የመጀመሪያው ኃጢአት ምን ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የመጀመሪያው ኃጢአት ምን ነበር?
የዚህ ጥያቄ መልስ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። እንዴት? አዳምና ሔዋን ለአምላክ አለመታዘዛቸው እስካሁን ድረስ በመላው የሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 5:12) ሆኖም የአንድን ዛፍ ፍሬ መብላት ይህን ያህል አሳዛኝ ውጤት ያስከተለው እንዴት ነው?
አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችና ፍሬያማ ዛፎች በሚገኙበት በጣም በሚያምር የአትክልት ሥፍራ ውስጥ አስቀመጣቸው። ከእነዚህ ዛፎች መካከል እንዳይበሉ የተከለከሉት ከአንዱ ብቻ ይኸውም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ነበር። አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነጻነት ያላቸው ፍጡራን እንደመሆናቸው መጠን አምላክን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ሊመርጡ ይችሉ ነበር። ይሁንና ለአዳም “ከእርሱ [መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ] በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር።—ዘፍጥረት 1:29፤ 2:17
ተገቢ የሆነ ማዕቀብ
አዳምና ሔዋን በአትክልት ሥፍራው ውስጥ ከሚገኙት ከሌሎቹ ዛፎች መብላት ይችሉ ስለነበር ይህ ማዕቀብ ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አላደረገባቸውም። (ዘፍጥረት 2:16) ከዚህም በላይ ማዕቀቡ አዳምና ሔዋን መጥፎ ዝንባሌ እንዳላቸው የሚያሳይም ሆነ ክብራቸውን የሚነካ አልነበረም። አምላክ፣ ከእንስሳ ጋር የጾታ ግንኙነት እንደ መፈጸም ወይም እንደ መግደል የመሳሰሉትን መጥፎ ድርጊቶች የሚከለክል ሕግ ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ አንዳንዶች፣ ፍጹም የሆኑ ሰዎች ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባ መጥፎ ነገር የማድረግ ዝንባሌ አላቸው ብለው ይከራከሩ ነበር። ሆኖም መብላት ተፈጥሯዊና ተገቢ ነገር ነው።
አንዳንዶች እንደሚሉት የተከለከለው ፍሬ የጾታ ግንኙነትን ያመለክታል? ይህ ዓይነቱ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አዳም ሕጉ ሲሰጠው ሔዋን ያልተፈጠረች ከመሆኑም በላይ ከዚያ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ በብቸኝነት ኖሯል። (ዘፍጥረት 2:23) ሁለተኛ፣ አምላክ ለአዳምና ለሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ሕጉን እንዲያፈርሱ አዟቸው ሲያበቃ የታዘዙትን በመፈጸማቸው በሞት ይቀጣቸዋል ማለት የማይመስል ነገር ነው! (1 ዮሐንስ 4:8) ሦስተኛ፣ ሔዋን ፍሬውን የበላችው ከአዳም በፊት ሲሆን በኋላም ለባሏ ሰጥታዋለች። (ዘፍጥረት 3:6 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም የተከለከለው ፍሬ የጾታ ግንኙነትን እንደማያመለክት ግልጽ ነው።
በራስ ለመመራት የተደረገ ሙከራ
መልካምና ክፉን የሚያሳውቀው ዛፍ እውነተኛ ዛፍ ነበር። ዛፉ አምላክ ገዢያቸው እንደመሆኑ መጠን ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለመወሰን ያለውን መብት ይወክላል። በመሆኑም የተከለከለውን ዘፍጥረት 3:4, 5
