አዞ ትፈራለህ?
አዞ ትፈራለህ?
በሕንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ብዙ ሰዎች አዞ ይፈሩ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት በርካታ የአዞ ዝርያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፤ ይሁን እንጂ “ይህ የሚከሰተው አልፎ አልፎ በመሆኑ . . . አዞዎች ሰው ከሚበሉ እንስሳት አይመደቡም።” (ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ) አንዳንድ ሰዎች አዞዎችን መልከ ጥፉና አስፈሪ ፍጥረታት አድርገው ቢመለከቷቸውም እነዚህን እንስሳት በጣም የሚያደንቁ ሰዎችም አሉ። እስቲ ሕንድ ውስጥ ስለሚገኙት የጨዋማ ውኃ አዞዎች እንዲሁም ማገርና ጌቪየል ስለሚባሉት የአዞ ዝርያዎች እንመልከት።
ትልቁ የጨዋማ ውኃ አዞ
በደረታቸው ከሚሳቡ እንስሳት ሁሉ ትልቁ የጨዋማ ውኃ አዞ ሲሆን ከ7 ሜትር በላይ ሊረዝምና እስከ 1,000 ኪሎ ግራም ሊመዝን ይችላል። በጨዋማ ውኃ ውስጥ ብቻ የሚኖረው ይህ አዞ ወንዞች ወደ ባሕር በሚገቡበት ሥፍራና በባሕር ውስጥ እንዲሁም ከሕንድ ጀምሮ እስከ ሰሜን አውስትራሊያ ባሉት ማንግሮቭ የተባለ ዛፍ በሸፈናቸው ረግረግ ቦታዎች ይገኛል። ሥጋ በል እንስሳት እንደመሆናቸው መጠን አይጦችን፣ እንቁራሪቶችን፣ እባቦችን፣ ሸርጣኖችን፣ ኤሊዎችንና አልፎ አልፎ ደግሞ አጋዘኖችን ይመገባሉ። ትልቁ ተባዕት አዞ በቀን ውስጥ የሚመገበው በአማካይ ከ500 እስከ 700 ግራም የሚመዝን ምግብ ነው። አዞዎች ፀሐይ በመሞቅ ወይም ውኃ ላይ በመንሳፈፍ ስለሚኖሩ እንዲሁም ጥሩ የምግብ አፈጫጭ ሥርዓት ስላላቸው የሚጠቀሙት ጥቂት ኃይል ነው። ትልቁ የጨዋማ ውኃ አዞ አልፎ አልፎ ሰዎች ሳያስቡት ጥቃት ሊሰነዝርባቸው ይችላል። እነዚህ የአዞ ዓይነቶች ከአፍንጫቸውና ከዓይናቸው በስተቀር መላ ሰውነታቸውን በውኃ ውስጥ በማጥለቅ ጭራቸውን ወዲያና ወዲህ እያወዛወዙ ይዋኛሉ፤ ለመራመድ ደግሞ አጫጭር እግሮቻቸውን ይጠቀማሉ። ምግባቸውን ለማደን መዝለል የሚችሉ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ የሚያድኗቸውን እንስሳት እየሮጡ ያሳድዳሉ። እነዚህ አዞዎች እንደ ሌሎቹ ዝርያዎች ሁሉ ጥሩ የማሽተት፣ የማየትና የመስማት ችሎታ አላቸው። ተባዕቱ የጨዋማ ውኃ አዞ የጾታ ግንኙነት በሚያደርግባቸው ወቅቶች ድንበሩን በተጠንቀቅ ይጠብቃል፤ እንስቷም ብትሆን የጣለቻቸውን እንቁላሎች በዓይነ ቁራኛ ትጠብቃለች።
አፍቃሪ እናቶች
እንስቷ አዞ በውኃው አቅራቢያ የበሰበሰ ቅጠላ ቅጠልና ጭቃ በመቆለል ጎጆ ትሠራለች። እስከ 100 የሚደርሱ ሞላላ ቅርጽና ጠንካራ ሽፋን ያላቸውን እንቁላሎች ትጥልና ትሸፍናቸዋለች፤ ጠላትም እንዳይበላባት ትጠብቃለች። ከዚያም በጎጆው ላይ የረበረበችው ቅጠላ ቅጠል እንዲበሰብስ ውኃ ትረጭበታለች፤ ይህም ጎጆው እንቁላሎቹ እንዲፈለፈሉ የሚያስችል በቂ ሙቀት እንዲኖረው ይረዳል።
ከዚህ በኋላ አንድ አስደናቂ ነገር ይፈጸማል። እያንዳንዱ እንቁላል የሚፈለፈልበት የሙቀት መጠን የአዞዎቹን ጾታ ይወስናል። አይገርምም?
