በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለወጣቶች የሚሆን እርዳታና ጥበቃ

ለወጣቶች የሚሆን እርዳታና ጥበቃ

ለወጣቶች የሚሆን እርዳታና ጥበቃ

ልጅነቷን ያልጨረሰች አንዲት ልጅ ከጋብቻ ውጭ አርግዛ ከማየት የበለጠ የሚያሳዝን ነገር አይኖርም። ያም ሆኖ ይህ ችግር በጣም እየተስፋፋና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በአንድ መንገድ ወይም በሌላው የሚነካ እየሆነ መጥቷል። የለጋ ወጣቶች እርግዝና የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት “ከዝሙት ሽሹ” የሚለው የአምላክ ትእዛዝ ትክክል መሆኑን ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች አንዱ ነው።—1 ቆሮንቶስ 6:18

ሆኖም የአምላክን መንገዶች ተምረው ያደጉ አንዳንድ ልጃገረዶች የተማሩትንና ያወቁትን ችላ ለማለትና ለመተላለፍ መምረጣቸው አልቀረም። ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት ያረግዛሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጸምበት ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዴት ይሰማቸዋል? እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ የወደቀች ወጣት ሴት ንስሐ መግባቷን በምታሳይበት ጊዜ ወላጆቿም ሆኑ ሌሎቹ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ፍቅራዊ እርዳታና ድጋፍ ሊሰጧት ይገባል።

አሁንም እንደገና የኒኮልን ሁኔታ እንመልከት። ወላጆቿ የይሖዋ ምሥክር እንድትሆን አድርገው አሳድገዋት ነበር። በመሆኑም ሳታገባ አርግዛ በተገኘች ጊዜ በጣም ተበሳጭተዋል። ቢሆንም ኒኮል “ክርስቲያን ባልንጀሮቼ እቤቴ እየመጡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠናና ወደ ይሖዋ እንድቀርብ ያበረታቱኝ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

እንዲህ ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች ዝሙትን ይደግፋሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ክፉ አድራጊዎችን ‘መለወጥ’ እንደሚቻል ይገነዘባሉ። (ሮሜ 12:2) አምላክ ንስሐ የገቡ በደለኞችን ይቅር እንደሚል የማይናወጥ እምነት አላቸው። (ኤፌሶን 1:7) በተጨማሪም አንድ ሕፃን ከጋብቻ ውጭ የተረገዘ ቢሆንም እሱ ምንም የሠራው ጥፋት እንደሌለ ይገነዘባሉ። ስለሆነም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዲህ ያለውን ሕፃን ከማግለል ይልቅ በመካከላቸው ለሚገኝ ማንኛውም ሕፃን የሚያሳዩትን ፍቅር፣ ሐዘኔታና ደግነት ለእርሱም አይነፍጉትም።—ቆላስይስ 3:12

አንዲት ነጠላ እናት መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረች። ብዙም ሳትቆይ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተቀበለችና በሕይወቷ ውስጥ ትላልቅ ለውጦች አደረገች። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ስትናገር “ሁሉም ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ልባዊ አሳቢነት አሳይተውናል። አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ የምግብ፣ የአልባሳትና የገንዘብ እርዳታ አድርገውልኛል። ከእነርሱ ጋር በመስክ አገልግሎት የመካፈል ብቃት ባገኘሁ ጊዜ ልጆቼን ጠብቀውልኛል። ለይሖዋ ልባዊ የሆነ ፍቅር እንዳዳብር የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገውልኛል” ብላለች።

መከላከል

ይሁን እንጂ ወጣቶች ቀድሞውኑ እንዲህ ባለው ችግር ውስጥ እንዳይወድቁ መከላከል በጣም የተሻለ ይሆናል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ፍቅርና የቤተሰብ መተሳሰብ በሰፈነበት ቤት ውስጥ እንዲኖሩ የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ኤድስና ያልተፈለገ እርግዝና የመሰሉትን ማስፈራሪያዎች ከመጠቀም ይልቅ ልጆቻቸው ለይሖዋ አምላክና ለሕግጋቱ ፍቅር እንዲያድርባቸው ለማድረግ ይሞክራሉ። (መዝሙር 119:97) ልጆች ትክክለኛ የሆነ የሥነ ተዋልዶ መረጃ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸውና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከጨቅላነታቸው ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች መማር እንዳለባቸው ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) በየአካባቢው በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች መደበኛ የሆነ ትምህርት ይሰጣል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በግል እንዲያጠኑም ይበረታታሉ። ወላጆች ለልጆቻቸው የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲሰጡ የሚያስችሏቸው እንደ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶቻቸው ያሉ ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። *

ጥብቅ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች መከተል ዓለምን ካጥለቀለቀው የብልግና ማዕበል ጋር በቀጥታ ይጋጫል። ቢሆንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶችን ያልተፈለገ እርግዝና ከሚያስከትለው አሳዛኝ መከራ የሚያድን መንገድ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከጋብቻ ውጭ የወለዱ እናቶችን በደግነትና በሐዘኔታ ይይዛሉ