በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?

ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?

ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ ሐሰት መሆኑን ሳይንስ እንዳረጋገጠ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ግጭት የተፈጠረው በሳይንስና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ሳይሆን በሳይንስና ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖች ተብለው በሚጠሩት ሃይማኖታዊ ወገኖች እምነት መካከል ነው። ከእነዚህ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ፣ ግዑዙ ፍጥረት በሙሉ ከ10,000 ዓመታት በፊት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል ብለው በሐሰት ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን አባባል አይደግፍም። ይህ ቢሆን ኖሮ ባለፈው መቶ ዓመት ሳይንስ የደረሰባቸው ብዙ ግኝቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ የጥርጣሬ ደመና ያጠሉ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ላይ የተደረገ ጥንቃቄ የታከለበት ጥናት ይህ ሐሳብ ከተረጋገጡ ሳይንሳዊ ሐቆች ጋር እንደማይጋጭ ያሳያል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ከወግ አጥባቂ “ክርስቲያኖች” እና ከብዙዎቹ ክሪኤሽኒስቶች (የፍጥረት አማኞች) ጋር አይስማሙም። ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ትንታኔ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምን እንደሆነ ያሳያል።

“በመጀመሪያ” የተባለው የትኛው ጊዜ ነው?

የዘፍጥረት ዘገባ የሚጀምረው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው ቀላል፣ ሆኖም ብዙ መልእክት የያዘ አገላለጽ ነው። (ዘፍጥረት 1:1) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው ድርጊት ከቁጥር 3 ጀምሮ በተተረኩት የፍጥረት ቀናት ውስጥ እንደማይካተት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይስማማሉ። ይህም ትልቅ ትርጉም አለው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው በውል ተለይተው ከማይታወቁ ዘመናት አስቀድሞ፣ አጠቃላዩ ጽንፈ ዓለም ተፈጥሯል፤ ይህ ፕላኔቷ ምድራችንንም ይጨምራል።

ጂኦሎጂስቶች የምድር ዕድሜ 4 ቢሊዮን ዓመት እንደሚሆን የሚገምቱ ሲሆን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ደግሞ የጽንፈ ዓለም ዕድሜ 15 ቢሊዮን ዓመት እንደሚሆን የሚገልጽ ስሌት ሠርተዋል። ታዲያ እነዚህ ግኝቶችም ሆኑ በዚህ ረገድ ወደፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎች ከዘፍጥረት 1:1 ጋር ይጋጫሉ? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሰማያትንና የምድርን’ ትክክለኛ ዕድሜ ለይቶ አይናገርም። በዚህም ምክንያት ሳይንስ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስሕተት መሆኑን አያሳይም።

የፍጥረት ቀኖች ርዝማኔያቸው ምን ያህል ነበር?

ስለ ፍጥረት ቀናት ርዝማኔስ ምን ሊባል ይችላል? የእያንዳንዳቸው ርዝማኔ ቃል በቃል 24 ሰዓት ነው? አንዳንዶች የዘፍጥረት ጸሐፊ የሆነው ሙሴ ከጊዜ በኋላ ስለ ሳምንታዊው ሰንበት ሲናገር፣ ከስድስቱ የፍጥረት ቀናት በኋላ ያለው ሰባተኛው ቀን ለሰንበት እንደ ምሳሌ መሆኑን ስለጠቀሰ እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ርዝማኔው ቃል በቃል 24 ሰዓት ነው ይላሉ። (ዘፀአት 20:11) ታዲያ የዘፍጥረት ዘገባ ይህን አባባል ይደግፋል?

በፍጹም። “ቀን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል 24 ሰዓትን ብቻ ሳይሆን የተለያየ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ የአምላክን የፍጥረት ሥራ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ ስድስቱንም ቀናት እንደ አንድ ቀን አድርጎ ጠቅሷል። (ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን “እግዚአብሔርም ብርሃኑን ‘ቀን’፣ ጨለማውን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:5) እዚህ ላይ “ቀን” ተብሎ የተገለጸው ከ24 ሰዓት ውስጥ ከፊሉ ጊዜ ብቻ ነው። እንግዲያው፣ የእያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ርዝማኔ 24 ሰዓት ነው ብሎ በጭፍን ለመናገር የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም።

ታዲያ የፍጥረት ቀኖቹ ርዝማኔ ምን ያህል ነበር? በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ የተሠራባቸው ቃላት እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ረዥም ዘመናትን እንደሚያመለክት ይጠቁማሉ።

ፍጥረታት መታየት የጀመሩት ቀስ በቀስ ነው

ሙሴ የዘፍጥረትን ዘገባ የጻፈው በዕብራይስጥ ሲሆን ታሪኩን ያቀረበው ሁኔታውን በምድር ላይ ሆኖ ከሚያይ ሰው አንጻር ነው። እነዚህ ሁለት ነጥቦች ጽንፈ ዓለም የፍጥረት ጊዜ ወይም “ቀናት” ከመጀመራቸው በፊት እንደነበረ ካገኘነው እውቀት ጋር ተዳምረው፣ በፍጥረት ዘገባ ዙሪያ የተነሱት አብዛኞቹ ውዝግቦች መፍትሔ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። እንዴት?

