እናት ያላት የተከበረ የሥራ ድርሻ
እናት ያላት የተከበረ የሥራ ድርሻ
የአንዲት እናት የሥራ ድርሻ ብዙውን ጊዜ አድናቆት የማይቸረው ከመሆኑም ባሻገር ዝቅተኛ ግምት ይሰጠዋል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት አንዳንድ ሰዎች ልጆችን ለመንከባከብ ሥራ ንቀት ያድርባቸው ጀመር። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ልጆችን መንከባከብ ጠቀሜታው ተቀጥሮ ከመሥራት ያነሰ እንዲያውም የጭቆና መገለጫ መንገድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው አመለካከት ከልክ ያለፈ እንደሆነ የሚሰማቸው ሰዎች ቢኖሩም እናቶች የቤት እመቤት መሆንና ልጆችን መንከባከብ ዝቅተኛ ሥራ እንደሆነ እንዲሰማቸው ተደርገዋል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች አንዲት ሴት ሙሉ ችሎታዋን ለመጠቀም ከቤት ውጪ መሥራት እንደሚያስፈልጋት ይሰማቸዋል።
ሆኖም ብዙ ባሎችና ልጆች እናት በቤተሰብ ውስጥ ለምታከናውነው የሥራ ድርሻ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ። በፊሊፒንስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ካርሎ እንዲህ ብሏል:- “እኔን ዛሬ ለዚህ ያበቃኝ እናቴ የሰጠችኝ ሥልጠና ነው። አባቴ ሥነ ሥርዓት እንዲከበር የሚፈልግ ሰው ስለነበር ጥፋት ሲገኝብን ለመቅጣት ይቸኩላል፤ እናታችን ግን እኛን በማሳመንና ምክንያቱን በማስረዳት እንድናስተካክል ትረዳን ነበር። ለምትጠቀምበት የማስተማሪያ ዘዴ ከፍተኛ አድናቆት አለኝ።”
በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ፒተር ደግሞ እምብዛም ባልተማረች እናቱ እጅ ካደጉት ስድስት ልጆች መካከል አንዱ ነበር። አባቱ ቤተሰቡን ጥሎ ሄዷል። ፒተር ወደኋላ መለስ ብሎ በማሰብ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እናታችን የምትሠራው በሰው ቤትና በጽዳት ሠራተኝነት ስለነበር ገቢዋ ያን ያህል አልነበረም። ለሁላችንም የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል ይከብዳት ነበር። ብዙ ጊዜ እራት ሳንበላ አድረናል። ሌላው ተፈታታኝ ችግሯ ደግሞ ለምንኖርበት ቤት ኪራይ መክፈል ነበር። እናታችን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩባትም ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም። ራሳችንን ከሌሎች ጋር እንዳናወዳድር አስተምራናለች። ኃላፊነቷን
በድፍረት ባትወጣ ኖሮ ኑሮን በተሳካ መንገድ ለመምራት አንችልም ነበር።”በናይጄሪያ የሚኖር አህመድ የሚባል አንድ ባል ሚስቱ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ስላደረገችው እገዛ ምን እንደሚሰማው ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የሚስቴን የሥራ ድርሻ አደንቃለሁ። እኔ ቤት በማልኖርበት ወቅት ልጆቹ እንክብካቤ እንደማይጎድልባቸው እርግጠኛ ነበርኩ። ሚስቴ እየተቀናቀነችኝ እንዳለች ተሰምቶኝ አያውቅም፤ እንዲያውም አመሰግናታለሁ፣ ልጆቹም እኔን እንደሚያከብሩኝ ሁሉ እሷንም ማክበር እንዳለባቸው እንዲያውቁ አደርጋለሁ።”
አንድ ፍልስጥኤማዊ ሚስቱ በእናትነቷ ያገኘችውን ስኬት አንስቶ ከማመስገን ወደኋላ አይልም:- “ሊና ለሴት ልጃችን ብዙ ነገር ያደረገች ሲሆን ለቤተሰባችን መንፈሳዊነት የጎላ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። እኔ እንደሚመስለኝ የስኬታማነቷ ምንጭ ሃይማኖታዊ እምነቷ ነው።” ሊና የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ሴት ልጅዋን ለማስተማር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ትከተላለች።
ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእናቶች ስላለው አመለካከት ምን ማለት ይቻላል? እናቶች በጥንት ዘመን የልጆቻቸው አስተማሪ በመሆናቸው የተከበረ ቦታ ይሰጣቸው የነበረው እንዴት ነው?
