በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አምስት ቁልፍ ሐሳቦች

ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አምስት ቁልፍ ሐሳቦች

ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አምስት ቁልፍ ሐሳቦች

ጥሩ ሥራ የሚያገኘው ማን ነው? ሁልጊዜ የሚሳካለት ከፍተኛ ብቃት ያለው ሰው ብቻ ነው? “አይደለም። ብዙውን ጊዜ ሥራ የሚያገኘው፣ ሥራ በመፈለግ ረገድ የተዋጣለት ሰው ነው” በማለት ብራየን የተባሉ የቅጥር አማካሪ ተናግረዋል። አንተስ ሥራ በመፈለግ ረገድ የተዋጣልህ እንድትሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ አምስት ሐሳቦችን እንመልከት።

የተደራጀህ ሁን

ከጥሩ ሥራህ ተፈናቅለህ ከሆነ ወይም ደግሞ ለተወሰኑ ጊዜያት ያለ ሥራ ተቀምጠህ ከነበረ በቀላሉ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። በጀርመን የምትገኝ ካታሪና የተባለች ልብስ ሰፊ እንዲህ ብላለች:- “ከሥራ ስባረር ሌላ ሥራ እንደማገኝ ሙሉ እምነት ነበረኝ። ሆኖም ወራት እያለፉ ቢሄዱም ሥራ ማግኘት አልቻልኩም፤ ይህም ጭንቀት ለቀቀብኝ። ውሎ አድሮ ጉዳዩን አንስቼ ከጓደኞቼ ጋር መነጋገር ይከብደኝ ጀመር።”

የተስፋ መቁረጥን ስሜት መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? ጌት ኤ ጆብ ኢን 30 ዴይስ ኦር ለስ የተባለ መጽሐፍ “ዕለቱን ምን ስትሠራ እንደምትውል ለማወቅ የራስህን ‘የሥራ’ ፕሮግራም ማውጣትህ በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት ይመክራል። የመጽሐፉ አዘጋጆች “የዕለት የዕለት ግቦችን አውጣና ያከናወንከውን ነገር በጽሑፍ አስፍር” በማለት ሐሳብ ያቀርባሉ። በተጨማሪም “በእያንዳንዱ ቀን የዕለቱን እንቅስቃሴህን ከመጀመርህ በፊት ልክ ሥራ ስትሄድ እንደምትለብሰው ዓይነት አለባበስ መልበስ አለብህ” ይላሉ። ለምን? “ተገቢ አለባበስ መልበስህ ስልክ በምታወራበት ጊዜም እንኳን በራስ የመተማመን ስሜትህ እንዲጨምር ያደርጋል።”

አዎን፣ ሥራ ሳታገኝ ምንም ያህል ጊዜ ቢያልፍ ሥራ መፈለጉን ሥራዬ ብለህ ልትይዘው ይገባል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካታሪና የተጠቀመችው በዚህ ዘዴ ነው። እንዲህ ትላለች:- “የቀጣሪዎችን አድራሻና ስልክ ቁጥር ከሥራና ሠራተኛ አገናኝ ቢሮ ወሰድኩ። እንዲሁም በጋዜጣ ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን እየተከታተልኩ አመለክት ነበር። የስልክ ማውጫውን ጥሩ አድርጌ ተመለከትኩና ማስታወቂያ ያላወጡ ሆኖም ሠራተኛ ሊፈልጉ እንደሚችሉ የገመትኳቸውን ድርጅቶች በዝርዝር ጻፍኩ፤ ከዚያም አነጋገርኳቸው። እንዲሁም ሲቪ (ካሪኩለም ቪቴ) አዘጋጅቼ ወደ እነዚህ ድርጅቶች ላክሁ።” ካታሪና እንዲህ በተደራጀ መንገድ ፍለጋ ካካሄደች በኋላ የሚስማማትን ሥራ አገኘች።

