የምናረጀው ለምንድን ነው?
የምናረጀው ለምንድን ነው?
“ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው።” —ኢዮብ 14:1
ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ እንደ አላቂ ዕቃ በጊዜ ሂደት ማለቃቸው አይቀርም ብለህ ታስብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ መኪናዎችና ማሽኖች በየቀኑ ስለምንጠቀምባቸው ከጊዜ ብዛት ከአገልግሎት ውጪ ይሆናሉ። ከዚህ በመነሳት አንድ ሰው እንስሳትም በተመሳሳይ አርጅተው ይሞታሉ ወደሚል መደምደሚያ ላይ ይደርስ ይሆናል። ይሁንና የሥነ እንስሳት ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ኦስታድ ይህን ጉዳይ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከማሽኖች በጣም የተለዩ ናቸው፤ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ልዩ የሚያደርጋቸው በጣም ወሳኝ ነገር ራሳቸውን በራሳቸው ማደስ መቻላቸው ሳይሆን አይቀርም።”
ሰውነትህ አንድ አደጋ ከደረሰበት በኋላ ራሱን በራሱ የሚጠግንበት መንገድ አስገራሚ ነው። ነገር ግን በየጊዜው የሚያደርገውን ጥገና ብንመለከት ደግሞ እጅግ አስደናቂ ሆኖ እናገኘዋለን። አጥንትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ከላይ ሲታይ ሕይወት አልባ የሚመስለው አጥንት በአንድ ሰው የጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለማቋረጥ ራሱን ሲያፈርስና ሲገነባ የሚኖር ሕያው አካል ነው። በዚህ ሂደት አማካኝነት በሰውነታችን ውስጥ ያለው ጠቅላላ አጥንት በየ10 ዓመቱ ይታደሳል ለማለት ይቻላል።” ሌሎቹ የሰውነትህ ክፍሎች ደግሞ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይታደሳሉ። በቆዳህ፣ በጉበትህና በአንጀትህ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሴሎች በየቀኑ ይተካሉ ማለት ይቻላል። ሰውነትህ በየሴኮንዱ 25 ሚሊዮን የሚያክሉ ሴሎችን በአዲስ ይተካል። ይህ ባይሆን ማለትም ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች ባይጠገኑና በአዲስ ባይተኩ ኖሮ ገና በልጅነትህ ታረጅ ነበር።
እንደ ዕቃ በጊዜ ብዛት የማናልቅ የመሆናችን ሐቅ ይበልጥ አስደናቂ መሆኑ የታወቀው የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በሴሎች
ውስጥ ስለሚገኙ ሞለኪውሎች ማጥናት በጀመሩ ጊዜ ነበር። ሴሎችህ በአዳዲስ ሴሎች ሲተኩ እያንዳንዱ አዲስ ሴል መላ አካልህን ለማደስ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን አካትቶ የያዘው ዲ ኤን ኤ የተባለው ሞለኪውል ይኖረዋል። እንግዲያው በአንተ የሕይወት ዘመን ብቻ ሳይሆን ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ዲ ኤን ኤ ምን ያህል ጊዜ ሲባዛ እንደኖረ እስቲ አስብ! ሁኔታው ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ ለመረዳት ያህል የፎቶ ኮፒ ማሽን ተጠቅመህ አንድን ሰነድ ፎቶ ኮፒ ካደረግህ በኋላ በአዲሱ ቅጂ ሌላ ቅጂ እያዘጋጀህ ብትቀጥል ምን እንደሚሆን ለመገመት ሞክር። ይህንን በተደጋጋሚ ጊዜያት የምታደርግ ከሆነ የቅጂዎቹ ጥራት እየቀነሰ ይሄድና በመጨረሻ ጽሑፉ ፈጽሞ ወደማይነበብበት ደረጃ ይደርሳል። የሚያስደስተው ግን የእኛ ሴሎች በተደጋጋሚ ጊዜያት እየተከፈሉ የሚባዙ ቢሆኑም እንኳ በውስጣቸው ያለው ዲ ኤን ኤ ጥራቱን አይቀንስም ወይም እንደ ዕቃ እያለቀ አይሄድም። ለምን? ምክንያቱም ሴሎቻችን በሚከፈሉበት ጊዜ በዲ ኤን ኤ ላይ የሚፈጠረውን የቅጂ ስህተት የሚያስተካክሉበት የተለያዩ መንገዶች ስላሏቸው ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ የሰው ልጅ ከብዙ ዓመታት በፊት ከሕልውና ውጪ በሆነ ነበር!እያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል ከትልቁ አካል አንስቶ እስከ ትንሿ ሞለኪውል ድረስ ያለማቋረጥ በሌላ ስለሚተካና ስለሚታደስ በአገልግሎት ዘመን ብዛት ስለሚያልቁ ዕቃዎች የተሰጠው ምሳሌ ሰዎች የሚያረጁበትን ምክንያት ጥሩ አድርጎ አይገልጸውም። አብዛኛዎቹ የሰውነታችን ክፍሎች በተለያየ መንገድና በተለያየ ፍጥነት ለዓመታት ራሳቸውን ሲተኩ ወይም ሲጠግኑ ኖረዋል። ታዲያ ይህ ከሆነ ሁሉም በአንድ ጊዜ ሥራቸውን የሚያቆሙት ለምንድን ነው?
