የአትላንቲኩ ሳልሞን—ሕልውናው አደጋ ላይ የወደቀው “ንጉሥ”
የአትላንቲኩ ሳልሞን—ሕልውናው አደጋ ላይ የወደቀው “ንጉሥ”
አየርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ሳልሞኖች እንቁላል ለመጣል ወንዞችን ተከትለው ሽቅብ በሚያደርጉት ጉዞ ፏፏቴዎችን እየዘለሉ ለማለፍ ባላቸው ችሎታ ይታወቃሉ። እንዲያውም ስለ ሳልሞኖች በሚናገር አንድ ተረት ላይ አንድ ዓሣ አጥማጅ በወንዝ ዳር ዓሣ እያጠመደ ሳለ “በርካታ ሳልሞኖች [ፏፏቴውን] መዝለል አቅቷቸው” ወደ ወንዙ ሲወድቁ ይመለከታል። አንዳንዶቹ ዓሣዎች ያረፉት በወንዙ ዳርቻ ላይ ነበር። ዓሣ አጥማጁ በፏፏቴው ግርጌ በሚገኝ ገላጣ ድንጋይ ላይ እሳት አቀጣጠለና መጥበሻ ጣደበት። ተረቱ እንደሚለው “ፏፏቴውን ለመዝለል ሞክረው ያልተሳካላቸው አንዳንድ ሳልሞኖች በአጋጣሚ መጥበሻው ላይ ያርፋሉ።” በዚህም የተነሳ ዓሣ አጥማጁ ‘እርሱ በሚኖርበት አገር ሳልሞን በጣም የተትረፈረፈ ከመሆኑ የተነሳ ዓሣ አጥማጆች ምንም ሳይደክሙ ዓሣዎቹ በራሳቸው ፈቃድ እየዘለሉ መጥበሻው ላይ እንደሚያርፉ’ በጉራ ተናግሯል።
ይህ ተረት በተወሰነ መጠን የተጋነነ ቢሆንም ሳልሞኖች ፏፏቴዎችን እየዘለሉ ማለፍ መቻላቸው ግን እውነት ነው። በአየርላንድ የሚገኘው የሳልሞን የምርምር ወኪል ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “እንቁላላቸውን ለመጣል ወንዞችን ተከትለው ሽቅብ የሚጓዙት የባሕር ሳልሞኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።” በአንድ ጥናት መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ምልክት ተደርጎባቸው ወደ ባሕር ከተለቀቁት ወደ 44,000 የሚጠጉ ትናንሽ ሳልሞኖች መካከል ወደ ወንዙ የተመለሱት 3 በመቶ ብቻ (በግምት 1,300 የሚሆኑ) ነበሩ።
“የዓሣዎች ንጉሥ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የአትላንቲኩ ሳልሞን ቁጥሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ያሽቆለቆለው ለምንድን ነው? እንደ በፊቱ የተትረፈረፈ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አስገራሚና ልዩ የሆነውን የዚህን ዓሣ የሕይወት ዑደት መረዳታችን የችግሩን መንስኤና መፍትሔ ለመገንዘብ ያስችለናል።
የሳልሞን የሕይወት ዑደት
ሳልሞን የሕይወት ጉዞውን የሚጀምረው ከኅዳር እስከ የካቲት ባሉት ወራት ላይ ነው። እንስቷ ዓሣ በአንድ ወንዝ ውስጥ ባለ የጠጠርና የአሸዋ ወለል ላይ 30 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያላቸው ትናንሽ ጉድጓዶች ስትቆፍር ወንዱ ሳልሞን ጠላቶችን ለማባረር ዘብ ይቆማል። ከዚያም እንስቷ ዓሣ በእያንዳንዱ ጉድጓድ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎች ትጥልና በወንዴው ዘር ከዳበሩ በኋላ ጠጠርና ኮረት በማልበስ ትደብቃቸዋለች።