ማስታወቂያ ያልወጣባቸው ክፍት የሥራ ቦታዎች ይኖሩ እንደሆን አጠያይቅ

በጣም ትልቅ መረብ ያለው ዓሣ አጥማጅ ዓሣ የመያዝ አጋጣሚው ሰፊ ነው። አንተም በተመሳሳይ “መረብህን” እንዴት ማስፋት እንደምትችል ማወቅህ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህን ከፍ ያደርገዋል። ሥራ ለማግኘት የምትጥረው በጋዜጣ ወይም በኢንተርኔት የሚወጡ ማስታወቂያዎችን በመከታተል ብቻ ከሆነ መረብህ ትንሽ ስለሚሆን በርካታ የሥራ አጋጣሚዎች ያመልጡሃል። በጣም ብዙ ክፍት የሥራ ቦታዎች በማስታወቂያ አይወጡም። ስለነዚህ ክፍት የሥራ ቦታዎች ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ማስታወቂያዎችን ተከታትለህ ከማመልከት በተጨማሪ ካታሪና እንዳደረገችው ለአንተ የሚሆን ሥራ ይኖራቸው ይሆናል የምትላቸውን ድርጅቶች በስልክም ሆነ በአካል ለማነጋገር በየሳምንቱ ጊዜ መመደብ አለብህ። ማስታወቂያ እስኪያወጡ ድረስ አትጠብቅ። የድርጅቱ አስተዳዳሪ ሥራ እንደሌለ ቢነግርህም ሌላ የሚያውቀው ቦታ ካለ እንዲጠቁምህና ማንን ማናገር እንዳለብህ እንዲነግርህ ጠይቀው። የጠቆመህ ቦታ ካለ ወደ ድርጅቱ ማን እንደመራህ በመጥቀስ ቀጠሮ ያዝ።

ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ቶኒ በዚህ መንገድ ሥራ አግኝቷል። “ድርጅቶቹ ማስታወቂያ ባያወጡም እንኳን አነጋገርኳቸው። አንዱ ድርጅት ለጊዜው ክፍት የሥራ ቦታ እንደሌለውና በሦስት ወር ውስጥ በድጋሚ እንድሞክር ነገረኝ። እንደተባልኩት አደረግኩና ሥራ አገኘሁ” በማለት ተናግሯል።

ፕሪምሮዝ የተባለች በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ነጠላ እናትም ተመሳሳይ ነገር አድርጋ ነበር። እንዲህ ትላለች:- “የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ሥልጠና እየወሰድኩ ሳለሁ ከመንገዱ ባሻገር አዲስ ሕንጻ እየተገነባ መሆኑን አስተዋልኩ፤ ሕንጻው ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚደረግበት ቤት እንደሚሆንም አወቅኩ። የድርጅቱ ተቆጣጣሪ ከሆነው ሰው ጋር ቀጠሮ ለመያዝ በተደጋጋሚ ሞከርኩ። በመጨረሻም በወቅቱ ክፍት የሥራ ቦታ እንደሌለ ነገረኝ። ይሁንና ያለ ደመወዝም ቢሆን መሥራት የምችለው ነገር እንዳለ ለማረጋገጥ አዘውትሬ መሄዴን አላቆምኩም። ከጊዜ በኋላ ግን ጊዜያዊ ሠራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩ። የተሰጠኝን ሥራ ሁሉ በትጋት እሠራ ነበር። በመሆኑም ችሎታዬን አሻሻልኩና በድርጅቱ ውስጥ ቋሚ ሠራተኛ ሆንኩ።”

ጓደኞችህ፣ ዘመዶችህና የምታውቃቸው ሌሎች ሰዎች ማስታወቂያ ላይ ያልወጡ ክፍት የሥራ ቦታዎችን ያውቁ እንደሆነ መጠየቅም ሌላው አማራጭ ነው። በሰዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ ያለው ያኮቡስ የተባለ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ሰው በዚህ መንገድ ሥራ አግኝቷል። እንዲህ ብሏል:- “እሠራበት የነበረው ድርጅት በተዘጋበት ጊዜ ለጓደኞቼና ለዘመዶቼ ሥራ እየፈለግሁ እንደሆነ ነገርኳቸው። አንድ ቀን ጓደኛዬ ሱፐርማርኬት ወረፋ እየጠበቀ ሳለ ሰዎች የሚያወሩት ነገር ጆሮው ጥልቅ አለ። አንዷ ሴት ለሌላዋ ሥራ የሚፈልግ ሰው ታውቅ እንደሆነ ትጠይቃታለች። ጓደኛዬ ጣልቃ ይገባና ለሴትየዋ ስለ እኔ ይነግራታል። ከዚያም ቀጠሮ ያዙና ሥራ ለመቀጠር በቃሁ።”

