መጫወቻዎች ጥንትና ዛሬ
መጫወቻዎች ጥንትና ዛሬ
ፊሊፕና * ጓደኞቹ የተቆራረጠ ሲባጎ በመጠምጠም የሠሩት ኳስ ሲነጥር በደስታ ስሜት ይመለከታሉ። ከዚያ በኋላ ኳሳቸውን እየጠለዙ ሞቅ ያለ እግር ኳስ ይጫወቱ ጀመር። ማይክ ደግሞ በእጁ በያዘው የርቀት መቆጣጠሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) አማካኝነት ትንሿን መኪናውን እንደፈለገ ማዘዝ መቻሉ አስደንቆታል። መኪናዋን በቀላሉ ወደፊትና ወደኋላ ማስኬድ ችሏል። አንድሬያ እና ጓደኞቿም እንዲሁ ቤት ውስጥ ሆነው ለአሻንጉሊቶቻቸው ልብስና ጫማ እያደረጉ ሲያድጉ እንዴት እንደሚለብሱ እርስ በርሳቸው ይነጋገራሉ።
እነዚህ ልጆች ምን ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮች አሏቸው? ሁሉም አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው መጫወቻዎች ይዘዋል። አንዳንድ ጊዜ ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንደ አሻንጉሊት ያሉ መጫወቻዎችን የቅርብ ጓደኛቸው ያደርጓቸዋል። እንዲያውም የመጫወቻዎቹ ፎቶ በቤተሰቡ አልበም ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል። መጫወቻዎች ምን ታሪክ አላቸው? ለልጆች በጣም አስፈላጊ የሆኑትስ ለምንድን ነው?
የመጫወቻዎች አመጣጥ
አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ብዙውን ጊዜ ለመጫወቻነት የሚያገለግል መሣሪያ አሻንጉሊት ይባላል። ከጥንት ጀምሮ በበርካታ ባሕሎች ውስጥ አሻንጉሊቶች፣ መጫወቻዎችና የተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች ይገኙ ነበር። እነዚህ መጫወቻዎች ከቀላል እስከ ውስብስብ፣ ልጆች እንደ ፈረስ ከሚጋልቡበት ተራ እንጨት አንስቶ እስከረቀቀና የተወሳሰበ
የሞተር መሣሪያ ድረስ የተለያየ ደረጃ አላቸው።” ስለዚህ ለመዝናናትና ለመጫወት የሚያገለግል ማንኛውም ነገር መጫወቻ ሊባል ይችላል። ሰዎች በተፈጥሯቸው ጊዜ የሚያሳልፉበት ጨዋታ ስለሚፈልጉ ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ መጫወቻዎች ነበሩ ለማለት ይቻላል።ለምሳሌ ያህል በሰው መልክ የተሠሩ አሻንጉሊቶች ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ የሰውነታቸው ክፍሎች እንደ ጥንቷ ባቢሎንና ግብጽ ባሉ አገሮች ውስጥ ተገኝተዋል። አሻንጉሊቶች በጣም ጥንታዊ የሆኑ መጫወቻዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ኳስ ደግሞ ሌላው በጥንት ዘመን የነበረ መጫወቻ ነው። ምንም እንኳን ኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ የት እንደተሠራ ማወቅ ባይቻልም በአንድ የጥንት ግብጻዊ ሕፃን መቃብር ውስጥ እንደ ቦውሊንግ ባለ ጨዋታ ላይ ዒላማ ሆኖ የሚያገለግል በድንጋይ ኳስ የሚመታ የድንጋይ ብርሌ (ፒን) ተገኝቷል።