በመጋቢት ወይም በሚያዝያ እንቁላሉ ይፈለፈልና በዓይነቱ ለየት ያለ ቅርጽ ያለው ዓሣ ይወጣል። አለቪን ተብሎ የሚጠራው ይህ ዓሣ ቁመቱ ከ3 ሴንቲ ሜትር የማይበልጥ ሲሆን ከሥሩ የተንጠለጠለ ትልቅ ከረጢት አለው። መጀመሪያ ላይ ዓሣው በከረጢቱ ውስጥ የሚገኘውን ምግብ እየተመገበ ባለበት ተደብቆ ይቆያል። ከአራት ወይም አምስት ሳምንታት በኋላ የያዘውን ስንቅ ሲያጠናቅቅ ከጠጠሮቹ ሥር ይወጣና ወደ ዋናው ወንዝ ይገባል። አሁን ፍራይ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን 5 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመትና ትክክለኛ የዓሣ ቅርጽ ይኖረዋል። በዚህ ወቅት የሚያሳስቡት ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው። የመጀመሪያው አዲስ የምግብ ምንጭ ማለትም ትንንሽ ነፍሳትንና የባሕር ዕጽዋትን ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከአደጋ ተጠብቆ ሊኖር የሚችልበት አስተማማኝ ቦታ መፈለግ ነው። ፍራይ ተብሎ በሚጠራው የዕድሜ ክልል ላይ ከሚገኙት ሳልሞኖች መካከል ከ90 በመቶ የሚበልጡት ምግብ ወይም ቦታ አጥተው አሊያም እንደ ትራውት ባሉ ዓሣዎች፣ የወንዝ አመቴና ሳቢሳ ተብለው በሚጠሩት ወፎች ወይም ኦተር በሚባሉ እንስሳት ተበልተው ያልቃሉ።
በሳልሞንና በሌሎች ዓሣዎች ላይ ጥናት ያካሄዱት ማይክል እንደሚሉት “ከአንድ ዓመት ገደማ
በኋላ ሳልሞኖቹ ከ8-10 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ይኖራቸዋል። በዚህ ደረጃ ላይ ፓር ተብለው የሚጠሩ ሲሆን በጎንና ጎናቸው ላይ ባለው ጠቆር ያለ ነጠብጣብ ተለይተው ይታወቃሉ። የዓሣው ቁመት 15 ሴንቲ ሜትር ሲያክል ነጠብጣቦቹ ይጠፉና የሚያብረቀርቅ ብርማ መልክ ይኖረዋል። በዚህ ጊዜ ሳልሞኖችን ከሌሎች የዓሣ ዝርያዎች የሚለዩአቸው አስገራሚ የሆኑና የተወሳሰቡ ለውጦች በሰውነታቸው ላይ ይካሄዳሉ።”ማይክል ቀጥለው እንዲህ ይላሉ:- “በዚህ ዕድሜው ላይ ስሞልት ተብሎ የሚጠራው ሳልሞን ከግንቦት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ሰውነቱ በሚሰጠው ምልክት ተነሳስቶ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሳልሞኖች ጋር ይቀላቀልና በጋራ ወደ ወንዙ መድረሻ መትመም ይጀምራሉ።” ይሁን እንጂ በወንዝ ውስጥ መኖር የለመደ ዓሣ በጨዋማው ባሕር ውስጥ መኖር ይችላል? ማይክል ይህን ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል:- “እንደ እውነቱ ከሆነ አይችልም፤ ሆኖም ሳልሞኖች በባሕር ውኃ ውስጥ ያለውን ጨው ለማጣራት የሚያስችሉ ውስብስብ ለውጦች በስንጥባቸው ዙሪያ ያደርጋሉ። እነዚህ ለውጦች ተካሂደው ሲጠናቀቁ ከእጃችን መዳፍ የማይበልጥ ቁመት ያለው ስሞልት ጀብደኛ የሚያስብለውን ረጅም ጉዞ ይጀምራል።”
የባሕር ውስጥ ሕይወት
ይህ ትንሽ ዓሣ ተወልዶ ያደገበትን ወንዝ ለቅቆ የሚሄደው ለምንድን ነው? ደግሞስ ወዴት ነው የሚጓዘው? ገና በዕድሜ ለጋ የሆነው ሳልሞን የተሟላ የእድገት ደረጃው ላይ ለመድረስ ምግብ እንደ ልብ ወደሚያገኝበት አካባቢ መሄድ አለበት። በጉዞው ላይ የዓሣ አውጭ ወፎች፣ የአቆስጣዎች፣ የዶልፊኖችና የዓሣ ነባሪዎች እራት ከመሆን ካመለጠ ምግብ በብዛት ወደሚያገኝበት ቦታ ደርሶ የባሕር ዕጽዋትን እንዲሁም እንደ ሳንድ ኢል፣ ሄሪንግና ካፕሊን ያሉ ትናንሽ ዓሣዎችን እየተመገበ ያድጋል። ከአንድ ዓመት በኋላ ክብደቱ በ15 እጥፍ ይጨምራል። በሌላ አባባል ከጥቂት መቶ ግራሞች ተነስቶ ወደ 3 ኪሎ ግራም ያድጋል ማለት ነው። ለአምስት ዓመታት በውቅያኖስ ውስጥ ከቆየ 18 ኪሎ ግራም ወይም ከዚያ በላይ ክብደት ሊኖረው የሚችል ሲሆን ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ ሳልሞኖችም ተገኝተዋል።
