በለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች—እርግዝና የመላው ዓለም አሳዛኝ ችግር
በለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች—እርግዝና የመላው ዓለም አሳዛኝ ችግር
ለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች እርግዝና ወረርሽኝ ሆኗል ተብሏል። ይሁን እንጂ አንዲት ልጅ በምታረግዝበት ጊዜ ምን ያህል ችግርና ጭንቀት እንደሚያጋጥማት ካልታየ የችግሩን ግዝፈት ሙሉ በሙሉ መገንዘብ ያስቸግራል። እጅግ አነሰ ቢባል የእርሷን ብቻ ሳይሆን የመላ ቤተሰቧን ሕይወት የሚያመሳቅል ድንገተኛ ለውጥ በሕይወቷ ውስጥ ያጋጥማታል።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” በሚለው ጊዜ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ይህም የጾታ ስሜታቸው የሚያይልበት ወቅት ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) ይሁን እንጂ የለጋ ወጣቶችን እርግዝና የወሊድ መከላከያ ካለመጠቀም አንጻር ብቻ መመልከት ተገቢ አይደለም። ይህ ጉዳይ ውስብስብ ከሆኑ በርካታ ማኅበራዊና ስሜታዊ ችግሮች ጋር የሚዛመድ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለችግሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምክንያቶች
ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ ለልጅ እናትነት የሚዳረጉት አብዛኞቹ ወጣቶች ትዳራቸው ከፈረሰባቸው ወላጆች የተገኙ እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። ለዚህ ችግር የተጋለጡ አብዛኞቹ ወጣቶች “ምኞቴ በሙሉ የራሴ የምለው ቤተሰብ እንዲኖረኝ ብቻ ነበር” የሚል እሮሮ በተደጋጋሚ ያሰማሉ። ስለዚህ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ወደ እርግዝና የሚያመሩበትን ሁኔታ የሚያመቻቸው የቤተሰብ መፍረስ እንደሆነ ግልጽ ነው። በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ የሚገኙ እናቶችን ለመርዳት የተነደፈ አንድ ፕሮግራም እንዳመለከተው እነዚህ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ “ከእናቶቻቸው ጋር ያልሰከነ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ከአባቶቻቸው ጋር ደግሞ ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበራቸው” ናቸው። በ18 ዓመት ዕድሜዋ የልጅ እናት የሆነችው አኒታ ያለ አባት ያሳደገቻት እናቷ ለኑሮ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ለማቅረብ ብዙ የደከመች ብትሆንም አባት ያልነበራት መሆኗ ስሜታዊ ፍላጎቷ እንዳልተሟላላት ሆኖ እንዲሰማት አድርጓታል።
ሌሎች ልጆች ደግሞ ከጋብቻ ውጭ የሚያረግዙት ተገድደው በመደፈር ነው። አንዳንዶቹ ተገድደው መደፈራቸው ትክክለኛ ያልሆነ ባሕርይ እንዲከተሉ የሚገፋፋቸው የስሜት ቁስል የሚያሳድርባቸው ይመስላል። ለምሳሌ ጃስሚን ተገድዳ የተደፈረችው በ15 ዓመቷ ነበር። “ከዚያ ጊዜ አንስቶ ስለራሴ ፈጽሞ ደንታ ቢስ ሆንኩ። አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ አረገዝኩ” በማለት ታስታውሳለች። በተጨማሪም መነወር የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊያሳድር ይችላል። ጃስሚን “ለምንም ነገር የማልጠቅም ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር” በማለት ታማርራለች። አኒታም ያጋጠማት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም። “ከ7 እስከ 11 ዓመት ዕድሜዬ አንድ ወጣት ልጅ እያስገደደ ሩካቤ ሥጋ ይፈጽምብኝ ስለነበር ራሴን ጠላሁት። የጥፋተኝነት ስሜትም ይሰማኝ ነበር” ትላለች። በ17 ዓመት ዕድሜዋ ነፍሰ ጡር ሆነች።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወጣቶች ከሚገባው በላይ በራሳቸው መተማመናቸውና አዲስ ነገር ለማወቅ መጓጓታቸው ለዚህ ችግር ይዳርጋቸዋል። ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ የተጠቀሰችው ኒኮል “ሁሉን የማውቅና ማንኛውንም ነገር ማድረግ የምችል ይመስለኝ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ልጅም ልወልድ የምችል መሆኑን አለማሰቤ ነው” ስትል ስህተቷን አምናለች። ገና በለጋ ዕድሜዋ አባት የሌለው ልጅ እናት የሆነችው ካሮልም በተመሳሳይ