የድንጋይ በከራ ደግሞ ከሦስት ሺህ ዓመት በፊት በግሪክ የነበረ ሲሆን ጥንታዊ ቻይናውያንም ይሄው መጫወቻ ሳይኖራቸው እንደማይቀር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሮማውያን ሕፃናትም በአሻንጉሊቶችና እርስ በርሳቸው እንዲገጣጠሙ ተደርገው ከዝሆን ጥርስ በተሠሩ ማዕዘናት ይጫወቱ ነበር። ግሪካውያንና ሮማውያን ወንዶች ልጆችም እንዲሁ በትንንሽ ጋሪዎች ይጫወቱ ነበር፤ ይህም በመጓጓዣ መሣሪያዎች መልክ የተሠሩ መጫወቻዎች ባለፉት በርካታ ዓመታት ተወዳጅ እንደነበሩ ያሳያል። በአንድ ሙዚየም ውስጥ ከጥንት ሜክሲካውያን ባሕል እንደተገኘ የሚገመት በተሽከርካሪ ላይ የተጣበቀ ከሸክላ የተሠራ የእንስሳ ቅርጽ ይገኛል። ይህ ቅርጽ እንደመጫወቻ ያገለግል የነበረ ሳይሆን አይቀርም። የሚገርመው ነገር ከዚህ ባሕል ጋር በተያያዘ የተገኘ ሌላ ተሽከርካሪ የለም። በመካከለኛው ዘመን የእንስሳትን ፊኛ በመንፋት የእንቁላል ቅርጽ ያለው ወይም ድቡልቡል ኳስ ይሠራ ነበር። ልክ በዘመናችን እንዳለው የእግር ኳስ እነዚህም ኳሶች በእግር የሚመቱ ወይም ተይዘው የሚሮጡ ናቸው።
ቆየት ብሎ ማለትም በ18ኛው መቶ ዘመን እንግሊዝ ውስጥ የተቆራረጡ ነገሮችን በማገጣጠም ሥዕል መሥራት የሚቻልባቸው ጨዋታዎች (ፐዝልስ) ለማስተማሪያነት ተፈለሰፉ፤ እነዚህ ጨዋታዎች በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጣም ተወዳጅ ሆነው ነበር። በዚያን ጊዜ የጭቃ ቀለም ወይም ከለርም እንዲሁ ተወዳጅ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ ድርጅት ብቻ እንኳን ከአንድ መቶ ቢሊዮን የሚበልጡ የጭቃ ቀለሞችን ወይም ከለሮችን አምርቷል። ከዚህ ማየት እንደምትችለው በጊዜያችን የሚገኙት አንዳንድ መጫወቻዎች የተፈለሰፉት ከብዙ ዘመናት በፊት ሲሆን በሰዎች ሕይወትም ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
መጫወትም ሆነ መጫወቻ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
“መጫወት የእያንዳንዱ ሕፃን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ጨዋታ ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ እንዲሁም አካላቸው፣ አእምሯቸውና ማኅበራዊ ግንኙነት የማድረግ ችሎታቸው እንዲያድግ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። የልጅ ሥራ መጫወት ከሆነ መሣሪያዎቹ ደግሞ መጫወቻዎች ናቸው፤ በመሆኑም ትክክለኛ መጫወቻዎች ልጆች ሥራቸውን ጥሩ አድርገው እንዲያከናውኑ ይረዷቸዋል።” ይህ ተገቢ የሆኑ መጫወቻዎችን ስለ መምረጥ የተሰጠ መንግሥታዊ መመሪያ የእነዚህን ነገሮች አስፈላጊነት ያሳያል።
