ከመጥፎ ልጆች ጋር የገጠምኩት ምን ነክቶኝ ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከመጥፎ ልጆች ጋር የገጠምኩት ምን ነክቶኝ ነው?
“ከእሱ ጋር መቀራረብ እንዳልነበረብኝ አውቃለሁ፤ ሆኖም ከእሱ መራቅ አልቻልኩም። አንድ ወንድ ከእኔ ጋር መሆን ይፈልጋል የሚል እምነት አልነበረኝም።”—ናንሲ *
“ወደ በረዶ ሸርተቴ መጫወቻው የምሄደው ብቻዬን ነበር። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ እዚያ ካገኘኋቸው ‘ጓደኞቼ’ ጋር አዘውትሬ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራት ጀመርኩ።”—ዳን
ናንሲና ዳን በመጀመሪያ ሁለቱም ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ነበራቸው። ናንሲ ያደገችው ፈሪሀ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን እምነቷን ለሌሎች ማካፈል የጀመረችው ደግሞ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለች ነበር። ዳን ደግሞ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ነበር። ሆኖም ሁለቱም መንፈሳዊነታቸው ከባድ መሰናክል ገጥሞታል። ለምን? ከመጥፎ ሰዎች ጋር በመቀራረባቸው ነው።
እንደሚጎዳህ ብታውቅም እንዲያው ሳታስበው በጣም የተቀራረብከው ሰው ኖሮ ያውቃል? ግለሰቡ ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ያለው የክፍል ጓደኛህ አሊያም በፍቅር የማረከህ ተቃራኒ ፆታ ያለው ሰው ሊሆን ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” ሲል የሚሰጠው ምክር ትዝ ይልህ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ይሁን እንጂ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች ሁሉ መጥፎ ጓደኞች ናቸው? አንዳንድ ደስ የሚሉ፣ ብሎም የሚደነቁ ባሕርያት ቢኖሯቸውስ? በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ባልንጀራችን ቢሆንም በመንፈሳዊ ሁኔታ ምሳሌ የማይሆን ሰው ቢያጋጥመንስ? እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት እንዲህ ወዳሉ ሰዎች የምንሳበው እንዴትና ለምን እንደሆነ እንመልከት።
እንድንቀርባቸው የሚያደርገን ነገር ምንድን ነው?
ሰዎች ሁሉ የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል ስለሆነ ይሖዋን የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ጠባይ ሊኖራቸው እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል። በመሆኑም እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ባይሆኑም እንኳ አንዳንድ ሰዎች የተከበሩ እንዲያውም የሚወደዱ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስለማያውቁ ብቻ ሙሉ በሙሉ ልትርቃቸው ይገባል? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” ብሎ ሲመክረን ክርስቲያናዊ እምነትህን የማይጋሩ ሰዎችን ይጨምራል። (ገላትያ 6:10) ስለዚህ የቅርብ ጓደኞችህን በጥንቃቄ መምረጥ አለብህ ሲባል ከሌሎች እንደምትበልጥ የሚያስመስል ሁኔታ ታሳያለህ ማለት አይደለም። (ምሳሌ 8:13፤ ገላትያ 6:3) እንዲህ ዓይነቱ ጠባይ ክርስቲያናዊ እምነትህ እንዲነቀፍ ሊያደርግ ይችላል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ከመሆንም አልፈው ለመንፈሳዊ ነገሮች እምብዛም ወይም ምንም ፍላጎት ከሌላቸው ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መሥርተዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳን በረዶ ላይ የመንሸራተት ጥሩ ችሎታ አዳብሮ ነበር። በአካባቢያቸው ባለው የበረዶ ሸርተቴ መጫወቻ ዘወትር የሚያገኛቸው ሰዎች ክርስቲያኖች አልነበሩም። የኋላ ኋላም ዳን ከአዳዲስ “ጓደኞቹ” ጋር በመሆን ብልግና መፈጸምና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ጀመረ።