እንደ ሁኔታው ለውጥ አድርግ

ሥራ የማግኘት አጋጣሚህ ከፍ እንዲል እንደ ሁኔታው ለውጥ ማድረግ መቻል አለብህ። ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሃይሜ “ሙሉ ለሙሉ የምትፈልጉትን ዓይነት ሥራ ማግኘት የማይታሰብ ነገር ነው። የምትፈልጉት ዓይነት ባይሆንም እንኳን በማንኛውም ሥራ መርካትን መማር አለባችሁ” ብላለች።

እንደ ሁኔታው ለውጥ ማድረግ ሲባል ለአንዳንድ ሥራዎች ያለህን ጥላቻ ማስወገድ ማለት ሊሆን ይችላል። በሜክሲኮ የምትኖረውን የኤሪካን ሁኔታ ተመልከት። የዋና ጸሐፊነት ሙያ የነበራት ቢሆንም በመጀመሪያ ላይ የምትፈልገውን ሥራ ማግኘት አልቻለችም ነበር። “ማንኛውንም ተስማሚ ሥራ መቀበልን ተምሬያለሁ። ለጥቂት ጊዜ በሻጭነት ሠርቻለሁ። እንዲሁም መንገድ ላይ ታኮ [የምግብ ዓይነት ነው] እሸጥና የሰው ቤት አጸዳ ነበር። ከጊዜ በኋላ በሠለጠንኩበት ሙያ ሥራ ማግኘት ቻልኩ” በማለት ተናግራለች።

ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሜሪም እንዲሁ ከጸሐፊነት ሥራዋ በተፈናቀለች ጊዜ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንደሚገባት ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች:- “የቀድሞውን ዓይነት ሥራ ማግኘት አለብኝ ብዬ ድርቅ አላልኩም። ማንኛውንም ሥራ፣ ሌሎች ዝቅተኛ አድርገው የሚመለከቱትንም ጭምር ለማግኘት የሚያስችሉኝን አጋጣሚዎች ሁሉ እከታተል ነበር። በመሆኑም ሁለቱን ልጆቼን ለማሳደግ የሚረዳኝን ሥራ አገኘሁ።”

ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ሲቪ አዘጋጅ

አስተዳደር ነክ ሥራ ለመቀጠር የሚያመለክቱ ሰዎች የተማሩትን ትምህርትና የሥራ ልምዳቸውን የሚገልጽ ሲቪ አዘጋጅቶ ማሰራጨት ያስፈልጋቸዋል። የሆነ ሆኖ የምትፈልገው ሥራ ምንም ዓይነት ቢሆን በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ ሲቪ ላቅ ያለ ጠቀሜታ አለው። ናይጀል የተባሉ በአውስትራሊያ የሚገኙ የቅጥር አማካሪ “ሲቪ ቀጣሪዎች ስለማንነትህ እንዲያውቁ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ምን እንዳከናወንክና ለምን ዓይነት ሥራ እንደምታስፈልጋቸው ያስገነዝባቸዋል” ብለዋል።

ሲቪ ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ሙሉ ስምህን፣ አድራሻህን፣ ስልክ ቁጥርህን፣ የኢ-ሜይል አድራሻህንና የተወለድክበትን ቀን ጻፍ። ምን እንደምትፈልግ ግለጽ። የተማርከውን ትምህርት አስፍር፤ እንዲሁም ከምትፈልገው ሥራ ጋር በተያያዘ ያገኘኸው ሥልጠናና ያዳበርከው ችሎታ ካለ በደንብ አድርገህ ጻፍ። ቀደም ሲል ያገኘኸውን የሥራ ልምድ በዝርዝር ዘግብ። ያደረግኸውን ብቻ ሳይሆን የደረስክባቸውን አንዳንድ ግቦችና ለቀድሞ ቀጣሪዎችህ ምን ጥቅም እንዳስገኘህላቸው አስፍር። በተጨማሪም አሁን ለምትፈልገው ሥራ ብቁ ያደረጉህን የቀድሞ ሥራህ ገጽታዎች ጎላ አድርገህ ጥቀስ። ባሕርይህን፣ ፍላጎቶችህንና በትርፍ ጊዜ ማድረግ የምትወደውን ነገር የሚመለከቱ የግል ጉዳዮችን ጨምረህ ጻፍ። ሁሉም ድርጅቶች አንድ ዓይነት ነገር ስለማይፈልጉ ከእያንዳንዱ ማመልከቻህ ጋር የምታያይዘውን ሲቪ የተለያየ ማድረግ ሊኖርብህ ይችላል።