በእርግጥ መጫወቻዎች የሚወደዱበት ዋነኛው ምክንያት የሚያዝናኑ በመሆናቸው ነው። ቢሆንም ለልጆች እድገት የማይናቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እስቲ ስለሚከተሉት ምሳሌዎች አስብ:- አንድ ልጅ መጫወቻ ጋሪ በሚገፋበት ጊዜ ጡንቻዎቹን የመጠቀም ችሎታው እየዳበረ ይሄዳል። ገመድ በሚዘልበት ጊዜ የማቀናጀት ችሎታውን ያሳድጋል። በአንድ እግሩ ቆሞ ኳስ ሲመታ ወይም ብስክሌት ሲነዳ ሚዛኑን መጠበቅ ይማራል። የዕቃ ዕቃ ቤት ሲሠራ ወይም ሥዕል ሲስል ደግሞ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በጥንቃቄ መቆጣጠርን ይማራል።
ስለ ልጁ የማሰብ ችሎታስ ምን ለማለት ይቻላል? ልጁ በዜማና በግጥም የታጀቡ እንደ ገመድ ዝላይ ወይም አባርሮሽ ያሉ ጨዋታዎችን ሲጫወት የቋንቋ ችሎታው እያደገ ይሄዳል። በተጨማሪም የዕቃ ዕቃ ቤት ሲገነባ፣ የጨዋታ ደንብ ሲከተል፣ የተቆራረጡ ነገሮችን በማገጣጠም ምስል ሲሠራ፣ የሚያነበውን ታሪክ ገጸ ባሕርይ ወክሎ ድራማ ሲሠራ ወይም ደግሞ ሌላ ሰው የሚያስመስለውን ልብስ ለብሶ ሲጫወት አስተሳሰቡና የፈጠራ ችሎታው እየዳበረ ይሄዳል። ከዚህም በላይ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ሲጫወት፣ ሥዕል ሲስል ወይም የእጅ ሥራዎችን ሲሠራ ችሎታውና አስተሳሰቡ ያድጋል።
ልጆች ማኅበራዊ ግንኙነት የማድረግ ችሎታቸው እንዲያድግ ጨዋታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ፤ በቡድን ሆነው ኳስ ሲጫወቱ እንዴት ከሌሎች ጋር መግባባት እንደሚችሉ ይማራሉ። ዶክተር ብሩስ ዳንከን ፔሪ እንዲህ ብለዋል:- “ልጁ በዙሪያው ስላሉት ሰዎች ያለው ግንዛቤ እየጨመረ ስለሚመጣ ይበልጥ ለሌሎች አሳቢና ራስ ወዳድነት የማያጠቃው ይሆናል። ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር በሚጫወቱበት ጊዜ ራሳቸውን መቆጣጠርና የሚያስቆጣ ነገርን በትዕግሥት ማለፍን ጨምሮ እንዴት ከሰው ጋር መኖር እንደሚቻል ይማራሉ።”
ልጆች አዋቂዎች ሲያደርጉ ያዩትን ነገር ለመኮረጅ በመጫወቻዎቻቸው ይጠቀማሉ። ግሪካዊው ፈላስፋ አርስቶትል “አንድን ነገር መኮረጅ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ የሚኖረው የተፈጥሮ ስጦታ ነው” ብሎ ነበር። አዎን፣ ልጆች የሚጫወቱት ጨዋታ አብዛኛውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ እግረ መንገዳቸውን ትምህርት ይቀስሙበታል። አንዲት ልጅ ወደፊት እርሷ ራሷ ስትወልድ እንደምታደርገው አሻንጉሊቷን ለማስተኛት እሽሩሩ ስትላት በዓይነ ኅሊናችን መመልከት እንችላለን። ወይም ከጓደኞቿ ጋር ሆና የዕቃ ዕቃ ምግብ ትሠራ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ወንዶች ልጆች በአፋቸው የሞተር ድምጽ እያሰሙ “መኪናቸውን” ወዲያ ወዲህ በመንዳት ሲያድጉ ሊያጋጥማቸው ለሚችለው ሐቅ ልምምድ ያደርጋሉ። ይሁንና ለልጆችህ አሻንጉሊት በምትገዛበት ወቅት ልታስብባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ለምን?