የሙቀቱ መጠን ከ28 እስከ 31 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከሆነ በ100 ቀናት ውስጥ እንስቶች ይፈለፈላሉ፤ የሙቀቱ መጠን 32.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከሆነ ደግሞ በ64 ቀናት ውስጥ ተባዕት አዞዎች ይፈለፈላሉ። የሙቀቱ መጠን በ32.5 እና በ33 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መካከል ከሆነ እንቁላሎቹ ከሁለቱ አንዱን ጾታ ይዘው ይፈለፈላሉ። አንደኛው የጎጆ ጎን ከውኃው ዳርቻ ከሆነና ሌላው ወገኑ ከፀሐይ ትይዩ ከሆነ በሞቃታማው ገጽታ ያሉት እንቁላሎች ተባዕት፣ በቀዝቃዛው በኩል ያሉት ደግሞ እንስት ሆነው ይፈለፈላሉ።እናትየው ጫጩቶቿ ሲንጫጩ ስትሰማ እንቁላሎቹ የተሸፈኑበትን ጎጆ ታፈርሰዋለች፤ ከዚያም ጫጩቶቹ ራሳቸው የእንቁላሉን ቅርፊት ለመስበር በሚያስችል ልዩ ጥርሳቸው ተጠቅመው ከሽፋናቸው ካልወጡ አንዳንድ ጊዜ እርሷ ትሰብርላቸዋለች። በትልቁ መንገጭላዋ ቀስ ብላ ታነሳቸውና ከምላሷ ሥር ከትታ ወደ ውኃው ዳርቻ ትወስዳቸዋለች። ከተፈለፈሉ በኋላ ራሳቸውን ችለው መኖር ስለሚችሉ ወዲያውኑ ነፍሳትን፣ እንቁራሪቶችንና ትንንሽ ዓሣዎችን ማደን ይጀምራሉ። ጠንቃቃ የሆኑ እናቶች ግን ረግረግ ቦታ ከልለው ከልጆቻቸው ጋር በርካታ ወራት በማሳለፍ የሚንከባከቧቸው ሲሆን አባትየውም ልጆቹን በመንከባከቡና ከአደጋ በመጠበቁ ሥራ ይካፈላል።
ማገርና ባለ ረጅም አፍንጫው ጌቪየል
ማገርና ጌቪየል የሚባሉት የአዞ ዓይነቶች የሚገኙት ሕንድ ውስጥ ብቻ ነው። ከጨዋማ ውኃ አዞ በእጅጉ የሚያንሰው ማገር 4 ሜትር ገደማ ርዝመት አለው፤ የሚኖረውም በሕንድ በሚገኙ ጨው በሌላቸው ረግረጋማ የውኃ አካላት፣ በሐይቆችና በወንዞች ውስጥ ነው። ትንንሽ እንስሳትን በኃይለኛ መንገጭላው ይይዝና አስጥሞ በመግደል ለመብላት እንዲመቸው እየወዘወዘ ሥጋቸውን ይቆራርጣል።
ማገር አዞዎች ተጓዳኛቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው? ተባዕቱ ማገር ተጓዳኝ በሚፈልግበት ጊዜ ውኃውን በመንገጭላው ይመታል እንዲሁም ያጓራል። በኋላ ደግሞ ጎጆ በመጠበቅ፣ እንቁላሎቹ እንዲፈለፈሉ በመርዳትና ከተፈለፈሉ በኋላ ለጥቂት ጊዜ አብሮ በመቆየት እናቲቱን ያግዛታል።
ብርቅዬው ጌቪየል ከአዞ ዝርያ የሚመደብ ይሁን እንጂ በትክክል አዞ ካለመሆኑም በተጨማሪ ልዩ የሚያደርጉት በርካታ ነገሮች አሉት። ጌቪየል ዋነኛ ምግቡ የሆነውን ዓሣ ለማጥመድ ተስማሚ በሆነው ረጅምና ቀጭን መንገጭላው በቀላሉ ተለይቶ ይታወቃል። ርዝመቱ ከጨዋማ ውኃ አዞ ጋር እኩል ቢሆንም ሰዎችን አያጠቃም። የሰውነቱ ልስላሴና ቅርጽ በኃይል በሚፈሱት እንዲሁም ጥልቀት ባላቸው የሰሜናዊ ሕንድ ወንዞች ውስጥ በፍጥነት ለመጓዝ አስችሎታል። በመራቢያቸው ወቅት በተባዕቱ ጌቪየል አፍ ጫፍ ላይ ድቡልቡል ነገር ይበቅላል። ይህም ከተለመደው የተለየ እንስቲቱን የሚማርክ ከፍተኛ ድምፅ እንዲያወጣ ይረዳዋል።