አዲስ ሥራ ፈላጊ ከሆንክ ሲቪ ማዘጋጀት ይኖርብሃል? አዎን! እንደ ሥራ ልምድ ሊቆጠሩ የሚችሉ ያከናወንካቸው በርካታ ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በትርፍ ጊዜ የእንጨት ሥራ የመሥራት አሊያም ደግሞ ያረጁ መኪናዎችን የመጠገን ልማድ አለህ? እነዚህን መጻፍ ትችላለህ። ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ ታውቃለህ? የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ሆነህ ያከናወንከውንና ከግብ ያደረስከውን ሥራ አስፍር።—“የሥራ ልምድ ለሌላቸው የሚሆን የናሙና ሲቪ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ቀጣሪው ቃለ መጠይቅ ሊያደርግልህ ካልቻለ ስምህን፣ አድራሻህን፣ ስልክ ቁጥርህን፣ የኢ-ሜይል አድራሻህን እንዲሁም ሙያህንና ያገኘኸውን የሥራ ውጤት በአጭሩ የሚገልጽ አሥር ሴንቲ ሜትር በአሥራ አምስት ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ካርድ ትተህ ሂድ። አስፈላጊ መስሎ ከታየህ በካርዱ ጀርባ ላይ ፎቶህን ማድረግ ትችላለህ። ይህንን ካርድ ሥራ ለሚያፈላልጉልህ ሰዎች ሁሉ አከፋፍልና የምትፈልገውን ዓይነት ሥራ ለሚያሠራ ለማንኛውም ሰው እንዲሰጡልህ ጠይቃቸው። ይህን ካርድህን ያገኘ ሠራተኛ የሚፈልግ ሰው ቃለ መጠይቅ ሊያደርግልህና ምናልባት ሊቀጥርህ ይችላል!

ሥራ በምትፈልግበት ጊዜ ሲቪ ማዘጋጀትህ በሁኔታህ ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ ያደርጋል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ናይጀል “ሲቪ ማዘጋጀትህ የተደራጀ ሐሳብና ግብ እንዲኖርህ ይረዳሃል። እንዲሁም በቃለ መጠይቅ ወቅት ሊቀርቡልህ ለሚችሉ ጥያቄዎች ከወዲሁ በማዘጋጀት ልበ ሙሉ እንድትሆን ያደርግሃል።”—በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ለቃለ መጠይቅ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ

ለቃለ መጠይቅ መዘጋጀት ምንን ይጨምራል? ምናልባት መቀጠር ስለምትፈልግበት ድርጅት ለማወቅ ምርምር ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። ስለ ድርጅቱ ይበልጥ ባወቅህ መጠን በቃለ መጠይቁ ወቅት ስኬታማ የመሆንህ አጋጣሚ ያንኑ ያህል ከፍ ይላል። በተጨማሪም ስለ ድርጅቱ በጥልቀት ማወቅህ ድርጅቱ በእርግጥ አንተ የምትፈልገው ዓይነት ሥራ እንዳለው ወይም እዚያ መሥሪያ ቤት መሥራት እንደሚገባህ ለማወቅ ያስችልሃል።

ቀጥሎ ደግሞ በቃለ መጠይቁ ወቅት ምን እንደምትለብስ አስብ። የምትፈልገው ሥራ የጉልበት ሥራን የሚጨምር ከሆነ ከዚህ ጋር የሚስማማ ሥርዓታማና ንጹሕ አለባበስ ይኑርህ። ሥርዓታማ አለባበስና አጋጌጥ ያለህ መሆኑ ቀጣሪው ለራስህ አክብሮት እንዳለህና በዚህም የተነሳ ሥራህን በአክብሮት ልትይዝ እንደምትችል እንዲገነዘብ ያደርገዋል። እየፈለግህ ያለኸው የቢሮ ሥራ ከሆነ ደግሞ በአካባቢህ ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ተስማሚ እንደሆነ የሚታሰበውን ሥርዓታማ አለባበስ ልበስ። ናይጀል እንዲህ ብለዋል:- “ቃለ መጠይቅ ከሚደረግልህ ከረጅም ጊዜ አስቀድሞ ልብሶችህን ምረጥ፤ እንዲህ ማድረግህ እንዳትጣደፍና ለቃለ መጠይቅ ከመቅረብህ በፊት የሚሰማህ ውጥረት እንዳይባባስ ይረዳሃል።”