ዳን አኗኗሩ ከክርስትና ጎዳና ጋር እንደማይጣጣም ስለተገነዘበ ማገልገል የተወ ከመሆኑም ሌላ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆመ። አስፈላጊዎቹን ለውጦች ለማድረግ የሚያስችለውን ኃይል አግኝቶ ወደ እውነተኛው አምልኮ እስኪመለስ ድረስ በርካታ ዓመታት አለፉ።ሜላኒ በመንፈሳዊ ደካማ ከሆነች ከአንዲት የእምነት ባልንጀራዋ ጋር መቀራረብ ጀመረች። ሜላኒ “ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋት ስለተነገረኝ እቀርባት ጀመር” በማለት ትናገራለች። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች “ደካሞችን እርዷቸው” የሚል ማበረታቻ ይሰጣል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ሜላኒ ከአዲሷ ጓደኛዋ ጋር ወደ ቡና ቤቶች መሄድ የጀመረች ሲሆን በዚያ ከሚገኙ ሰዎች ጋር መቀራረቧ አሳፋሪ ድርጊት እንድትፈጽም አድርጓታል።
ቤተሰብ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
እንዲህ ዓይነት ቅርርብ እንድትፈጥሩ የሚያደርጋችሁ በቤተሰባችሁ ውስጥ ያለው ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ሚሼል ከሌሎች ጋር የማይቀራረቡና ለሰው ግድ የማይሰጣቸው ወንዶች የሚማርኳት ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ ይገርማት ነበር። እንዲህ ያሉት ልጆች የሚማርኳት የማይቀረብ የሆነውንና ጊዜ ሰጥቶ የማያጫውታትን አባቷን ስለሚያስታውሷት እንደሆነ ተገነዘበች። እንደዚህ ባለው የማይቀረብ ሰው ዘንድ ተቀባይነትና ትኩረት ለማግኘት ከነበራት ብርቱ ፍላጎት የተነሳ ሳታስበው እንደዚህ ያለው ዝምድና ይስባት እንደጀመር ይሰማታል።
በተቃራኒው ደግሞ ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጉት አንድ ወጣት ወላጆቹ ከመጠን በላይ ይቆጣጠሩት እንደነበር ተሰምቶት የሌሎች ሰዎች አኗኗር ምን እንደሚመስል ለማወቅ ጉጉት ያድርበት ይሆናል። በዚህም ሆነ በሌላ ምክንያት አንድ ወጣት ያመለጠው ነገር እንዳለ በማሰብ “የዓለም ወዳጅ” ከሆኑ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ያንን ለማግኘት መሞከሩ መፍትሔ ይሆናል? (ያዕቆብ 4:4) ቢል የደረሰበትን ሁኔታ ተመልከት።
ቢል ከልጅነቱ ጀምሮ እናቱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረችው ቢሆንም ሕይወቱን ለይሖዋ ከወሰነ ነፃነቱ እንደሚገደብበት ስለተሰማው ይህን እርምጃ ሳይወስድ ቀረ። ከእውነተኛው የክርስትና ጎዳና ውጪ ያለው ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ስለፈለገ ከዱርዬዎች ጋር ገጥሞ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እንዲሁም ዓመጽና ወንጀል መፈጸም ጀመረ። በመኪና ያሳድዱት ከነበሩት ፖሊሶች ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሲነዳ በደረሰበት አደጋ ሳቢያ ለብዙ ወራት ራሱን ሳተ። ሐኪሞቹ የመትረፍ ተስፋ እንደሌለው ተሰምቷቸው ነበር። ደግነቱ ቢል እንደገና ራሱን አወቀ። ይሁን እንጂ የማየት ችሎታውን ያጣ ከመሆኑም በላይ የአካል ጉዳተኛ ሆነ። ከደረሰበት መከራ ትምህርት አግኝቶ በአሁኑ ጊዜ የተጠመቀ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል። ይሁን እንጂ ቢል ከመከራ መማር የዕድሜ ልክ መዘዝ እንደሚኖረውም ተገንዝቧል።
ሌሎች ተጽዕኖዎች
አንዳንድ ጊዜ የመዝናኛው ዓለም ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ወጣቶች ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል መጻሕፍት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞችና የሙዚቃ ቪዲዮዎች ዋና ተዋናዩን መጀመሪያ ላይ ጨካኝ ወይም ነፈዝ አስመስለው ያቀርቡትና በኋላ ግን በልቡ አሳቢ እንደሆነ አድርገው መግለጻቸው የተለመደ ነው። ይህ የሚያስተላልፈው ነጥብ ደንዳናና ራስ ወዳድ መስለው የሚታዩ ሰዎች የሰው ችግር የሚገባቸውና አሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ነው። በተጨማሪም እንደዚህ ያለው ሰው ጥሩ ባሕርያቱ ግልጽ ሆነው እንዲታዩ የሚያስፈልገው ጥሩ ጓደኛ ማግኘት፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ተቃራኒ ፆታ ያለው ሰው ማግኘት እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት መልእክት የያዙ ታሪኮች በሕዝቡ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ናቸው። ይሁንና እንዲህ ያለው የፍቅር ቅዠት በገሐዱ ዓለም ምን ያህል ተፈጻሚነት ያለው ይመስልሃል? የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ ባለው ያልሆነ ቅዠት ተታልለው ራስ ወዳድና ኃይለኛ ከሆነ ሰው ጋር ጓደኝነት ከመመሥረታቸውም በላይ በጋብቻ የተሳሰሩ ሲሆን አንድ ቀን “ተለውጦ” ርኅሩኅ ሰው ይሆናል ብለው በከንቱ ሲጠባበቁ ኖረዋል።