የጾታ ግንኙነት መፈጸም የጀመረችው አዲስ ነገር ለማወቅ ባላት ፍላጎት ተነሳስታ ነበር። “የቀረብኝ ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ትላለች።የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል አለማወቅም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። በብሪታንያ የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪ የሆኑት ካረን ሮሊንግሰንና ስቲፈን ማኬይ እንዳሉት ከሆነ አንዳንድ ወጣቶች “ከወንድና ከሴት ግንኙነት ምን ነገር ሊጠበቅ እንደሚችልና ለእርግዝና አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምን እንደሆነ . . . ትክክለኛ እውቀት የላቸውም።” አንዳንድ ወጣቶች በጾታ ግንኙነትና በእርግዝና መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለ አይገነዘቡም። በአንድ ጥናት እንደተረጋገጠው በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ እናቶች “ምንም እንኳ ምንም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቅመው ባያውቁም አብዛኛውን ጊዜ ማርገዛቸውን ሲያውቁ በጣም ይደነግጣሉ ወይም ፈጽሞ ዱብ ዕዳ ይሆንባቸዋል።”
ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ በለጋ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች እርግዝና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለው ስለ ጾታ ግንኙነት ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱ ነው። የምንኖረው ብዙ ሰዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” በሆኑበት ዘመን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ኤልሳ በርንስ እና ካት ስኮት የተባሉት አውስትራሊያውያን ተመራማሪዎች “ከጋብቻ ውጭ በሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ላይ ይሰነዘር የነበረው ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞ በጣም ቀንሷል” ብለዋል። ሳያገቡ መውለድ እንደቀድሞዎቹ ዘመናት ነውር ተደርጎ መታየቱ ቀርቷል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ልጅ መውለድን እንደ ሽልማት ወይም እንደሚያስከብር ነገር ይቆጥራሉ።
የሚያስከትለው የስሜት ቁስል
የልጅነት እርግዝና የሚያስከትለው ውጤት የልጅነት አእምሮ ከሚያስበው የሕልም ዓለም ፈጽሞ
የተለየ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሴት ልጆች ማርገዛቸውን ሲያውቁ ከፍተኛ የሆነ የስሜት መረበሽ ይደርስባቸዋል። ብዙዎች በጣም እንደደነገጡና ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። የአሜሪካ የልጆችና የወጣቶች ሥነ ልቦና አካዳሚ “ከተለመዱት የስሜት መግለጫዎች መካከል ቁጣ፣ የጥፋተኝነት ስሜትና እውነታውን ለመቀበል አለመፈለግ ይገኙበታል” ይላል። ይሁን እንጂ እውነታውን ለመቀበል አለመፈለግ አንዲት ልጅ የሚያስፈልጋትን የሕክምና ክትትል እንዳታገኝ ስለሚያደርጋት አደገኛ ሊሆን ይችላል።ኤልቪንያ ብሞክረው ምን እሆናለሁ ብላ የፈጸመችው የጾታ ግንኙነት ምን ውጤት እንዳስከተለባት ባወቀችበት ቅጽበት ምን እንደተሰማት ስትናገር “በጣም ፈራሁ” ብላለች። ብዙ ወጣት ነፍሰ ጡሮች ስለደረሰባቸው ሁኔታ የልባቸውን ገልጠው የሚነግሩት ሰው የላቸውም ወይም ለመናገር ያፍራሉ። ስለሆነም አንዳንዶቹ በጥፋተኝነት ስሜትና በፍርሐት ተውጠው መቅረታቸው አያስደንቅም። በተጨማሪም ብዙዎቹ ነፍሰ ጡር ወጣቶች በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይሰቃያሉ። “የመኖር ፍላጎት አልነበረኝም። ወዲያው ብሞት ምንም ግድ አይሰጠኝም” ትላለች ጃስሚን። *
አንዲት ወጣት ሴት መጀመሪያ ላይ የሚሰማት ስሜት ምንም ይሁን ምን በራሷም ሆነ በጸነሰችው ሕፃን ላይ ዘላቂ ውጤት የሚያስከትሉ በርካታ ውሳኔዎችን ለመወሰን መገደዷ የማይቀር ነው። ወጣት ሴቶች እነዚህን ውሳኔዎች እንዴት በጥበብ ሊወስኑ እንደሚችሉ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 ራስን የመግደል ስሜትን ስለመቋቋም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 22, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ሕይወት ዋጋ ያለው ነገር ነው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና አሳዛኝ ገጽታ
ምንም እንኳ እዚህ ላይ የቀረበው አኃዛዊ መረጃ በዩናይትድ ስቴትስ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ቢሆንም በለጋ ዕድሜያቸው የሚያረግዙ ወጣቶች የሚገጥማቸውን ችግር በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ገጽታ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
● ከአሥር ልጃገረዶች መካከል አራቱ ሃያ ዓመት ሳይሞላቸው ያረግዛሉ፤ ይህም ማለት በዓመት ውስጥ 900,000 ወጣቶች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ያረግዛሉ።
● በለጋ ዕድሜያቸው የልጅ እናት ከሚሆኑት ወጣቶች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው።
● አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ እንግልትና በደል የሚደርስባቸው ከአዋቂዎች ይልቅ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሚወልዷቸው ሕፃናት ናቸው።
● ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች ከሆኑ 10 እናቶች መካከል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚጨርሱት አራቱ ብቻ ናቸው።
● በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ወጣቶችን ከሚያስረግዙት ወንዶች መካከል 80 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ያስረገዟትን ልጅ አያገቡም።
● ያረገዙትን ልጅ ከወለዱ በኋላ ከሚያገቡ በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል በትዳራቸው የሚጸኑት 30 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት የምትመሠርተው ትዳር ቢያንስ 25 ዓመት የሆናት ሴት ከምትመሠርተው ትዳር ይልቅ የመፍረስ ዕድሉ በሁለት እጥፍ ይጨምራል።
● በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚወልዷቸው ሕፃናት ያለ ጊዜያቸው የመወለድ ዕድላቸው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የሰውነት ክብደታቸው አነስተኛ ይሆናል። ይህም በጨቅላ ዕድሜያቸው የመሞት፣ የመታወር፣ የመስማት ችሎታቸውን የማጣት እንዲሁም ሥር በሰደደ የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ በአእምሮ ዝግመት፣ በአእምሮ ሕመም፣ ጡንቻን በሚያልፈሰፍስ በሽታ፣ የመማር ችሎታን በሚያሳጣ ሕመምና ቅዥቅዥ በሚያደርግ በሽታ የመጠቃት ዕድላቸውን ይጨምረዋል።
[ምንጭ]
ኖት ጀስት አናዘር ሲንግል ኢሹ:- ቲን ፕሬግናንሲ ፕሪቬንሽንስ ሊንክ ቱ አዘር ክሪቲካል ሶሻል ኢሹስ፣ ዘ ናሽናል ካምፔይን ቱ ፕሪቬንት ቲን ፕሬግናንሲ ከተባለው ቡክሌት የተወሰደ፣ የካቲት 2002
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና በዓለም ዙሪያ
ብራዚል:- “በ1998 በብራዚል የጤና ጣቢያዎች ከ19 ዓመት በታች የሆኑ 698,439 ወጣቶች ልጅ እንደወለዱ” ሪፖርት ተደርጓል። “ከእነዚህ መካከል 31,857 የሚሆኑት ከ10 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ናቸው። በዚህ ዕድሜ ልጅ መውለድ ደግሞ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል ነገር ነው።”—ፎሊያ ዲ ሳኦ ፓውሎ፣ ነሐሴ 25, 1999
ብሪታንያ:- “ብሪታንያ በምዕራብ አውሮፓ በለጋ ዕድሜያቸው ልጅ የሚወልዱ ወጣቶች በብዛት ከሚገኙባቸው አገሮች መካከል ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይዛለች። . . . በ1997 በእንግሊዝ 90,000 ገደማ የሚሆኑ ለጋ ወጣቶች ጸንሰዋል። ከእነዚህ መካከል ሦስት አምስተኛ (56,000) የሚሆኑት የወለዱ ሲሆን በዚሁ ዓመት በወጣነታቸው ከወለዱት እናቶች መካከል 90 በመቶ (50,000 ገደማ) የሚሆኑት ያላገቡ ናቸው።”—ሎን ፓረንት ፋሚሊስ፣ 2002
ማሌዥያ:- “በዚህች አገር ከ1998 አንስቶ ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር እያሻቀበ የመጣ ሲሆን አብዛኞቹ እናቶች ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ናቸው።”—ኒው ስትሬይትስ ታይምስ–ማኔጅመንት ታይምስ፣ ሚያዝያ 1, 2002
ሩስያ:- “ባለፈው ዓመት በሩስያ ከተወለዱት ሕፃናት መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የተወለዱት ከጋብቻ ውጭ ሲሆን ይህም ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ጨምሯል። መንግሥት ያወጣቸው አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እንዲህ ያለ ሁኔታ ታይቶ አይታወቅም። ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የወለዷቸው ናቸው።”—ዘ ሞስኮ ታይምስ፣ ኅዳር 29, 2001
ዩናይትድ ስቴትስ:- “ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚጸንሱ ወጣቶች ቁጥር እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በለጋ ዕድሜ ከሚገኙ 10 ወጣቶች መካከል አራቱ 20 ዓመት ሳይሞላቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ይጸንሳሉ።”—ዋትኤቨር ሃፕንድ ቱ ቻይልድሁድ? ዘ ፕሮብሌም ኦቭ ቲን ፕሬግናንሲ ኢን ዚ ዩናይትድ ስቴትስ፣ 1997
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች በሚለያዩበት ወይም በሚፋቱበት ጊዜ ሴት ልጆች ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ የማርገዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ወጣቶች በጾታ ግንኙነትና በእርግዝና መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት መኖሩን አይገነዘቡም
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እርግዝና በልጅቱም ሆነ በቤተሰቦቿ ሕይወት ላይ ብዙ ለውጥ ያስከትላል