በሴል ውስጥ ስለ እርጅና የተቀረጸ ፕሮግራም አለ?
ድመት 20 ዓመት ስትኖር ከእርሷ ጋር ተመጣጣኝ የሆነው ኦፖሰም 3 ዓመት ብቻ የሚኖረው ለምንድን ነው? * የሌሊት ወፍ 20 ወይም 30 ዓመት ስትኖር አይጥ ግን 3 ዓመት የምትኖረውስ ለምንድን ነው? አንዳንድ የኤሊ ዝርያዎች 150 ዓመት ሲኖሩ ዝሆን 70 ዓመት ብቻ የሚኖረው ለምንድን ነው? አመጋገብ፣ የሰውነት ክብደት፣ የአንጎል መጠን ወይም የእድገት ፍጥነት የመሳሰሉት ሁኔታዎች እነዚህ እንስሳት የተለያየ ዕድሜ የሚኖሩበትን ምክንያት ለማወቅ የሚያስችሉ አይደሉም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “የአንድ ዝርያ የዕድሜ ጣሪያ በሴሉ ውስጥ በሚገኝ ጄኔቲክ ኮድ ላይ ተቀርጾ ይገኛል” ብሏል። በጂኖች ላይ የመጨረሻው ከፍተኛ ዕድሜ ተቀርጿል። ታዲያ ይህ የተወሰነ የዕድሜ ጣሪያ ሲቃረብ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ሥራቸውን ለማቆም ማሽቆልቆል እንዲጀምሩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
የሞለኪዩላር ባዮሎጂስት ዶክተር የሆኑት ጆን ሜዲና እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “አንድ የሆነ ጊዜ ላይ ብቅ ብሎ ሴሎች እያከናወኑ ያሉትን የተለመደ ሥራ እንዲያቋርጡ የሚነግራቸው ምስጢራዊ መልእክት ያለ ይመስላል።” አክለውም “ሴሎች እንዲያውም መላው የሰውነታችን ክፍሎች እንዲያረጁና እንዲሞቱ ትእዛዝ የሚያስተላልፉ ጂኖች አሉ” ብለዋል።
ሰውነታችንን ለአሥርተ ዓመታት አትራፊ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ከቆየ አንድ ትልቅ ድርጅት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጆች ሳይታሰብ አዳዲስ ሠራተኞችን መቅጠርም ሆነ ማሠልጠን እንዲሁም ማሽኖቹን መጠገንና በሌላ መተካት ብሎም ሕንጻውን ማደስና መገንባት ያቆማሉ። ብዙም ሳይቆይ ሥራው ማሽቆልቆል ጀመረ። ነገር ግን እነዚህ ሥራ አስኪያጆች ውጤታማ የነበሩትን የአሠራር ሂደቶች የቀየሩት ለምንድን ነው? ይህ ጥያቄ ስለ እርጅና በሚያጠኑ ባዮሎጂስቶች ፊት ከተደቀነው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ዘ ክሎክ ኦፍ ኤጅ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ስለ እርጅና በሚደረግ ጥናት ታላቁ ምስጢር ሴሎች ራሳቸውን መተካታቸውን ለምን እንደሚያቆሙና እንደሚሞቱ ለመረዳት አለመቻሉ ነው።”
እርጅና ሊወገድ ይችላል?