አንዳንድ ወጣቶች ከማይሆን ሰው ጋር የሚገጥሙት ለምን እንደሆነ አንድ ተጨማሪ ምክንያት እንመልከት። የሚፈልጋቸው እንደሌለ ስለሚሰማቸው የወደዳቸው መስሎ የቀረባቸውን ማንኛውንም ሰው ይቀበላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ናንሲ መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻ “በጌታ መሆን አለበት” በማለት የሚሰጠውን ሐሳብ ታውቃለች። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ሆኖም ማንም እንደማይወዳት ሁልጊዜ ይሰማት ስለነበር እምነቷን የማይጋራ አንድ የሥራ ባልደረባዋ ፍቅር ሲያሳያት በቀላሉ ተሸነፈችለት። ከእሱ ጋር እየተቀጣጠረች መገናኘት ጀመረችና በአንድ ወቅት የፆታ ብልግና ልትፈጽም ምንም አልቀራትም ነበር።
ከላይ የቀረቡት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አንድ ወጣት ክርስቲያን መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰዎች ጋር የሚገጥምባቸው በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን እንደዚህ ካሉት ሰዎች ጋር የቅርብ ጓደኝነት መመሥረትን ትክክል ለማስመሰል የሚቀርቡት ሰበብ አስባቦችም ማለቂያ ያላቸው አይመስልም። ሆኖም እንደዚህ ያሉት ቅርርቦች አሳዛኝ፣ ብሎም ጎጂ ውጤቶች ማስከተላቸው የማይቀር ነው። ለምን?
ጓደኝነት ያለው ኃይል
ቀስ በቀስ ጓደኞችህን መምሰልህ የማይታበል ሐቅ ነው። በዚህ መንገድ አብረናቸው የምንውላቸው ሰዎች በእኛ ላይ ከፍተኛ የሆነ ኃይልና ተጽዕኖ አላቸው። እንደዚህ ያለው ኃይል ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን እንደሚችል ምሳሌ 13:20 ያሳያል። “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል።” በአንድ መኪና አብረው እንደሚሄዱ ሁለት ሰዎች ሁሉ የቅርብ ጓደኞችም በተመሳሳይ አቅጣጫ ተጉዘው ወደ አንድ ሥፍራ ይደርሳሉ። ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ጓደኛዬ የሚጓዝበት መንገድ እኔ ወደምፈልገው ቦታ ያደርሰኛል? ያወጣኋቸው መንፈሳዊ ግቦች ላይ እንድደርስ ይረዳኛል?’
እርግጥ ነው፣ ራስን በሐቀኝነት መመዘን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ስሜታችን ኃይለኛ ግፊት ያሳድርብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስሜታችን በጓደኛ ምርጫ ረገድ አስተማማኝ መመሪያ ሊሆነን ይችላል? “ልብህ የሚልህን ስማ” የሚለውን ምክር በተደጋጋሚ ሰምተህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ምሳሌ 28:26 [የ1954 ትርጉም] “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው” ይላል። ለምን? ምክንያቱም “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም።” (ኤርምያስ 17:9፤ ዘኍልቁ 15:39) ተንኰለኛ መሆን ማለት ከሐዲ፣ ዋሾ ወይም አታላይ መሆን ማለት ነው። በአታላይነቱና በከዳተኛነቱ የታወቀን ሰው ታምነዋለህ? ምሳሌያዊ ልባችንም አታላይ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የመሠረትነው ጓደኝነት ለእኛ ጥሩ መስሎ ስለታየን ብቻ አይጎዳንም ማለት አይቻልም።
የአምላክ ቃል ከምንም ነገር በላይ አስተማማኝ መመሪያ ነው። ፍጽምና ከሚጎድለው ልብህ በተቃራኒ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተል ለሐዘን አይዳርግህም። አንድ ሰው ጥሩ ጓደኛ ሊሆንህ እንደሚችል ለመወሰን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው? ደግሞስ የዕድሜ ልክ ወዳጅ ማለትም የትዳር ጓደኛ በመምረጥ ረገድ መጥፎ ምርጫ ከማድረግ መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ መልስ ያገኛሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ስሞቹ ተለውጠዋል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መገናኛ ብዙኃን ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉብን ይችላሉ