መጫወቻዎችን በጥንቃቄ መምረጥ
“በአሁኑ ጊዜ መጫወቻዎች የዓመጽንና የሕገ ወጥነትን አስተሳሰብ ያስፋፋሉ” በማለት የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ሁሉም መጫወቻዎች እንዲህ ናቸው ማለት ባይሆንም የጥንቶቹን የመሰሉ መጫወቻዎች ቁጥራቸው ጥቂት እንደሆነና “አስቀያሚ፣ ጡንቻማ . . . ገጽታቸው ላይ ጭካኔ የሚነበብባቸው” አሻንጉሊቶች ግን በብዛት እንደሚገኙ በሜክሲኮ በሚታተም ላ ሆርናዳ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ገልጿል። ይህ ጽሑፍ ፓትሪስያ ኧርሊክ የተባሉ የዛቺሚልኮ ኦቶኖመስ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪና ተመራማሪን ጠቅሶ እንደዘገበው በገበያ ላይ ከሚገኙት መጫወቻዎች መካከል አብዛኞቹ ዓመጽ፣ ጠብ አጫሪነት፣ ኃይለኝነት፣ ጸጥ ለጥ ብሎ መገዛትና ፍርሃት የነገሠበት አገዛዝ ተፈላጊ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።
ዓመጽን ለሚያበረታቱ መጫወቻዎች መጋለጥ “በልጆች የመማር ችሎታና እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማድረጉም ባሻገር ጎጂ የሆኑ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችል” በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ናሽናል አሶሲዬሽን ኦቭ ስኩል ሳይኮሎጂስትስ አረጋግጧል። ዓመጽ የሚያሳዩ የቪዲዮና የኮምፒውተር ጨዋታዎች ቁጡ ወደ መሆንና ወንጀል ወደ መፈጸም ሊመሩ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ ልጆችን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው አዋቂዎች ጥሩ የሆኑ መጫወቻዎችን ስለ መምረጡ ጉዳይ በጥንቃቄ ሊያስቡበት ይገባል።—በገጽ 22 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ዘመናዊው ቴክኖሎጂ መጫወቻዎች በተለያየ ዓይነትና ውስብስብ በሆነ መንገድ እንዲሠሩ አስችሏል። ይሁን እንጂ ቤተሰቦች መጫወቻዎቹን ለመግዛት አቅማቸው ላይፈቅድ ይችላል፤ ወይም ደግሞ ልጆቹ ቶሎ የሚሰለቿቸውና ብዙም ጥቅም የማይሰጧቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በአውስትራሊያ የምትገኝ ሊያን የተባለች ነጠላ የሆነች የአምስት ልጆች እናት እንደሚከተለው ብላለች:- “ትልልቆቹ ወንዶች ልጆቼ ማስታወቂያዎች ተጽዕኖ ስለሚያደርጉባቸው ብዙውን ጊዜ ውድ የሆኑ የኮምፒውተር ጨዋታዎች እንዲገዙላቸው ይጠይቃሉ። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ መጫወትና ልምምድ ማድረግ የሚፈልጉት በርካሽ ዋጋ በሚገዙት የላስቲክ ኳስና የኳስ መምቻ ዘንግ ይመስላል። ቀላል የሆኑ መጫወቻዎች በጣም እንደሚበረክቱና የልጆቼን የአስተሳሰብ አድማስ እጅግ እንደሚያሰፉ ተገንዝቤያለሁ።”
ለምን የራስህን መጫወቻ አትሠራም?
ትንሽ ልጅ ከሆንክና አዲስ የመጡ መጫወቻዎችን መግዛት የማትችል ከሆነ የፈጠራ ችሎታህንና አእምሮህን በመጠቀም መደሰት ትችላለህ። በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ እንደ አንተ ያሉ ሕፃናት መጫወቻዎቻቸውን ራሳቸው ይሠራሉ።
በእነዚህ ገጾች ላይ የሚገኙትን ፎቶዎች ተመልከት። ልጆቹ የተደሰቱ ይመስላሉ ብትባል አትስማማም? አንዳንድ “መኪናዎችን” መሥራት ቀላል አይደለም። አሮጌ ሽቦዎችን መሰብሰብና ትክክለኛ ቅርጽ እንዲይዙ አድርገህ መጠምጠም አለብህ። ጎማ ወይም ፕላስቲክ ክብ አድርገህ በመቁረጥ የመኪና ጎማ መሥራት ትችላለህ። ለስላሳ መጠጥና ወተት ከሚሸጥባቸው መያዣዎች ባቡር ስለ መሥራትስ ምን ትላለህ? ወይም ከተቆራረጠ እንጨት የጭነት መኪና ስለ መሥራት ምን ይሰማሃል? ይህ አፍሪካዊ ልጅ ቤት ውስጥ እንደሠራው ትንሽ ዶቅዶቄ አንዳንድ ጊዜ መጫወቻዎች ላይ ተቀምጦ መንዳት ይቻላል። እነዚህ ልጆች የሚጫወቱባቸው ነገሮች የግድ በውድ ዋጋ መገዛት እንደሌለባቸው ተገንዝበዋል። መጫወቻዎቹን መሥራት አንድ ራሱን የቻለ ጨዋታ ነው። አንተስ ለምን ለመሥራት አትሞክርም?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ጥሩ መጫወቻ የሚባለው . . .
