የአትክልተኞች ወዳጅ ከሆነችው ጥንዚዛ ጋር ተዋወቁ
የአትክልተኞች ወዳጅ ከሆነችው ጥንዚዛ ጋር ተዋወቁ
ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ይህች በቀለማት ያሸበረቀች ነፍሳት ብሪታንያ ውስጥ ሌዲበርድ * ተብላ የምትጠራ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ሌዲባግ ትባላለች። በሌሎች አገሮችም የተለያዩ መጠሪያዎች አሏት። ምንም እንኳ ጥንዚዛዎች ሁሉም ሰው የሚወዳቸው ነፍሳት ባይሆኑም የዚህች ጥንዚዛ ዝርያዎች ግን በአብዛኛው የሚወደዱ ናቸው። እነዚህ ጥንዚዛዎች የልጆችን ትኩረት ይስባሉ፤ አትክልተኞችና ገበሬዎችም የእነዚህ ነፍሳት መኖር ያስደስታቸዋል። ታዲያ እንዲህ እንዲወደዱ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው?
አብዛኞቹ የእነዚህ ትናንሽ ጥንዚዛ ዝርያዎች የአትክልት ቅማሎችን (በግራ በኩል ያለውን ስዕል ተመልከት) ይበላሉ። እነዚህ የአትክልት ቅማሎች በጣም ትናንሽ የሆኑ ነፍሳት ሲሆኑ የጓሮ አትክልቶችንና የአንዳንድ ሰብሎችን ፈሳሽ በመምጠጥ ተክሉን ያደርቁታል። አንዳንድ ትላልቅ ጥንዚዛዎች በሕይወት ዘመናቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአትክልት ቅማሎችን ይበላሉ። በዕጭነት ጊዜያቸውም የሚመገቡት መጠን እንዲህ ቀላል አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ጥንዚዛዎች ሌሎች ተባዮችን የሚበሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ዝርያዎች በተክል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሻጋታዎችን ጭምር ይመገባሉ። በመሆኑም ይህችን ጥንዚዛ አትክልተኞችና ገበሬዎች ቢወዷት ምንም የሚያስደንቅ አይደለም!
በ1800ዎቹ ዓመታት መጨረሻ አካባቢ ሰዎች ባላወቁት መንገድ ኮቶኒ ኩሺን ስኬል የተባሉ ነፍሳትን ከአውስትራሊያ ወደ ካሊፎርኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ ይዘው ገብተው ነበር። እነዚህ ተባዮች በፍጥነት ተራብተው በፍራፍሬ ዛፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በፍራፍሬ ኢንዱስትሪ ላይ ስጋት ፈጠሩ። ነገር ግን ነፍሳቱ በመጡበት አገር ማለትም በአውስትራሊያ በሰብል ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርሱ ሲታወቅ የእነዚህን ነፍሳት የተፈጥሮ ጠላት ለማወቅ ምርምር የሚያደርግ ሰው ወደዚያ ተላከ። ይህ ሰው እነዚህን ነፍሳት አድኖ የሚበላቸው ቪዳልየ የተባለ የጥንዚዛ ዝርያ መሆኑን ደረሰበት። ከዚያም 500 የሚያክሉ ጥንዚዛዎች ወደ ካሊፎርኒያ እንዲመጡ በመደረጉ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኮቶኒ ኩሺን ስኬል የተባሉትን ነፍሳት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ተቻለ። በዚህም መንገድ የፍራፍሬ ተክሎቹን ከጥፋት ማዳን ተችሏል።
የጥንዚዛ የሕይወት ዑደት
ማራኪ የሆኑት እነዚህ ትናንሽ ጥንዚዛዎች ከላይ ጎበጥ ብለው ከታች ጠፍጣፋ ናቸው። ጥንዚዛዎቹ በልተው የማይጠግቡ ቢሆኑም እንኳ የአብዛኞቹ ዝርያዎች ርዝመት ከግማሽ ኢንች አይበልጥም። ጠንካራ የሆነውና የሚያብረቀርቀው የሰውነታቸው ክፍል ለመብረር የሚያገለግላቸውንና በጣም ስስ የሆነውን ክንፋቸውን የሚሸፍንላቸው ከመሆኑም ሌላ ውበት ይጨምርላቸዋል። ጥንዚዛው ለመብረር በሚፈልግበት ጊዜ ጠንካራው ሽፋን ይከፈትና ቦታውን ለክንፉ ይለቅቃል። ይህች የጥንዚዛ ዓይነት ብዙውን ጊዜ መልኳ ቀይ ሆኖ ጥቁር ነጠብጣብ ጣል ጣል ያደረገበት ቢሆንም በግምት ወደ 5,000 የሚጠጉት የዚህች ነፍሳት ዝርያዎች የተለያዩ ዓይነት ነጠብጣቦች አሏቸው። አንዳንዶቹ ብርቱካንማ ወይም ቢጫ መልክ ኖሯቸው ጥቁር ጣል ጣል ያደረገባቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጥቁር ሆነው ቀይ ጣል ጣል ያለባቸው ናቸው። ጥቂቶቹ ምንም ነጠብጣብ የላቸውም። ባለ አራት ማዕዘን ነጠብጣብ ጣል ጣል ያደረገባቸው ወይም ሽንትር ያላቸውም አሉ።
አብዛኞቹ ዝርያዎች የአንድ ዓመት ዕድሜ አላቸው። ትላልቆቹ ጥንዚዛዎች የክረምቱን ወራት ደረቅ የሆነ መጠለያ ፈልገው በእንቅልፍ ያሳልፋሉ። በጋ ሲገባ በቅማሎች የተወረሩ ተክሎችን ፍለጋ ወዲያ ወዲህ መብረር ይጀምራሉ። በመራቢያ ወቅታቸው ሴቷ ጥንዚዛ ቢጫ ቀለም ያላቸው ብዙ እንቁላሎችን (በቀኝ በኩል ያለውን ፎቶ ተመልከት) በርካታ የአትክልት ቅማሎች በሚገኙበት በቅጠሉ ጀርባ ላይ ትጥላለች። ከዚያም እያንዳንዱ
እንቁላል ስድስት እግር ያለው እጭ ሆኖ ይፈለፈላል። ይህ እጭ ሲታይ ጥንዚዛ ሳይሆን ትንሽ አርጃኖ (በገጽ 16 ላይ ከታች መሃል ያለውን ፎቶ ተመልከት) ይመስላል። እጩ ጊዜውን የሚያሳልፈው የአትክልት ቅማሎችን በመመገብ ስለሆነ ብዙም ሳይቆይ የላይኛው ቆዳ ይወጠራል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ቆዳውን ከቀየረ በኋላ ወደ ሙሽሬነት (pupa) ተለውጦ ተክሉ ላይ ይጣበቃል። ከዚያም ሙሽሬው ሙሉ ጥንዚዛ እስኪሆን ድረስ እድገት ማድረጉን ይቀጥላል። በመጀመሪያ ላይ ለስላሳ እንዲሁም አመድማ መልክ ያለው ሲሆን እስኪጠነክር ድረስ እዚያ ተክሉ ላይ እንደተጣበቀ ይቆያል። ከዚያም በአንድ ቀን ውስጥ ዋነኛ መልኩን ይይዛል።የተለያየ ቀለም ያላትን የዚህችን ጥንዚዛ ዝርያዎች ጠላቶቻቸውም ቢሆኑ አይጠጓቸውም። ጠላት ሊይዛት ሲሞክር ከመገጣጠሚያዎቿ አካባቢ በጣም የሚያስጠላ ሽታና መጥፎ ጣዕም ያለው ቢጫ ፈሳሽ ትረጫለች። እንደ ወፍና ሸረሪት የመሳሰሉ አዳኞቻቸው በመጀመሪያ ላይ እነርሱን ለማደን በሞከሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን መጥፎ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይረሱትም። የጥንዚዛዎቹ ደማቅ ቀለም ያን ሁኔታ ዘወትር ያስታውሳቸዋል።
ችግር የፈጠረ ጥንዚዛ
ተባዮችን ለማጥፋት ታገለግል የነበረች የዚህች ጥንዚዛ ዝርያ በአንድ ወቅት እርሷ ራሷ አጥፊ ተባይ ሆና ነበር። ሃርለኩዊን እንዲሁም መልቲከለርድ ኤዢያን ሌዲ ቢትል ተብላ የምትጠራው ይህች ዝርያ በሰሜን ምሥራቅ እስያ ከሌሎች የጥንዚዛ ዝርያዎች ጋር በሰላም ትኖር ነበር። የተክል ቅማሎችንና ሌሎች ተባዮችን በብዛት የመመገብ ለየት ያለ ባሕርይ ስላላት በቅርቡ ወደ ደቡብ አሜሪካና ወደ አውሮፓ ተወሰደች። የሚያሳዝነው ግን ይህች ጥንዚዛ በዚያ ይኖሩ የነበሩ የሌሎች ዝርያዎችን ምግብ ሙልጭ አድርጋ በመብላት ነባሮቹን ዝርያዎች አደጋ ላይ ጣለቻቸው። ከዚህም በላይ ትመገባቸው የነበሩት የተክል ቅማሎችም ሆኑ ሌሎች ተባዮች ሲያልቁ ጥንዚዛዋ በመራቧ በዚያ የነበሩትን የጥንዚዛ ዝርያዎችና ሌሎች ጠቃሚ ነፍሳትን ማግበስበስ ጀመረች። ይህ ሁኔታ በሌሎች የጥንዚዛ ዝርያዎች ላይ የመጥፋት አደጋ በመፍጠሩ የነፍሳት ተመራማሪዎችን ስጋት ላይ ጣላቸው። ሃርለኩዊን ተብላ የምትጠራው የዚህች ጥንዚዛ ዝርያዎች ለመሰብሰብ የደረሰ ፍራፍሬን መብላታቸው እንዲሁም በክረምት ወራት ሙቀት ለማግኘት በብዛት ወደ ሰዎች ቤት መግባታቸው እንዲጠሉ አድርጓቸዋል።
በጣም ጥቂት የሆኑ የሌዲበርድ ዝርያዎች ተባዮችን ከመብላት ይልቅ እንደ ባቄላና ዱባ የመሳሰሉትን አንዳንድ ተክሎች ይመገባሉ። ደስ የሚለው ግን አብዛኞቹ ዝርያዎች በአትክልተኞች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው።
ጥንዚዛውን የሚስቡ ነገሮች
እነዚህን የጥንዚዛ ዝርያዎች እንዴት ወደ አትክልት ቦታህ መሳብ ትችላለህ? የአበባ ተክሎች በተፈጥሯቸው የአበባ ዱቄትና የአበባ ማር (ኔክታር) ስላላቸው ይስቧቸዋል። እንዲሁም ሌሎች አትክልቶችና የገንዳ ውኃ ወደ ጓሮህ እንዲመጡ ይጋብዟቸዋል። የሚቻል ከሆነ ፀረ ተባይ ኬሚካል አትጠቀም። በተክሎች ላይ የሚገኙ ወይም መሬት የወዳደቁ ደረቅ ቅጠሎች ጥንዚዛዎቹ ክረምቱን በእንቅልፍ ለማሳለፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥሩላቸዋል። በአትክልት ቦታህ የምታገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ትል ወይም እንቁላል ላለመጨፍለቅ ተጠንቀቅ። ምናልባት ሳታውቀው ቀጣዩን የጥንዚዛ ትውልድ ልታጠፋ ትችላለህ።
እነዚህ በጣም ደስ የሚሉ ትንንሽ ፍጥረታት ጎጂ የሆነውን ፀረ ተባይ መግዛት ሳያስፈልግህ የአትክልት ቦታህን ከተባይ ነጻ እንደሚያደርጉልህ አትዘንጋ። እነዚህ ጥንዚዛዎች ከተጠነቀቅኽላቸው መልሰው ይክሱሃል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” ሲል እንደተናገረው እነዚህ የጥንዚዛ ዝርያዎች ፈጣሪያችን ላለው ጥበብ ተጨማሪ ማስረጃ ናቸው።—መዝሙር 104:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 “ሌዲበርድ” የሚለው መጠሪያ የመጣው “የእመቤታችን ወፍ” ከሚለው አባባል ሲሆን ይህም ከማርያም ጋር የተያያዘ ነው።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ከላይ:- © Waldhäusl/Schauhuber/Naturfoto-Online; በስተ ግራ ያሉት ሁለቱ:- Scott Bauer/Agricultural Research Service, USDA; መሃል:- Clemson University - USDA Cooperative Extension Slide Series, www.insectimages.org; እንቁላሎች:- Bradley Higbee, Paramount Farming, www.insectimages.org
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
በስተ ግራ:- Jerry A. Payne, USDA Agricultural Research Service, www.insectimages.org; ከግራ ሁለተኛ:- Whitney Cranshaw, Colorado State University, www.insectimages.org; ከግራ ሦስተኛ:- Louis Tedders, USDA Agricultural Research Service, www.insectimages.org; ከግራ አራተኛ:- Russ Ottens, The University of Georgia, www.insectimages.org; በቅጠል ላይ ያሉ ጥንዚዛዎች:- Scott Bauer/Agricultural Research Service, USDA