እውነተኛ አምላክ አንድ ብቻ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
እውነተኛ አምላክ አንድ ብቻ ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ወንድና ሴት አማልክት መካከል ሞሎክ፣ አስታሮት፣ በኣል፣ ዳጎን፣ ሜሮዳክ፣ ድያ፣ ሄርሜንና አርጤምስ የሚባሉት ይገኙበታል። (ዘሌዋውያን 18:21፤ መሳፍንት 2:13፤ 16:23፤ ኤርምያስ 50:2፤ የሐዋርያት ሥራ 14:12፤ 19:24) ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሁሉን የሚችል አምላክ እንደሆነ ተደርጎ የተጠቀሰው ይሖዋ ብቻ ነው። ሙሴ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ በዘመረው የድል መዝሙር ላይ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ?” ብሏል።—ዘፀአት 15:11
በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች አማልክት ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ለይሖዋ ነው። ሆኖም ከእውነተኛው አምላክ የሚያንሱት የእነዚህ አማልክት ሚና ምንድን ነው? እነዚህም ሆኑ ለብዙ ዘመናት ሲመለኩ የቆዩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች አማልክት፣ ሁሉን የሚችለው አምላክ የይሖዋ የበታች የሆኑ እውን አማልክት ናቸው?
በሰዎች ምናብ የተፈጠሩ አማልክት
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 83:18፤ ዮሐንስ 17:3) ነቢዩ ኢሳይያስ አምላክ ራሱ የተናገራቸውን ቃላት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም።”—ኢሳይያስ 43:10, 11
ሌሎቹ አማልክት በሙሉ ከይሖዋ የሚያንሱ ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ከናካቴው ሕልውና የሌላቸውና በሰዎች ምናብ የተፈጠሩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን አማልክት ‘ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት የማይችሉ በሰው እጅ የተሠሩ’ ብሏቸዋል። (ዘዳግም 4:28) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በግልጽ ያስተምራል።
ቅዱሳት መጻሕፍት ከይሖዋ በስተቀር ማንኛውንም አማልክት ማምለክ እንደሌለብን ማስጠንቀቃቸው ምንም አያስደንቅም። ለምሳሌ ያህል፣ ለሙሴ ከተሰጡት አሥር ትእዛዛት መካከል የመጀመሪያው የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የትኛውንም ሌላ አምላክ እንዳያመልክ የሚከለክል ነበር። (ዘፀአት 20:3) ለምን?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሕልውና የሌለውን አምላክ ማምለክ ፈጣሪን መስደብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሐሰተኛ አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎችን “የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም” ብሏቸዋል። (ሮሜ 1:25) የሰዎች ምናብ የፈጠራቸው እነዚህ አማልክት አብዛኛውን ጊዜ በተፈጥሮ ከሚገኙ እንደ ብረት ወይም እንጨት ካሉ ነገሮች በሚሠሩ ምስሎች ይወከላሉ። ብዙዎቹ አማልክት እንደ ነጎድጓድ፣ ውቅያኖስና ነፋስ ካሉ የተፈጥሮ ኃይሎች ጋር ዝምድና እንዳላቸው ተደርጎ ይታመናል። ስለዚህ እንዲህ ያሉትን የሐሰት አማልክት ማምለክ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ማቃለል እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።
የሐሰት አማልክትና እነርሱን የሚወክሉት ምስሎች በፈጣሪ ፊት አስጸያፊ ናቸው። ያም ሆኖ አምላክ በዋነኝነት እንደሚጸየፍ የተናገረው እነዚህን ሐሰተኛ አማልክት የሚሠሩትን ሰዎች ነው። የሚከተሉት ኃይለኛ ቃላት የይሖዋን ስሜት ይገልጻሉ:- “የአሕዛብ ጣዖታት ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣ የሰው እጅ ያበጃቸው ናቸው። አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፤ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ በአፋቸውም እስትንፋስ የለም። እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።”—መዝሙር 135:15-18
ኢሳይያስ 44:10) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የሕዝብ አማልክት ሁሉ [እርባና ቢስ] ጣዖታት ናቸው” ይላል። (መዝሙር 96:5) ሐሰተኛ አማልክት ምንም አይረቡም፤ የማይረባን ነገር ማምለክ ደግሞ ምንም ፋይዳ የለውም።
መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ አምላክ ሌላ ሕይወት ያለውንም ሆነ የሌለውን ማንኛውንም ነገር እንዳናመልክ ያስጠነቀቀበት ተጨማሪ ምክንያት አለው። እንዲህ ዓይነቱ አምልኮ ብዙ ጊዜና ጉልበት ያባክናል። ነቢዩ ኢሳይያስ “ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣ ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው?” ማለቱ ተገቢ ነው። (ኢየሱስ፣ መላእክትና ዲያብሎስ
ሰዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አልፎ አልፎ አምላክ ተብለው ተጠርተዋል። ይሁን እንጂ በጥንቃቄ ከመረመርን በእነዚህ ቦታዎች ላይ የገባው “አምላክ” የሚለው ቃል ሰዎቹ መመለክ እንዳለባቸው የሚያሳይ ቃል አለመሆኑን መገንዘብ እንችላለን። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በተጻፈባቸው የጥንት ቋንቋዎች ላይ “አምላክ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ኃያል የሆነን ወይም መለኮታዊ ባሕርይ ያለውን አሊያም ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር በጣም የሚቀራረብን አካል ለማመልከት ይሠራበት ነበር።
ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ብለው ጠርተውታል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዮሐንስ 1:1, 18) ታዲያ ይህ ሲባል ኢየሱስ መመለክ አለበት ማለት ነው? እርሱ ራሱ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ” ብሏል። (ሉቃስ 4:8) በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ኢየሱስ ታላቅ ኃይልና መለኮታዊ ባሕርይ ያለው ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መመለክ እንደሚገባው አይናገርም።
መላእክት ራሳቸው ‘አምላክ መሰል’ ተብለዋል። (መዝሙር 8:5 NW ፤ ዕብራውያን 2:7) ሆኖም የሰው ልጆች መላእክትን እንዲያመልኩ የሚያበረታታ አንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ አናገኝም። እንዲያውም በአንድ ወቅት አረጋዊ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ፊቱ በቆመው አንድ መልአክ ስለተደነቀ ሊሰግድለት በግንባሩ ተደፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ መልአኩ “ተው! ይህን አታድርግ! . . . ለእግዚአብሔር ስገድ” ብሎታል።—ራእይ 19:10
ሐዋርያው ጳውሎስ ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ዲያብሎስ ‘የዚህ ዓለም ገዥ’ እንደመሆኑ መጠን ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የሐሰት አማልክት የሚቀርበውን አምልኮ ያስፋፋል። (ዮሐንስ 12:31) ስለሆነም በሰው እጅ የተሠሩትን አማልክት ማምለክ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰይጣንን ማምለክ ነው። ይሁን እንጂ ሰይጣን የእኛ አምልኮ የሚገባው አምላክ አይደለም። ራሱን በራሱ ገዢ ያደረገ ሐሰተኛ አምላክ ነው። ይዋል ይደር እንጂ የእርሱም ሆነ የሁሉም ዓይነት ሐሰት አምልኮ መጨረሻ ጥፋት ነው። አዎን፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መላውን የሰው ዘር ጨምሮ ፍጥረታት በሙሉ እውነተኛና ሕያው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን ለዘላለም አምነው ይቀበላሉ።—ኤርምያስ 10:10
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጣዖት አምልኮ ምን ያስተምራል?—መዝሙር 135:15-18
▪ ኢየሱስና መላእክት ሊመለኩ ይገባል?—ሉቃስ 4:8
▪ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ማን ነው?—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከግራ ወደ ቀኝ ያሉት ምስሎች:- ማርያም፣ በጣሊያን፤ የበቆሎ አምላክ የተባለችው ማያ፣ በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ፤ አስታሮት፣ በከነዓን፤ ምትሃታዊ ኃይል አለው የሚባል ጣዖት፣ በሴራ ሊዮን፤ ቡድሃ፣ በጃፓን፤ ቺኮመኮአትል፣ በአዝቴክ፣ ሜክሲኮ፤ የጭልፊት ራስ ያለው ሆረስ፣ በግብጽ፤ ድያ፣ በግሪክ
[ምንጭ]
የበቆሎ አምላክ፣ የጭልፊት ራስ ያለው ሆረስ እና ድያ:- Photograph taken by courtesy of the British Museum