በተፈጥሮ ገጽታ ላይ ያላቸው ሚና
አዞዎች ለአካባቢያችን ምን ጠቀሜታ ያበረክታሉ? በወንዞችና በሐይቆች ውስጥ እንዲሁም በእነዚህ አካባቢዎች ባለው ደረቅ ምድር ላይ የሚያገኙትን የዓሣዎችና የእንስሳት ጥንብ በመመገብ አካባቢውን ያጸዳሉ። ይህም
ውኃው ንጹሕ እንዲሆን ይረዳል። ልክ እንደ አዳኝ ዒላማ የሚያደርጉት የደከሙ፣ የቆሰሉና የታመሙ ፍጥረታትን ነው። አዞዎች የሰው ልጆች በዋነኝነት ለምግብነት የሚጠቀሙባቸውን ካርፕ እና ቲላፒያ የተባሉትን ዓሣዎች እንደሚመገበው አጥፊው ካትፊሽ ያሉ ዓሣዎችንም ይበላሉ።ከጥፋት ለመዳን እየታገለ እንጂ —የአዞ እንባ እያነባ አይደለም
‘እገሌ የአዞ እንባ አነባ’ ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ? ይህ አባባል እውነተኛ ወይም ልባዊ ያልሆነ ሐዘንንና ልቅሶን ያመለክታል። እርግጥ ነው፣ አዞ በሰውነቱ ውስጥ የሚገኘው የጨው መጠን ሲበዛበት የሚያስወግደው በማንባት ነው። ይሁን እንጂ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለአዞዎች ከልብ ተለቅሶላቸው ሊሆን ይችላል። በዚያ ወቅት በሕንድ ውስጥ በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ አዞዎች ይኸውም ቀደም ሲል ከነበሩት 10 በመቶ የሚያህሉት ብቻ ቀርተው ነበር። ቁጥራቸው ለምን ተመናመነ? ሰዎች መኖሪያቸውን እያስፋፉ ሲሄዱ አዞዎች በግልገሎችና በአቅመ ደካማ የቤት እንስሳት ላይ ጥቃት ያደርሳሉ በሚል ሰበብ ይገድሏቸው ጀመር። ብዙ ሰዎች የአዞ ሥጋና እንቁላል ይወዳሉ። የአዞዎች የዝባድ እጢ ሽቶ ለመቀመም ያገለግል ነበር። ከዚህም በላይ የግድብ ግንባታና የውኃ ብክለት የአዞዎች ቁጥር እንዲመናመን አድርጓል። ይሁን እንጂ አዞዎች ወደ መጥፋቱ እንዲቃረቡ አድርጎ የነበረው ዋነኛ ምክንያት የቆዳቸው ተፈላጊነት ሳይሆን አይቀርም። ከአዞ ቆዳ የሚሠሩ ጫማዎች፣ የእጅ ቦርሳዎች፣ ሻንጣዎች፣ ቀበቶዎችና ሌሎችም እቃዎች ውበት ያላቸውና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ በመሆናቸው በጣም ተፈላጊነት አላቸው። ይህ ችግር ጨርሶ ባይቀረፍም እንኳ አዞዎችን ከጥፋት ለመታደግ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በጣም ስኬታማ እየሆነ ነው!—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።
አዞ የማንፈራበት ጊዜ ይመጣል!