እርጅና “ከሁሉም ባይሎጂካዊ ችግሮች እጅግ ውስብስብ የሆነ” ተብሎ ተጠርቷል። ለአሥርተ ዓመታት የተደረጉ ጥረቶችና ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች የእርጅናን መንስኤም ሆነ መፍትሔ ለማወቅ አላስቻሉም። በ2004 ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተሰኘ መጽሔት ስለ እርጅና የሚያጠኑ 51 ሳይንቲስቶችን ያቀፈ አንድ ቡድን ያወጣውን ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት ለሕትመት አብቅቶ ነበር። መልእክቱም “ለገበያ ከቀረቡ መድኃኒቶች መካከል እርጅናን ለማዘግየት፣ ለማስቀረት ወይም ወደኋላ ለመመለስ የሚያስችል አንድም መድኃኒት የለም” የሚል ነበር። ጥሩ አመጋገብም ሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤንነትን ከማሻሻሉ በተጨማሪ በበሽታ ተጠቅቶ ያለ ዕድሜ ከመሞት ይከላከል ይሆናል። ይሁን እንጂ እርጅናን ምንም ነገር ሊያዘገየው አይችልም። ይህ መደምደሚያ ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?” ሲል የተናገራቸውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው የሚገኙትን ቃላት ያስታውሰናል።—ማቴዎስ 6:27
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ሜዲና ለእርጅና መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅለል አድርገው ሲናገሩ “በመጀመሪያ ደረጃ ለምን እንደምናረጅ አናውቀውም። . . . ካንሰርን ለማጥፋት ጦርነት ካወጅን አሥርተ ዓመታት ቢያልፉንም እንኳ መድኃኒቱን እስካሁን ማግኘት አልቻልንም። እርጅና የሚከሰትበት ሂደት ደግሞ ከካንሰር ይበልጥ እጅግ የተወሳሰበ ነው” ብለዋል።
ወሳኝ ወደ ሆነ መደምደሚያ የሚያደርስ ምርምር
ሕይወት ያላቸው ነገሮች በውስጣቸው ምን ሂደት እንደሚከናወንና ለምን እንደሚያረጁ ለማወቅ የሚደረገው ምርምር የተሻለ ዕድሜ የመኖር ተስፋችንን አያጨልምብንም። አንዳንዶች እያደረጉት ያለው ምርምር ስለ እርጅና ሊሸሹት ወደማይችሉት ወሳኝ መደምደሚያ መርቷቸዋል። ማይክል ቢሂ የተባሉ ሞለኪዩላር ባዮሎጂስት “የዘመናችን ባዮኬሚስትሪ ላለፉት አራት አሥርተ ዓመታት ባደረገው ጥረት ስለ ሴል ምስጢር የነበሩ ነገሮችን ግልጥልጥ አድርጓል። . . . ሕይወትን ከሥረ መሠረቱ ለማወቅ በሴል ላይ የተደረገው እየተጠናከረ የመጣ ምርምር ያስገኘው ውጤት ሴል ‘ንድፍ’ አውጪ እንዳለው ጥርት ባለ ድምፅ ይናገራል!” ብለዋል። ሕይወት ያላቸውን ነገሮች አንድ ከፍተኛ ችሎታ ያለው አካል ነድፏቸዋል። እርግጥ ነው እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የመጀመሪያው ሰው ማይክል ቢሂ አይደሉም። በጥንት ዘመን የኖረ አንድ መዝሙራዊ በሰው ልጅ አካል አሠራር ላይ በጥልቅ ካሰላሰለ በኋላ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 139:14
ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ሠሪ ካላቸው የሚከተለውን ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው:- ታላቅ ንድፍ አውጪ የሆነው አምላክ ሰዎችን የፈጠረው እንደ ብዙዎቹ እንስሳት ጥቂት ዓመታት ብቻ ኖረው እንዲሞቱ አድርጎ ነው? ወይስ ከእንስሳት የበለጠ ዕድሜ እንዲኖሩ ይፈልጋል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 ኦፖሰም በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የማርሱፒያ ዝርያ ሲሆን ከፍልፈል ጋር የሚመሳሰል እንስሳ ነው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ድንቅ ሆነን ተፈጥረናል’
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምናረጀው ሴሎቻችን በአገልግሎት ብዛት ስለሚያልቁ ነው?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ዲ ኤን ኤ:- ፎቶ:- www.comstock.com