የዘፍጥረትን ዘገባ በጥንቃቄ ስንመረምረው በአንዱ “ቀን” የተጀመሩት ክንውኖች በቀጣዩ ቀን ወይም በቀጣዮቹ ቀናትም ይቀጥላሉ። ለምሳሌ ከመጀመሪያው “ቀን” በፊት፣ ቀደም ሲል ከተፈጠረችው ፀሐይ የሚመጣው ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ ያገደው ነገር ነበረ፤ ምናልባትም ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከልሎት ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 38:9) በመጀመሪያው “ቀን” ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ የከለለው ነገር መወገድ ጀመረና ደብዘዝ ያለ ብርሃን ወደ ምድር ከባቢ አየር ዘልቆ መግባት ቻለ። *

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሁለተኛው “ቀን” ብርሃን በደንብ እንዳያልፍ የሚከልለው ነገር ይበልጥ በመጥራቱ በላይ ካለው ጥቅጥቅ ደመናና በታች ካለው ውቅያኖስ መካከል ጠፈር ሊኖር ቻለ። በአራተኛው “ቀን” ፀሐይና ጨረቃ “በሰማይ” ላይ መታየት እስኪችሉ ድረስ ከባቢ አየሩ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ ሄደ። (ዘፍጥረት 1:14-16) በሌላ አነጋገር በምድር ላይ ሆኖ ሁኔታውን ከሚከታተል ሰው አንጻር ፀሐይና ጨረቃ በግልጽ መታየት ጀመሩ። እነዚህ ክስተቶች የተከናወኑት ደረጃ በደረጃ ነው።

በተጨማሪም የዘፍጥረት ዘገባ፣ ከባቢ አየሩ ብርሃን እንዳያገኝ የከለለው ነገር እየተገፈፈ በሄደ መጠን ነፍሳትንና ስስ ክንፍ ያላቸውን (membrane-winged) ፍጥረታት ጨምሮ የሚበሩ እንስሳት በአምስተኛው “ቀን” መታየት እንደጀመሩ ይገልጻል። ይሁን እንጂ በስድስተኛውም “ቀን” አምላክ “የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር” ይሠራ እንደነበር ያመለክታል።—ዘፍጥረት 2:19

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ በእያንዳንዱ “ቀን” ወይም የፍጥረት ወቅት የተፈጸሙት ዐበይት ክንውኖች በአንድ አፍታ ሳይሆን ቀስ በቀስ እንደተፈጠሩና ምናልባትም በአንዱ “ቀን” የተጀመረው የፍጥረት ሥራ ወደ ቀጣዮቹ የፍጥረት “ቀናትም” እየተሸጋገረ ቀጥሎ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል።

እንደየወገናቸው

ዕፅዋትና እንስሳት ቀስ በቀስ ወደ ሕልውና መምጣታቸው አምላክ የተለያየ ዓይነት ዝርያ ያላቸውን ፍጥረታት ለመፍጠር በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ ያመለክታልን? በፍጹም። ታሪኩ በግልጽ የሚያሳየው አምላክ ዋና ዋናዎቹን የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ በሙሉ መፍጠሩን ነው። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 20-25) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ የአካባቢያቸውን ሁኔታ መለዋወጥ እንዲላመዱት የሚያስችላቸው ፕሮግራም በውስጣቸው ተቀርጾ ነበር? የአንድን ‘ወገን’ ድንበር የሚደነግገው ምንድን ነው? ይህንን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው’ እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:21) ይህ አነጋገር በአንድ ‘ወገን’ ውስጥ የሚፈጠረው የዓይነት መብዛት ገደብ እንዳለው ያመለክታል። ዋና ዋናዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ባለፉት ረዥም ዘመናት ውስጥ የታየባቸው ለውጥ በጣም ጥቂት መሆኑን የቅሪተ አካል ማስረጃዎችና ዘመናዊ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ከሚናገሩት በተቃራኒ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያውም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ዘመን እንደተፈጠረ የዘፍጥረት መጽሐፍ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ዘፍጥረት ስለ ጽንፈ ዓለም አፈጣጠርና በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ወደ ሕልውና ስለመምጣታቸው ያሰፈረው ዘገባ በቅርብ ጊዜ ከተደረሰባቸው ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር ይስማማል።

በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት የራሳቸው ፍልስፍና ስላላቸው ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ ስለመሆኑ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አይቀበሉትም። ይሁን እንጂ ሙሴ ጥንታዊ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማለትም በዘፍጥረት ላይ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለውና ሕይወትም ወደ ሕልውና የመጣው ደረጃ በደረጃና በረዥም ዘመን ውስጥ መሆኑን መጻፉ ትኩረት የሚስብ ነው። ሙሴ ከ3,500 ዓመታት በፊት እንዲህ ያለውን ከሳይንስ አንጻር ትክክል የሆነ እውቀት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ አንድ አሳማኝ ማብራሪያ አለ። ይኸውም እንዲህ ያለውን ጥልቅ እውቀት ለሙሴ የሰጠው ሰማያትንና ምድርን ለመፍጠር ኃይልና ጥበብ ያለው አካል ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት’ እንደሆነ ለሚያቀርበው ሐሳብ ክብደት ይሰጠዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 እዚህ ላይ በመጀመሪያው “ቀን” የሆነውን ነገር ለመግለጽ ያገለገለው የዕብራይስጥ ቃል አጠቃላይ ብርሃንን የሚያመለክት ኦር የተባለ ቃል ሲሆን በአራተኛው “ቀን” ለተገኘው ብርሃን ያገለገለው ግን የብርሃኑን ምንጭ ለይቶ የሚጠቅስ ማኦር የሚል ቃል ነው።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ አምላክ ጽንፈ ዓለምን ከፈጠረ ምን ያህል ጊዜ ሆኖታል?—ዘፍጥረት 1:1

▪ ምድር የተፈጠረችው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው 6 ቀናት ውስጥ ነው?—ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም

▪ ሙሴ ስለ ምድር አፈጣጠር የጻፈው ነገር ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?—2 ጢሞቴዎስ 3:16

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያውም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ዘመን እንደተፈጠረ አያስተምርም

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ጽንፈ ዓለም:- IAC/RGO/David Malin Images

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

NASA photo