ናይጀል ቃለ መጠይቅ ከምታደርግበት ሰዓት 15 ደቂቃ ቀድመህ በቦታው እንድትገኝ ይመክራሉ። እርግጥ በጣም ቀደም ብሎ መገኘቱ ጥሩ አይደለም። ዘግይቶ መድረሱ ደግሞ የከፋ ነው። ቃለ መጠይቅ የሚደረግባቸው የመጀመሪያዎቹ ሦስት ሴኮንዶች ወሳኝ እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህ ሰው በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ፣ ለአንተ በሚኖረው አመለካከት ላይ ከባድ ተጽዕኖ የሚያደርጉትን አቋምህንና ጸባይህን ይገመግማል። ዘግይተህ መድረስህ በከፍተኛ ሁኔታ አሉታዊ ግምት እንዲሰጥህ ምክንያት ይሆናል። መጀመሪያ የተፈጠረውን አመለካከት ማስተካከል የሚቻልበት ሁለተኛ አጋጣሚ እንደሌለ አስታውስ።

ሌላው ማስታወስ ያለብህ ነገር ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህ ሰው ጠላትህ አለመሆኑን ነው። እርሱም ቢሆን ሥራውን ያገኘው በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ አልፎ ሊሆን ስለሚችል ምን እንደሚሰማህ ያውቃል። እንዲያውም ቃለ መጠይቅ እንዴት ማድረግ እንደሚችል ያገኘው ሥልጠና ጥቂት ሊሆን ወይም ደግሞ ጨርሶ ሠልጥኖ ላያውቅ ስለሚችል ይደናገጥ ይሆናል። ከዚህም በላይ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህ ራሱ ቀጣሪው ከሆነ ለሥራው ብቃት ያለው ሰው ካልቀጠረ ድርጅቱ ሊከስርበት ይችላል።

ጅምሩ እንዲያምር በአካባቢህ የተለመደ ከሆነ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህን ሰው ፈገግ በልና ጠበቅ አድርገህ በመጨበጥ ሰላምታ ስጠው። በቃለ መጠይቁ ወቅት ቀጣሪው ምን እንደሚጠብቅብህና ምን ዓይነት ችሎታ እንዲኖርህ እንደሚፈልግ በትኩረት ተከታተል። ናይጀል መወገድ ያለባቸውን ነገሮች በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “አትቁነጥነጥ ወይም አካሄድህ፣ አቋቋምህና አቀማመጥህ ከሥርዓት ውጪ አይሁን፤ ጥሩ አቋም መያዝህ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዳለህ ያሳያል። በጣም ዘና አትበል ወይም ከልክ በላይ አታውራ፤ እንዲሁም ጸያፍ አነጋገር ጨርሶ አትጠቀም። በተጨማሪም ስለ ቀድሞ አሠሪህና የሥራ ባልደረቦችህ አሉታዊ ነገር አትናገር፤ ስለ እነርሱ አሉታዊ ነገር ካወራህ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህ ሰው ይህንንም ሥራ በተመለከተ አፍራሽ አመለካከት እንደሚኖርህ ሊሰማው ይችላል።”

ባለሙያዎቹ በቃለ መጠይቅ ወቅት መደረግና መባል ስላለባቸው ነገሮች የሚከተለውን ሐሳብ ያቀርባሉ:- ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልህን ሰው ዓይን ዓይኑን እይ፤ በምትናገርበት ጊዜ የራስህ የሆነ አካላዊ መግለጫ ተጠቀም፤ በግልጽ ተናገር። ጥያቄ ስትጠየቅ እጥር ምጥን ያለና እውነተኛ መልስ ስጥ፤ ስለ ድርጅቱና ስለ ወደፊቱ ሥራህ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች አንሳ። ቃለ መጠይቁ ካበቃ በኋላ ሥራውን የምትፈልገው ከሆነ ይህንኑ በድጋሚ ተናገር። እንዲህ ማድረግህ ጉጉት እንዳለህ የሚያሳይ ነው።

ከላይ የተዘረዘሩትን ሐሳቦች ተግባራዊ ካደረግክ በቅርቡ ሥራ ታገኝ ይሆናል። ሥራ ካገኘህ በኋላ ከሥራው የመፈናቀል አጋጣሚህ በጣም እንዲቀንስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሥራ ልምድ ለሌላቸው የሚሆን የናሙና ሲቪ

