና ላይ የተሰማራውን ኅብረተሰብ ብቻ አይደለም። የአንዳንድ ግዛቶች አውራ ጎዳናዎችን እያበላሸና የአገልግሎት ዘመናቸውን በ75 በመቶ እየቀነሰው ነው። በተጨማሪም በመሪ-ዳርሊንግ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ የገጠር ከተሞች ውስጥ ያሉ ሕንጻዎችን፣ ቧምቧዎችንና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን እያበላሸ ነው።

ችግሩን ማስወገድ ይቻል ይሆን?

ለሚቀጥሉት ከ50 እስከ 100 ለሚጠጉ ዓመታት አብዛኛው ጨዋማ የከርሰ ምድር ውኃ ወደ ላይ መውጣቱን የሚቀጥል ይመስላል። አንድ ዘገባ እንደሚያሳየው አሁን የሚወለድ ሕፃን 30 ዓመት ሲሞላው በአውስትራሊያ ያለችውን የቪክቶሪያን ግዛት ወይም ታላቋ ብሪታንያን የሚያክል መሬት ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ይህን ውድመት ለማስቀረት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

መንግሥት ያወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ጤናማ የሆነውን የተፈጥሮ ገጽታና ምርታማውን ምድር እንዳለ ለማቆየት [በመሪ-ዳርሊንግ] ሸለቆ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ መቀየር ይኖርብናል። . . . ይህ በጣም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። . . . ነገር ግን አሁን ያለው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ባይለወጥ ከሚገጥሙን ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ኪሳራዎች አንጻር ስናየው ወጪው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”

በሸለቆው ውስጥ ዛፎችን ለመትከል ብርቱ ጥረት ቢደረግ ችግሩ ደረጃ በደረጃ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ዘዴው የሚያዋጣ ሆኖ አልተገኘም። አንድ ሳይንሳዊ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “አካባቢውን ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ሁኔታው መመለስ አንችልም። [ዛፎችን መትከል] ምናልባት መሻሻል ቢያስገኝ እንኳን ለውጡ በጣም አዝጋሚ ነው።”

እስከዚያው ድረስ ግን ገበሬዎች ስራቸውን በጣም አጥልቀው መስደድ የሚችሉ ወይም ጨውን የመቋቋም ኃይል ያላቸውን ተክሎች እንዲተክሉ እየተበረታቱ ነው። አንዳንድ ባለ ሀብቶች ደግሞ እርሻቸውን ያበላሸባቸውን ጨው ቆፍረው በማውጣት በጨው ሽያጭ በመተዳደር ላይ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የጨዋማ ውኃ ኩሬ በመሥራት ዓሣዎችን እያረቡና የባሕር ውስጥ እጽዋትን እያሳደጉ ለመሸጥ አቅደዋል።

የችግሩ ተጠቂ አውስትራሊያ ብቻ አይደለችም። በቅርቡ ትልቅ የለውጥ እርምጃዎች ካልተወሰዱ በስተቀር ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ የጥንቷን ግሪክ አስመልክቶ የተናገረው የሚከተለው አባባል በእኛም ዘመን በድጋሚ እንዳይፈጸም ያስፈራል:- “ቀደም ሲል ምርታማ የነበረ ምድር አሁን ለምነቱን አጥቶ አግጥጦ ሲታይ ልክ የበሽተኛ ሰው አጽም ይመስላል።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በጣም የተለመደው የጨው ዓይነት ሶድየም ክሎራይድ ነው። ጥቅም ላይ የዋሉት ሌሎች የጨው ዓይነቶች ደግሞ ፖታሲየም ክሎራይድና አሞኒየም ናይትሬት ናቸው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

መሪ- ዳርሊንግ ሸለቆ

[ምንጭ]

ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውኃ በሸፈነው ሜዳ መሃል በሚገኝ የዛፍ ጉቶ ላይ የተጋገረ የጨው ዝቃጭ

በአንድ ወቅት ለም የነበሩ ቦታዎች በላይኛው የአፈር ንጣፋቸው ላይ ጨው በመጠራቀሙ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል

[ምንጭ]

© CSIRO Land and Water

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በለምለም ቦታዎች መሃል ደረቅ መሬት መኖሩ ችግሩ መከሰቱን የሚያሳውቅ የመጀመሪያው ምልክት ነው

ወደ ላይኛው የአፈር ንጣፍ የወጣ ጨው አትክልቶችን ያወድማል

በአንድ ወቅት ምርታማ በነበረ የእርሻ መሬት ላይ የተከማቸ ጨው ያስከተለው ውጤት

የከርሰ ምድር ውኃ ወደ ላይኛው የመሬት ክፍል ከፍ እያለ ሲመጣ የሚያስከትለው ውጤት

[ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች የተወሰዱት:- © CSIRO Land and Water