● ከልጁ ዕድሜ፣ ችሎታና አቅም ጋር የሚመጣጠንና ለአደጋ የማያጋልጠው
● በጥሩ ሁኔታ የተሠራና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ (ልጆች በቀላሉ እንዳይገነጣጥሉት)
● የልጆችን ትኩረት የሚስብና የሚያስደስታቸው
● የልጆችን የፈጠራ ችሎታ የሚያሳድግና የአስተሳሰብ አድማስ የሚያሰፋ
● ዋጋው ከአቅም በላይ ያልሆነ
● መርዝነት የሌለው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በመጫወቻዎች ምክንያት አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከል . . .
● ለትልልቅ ልጆች የተዘጋጁ መጫወቻዎችን በዕድሜ ትንንሽ የሆኑ ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጥ
● መጫወቻው ላይ ያለውን ማስጠንቀቂያና መመሪያ በጥንቃቄ አንብብ፤ ከተቻለ ከልጅህ ጋር ማንበቡ ይመረጣል
● ለልጅህና አብረውት ለሚጫወቱ ጓደኞቹ መጫወቻዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻልና በትክክል ማስቀመጥ እንዳለባቸው አስተምራቸው
● ጎጂ እስከሚባለው ደረጃ የሚደርስ ድምፅ የሚያሰሙ መጫወቻዎችን አስወግድ
● በየጊዜው መጫወቻዎቹን ፈትሻቸው። የተበላሹ መጫወቻዎች መጠገን አሊያም ወዲያውኑ መጣል አለባቸው
● ኢላማ መምቻዎች፣ ሹል ጫፍ ያላቸው፣ ኤሌክትሮኒክስ የሆኑና እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ መጫወቻዎችን መጠቀም ያለባቸው ትልልቅ ልጆች ሲሆኑ አዋቂዎችም አብረዋቸው ሊሆኑ ይገባል
● ሊዋጡ ከሚችሉ ትንንሽ አካላት ተገጣጥመው የተሠሩ መጫወቻዎች ለትንንሽ ልጆች መሰጠት የለባቸውም
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተሽከርካሪ ላይ የተቀመጡ አንበሳና ጃርት፣ በሁለተኛው ሺህ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ኢራን
[ምንጭ]
አንበሳና ጃርት:- Erich Lessing/Art Resource, NY
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሸክላ አሻንጉሊት፣ በ600 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ፣ ጣሊያን
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስፒኒንግ ቶፕ (እሽክርክሪት)፣ በ480 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ፣ ጥንታዊ ግሪክ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከበቆሎ ልጣጭ የተሠራች አሻንጉሊት፣ አሜሪካ በቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ወቅት
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጭቃ ቀለም ወይም ከለር፣ በ1900 መጀመሪያ ላይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል2]
ቤታቸው የተሠሩ መጫወቻዎችን የያዙ ልጆች
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የሸክላ አሻንጉሊት:- Erich Lessing/Art Resource, NY; እሽክርክሪት:- Réunion des Musées Nationaux/ Art Resource, NY; ከበቆሎ ልጣጭ የተሠራች አሻንጉሊት:- Art Resource, NY