ስለ እናቶች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
ሰው ሲፈጠር በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ ለሴቷ የተከበረ የሥራ ድርሻ ተሰጥቷት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ “እግዚአብሔር አምላክ፣ ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት [“ማሟያ፣” NW] አበጅለታለሁ’ አለ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:18) ስለዚህ የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን የተፈጠረችው ለአዳም ማሟያ እንድትሆነው ነበር። ሔዋን ለእርሱ ፍጹም ተስማሚ የሆነች ረዳት እንድትሆን ተደርጋ ተፈጥራ ነበር። አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱና ተንከባክበው እንዲያሳድጉ፣ እንዲሁም ምድርንና በውስጧ ያሉትን እንስሳት እንዲንከባከቡ አምላክ በነበረው ዓላማ ውስጥ ሔዋንም ትልቅ ቦታ ነበራት። ከአንድ እውነተኛ አጋር እንደሚጠበቀው ሁሉ የሐሳብና የሞራል ድጋፍ ትሰጠዋለች። አዳም ከፈጣሪው ይህችን ውብ ስጦታ ሲያገኝ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:23
ከጊዜ በኋላ አምላክ ሴቶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው መመሪያዎችን አውጥቷል። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን እናቶች ሊከበሩ እንጂ በንቀት ዓይን ሊታዩ እንደማይገባቸው ደንግጓል። አንድ ልጅ ‘አባቱንና እናቱን ቢረግም’ በሞት ይቀጣ ነበር። ክርስቲያን ወጣቶችም ‘ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ’ በጥብቅ ተመክረዋል።—ዘሌዋውያን 19:3፤ 20:9፤ ኤፌሶን 6:1፤ ዘዳግም 5:16፤ 27:16፤ ምሳሌ 30:17
እናቲቱ በአባትየው አመራር ሥር ሆና የሴቶችም ሆነ የወንዶች ልጆቿ አስተማሪ መሆን ይጠበቅባታል። አንድ ወንድ ልጅ ‘የእናቱን ትምህርት እንዳይተው’ ታዟል። (ምሳሌ 6:20) በተጨማሪም በምሳሌ 31 ላይ “ንጉሥ ልሙኤልን እናቱ ያስተማረችው ቃል” ይገኛል። ይህች እናት ልጅዋ የአልኮል መጠጦችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከመጠቀም እንዲርቅ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ስትመክረው “ነገሥታት የወይን ጠጅ ሊጠጡ፣ ገዦችም የሚያሰክር መጠጥ ሊያስጐመጃቸው አይገባም፤ አለዚያ ጠጥተው የሕጉን ድንጋጌ ይረሳሉ፤ የተጨቈኑትን ሁሉ መብት ይገፋሉ” ብላለች።—ምሳሌ 31:1, 4, 5
ከዚህም ሌላ ለማግባት የሚያስብ ወጣት ሁሉ የንጉሥ ልሙኤል እናት “ከቀይ ዕንቊ እጅግ ትበልጣለች” በማለት ስለገለጸቻት ‘ጠባየ መልካም ሚስት’ የተሰጠውን መግለጫ ቢመለከተው ይጠቀማል። ከዚያም የንጉሡ እናት እንዲህ ዓይነቷ ሚስት ለቤተሰቧ ስለምታበረክተው ጠቃሚ ድርሻ ከገለጸች በኋላ “ቊንጅና አታላይ ነው፤ ውበት ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት” ብላለች። (ምሳሌ 31:10-31) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ፈጣሪያችን ሴቶችን በቤተሰቡ ውስጥ የክብር ቦታና ኃላፊነት እንዲኖራቸው አድርጓል።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሚስቶችና እናቶች ይከበራሉ፣ እንዲሁም በከፍተኛ አድናቆት ይታያሉ። ኤፌሶን 5:25 “ባሎች ሆይ፤ . . . ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ይላል። እናቱና አያቱ “ቅዱሳት መጻሕፍትን” እንዲያከብር አድርገው ላሳደጉት ለወጣቱ ጢሞቴዎስም በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት “አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና አስተናግዳቸው” የሚል ምክር ተሰጥቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ስለዚህ አንድ ሰው አንዲትን አረጋዊት ሴት ልክ እንደ እናቱ አድርጎ ማክበር ይኖርበታል። በእርግጥም አምላክ ለሴቶች ከፍ ያለ ግምት ያለው ሲሆን የክብር ቦታም ይሰጣቸዋል።
አድናቆትህን ግለጽ
ሴቶች ዝቅ ተደርገው በሚታዩበት ባሕል ውስጥ ያደገ አንድ ሰው እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በወንዶች የበላይነት ላይ ያተኮረ ትምህርት የቀሰምኩ ከመሆኑም በላይ ሴቶች በደል ሲፈጸምባቸውና አክብሮት ሲነፈጋቸው ስመለከት ኖሬያለሁ። ስለዚህ ሴቶችን ፈጣሪ በሚያያቸው መንገድ ማለትም ማሟያና ረዳት እንደሆኑ እንዲሁም ልጆቻቸውን በማስተማሩ ተግባር ከባሎቻቸው ጋር ተጋግዘው የመሥራት ኃላፊነት እንዳላቸው ለመቀበል ትግል ማድረግ ነበረብኝ። ለሚስቴ የምሥጋና ቃላት መናገር አስቸጋሪ ቢሆንብኝም በልጆቼ ላይ የማየው መልካም ባሕርይ የሚስቴ ጥረት ውጤት እንደሆነ እገነዘባለሁ።”
በእርግጥም ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነታቸውን የሚወጡ እናቶች በሥራቸው ሊኮሩ ይችላሉ። ጊዜና ጉልበት ቢያጠፉለት የማይቆጭ ሥራ ነው። ለዚህ ሥራቸው ምሥጋናና ልባዊ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ከእናቶች ብዙ ነገር መማር እንችላለን፤ ይኸውም በዕድሜያችን ሁሉ ሊጠቅሙን የሚችሉ ጥሩ ልማዶች፣ ለጥሩ ወዳጅነት በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥርዓታማ ጠባይ እንዲሁም ወጣቶች በትክክለኛው የሕይወት ጎዳና መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ የሚረዳቸውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አስተዳደግ የመሳሰሉትን ነገሮች መማር እንችላለን። እናትህ ላደረገችልህ ነገር በቅርቡ ምሥጋናህን ገልጸህላታል?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፒተርን እናቱ ተስፋ እንዳይቆርጥ አስተምራዋለች
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አህመድ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሚስቱ ያበረከተችውን እገዛ በእጅጉ ያደንቃል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሊና ባል ልጃቸው ጥሩ ባሕርይ ሊኖራት የቻለው በሚስቱ ሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል