ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ “ቀኑን ሙሉ ቴሌቪዥን ተከፍቶ መዋሉ፣ ቤተሰብ አንድ ላይ አለመመገቡ አልፎ ተርፎም ለልጆች ተሽከርካሪ ጋሪ መሠራቱ” ወላጆችና ልጆች እርስ በርስ እንዳይነጋገሩ እንቅፋት ሆኗል። ይህ ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ ልጆች ትምህርት ቤት በሚገቡበት ጊዜ ሐሳባቸውን መግለጽ ስለማይችሉ “ኩርፊያ የሚቀናቸው” እንዲሆኑ ማድረጉ ነው።—ዚ ኢንዲፔንደንት፣ ብሪታንያ
▪ በስፔን 23 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ናቸው። በፈረንሳይ ደግሞ 43 በመቶ፣ በዴንማርክ 45 በመቶ እንዲሁም በስዊድን 55 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ናቸው።—ኢንስቲቱቶ ዴ ፖሊቲካ ፋሚለያር፣ ስፔን
▪ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብሪታንያውያን በየቀኑ ማታ ማታ የሚተኙት ከ5 ሰዓት ላነሰ ጊዜ መሆኑ “ትኩረትን የመሰብሰብ፣ የመርሳት [እና] የባሕርይ መለዋወጥ ችግር” እያስከተለባቸው ነው። በተጨማሪም የእንቅልፍ ማጣት “ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት፣ ለስኳር በሽታ፣ ለመንፈስ ጭንቀት፣ ለፍቺና ለከባድ የመኪና አደጋ የመጋለጥ አጋጣሚያቸውን” ከፍ ሊያደርገው ይችላል።—ዚ ኢንዲፔንደንት፣ ብሪታንያ
ዓመጽ ‘ለጊዜ ማሳለፊያነት’
“በወጣቶች የሚፈጸሙ የድብደባና ሌሎችን የማዋረድ ድርጊቶች እንዲሁም እነዚህን ድርጊቶች በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ በቪዲዮ የመቅረጽ ሁኔታ እየተበራከተ ነው” በማለት ኤል ፓይስ የተሰኘው የስፔን ጋዜጣ ዘግቧል። አንዳንድ የድብደባው ሰለባዎች ከደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ፈጽሞ አያገግሙም። ይሁንና ወጣቶች እንዲህ ያሉትን ወንጀሎች የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? “ይህን የሚያደርጉት ለመስረቅ ብለው፣ አለዚያም በዘረኝነት ስሜት ተገፋፍተው ወይም የዱርዬዎች ቡድን አባላት ስለሆኑ አይደለም። ይህን ዘግናኝና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ወንጀል የሚፈጽሙት እንዲያው ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ብቻ ነው” በማለት ኤክስኤል የተሰኘው መጽሔት ይናገራል። በወንጀል ጥናት ልዩ ሥልጠና የወሰዱት ቢቴንቴ ጋሬዶ የተባሉ አንድ የሥነ ልቦና ሊቅ ወጣቶቹ ወንጀሉን የሚፈጽሙት “አንዳንድ ጊዜ ሲሰክሩ አንዳንዴ ደግሞ ሳይሰክሩ” እንደሆነ ተናግረዋል። “ሆኖም ሁሉንም የሚያመሳስላቸው የጋራ ባሕርይ ቢኖር ምን እንዳደረጉ ቢያውቁም ፈጽሞ የማይጸጽታቸው መሆኑ ነው።”
“እርጉዝ” ሮቦት
ከዚህ ቀደም ለእርጉዞች የጤና ክትትል የሚያደርጉ ባለሞያዎች ሥልጠና የሚወስዱት ለሕክምና በሚመጡ ታማሚዎች ነበር። አሁን አሁን ግን ኖኤል የሚል ስያሜ የተሰጣት “ምጥ እንደያዛት ሴት እንድትሆን ተደርጋ የተሠራች ሮቦት ተመራጭ እየሆነች” መምጣቷን አሶሺዬትድ ፕሬስ ያወጣው ሪፖርት ይጠቁማል። ከሰዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የልብ ምትና የማኅፀን አፍ መከፈት እንዲኖራት ተደርጋ የተሠራችው ይህች “እርጉዝ” ሮቦት በውስጧ በተቀረጸላት ፕሮግራም መሠረት በርካታ የወሊድ ችግሮች እንዲያጋጥሟት፣ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ቶሎ እንድትወልድ ወይም ምጥ እንዲበዛባት ማድረግ ይቻላል። ኖኤል የምትወልደው “ሕፃን” ቀላ ያለ መልክ ካለው ጤናማ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን ሰማያዊ ቀለም ያለው ከሆነ ደግሞ በወሊድ ጊዜ ለሞት የሚያደርስ የኦክስጅን እጥረት እንዳጋጠመው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ተማሪዎቹን ለማሠልጠን ሮቦት መጠቀም ያስፈለገው ለምንድን ነው? “በልምምድ ሰዓት ሕይወት ባላት ሴት ላይ ስህተት ከመሥራት 20,000 ዶላር በምታወጣ ሮቦት ላይ ስህተት መፈጸም ስለሚሻል ነው” በማለት ዘገባው ገልጿል።
ትንንሽ “ደንበኞች”
ሮም፣ ጣሊያን የሚገኘው ላ ሳፕዬንሳ ዩኒቨርሲቲ በገለጸው መሠረት ገና የሦስት ዓመት ልጆች እንኳ የአንድን ሸቀጥ የተለያዩ ዓይነት ምርቶች ለይተው የሚያውቁ ሲሆን በስምንት ዓመታቸው ደግሞ እነርሱ ራሳቸውም “ደንበኞች” ይሆናሉ። በልጆቹ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ግፊት የሚያሳድሩት የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ሲሆኑ እነዚህ ማስታወቂያዎች ልጆቹ ወላጆቻቸው አንዳንድ ምርቶችን እንዲገዙ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ትንንሽ “አምባ ገነኖች” እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል በማለት ላ ሬፑብሊካ ይናገራል። ጋዜጣው በመቀጠል ማስታወቂያዎች በልጆች ላይ ምን “አደጋ” እንደሚያስከትሉ ሲገልጽ “ያዩትን ሁሉ መግዛት የግድ እንደሆነ በሚያምኑበት የቅዠት ዓለም ውስጥ መኖር ይጀምራሉ” ብሏል።
በሐሩር ክልል ላሉ በሽታዎች እምብዛም ትኩረት አይሰጥም
በሐሩር ክልል ያሉ አብዛኞቹ በሽታዎች በሕክምናው መስክ በሚደረጉ ምርምሮች ችላ እየተባሉ ነው። ለምን? ስኮትላንድ በሚገኘው ዱንዲ ዩኒቨርሲቲ ሞለኪውላር ባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ፈርጉሰን “የሚያሳዝነው ነገር . . . የመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች [አዲስ መድኃኒት] ለማግኘት የሚያደርጉት ምርምር የለም” በማለት ተናግረዋል። መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የሚያወጡትን ገንዘብ መልሰው የማግኘት አጋጣሚ ስለሌላቸው እንደዚያ ለማድረግ አይገፋፉም። እነዚህ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ ለሚያስገኙት እንደ አልዛይመር፣ ከልክ በላይ መወፈርና ስንፈተ ወሲብ ላሉ ችግሮች መድኃኒት ማምረት ይመርጣሉ። በዚህ መሃል ግን ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደገለጸው “አስተማማኝና ፍቱን የሆነ መድኃኒት ባለመኖሩ ምክንያት በወባ ሳቢያ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ [በግምት] 1 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ።”