በ1950ዎቹ ዓሣ አስጋሪዎች በግሪንላንድ ጠረፍ አቅራቢያ በርካታ ሳልሞኖችን ማጥመድ እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ ሳልሞኖች በብዛት ተሰባስበው የሚመገቡባቸው ቦታዎች አይታወቁም ነበር። ቆየት ብሎ ደግሞ ከስኮትላንድ በስተ ሰሜን በሚገኙት የፌሮ ደሴቶች ዙሪያ ሌላ የሳልሞኖች መመገቢያ ቦታ ተገኘ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በርካታ የዚህ ዓይነት መመገቢያ ሥፍራዎች የተገኙ ሲሆን በግግር በረዶ በሚሸፈነው የአርክቲክ ውቅያኖስ ውስጥ እንኳን የሚመገቡ ሳልሞኖች እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ቦታዎች መገኘት በአትላንቲኩ ሳልሞን ሕልውና ላይ ትልቅ አደጋ ፈጠረ። በግሪንላንድና በፌሮ ደሴቶች ላይ ትላልቅ የዓሣ ማስገሪያ ጣቢያዎች ተቋቋሙ። ዓሣ አስጋሪዎቹ በብዙ ሺህ ቶኖች የሚቆጠሩ ሳልሞኖች ማጥመድ ሲጀምሩ ዘራቸውን ለመተካት ወደ ወንዞቹ የሚመለሱት ሳልሞኖች ቁጥር በድንገት አሽቆለቆለ። የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘቡት መንግሥታት ዓሣ አስጋሪዎቹን ለመቆጣጠር የተለያዩ ገደቦችና ኮታዎች ያወጡ ሲሆን ይህ እርምጃ በባሕር ውስጥ ያሉትን ሳልሞኖች ሕልውና ለመታደግ አስችሏል።
ከባሕር ወደ ወንዝ የሚደረገው የመልስ ጉዞ
ከጊዜ በኋላ እድገቱን የጨረሰው ሳልሞን ወዳደገበት ወንዝ ተመልሶ አጋር የምትሆነው እንስት ሳልሞን ይፈልግና ከላይ የተመለከትነው የሕይወት ዑደት እንደገና ይጀምራል። “በጣም የሚያስገርመው” ይላሉ ማይክል “ይህ አስደናቂ ዓሣ ከዚህ በፊት ሄዶበት የማያውቀውን በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ውቅያኖስ አቅጣጫውን ሳይስት ማቋረጥ ይችላል። የዚህ ችሎታው ምስጢር እስካሁን ድረስ ለሳይንቲስቶች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶች ሳልሞኖች የሚጓዙት የምድርን መግነጢሳዊ ኃይል፣ የውቅያኖስ ሞገድን ወይም ከዋክብትን በመጠቀም ነው ይላሉ። ወንዞች ከውቅያኖሶች ጋር ወደሚቀላቀሉበት ቦታ ሲደርሱ ግን ያደጉበትን ወንዝ ‘በሽታው’ ወይም በኬሚካላዊ ውህደቱ ለመለየት ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል።”
ማይክል ሲቀጥሉ እንዲህ ይላሉ:- “ጨዋማ ባልሆነው የወንዝ ውኃ ውስጥ ለመኖር እንዲችሉ በሰውነታቸው ላይ በድጋሚ ማስተካከያ ያደርጉና ወደ ወንዙ ይገባሉ። በዚህ ወቅት ከቀድሞው የተሻለ ክብደትም ሆነ ጥንካሬ ያላቸው እነዚህ ሳልሞኖች ከትውልድ ሥፍራቸው ለመድረስ ያላቸው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በጉዟቸው ላይ ፏፏቴ ወይም ፈረሰኛ ውኃ ቢያጋጥማቸው እንኳን ግንባራቸውን ሳያጥፉ እያንዳንዱን እንቅፋት አሸንፈው ለማለፍ ይታገላሉ።”
