ብዙ አማራጭ እያለ እርካታ የጠፋው ለምንድን ነው?
ብዙ አማራጭ እያለ እርካታ የጠፋው ለምንድን ነው?
ሳይንቲፊክ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንዳመለከተው በዛሬው ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች “በተለያዩ የኑሮ ዘርፎች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ብዙ አማራጭ” አላቸው። በእርግጥም አሜሪካውያን ከሸቀጣ ሸቀጥ፣ ከአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ከሥራና ሌላው ቀርቶ ከሰዎች ጋር ካላቸው ግንኙነት አንጻር በጣም ብዙ አማራጭ አላቸው። አማራጭ በበዛ መጠን በሕይወት ውስጥ እርካታ የማግኘቱ አጋጣሚም የዚያኑ ያህል ይጨምራል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስላል። ይሁን እንጂ ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው። ለምን?
ጽሑፉ እንዳመለከተው ለምርጫ ያለን አመለካከት ደስታችንን ይነካል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች በጣም ጥሩ ምርጫ ለማድረግ ሲሉ በዕቃው ላይ የተለጠፉ ጽሑፎችን በጥንቃቄ በማንበብና አዳዲስ ዕቃዎችን አገላብጠው በማየት ብዙ ጊዜና ጉልበት ያባክናሉ፤ ከዚያ በኋላም የገዙትን ዕቃ ሌሎች ከገዙት ጋር ያወዳድራሉ። ሌሎች ደግሞ የተሻሉ አማራጮች ቢቀርቡላቸውም እንኳ “ጥሩ ነው የሚሉትን” እስካገኙ ድረስ በዚያ ይረካሉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የፈለጉትን ዓይነት ዕቃ ሲያገኙ ሌላ መፈለጋቸውን ያቆማሉ።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሁልጊዜ ምርጥ ዕቃ መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች አማራጭ በበዛ ቁጥር ውሳኔ ማድረግ ይከብዳቸዋል። ምርጫ ካደረጉ በኋላም “በጊዜ እጦት ምክንያት ሳያይዋቸው የቀሩትን አማራጮች በማሰብ ይቆጫሉ” በማለት ሳይንቲፊክ አሜሪካን ተናግሯል። ውሎ አድሮ እነዚህ ሰዎች “በሕይወታቸው ውስጥ የሚያገኙት እርካታ፣ ደስታና ብሩሕ አመለካከት የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ጭንቀታቸው ይጨምራል።” ከዚህ በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? መጽሔቱ እንዲህ ብሏል:- “አማራጭ ከመጠን በላይ መብዛቱ ቢያንስ ቢያንስ በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ እየተስፋፋ ላለው ደስታ የማጣት ስሜት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለን እንድናምን የሚያስችለን በቂ ምክንያት አለን።”
ይሁን እንጂ የጥናቱ ተመራማሪዎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ውጥረት መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል። እንዴት?
● ማግኘት የምንፈልገው ነገር ያን ያህል አንገብጋቢ እስካልሆነ ድረስ ብዙ አማራጮችን ላለመመልከት መወሰን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ልብስ ለመግዛት ስትሄድ ጥቂት ሱቆችን ብቻ ለመጎብኘት ወስን።
● ልታገኘው የማትችለውን ‘ምርጥ’ ነገር ከመፈለግ ይልቅ መሠረታዊ ፍላጎትህን ሊያሟላልህ የሚችለውን ለመውሰድ ወስን። ከዚያ በኋላ ስለዚያ ነገር ማሰብህን አቁም።
● ሳትመርጣቸው የቀሩ ነገሮች ባላቸው በጎ ጎን ላይ ከማሰላሰል ተቆጠብ። አንተ የመረጥከው ዕቃ ባለው ጥሩ ጎን ላይ ብቻ ለማተኮር ጥረት አድርግ።
● “የኋላ ኋላ እንዳታዝን ብዙ ተስፋ አታድርግ” የሚል አባባል አለ። በሕይወትህ ውስጥ የተሻለ እርካታ ለማግኘት ከፈለግህ ይህን ምክር ተግባራዊ አድርግ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
ከሳይንቲፊክ አሜሪካን መጽሔት ተሻሽለው የወጡ