እስከተዋደዱ ድረስ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
እስከተዋደዱ ድረስ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?
በአንድ ጥናት ላይ ጥያቄ ከቀረበላቸው ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት፣ ሁለት ሰዎች እስከተዋደዱ ድረስ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምንም ስህተት እንደሌለው ተናግረዋል። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በመገናኛ ብዙኃን የሚንጸባረቅ ከመሆኑም በላይ ትክክል እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ብዙውን ጊዜ ቴሌቪዥንም ሆነ ፊልሞች ሁለት ሰዎች ከተዋደዱ የጾታ ግንኙነት መፈጸማቸው የተለመደ ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል።
እርግጥ አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ከዓለም መመሪያ ለማግኘት አይሞክሩም። ምክንያቱም ዓለም የገዢውን የዲያብሎስን አስተሳሰብ እንደሚያንጸባርቅ ያውቃሉ። (1 ዮሐንስ 5:19) ከዚህም በተጨማሪ ‘የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛና ፈውስ የሌለው’ እንደሆነ ስለሚያውቁ በስሜታቸው ብቻ ላለመመራት ጥንቃቄ ያደርጋሉ። (ኤርምያስ 17:9) ከዚህ ይልቅ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች መመሪያ ለማግኘት ወደ ፈጣሪያቸውና በመንፈስ አነሳሽነት ወደተጻፈው ቃሉ ዘወር ይላሉ።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
የጾታ ግንኙነት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው
ያዕቆብ 1:17 “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ይላል። ውድ ከሆኑት ስጦታዎች መካከል በትዳር ውስጥ የሚደረገው የጾታ ግንኙነት አንዱ ነው። (ሩት 1:9 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 7:2, 7) የጾታ ግንኙነት፣ የሰው ልጆች መውለድ እንዲችሉ እንዲሁም ባልና ሚስት ፍቅርና መተሳሰብ በሚንጸባረቅበት ብሎም ደስታ በሚሰጥ መንገድ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ቅርርብ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። . . . ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 5:18, 19
ይሖዋ በስጦታዎቹ እንድንደሰትና እንድንጠቀም የሚፈልግ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም ሲል ሕይወታችንን የምንመራባቸው ከሁሉ የተሻሉ ሕግጋትንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። (መዝሙር 19:7, 8) ይሖዋ ‘የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ’ በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 48:17) ታዲያ የፍቅር ተምሳሌት የሆነው በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ በእርግጥ የሚጠቅመንን ነገር ይከለክለናል?—መዝሙር 34:10፤ 37:4፤ 84:11፤ 1 ዮሐንስ 4:8
ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው
አንድ ወንድና ሴት በጋብቻ ሲጣመሩ በምሳሌያዊ አነጋገር “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ። ሁለት ያልተጋቡ ግለሰቦችም የጾታ ግንኙነት ሲፈጽሙ (ዝሙት ተብሎም ይጠራል) “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ። ሆኖም ይህ ጥምረት በአምላክ ዓይን ርኩስ ከመሆኑም በተጨማሪ ፍቅር የጎደለው ነው። * እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?—ማርቆስ 10:7-9፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10, 16
አንደኛው ምክንያት ዝሙት ዘላቂ የሆነ ቃል ኪዳን ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም ግንኙነት በመሆኑ ነው።
እንዲህ ያለው ድርጊት አንድ ሰው ለራሱ ያለውን አክብሮት እንዲያጣ ከማድረጉም በላይ በሽታ፣ ያልተፈለገ እርግዝናና የስሜት ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ግለሰቡ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲጥስ ያደርገዋል። በመሆኑም ዝሙት የሚፈጽም ሰው ሌላው ግለሰብ አሁን ስላለውም ሆነ ወደፊት ስለሚኖረው ደስታና ደኅንነት ምንም እንደማያስብ ያሳያል።ለአንድ ክርስቲያን ደግሞ ዝሙት መፈጸም የመንፈሳዊ ወንድሙን ወይም እህቱን መብት መጋፋት ወይም መተላለፍ ጭምር ይሆንበታል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-6) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ አገልጋይ ነን የሚሉ ሰዎች ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ የክርስቲያን ጉባኤን ያረክሳሉ። (ዕብራውያን 12:15, 16) እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ዝሙት የፈጸመው ሰው ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም እንዳይኖረውና ያላገባ ከሆነ ደግሞ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን ጠብቆ ትዳር መመሥረት እንዳይችል ያደርጉታል። ከዚህም በላይ የራሳቸውን ቤተሰብ መልካም ስም ያጎድፋሉ፤ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ዝሙት የፈጸመውን ሰው ቤተሰብ ይበድላሉ። በመጨረሻም የጽድቅ ሕግጋቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በመጣስ አምላክን ስላሳዘኑት ለእርሱ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳያሉ። (መዝሙር 78:40, 41) ይሖዋ፣ ንስሐ የማይገቡ ግለሰቦችን ለፈጸሟቸው እንዲህ ለመሰሉ መጥፎ ድርጊቶች ‘ይበቀላቸዋል።’ (1 ተሰሎንቄ 4:6) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ቢነግረን ምን ያስገርማል?—1 ቆሮንቶስ 6:18
የምትወደውን ሰው ለማግባት እያሰብክ ነው? ከሆነ የምትጠናኑበትን ወቅት እርስ በርስ ለመተማመንና ለመከባበር የሚያስችላችሁ ጠንካራ መሠረት ለመጣል ለምን አትጠቀሙበትም? እስቲ አስቡት:- አንድ ወንድ ራሱን የማይገዛ ከሆነ አንዲት ሴት እንዴት ሙሉ በሙሉ ልታምነው ትችላለች? አንዲት ሴት የራሷን የጾታ ፍላጎት ለማርካት ወይም ወንዱን ለማስደሰት ብላ የአምላክን ሕግ ችላ የምትል ከሆነ አንድ ወንድ እሷን ለማፍቀርና ለማክበር ቀላል ይሆንለታል?