ወደ ትውልድ ቦታቸው በሚመለሱበት ወቅት ግድቦች፣ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎችና እነዚህን የመሳሰሉ አስቸጋሪ የሆኑ ሰው ሠራሽ ጋሬጣዎች ያጋጥሟቸዋል። በዚህ ጊዜ ምን ያደርጋሉ? ስለ ሳልሞኖች ጥናት የምታካሂደው ዴርድሬ እንዲህ ትላለች:- “የሳልሞኖች ደኅንነት የሚያሳስባቸው በርካታ ሰዎች አማራጭ መንገድ ያዘጋጃሉ። ትልቁን ጋሬጣ አሳብሮ የሚያልፍና ብዙም አቀበትነት የሌለው መተላለፊያ ይገነባል። የዓሣ መተላለፊያ ወይም መወጣጫ ብለን የምንጠራው ይህ ዘዴ ሳልሞኖቹ እንቁላላቸውን ወደሚጥሉበት ሥፍራ ሲጓዙ በከፍታ ቦታ ላይ ወዳለው ውኃ በቀላሉ ለመዝለል ያስችላቸዋል።”
“ይሁን እንጂ ይህ ዘዴ የሚሠራው ሁልጊዜ አይደለም” ትላለች ዴርድሬ። “በተሠራላቸው አማራጭ መንገድ የማይጠቀሙ አንዳንድ ሳልሞኖችን ተመልክቻለሁ። የሚያውቁት በመጀመሪያ ያለፉበትን አቅጣጫ ብቻ ስለሆነ
ከፊታቸው የተጋረጠውን ሰው ሠራሽ እንቅፋት ዘለው ለማለፍ ያለማቋረጥ ይሞክራሉ። አብዛኞቹም በድካም ወይም ከጋሬጣው ጋር በመላተማቸው ምክንያት ይሞታሉ።”የሳልሞን እርባታ ጣቢያዎች
የሳልሞን ሥጋ ገንቢ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ነው። ከባሕር የሚጠመደው የአትላንቲኩ ሳልሞን ቁጥር እየቀነሰ በመሄዱ ዓሣውን አርብተው ለገበያ የሚያቀርቡ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል። የስሞልት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ በየብስ ላይ በሚገኙ ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ እንዲያድጉ ይደረጋል። ከዚያም በባሕር ላይ ወደሚገኝ በሽቦ አጥር የተከለለ የእርባታ ጣቢያ ይዛወሩና እድገታቸውን አጠናቅቀው ለምግብ ቤቶችና ለሱቆች እስከሚሸጡበት ጊዜ ድረስ ይቀለባሉ።
በዚህ መንገድ የሚያድጉ ሳልሞኖችም ግን ለችግር መጋለጣቸው አልቀረም። ዓሣ አርቢዎቹ የሚቀልቧቸው ሰው ሠራሽ የሆኑ ምግቦችን ነው። ይህ ሳልሞኖቹ በአንድ ቦታ ታጉረው ከመቀመጣቸው ጋር ተዳምሮ ለበሽታና የባሕር ቅማል እንደሚባለው ላሉ ጥገኛ ተህዋሲያን እንዲጋለጡ አድርጓል። ሳልሞኖቹን ከበሽታ ለመከላከል ተብለው ከሚረጩት ጸረ ተህዋሲያን መካከል አንዳንዶቹ በጣም ኃይለኛ ናቸው። ኧርነስት የተባለ ጠላቂ ዋናተኛ እንዲህ ይላል:- “በእነዚህ የእርባታ ጣቢያዎች ሥር እዋኝ ነበር፤ በአብዛኞቹ ቦታዎች በባሕሩ ወለል ላይ ሕይወት የሚባል ነገር እንደሌለ በግልጽ ይታያል።”
ሕልውናው አደጋ ላይ የወደቀው “ንጉሥ”
በርካታ የባሕር ሳልሞኖች ወዳደጉበት ወንዝ ከመመለሳቸው በፊት በዓሣ አስጋሪዎች መረብ ይያዛሉ። ከባሕር የሚጠመዱት ሳልሞኖች በገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ዓሣ አስጋሪዎች በሕገወጥ መንገድ ይይዟቸዋል። ከእነርሱ አምልጠው ወደ ወንዛቸው መመለስ የቻሉት ደግሞ በመንጠቆ የማጥመድ ፈቃድ ያላቸውን ዓሣ አጥማጆች ማለፍ ይኖርባቸዋል። ሳልሞኖችን ለመታደግ ሲባል የማጥመጃ ቦታዎችን በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻ እንዲወሰኑ ማድረግ፣ ከባድ ቀረጥ መጣልና በተወሰኑ ወራት ብቻ እንዲጠመድ ማድረግን የመሳሰሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። ያም ሆኖ ግን ወንዞችን ተከትለው ሽቅብ ከሚጓዙት ሳልሞኖች መካከል ከአምስቱ አንዱ በዓሣ አጥማጆች እንደሚያዝ ይገመታል።