ስም:-

የትውልድ ዘመን:-

አድራሻ:-

ስልክ ቁጥርና የኢ-ሜይል አድራሻ:-

ዓላማ:- በፋብሪካው ውስጥ ለጀማሪ የሚሆን ሥራ እፈልጋለሁ።

የትምህርት ደረጃ:- በምኖርበት ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በ2004 አጠናቅቄአለሁ።

ሥልጠናዎች:- ቋንቋ፣ ሒሳብ፣ ኮምፒውተርና የእንጨት ሥራ ተምሬያለሁ።

ሙያና ችሎታ:- ጥሩ የእጅ ሙያ አለኝ። የቤተሰቤን መኪና በአስፈላጊው ጊዜ እጠግናለሁ። ቤቴ በሚገኝ የእንጨት ሥራ ክፍል ውስጥ የእንጨት ወንበሮችንና ጠረጴዛ ሠርቻለሁ። የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን ስሠራ በሒሳብ ችሎታዬ እጠቀማለሁ። የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ሆኜ በተካፈልኩበት አንድ የሕንጻ ግንባታ ላይ ጣራ ሠርቻለሁ። የተለያዩ የኮምፒውተር ዓይነቶችን አጠቃቀም ከማወቄም በላይ አዳዲስ ፕሮግራሞችን መማር ያስደስተኛል።

የግል መረጃዎች:- እምነት የሚጣልብኝ ነኝ፤ በመጨረሻው የትምህርት ዓመት ከትምህርት ቤት የቀረሁት ሁለት ቀን ብቻ ነው። ሐቀኛ ነኝ፤ ገንዘብ ያለበትን የወደቀ ቦርሳ አግኝቼ ለባለቤቱ መልሻለሁ። ተግባቢ ነኝ፤ ሕዝብ በፈቃደኝነት በሚገነባቸው የግንባታ ሥራዎች ላይ ዘወትር እካፈላለሁ፤ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል። የቅርጫት ኳስ መጫወት ደስ ይለኛል። በትርፍ ጊዜዬ መኪና መጠገንና የእንጨት ሥራ መሥራት እወዳለሁ።

ምሥክር:- ከተጠየቅኩኝ ማቅረብ እችላለሁ። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.42 በደንብ የሚያውቁህ አስተማሪዎች ወይም ንግድ ያላቸው የቤተሰብህ ወዳጆች ስለአንተ ምሥክርነት እንዲሰጡ ልታደርግ ትችላለህ። ቀጣሪው የእነዚህን ሰዎች ስም እንድትሰጠው ከጠየቀህ ምናልባት ሊቀጥርህ ፈልጎ ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ። ምሥክር የምታደርጋቸው ሰዎች ፈቃደኛ መሆናቸውን መጠየቅ እንዳለብህ አትዘንጋ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቃለ መጠይቅ ወቅት ሊቀርቡልህ የሚችሉ ጥያቄዎች

❑ ይህን ሥራ የፈለግከው ለምንድን ነው?

❑ በዚህ ድርጅት ውስጥ መሥራት የፈለግከው ለምንድን ነው?

❑ ስለ ሥራው/ድርጅቱ/ኢንዱስትሪው ምን የምታውቀው ነገር አለ?

❑ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ሥራ ሠርተህ ታውቃለህ?

❑ አጠቃቀማቸውን የምታውቃቸው ማሽኖች አሉ?

❑ በዚህ ዓይነቱ ሥራ ልምድ አለህ?

❑ ለሥራው ሊጠቅም የሚችል ምን ልዩ ችሎታ አለህ?

❑ እስቲ ስለ ራስህ ንገረኝ።

❑ “እኔን ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ” የምትላቸውን አምስት ቃላት ንገረኝ።

❑ የሥራ ጫና ቢኖር የመሥራት ብቃት አለህ?

❑ የበፊቱን ሥራህን ለምን ተውክ?

❑ ለረጅም ጊዜ ሥራ ሳትሠራ የቆየኸው ለምንድን ነው?

❑ የቀድሞ አሠሪህ ለአንተ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

❑ ከበፊቱ ሥራህ ምን ያህል ቀን ቀርተሃል?

❑ ለወደፊቱ ምን ዕቅድ አለህ?