ፍቅር የተንጸባረቀባቸውን የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ቸል የሚሉ ሰዎች የዘሩትን እንደሚያጭዱም አስታውሱ። (ገላትያ 6:7) መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙትን የሚፈጽም . . . በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ምሳሌ 7:5-27) እርግጥ፣ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ አንድ ወንድና ሴት ከልብ ንስሐ ከገቡ፣ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለማደስ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉና አንዳቸው በሌላው ላይ ያላቸውን እምነት ካጠናከሩ ስለፈጸሙት ድርጊት ያደረባቸው መጥፎ ስሜት ቀስ በቀስ ሊቀንስ ይችላል። እንደዚህም ሆኖ ቀድሞ የሠሩት ነገር አብዛኛውን ጊዜ ጠባሳ ይተዋል። አሁን ተጋብተው የሚኖሩ አንድ ወጣት ባልና ሚስት፣ ሳይጋቡ በፊት ዝሙት በመፈጸማቸው በጣም ይጸጸታሉ። አንዳንድ ጊዜ ባልየው ‘በትዳራችን ውስጥ አለመግባባት የሚፈጠረው ጋብቻችን ንጹሕ በሆነ መንገድ ባለመጀመሩ ይሆን?’ እያለ ራሱን ይጠይቃል።
እውነተኛ ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም
እውነተኛ ፍቅር፣ በተቃራኒ ጾታ መካከል የሚኖረውን የፍቅር ስሜት ሊጨምር ቢችልም “ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም” ወይም ደግሞ “ራስ ወዳድ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ከዚህ ይልቅ ለሌላው ሰው ደኅንነትና ዘላለማዊ ደስታ የቆመ ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር አንድ ወንድና ሴት እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩና የጾታ ግንኙነትንም አምላክ በሰጠው ትክክለኛ ቦታ ማለትም በጋብቻ ውስጥ ብቻ እንዲያደርጉት ይገፋፋቸዋል።—ዕብራውያን 13:4
እውነተኛ ደስታ የሰፈነበት ትዳር የሚያስገኘው የመተማመንና የደህንነት ስሜት በተለይ ልጆች በሚወለዱበት ጊዜ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም አምላክ፣ ልጆች ፍቅርና የተረጋጋ ሁኔታ በሰፈነበት አስተማማኝ ቤተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ይፈልጋል። (ኤፌሶን 6:1-4) ሁለት ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ከልብ ቃል ሊገቡ የሚችሉት በጋብቻ ሲቆራኙ ብቻ ነው። ይህን ሲያደርጉ በቀሪው ሕይወታቸው በደስታም ሆነ በመከራ ጊዜ እርስ በርስ ለመተሳሰብና ለመደጋገፍ በልባቸው እንዲሁም ብዙውን ጊዜ በአንደበታቸው ጭምር ቃል ኪዳን ይገባሉ።—ሮሜ 7:2, 3
በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት በመካከላቸው ያለውን ትስስር ይበልጥ ሊያጠናክር ይችላል። ደስታ በሰፈነበት ትዳር ውስጥ ባልና ሚስቱ ትዳራቸውን ሳያቃልሉ፣ ኅሊናቸውን ሳያቆሽሹ ወይም ፈጣሪያቸውን ሳያሳዝኑ የጾታ ግንኙነት ይበልጥ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሊሆንላቸው ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ማንኛውም ዓይነት የጾታ ግንኙነት የሚያመለክት ሲሆን ይህም በአፍ የሚፈጸም ወሲብን ጨምሮ የጾታ ብልቶችን ጸያፍ በሆነ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል።—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የነሐሴ 2004 ንቁ! ገጽ 10ን እና የየካቲት 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13, 14ን ተመልከቱ።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ አምላክ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን እንዴት ይመለከተዋል?—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
▪ ዝሙት ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?—1 ቆሮንቶስ 6:18
▪ እርስ በርስ የሚዋደዱ ሁለት ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5