ቴሌቪዥን የጊዜ ሌባ ነው?
ቴሌቪዥን የጊዜ ሌባ ነው?
አንድ ሰው ‘አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ልስጥህና ከእንግዲህ በሕይወትህ ሙሉ ቴሌቪዥን ማየት ይቅርብህ’ ቢልህ ትስማማ ነበር? ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህ ጥያቄ ከቀረበላቸው አሜሪካውያን መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት እንደማይስማሙ ተናግረዋል። በሌላ ጥናት ላይ ደግሞ ወንዶች ከሁሉ አስበልጠው የሚመኙት ነገር ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ሰላምና ደስታ ማግኘት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሰላምና ደስታ ከሚመኟቸው ነገሮች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡ ሲሆን በሕይወታቸው በአንደኛ ደረጃ ማግኘት የሚፈልጉት ትልቅ ቴሌቪዥን ነው!
ቴሌቪዥን በመላው ዓለም በጣም ተወዳጅ የሆነ ዕቃ ነው። በ1931 ቴሌቪዥን ገና አዲስ ግኝት በነበረበት ጊዜ የአሜሪካ የሬዲዮ ኮርፖሬሽን ሊቀ መንበር የነበሩት ሰው “ቴሌቪዥን የመጨረሻው የእድገት ደረጃ ላይ ሲደርስ የምድር ሕዝብ ሁሉ ተመልካች ይሆናል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው” ብለው ነበር። እነዚያ ቃላት በወቅቱ በጣም የተጋነኑ መስለው ይሆናል፤ ዛሬ ግን አይደሉም። በመላው ዓለም ያሉት ቴሌቪዥኖች ብዛት 1.5 ቢሊዮን እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን የተመልካቾቹ ቁጥር ከዚህ በጣም የበለጠ ነው። ወደድንም ጠላን ቴሌቪዥን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ከዚህ መመልከት እንችላለን።
ብዙ ሰዎች ቴሌቪዥን ለማየት የሚያውሉት ጊዜ በጣም የሚያስገርም ነው። በቅርቡ የተደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳሳየው ሰዎች በየቀኑ በአማካይ ከሦስት ሰዓት በላይ ቴሌቪዥን በማየት ያሳልፋሉ። ሰሜን አሜሪካውያን በየቀኑ ለአራት ሰዓት ተኩል ያህል ቴሌቪዥን የሚያዩ ሲሆን ጃፓናውያን ደግሞ በየቀኑ አምስት ሰዓት ያህል ቴሌቪዥን በመመልከት የአንደኝነትን ቦታ ይዘዋል። እነዚህ ሰዓታት ሲደመሩ ቴሌቪዥን በማየት ረጅም ጊዜ እንደሚጠፋ መገንዘብ ይቻላል። በየቀኑ ለአራት ሰዓት ያህል ቴሌቪዥን የምናይ ከሆነ ዕድሜያችን 60 ዓመት ሲሞላ ቴሌቪዥን በማየት በድምሩ 10 ዓመት አጥፍተናል ማለት ነው። ሆኖም ማንኛችንም ብንሆን “የዕድሜውን አንድ ስድስተኛ ቴሌቪዥን በማየት ያሳለፈው ውድ ጓደኛችን እዚህ ተኝቷል” ተብሎ በመቃብራችን ላይ እንዲጻፍ አንፈልግም።
ሰዎች ለሰዓታት ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን የሚያዩት ስለሚያስደስታቸው ነው? ላይሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች ቴሌቪዥን በማየት በጣም ብዙ ሰዓት እንደሚያባክኑ የሚያምኑ ከመሆኑም በላይ ጊዜያቸውን ጠቃሚ ለሆነ ነገር ባለማዋላቸው የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች “የቴሌቪዥን ሱሰኞች” እንደሆኑ ይናገራሉ። የቴሌቪዥን ሱስንና የአደገኛ ዕፆችን ሱስ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖርም ሱስ የሚያስይዙበት መንገድ ግን የተለያየ ነው። የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች ዕፁን በመውሰድ ረጅም ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህን ጊዜ ለመቀነስ ወይም ልማዱን ለመተው ቢፈልጉም አይችሉም። ዕፅ ለመውሰድ ሲሉ አስፈላጊ የሆኑ ማኅበራዊና የቤተሰብ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉበትን ጊዜ መሥዋዕት ያደርጋሉ። በተጨማሪም ዕፁን ሳይወስዱ ከቀሩ ሰውነታቸው የሚያጣው ነገር ስላለ ይሠቃያሉ። ቴሌቪዥን የማየት ሱስ የተጠናወታቸው ሰዎችም እነዚህ ሁሉ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።
ንጉሥ ሰሎሞን “ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም” በማለት ምሳሌ 25:27) ቴሌቪዥን በመመልከት ረገድም ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። ቴሌቪዥን ጠቃሚ የሆነ ብዙ ነገር ቢያቀርብም ቴሌቪዥን በመመልከት ረጅም ጊዜ ማጥፋት ግን አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ሊሻማበት ይችላል፤ ልጆች እንዳያነቡ እንቅፋት ሊሆን፣ በትምህርታቸው እንዲዳከሙ ሊያደርግ እንዲሁም ከልክ በላይ መወፈርን ሊያስከትል ይችላል። ቴሌቪዥን በማየት ብዙ ሰዓት የምታጠፋ ከሆነ በምላሹ የምታገኘውን ውጤት ማሰቡ ብልህነት ነው። ጊዜያችን ሊባክን የማይገባው እጅግ ውድ ነገር ነው። በተጨማሪም ስለምናየው ፕሮግራምም ማሰቡ አስተዋይነት ነው። ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንመለከተዋለን።
ጽፏል። (