ዛፍ መብላት የአምላክን ንብረት ከመውሰድ ወይም ከስርቆት ያለፈ ትርጉም ነበረው፤ ድርጊታቸው በትዕቢት ተነሳስተው የአምላክን ገዢነት ችላ በማለት ራሳቸውን ለመምራት ሙከራ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ነበር። ሰይጣን፣ እርሷና ባሏ ፍሬውን ከበሉ ‘እንደማይሞቱ’ ለሔዋን በውሸት ከነገራት በኋላ አክሎ “ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” ሲል እንደተናገረ ልብ ማለት ያስፈልጋል።—ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ፍሬውን ከበሉ በኋላ እንደ አምላክ መልካምና ክፉውን ለማወቅ አልቻሉም። እንዲያውም ሔዋን ለአምላክ “እባብ አሳሳተኝ” በማለት ተናግራለች። (ዘፍጥረት 3:13) የሰይጣን አፈ ቀላጤ ለሆነው እባብ የአምላክን ትእዛዝ መድገሟ ሕጉን ታውቅ እንደነበር ይጠቁማል። (ራእይ 12:9) ይህ ደግሞ ሔዋን እያወቀች ትእዛዙን መጣሷን ያሳያል። (ዘፍጥረት 3:1-3) አዳም ግን አልተታለለም። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) ፈጣሪውን በታማኝነት ከመታዘዝ ይልቅ ሚስቱን በመስማት የእሷን መንገድ ተከትሏል።—ዘፍጥረት 3:6, 17
አዳምና ሔዋን በራሳቸው ለመመራት በመምረጣቸው ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ዝምድና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አበላሹት፤ እንዲሁም ኃጢአት በጂኖቻቸው ላይ ዘላቂ አሻራ እንዲተው አድርገዋል። እርግጥ ነው፣ አዳምና ሔዋን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖሩ ቢሆንም አንድ ቅርንጫፍ ከዛፉ ከተቆረጠ በኋላ መሞት እንደሚጀምር ሁሉ እነርሱም ኃጢአት በሠሩበት “ቀን” መሞት ጀመሩ። (ዘፍጥረት 5:5) ከዚህም በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ውስጣዊ ሰላማቸው እንደጠፋ ተሰማቸው። ራቁታቸውን መሆናቸውን ስላወቁ ከአምላክ ለመደበቅ ሞከሩ። (ዘፍጥረት 3:7, 8) የጥፋተኝነትና በራስ ያለመተማመን ስሜት እንዲሁም እፍረት ተሰማቸው። በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ሕሊናቸው ስለወቀሳቸው ውስጣቸው ተረበሸ።
አምላክ ቃሉንና ቅዱስ የሆኑት መሥፈርቶቹን ለመጠበቅ ሲል አዳምንና ሔዋንን ሞት የፈረደባቸው ሲሆን ከዔድን ገነትም አስወጣቸው። (ዘፍጥረት 3:19, 23, 24) በመሆኑም ገነት፣ ደስታና የዘላለም ሕይወት በኃጢአት፣ በመከራና በሞት ተተኩ። ይህ ለሰው ልጆች ምንኛ አሳዛኝ ክስተት ነው! ሆኖም አምላክ በባልና ሚስቱ ላይ የሞት ፍርድ ካስተላለፈ በኋላ ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር በማይጋጭ ሁኔታ ኃጢአታቸው ያስከተለውን መጥፎ ውጤት ሁሉ ለማስተካከል ወዲያውኑ ቃል ገባ።
ይሖዋ የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች ከኃጢአትና ከሞት ነጻ የሚወጡበትን መንገድ አዘጋጀ። ይህንን ዓላማውን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ፈጽሞታል። (ዘፍጥረት 3:15፤ ማቴዎስ 20:28፤ ገላትያ 3:16) አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ኃጢአትንም ሆነ የኃጢአት ውጤቶችን በማስወገድ እንደ መጀመሪያ ዓላማው መላዋን ምድር ወደ ገነትነት ይለውጣታል።—ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የተከለከለው ፍሬ የጾታ ግንኙነትን እንደማያመለክት እንዴት እናውቃለን?—ዘፍጥረት 1:28
▪ የተከለከለውን ፍሬ መብላት ምን ትርጉም ነበረው?—ዘፍጥረት 3:4, 5
▪ አምላክ፣ ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች ለማስወገድ ምን ዓይነት ዝግጅት አድርጓል?—ማቴዎስ 20:28
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የተከለከለው ፍሬ የጾታ ግንኙነትን አያመለክትም
[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሔዋን መልካሙንና ክፉውን ለራሷ በመወሰን እንደ አምላክ ለመሆን ፈለገች