አሁን ጥቂቶቹን የአዞ ዝርያዎች በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተሃል፤ ታዲያ ስለ አዞዎች ምን ተሰማህ? ቀደም ሲል የነበረህ አሉታዊ አመለካከት በአድናቆት ስሜት እንደተተካ ተስፋ እናደርጋለን። በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ እንስሳት አፍቃሪዎች ትልቁ የጨዋማ ውኃ አዞ እንኳን የማይፈራበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ይህ እውን የሚሆነው በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳትን የፈጠረው አምላክ በሰውና በእንስሳት መካከል ሰላም ሲያሰፍን ነው።—ኢሳይያስ 11:8, 9
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ማድራስ የአዞ ርቢ ጣቢያ
በአንዳንድ የእስያ አገሮች ጥቂት ቁጥር ያላቸው አዞዎች ብቻ እንደቀሩ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ በ1972 በማድራስ ከተማ በሚገኘው የእባቦች ፓርክ ውስጥ አዞዎች ጥበቃ ይደረግላቸው ጀመር። ሕንድ ውስጥ፣ በደረታቸው ለሚሳቡ እንስሳት ጥበቃ የሚደረግባቸው ከ30 የሚበልጡ ማዕከሎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውና ትልቁ ማድራስ የአዞ ርቢ ጣቢያ ነው። ይህ ጣቢያ ራምየለስ ህዊተከር በተባሉ የሥነ እንስሳት ተመራማሪ በ1976 ተቋቋመ። ጣቢያው ኮሮማንዴል የተባለ ዛፍ በሚገኝበት ዳርቻ ባለ 3.5 ሄክታር መሬት ላይ የተቋቋመ ሲሆን ለሚያማምሩ ወፎችና ነፍሳት መስህብ የሚሆኑ 150 የዛፍ ዝርያዎችም ይገኙበታል።
ጌቪየልና ሌሎች የአዞ ዝርያዎች ከሌላ ቦታ ተይዘው መጥተው፣ ጥቂቶቹ በረግረጋማ ቦታዎችና በወንዞች ውስጥ ሲለቀቁ የተቀሩት ደግሞ ወደተለያዩ የመራቢያና የምርምር ማዕከሎች ተወሰዱ። ጣቢያው አንዳንድ ጊዜ ቁጥራቸው እስከ 2,500 የሚደርሰውን ትንንሽ አዞዎች መንከባከቢያ ቦታ አለው፤ እነዚህ ትንንሽ አዞዎች የሚኖሩት በኩሬዎች ውስጥ ሲሆን የአገሬው ዓሣ አጥማጆች በየቀኑ እያጠመዱ የሚያመጧቸው ዓሣዎች ተከትፈው ይመገባሉ። ወፎች ዓሣዎቹን ወይም በደረታቸው የሚሳቡ ደካማ የሆኑ ትንንሽ እንስሳትን እንዳይወስዱ ለመከላከል ኩሬው በመረብ ይሸፈናል። ካደጉ በኋላ ወደ ትልልቅ ኩሬዎች ይዘዋወራሉ፤ ሦስት ዓመት ገደማ እስኪሆናቸው ድረስ የሚመገቡት ዓሣ ብቻ ሲሆን በዚህ ወቅት ከ1.25 እስከ 1.5 ሜትር ድረስ ይረዝማሉ። ከዚህ በኋላ ደግሞ ከትልልቅ የሥጋ ማሸጊያ ድርጅቶች የሚመጣላቸውን ትርፍራፊ የበሬ ሥጋ ይመገባሉ። መጀመሪያ ላይ በሕንድ ውስጥ የሚገኙ 3 የአዞ ዝርያዎች ብቻ በጣቢያው ይረቡ ነበር፤ አሁን ግን በጣቢያው 7 ዓይነት ዝርያዎች ይገኛሉ። ለወደፊቱ ደግሞ በዓለም ላይ እንዳሉ የተረጋገጡትን የአዞ ዝርያዎች በሙሉ ደረጃ በደረጃ የማርባት እቅድ ተይዟል። ቆዳቸውንና ሥጋቸውን ለመሸጥ ሲባል በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳትን የማርባቱ ጉዳይ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር። ህዊተከር ለንቁ! ዘጋቢ እንደገለጹት የእነዚህ እንስሳት ሥጋ ጣፋጭ ከመሆኑም በላይ የኮሌስትሮል መጠኑም ዝቅተኛ ነው። ለእነዚህ ትልልቅ ፍጥረታት እየተደረገ ያለው ስኬታማ ጥበቃ እንስሳቱ ጨርሶ እንዳይጠፉ ማድረግ ከማስቻሉም በላይ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ትልቅ የጎብኚዎች መስህብ የሆነው ማድራስ የአዞ ርቢ ጣቢያ ኅብረተሰቡ ለአዞዎች ያለውን የተዛባ አመለካከት በመልካም አስተሳሰብ እንዲተካ የማድረግ ተጨማሪ እቅድ ይዟል።
[ምንጭ]
ራምየለስ ህዊተከር፣ ማድራስ የአዞ ርቢ ጣቢያ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትልቁ የጨዋማ ውኃ አዞ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሴቷ የጨዋማ ውኃ አዞ የተፈለፈሉ ልጆቿን በመንገጭላዋ ታጓጉዛለች
[ምንጭ]
© Adam Britton, http://crocodilian.com
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማገር
[ምንጭ]
© E. Hanumantha Rao/Photo Researchers, Inc.
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለ ረጅም አፍንጫው ጌቪየል