❑ መቼ ሥራ መጀመር ትችላለህ?

❑ ምን ልዩ ተሰጥኦዎች አሉህ?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የቤት ውስጥ ሥራ መፍጠር

• በራስ ቤት ውስጥ የሌሎች ሰዎችን ልጆች መጠበቅ

• የጓሮ አትክልትና አበባ መሸጥ

• ልብስ መስፋት፣ ማስተካከልና መጠገን

• የተወሰኑ ሥራዎችን ሠርቶ ለፋብሪካዎች ማቅረብ

• እንጀራና ዳቦ ጋግሮ ወይም ምግብ አዘጋጅቶ መሸጥ

• ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ ወይም ቅመማ ቅመም እያዘጋጁ ማቅረብ

• ያልጋ ልብስ፣ ሹራብ፣ ጥልፍ፣ የሸክላ ሥራ ወይም ሌሎች የእጅ ሥራዎች መሥራት፣ ጥጥ መፍተል

• ሶፋና ወንበር ማደስ

• የሒሳብ መዝገብ ያዥነት፣ ታይፕ መጻፍ፣ የቤት ውስጥ የኮምፒውተር አገልግሎት መስጠት

• ፀጉር ማስተካከል፣ ሽሩባ መሥራት

• ቤት አከራይቶ ተከራዩን መቀለብ

• መኪና ማጠብና መወልወል (ደንበኛው ወደ ቤት እንዲያመጣ በማድረግ)

• ውሻ ማጠብ፣ ማንሸራሸር

• የበር ቁልፍ መሥራትና መጠገን (ቤት ውስጥ ወርክሾፕ ካለ)

• አርቲፊሻል አበባ ሠርቶ መሸጥ

• ልብስ ማጠብና መተኮስ

• ዶሮ ማርባት፣ ላም እያረቡ ወተት መሸጥ

• የሚቻል ከሆነ እነዚህን ሥራዎች እንደምትሠራ አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ ማስታወቂያ ጽፈህ ለጥፍ።

ከቤት ውጭ ሥራ መፍጠር

• ቤት መጠበቅ (ባለቤቶቹ በማይኖሩበት ጊዜ)

• ጽዳት:- ግንባታቸው የተጠናቀቀና የተለቀቁ ሱቆችን፣ መኖሪያ ቤቶችንና መሥሪያ ቤቶችን ማጽዳት እንዲሁም መስኮቶችን መወልወል (የመሥሪያ ቤት፣ የቤት)

• ልዩ ልዩ የጥገና ሥራ

• ረዳት ሆኖ መሥራት:- የአናጺ፣ የግንበኛ፣ የቀለም ቀቢ፣ ወዘተ . . .

• እርሻ:- አጨዳ፣ ቡና መልቀምና እህል ማበጠር

• ጥበቃ:- ቤት፣ ንብረት መጠበቅ

• ደላላነት:- ቤት፣ ንብረት ማሻሻጥ

• መላላክ

• ጋዜጣና መጽሔት ማዞር እንዲሁም ማስታወቂያዎችን ማደል (አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች)፣ ለደንበኞች ጋዜጣ ማድረስ

• ዕቃ መሸከም

• አትክልተኝነት:- ቁፋሮ፣ ሣር ማጨድ፣ ጥድ መከርከምና ዛፍ መቁረጥ

• ሾፌርነት

• እየተዘዋወሩ ፎቶግራፍ ማንሳት (ግለሰቦችን ወይም በድግስ ቦታ)

• ቧንቧ ሥራ፣ የኤሌክትሪክ ሥራ

• ግንበኝነት፣ አናጺነት እንዲሁም ቀለም ቀቢነት

• ልጆችን በየቤታቸው ማስተማር

• ቅቤ፣ ማርና ሌላ ምርት ከምንጩ አምጥቶ መሸጥ

• ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

ሥራ ለመቀጠር

ለቃለ መጠይቅ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ

ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ሲቪ አዘጋጅ

እንደ ሁኔታው ለውጥ አድርግ

ማስታወቂያ ያልወጣባቸው ክፍት የሥራ ቦታዎች ይኖሩ እንደሆን አጠያይቅ

የተደራጀህ ሁን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥራ ለማግኘት መንፈሰ ጠንካራ መሆንና ጥንቃቄ የሞላበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀልጣፋ መሆንህ በቃለ መጠይቁ ወቅት ይረዳሃል