በተጨማሪም የባሕር ሳልሞኖች በተለያዩ በሽታዎች የሚጠቁ ሲሆን ይህም ለቁጥራቸው መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። አልሰሬቲቭ ደርማል ኒክሮሲስ የሚባለው በሽታ ከእነዚህ አንዱ ሲሆን በዚህ በሽታ የተጠቃ ዓሣ በቆዳው ላይ ቁስል ይወጣበትና ከጊዜ በኋላ ይሞታል። የሳልሞኖችን ብሎም የሌሎችን የውኃ ውስጥ ፍጥረታት ሕልውና እየተፈታተነ ያለው ሌላው አደጋ ደግሞ የኢንዱስትሪ ፍሳሽና ወደ ወንዞች ውስጥ ሰርጎ የሚገባው ጸረ ተባይ መድኃኒት ነው።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተደቀኑበት “የዓሣዎች ንጉሥ” ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋል ቢባል አያስገርምም። ብዙ ሰዎች ችግሮቹን ለመቅረፍ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ እያደረጉ ቢሆንም አደጋው ሙሉ በሙሉ የሚወገድ አይመስልም። የተፈጥሮ ሚዛን ወደነበረበት ሁኔታ የሚመለሰው የምድር ፈጣሪ የሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ ሰዎች ምድርን እንዳያጠፏት ለመታደግ ጣልቃ ሲገባ ብቻ ይሆናል።—ኢሳይያስ 11:9፤ 65:25
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የአትላንቲኩ ሳልሞን ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከሩሲያና ከስፔይን ተነስቶ በፌሮ ደሴቶችና በግሪንላንድ ወደሚገኙ ምግብ እንደልብ የሚገኝባቸው ቦታዎች የሚጓዝ ሲሆን ከዓመታት በኋላ እንቁላሉን ለመጣል ወደመጣበት ይመለሳል
[ካርታ]
ዩናይትድ ስቴትስ
ግሪንላንድ
አይስላንድ
የፌሮ ደሴቶች
ሩሲያ
ፈረንሳይ
ስፔይን
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]
አስገራሚው የሳልሞን የሕይወት ዑደት
የሳልሞን እንቁላሎች
↓
ዓይናቸው መታየት የጀመረ እንቁላሎች
↓
አለቪን
↓
ፍራይ
↓
ፓር
↓
ስሞልት
↓
እድገቱን ያጠናቀቀ ሳልሞን
↓
እንቁላል ሲጣል
[ሥዕሎች]
አለቪን
ፓር
[ምንጮች]
የሳልሞን የሕይወት ዑደት:- © Atlantic Salmon Federation/J.O. Pennanen; አለቪን:- U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C.; ፓር:- © Manu Esteve 2003
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ወዳደገበት ወንዝ ሽቅብ የሚመለሰው ሳልሞን ይህን ፏፏቴ መዝለል ወይም በተዘጋጀለት የዓሣ መወጣጫ በኩል (በስተቀኝ በትልቁ የሚታየው) በቀላሉ ማለፍ ይችላል
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሳልሞንን ሕልውና አደጋ ላይ ከጣሉት ነገሮች መካከል ዓሣዎችን በብዛት የማጥመድ ልማድና በዓሣ ማርቢያ ጣቢያዎች የሚከሰቱት በሽታዎች ተጠቃሽ ናቸው
[ምንጮች]
ፎቶ:- Vidar Vassvik
UWPHOTO © Erling Svensen
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Joanna McCarthy/SuperStock