ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ አንድ ጥናት በገለጸው መሠረት “መኪና እየነዱ በሞባይል ስልክ የሚያወሩ ሰዎች፣ ስልኩ በእጅ የሚያዝ ባይሆንም እንኳ ያሉበት ሁኔታ ሰክረው መኪና ከሚያሽከረክሩ ሰዎች ጋር አንድ ዓይነት ነው።”—የሮይተር ዜና አገልግሎት፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ በ2006፣ በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ብቻ በጓቲማላ ከተማ የሕዝብ አውቶቡሶች ላይ መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች 30,200 የዝርፊያ ወንጀሎች ተፈጽመዋል። በእነዚህ ወቅቶች አሥራ አራት የአውቶቡስ ሹፌሮች ወይም ረዳቶቻቸው እንዲሁም አሥር መንገደኞች ተገድለዋል። —ፕሬንሳ ሊብሬ፣ ጓቲማላ
▪ የዓለም የጤና ድርጅት ደም መሰብሰብንና መመርመርን በተመለከተ ላቀረበው መጠይቅ መልስ ከሰጡት 124 አገሮች ውስጥ 56ቱ “ከለጋሾች በወሰዱት ደም ሁሉ ላይ የኤች አይ ቪ፣ የሄፐታይተስ ቢ እና ሲ እንዲሁም የቂጥኝ ምርመራ አላደረጉም።”—የዓለም የጤና ድርጅት፣ ስዊዘርላንድ
▪ በአውስትራሊያ ከመጋባታቸው በፊት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በ1960ዎቹ ዓመታት 5 በመቶ ገደማ የነበረ ሲሆን በ2003 ግን ከ70 በመቶ በላይ ሆኗል።—የሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ፣ አውስትራሊያ
የስኳር ሕመም—ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ
ከዓለም አቀፉ የስኳር ሕመም ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙሪያ የስኳር በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን ወደ 230 ሚሊዮን ማደጉን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ከፍተኛ የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር ካላቸው 10 አገሮች ውስጥ ሰባቱ በማደግ ላይ የሚገኙ ናቸው። “የስኳር ሕመም በዓለማችን ላይ ከተከሰቱት ከባድ የጤና መቅሠፍቶች መካከል አንዱ ነው” በማለት ማርቲን ሲሊንክ የተባሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል። ዘገባው “በአንዳንድ ድሃ አገሮች ውስጥ በሽታው ፈጽሞ ጊዜ የማይሰጥ ሆኗል” ይላል።
የዓለም ረዥሙ የባቡር ሐዲድ
በሐምሌ 2006 የተመረቀው የዓለም ረዥሙ የባቡር ሐዲድ ቤይጂንግን የቲቤት ዋና ከተማ ከሆነችው ከላሰ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን 4,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። “ሐዲዱ” ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “የመክዳት ባሕርይ ያለውን የፐርማፍሮስት ምድር አቋርጦ የሚያልፍ ከመሆኑም ባሻገር ከባሕር ወለል በላይ እስከ 4,800 ሜትር ከፍታ የሚደርስ መሆኑ ድንቅ የምሕንድስና ውጤት እንዲሆን አድርጎታል።” መሃንዲሶቹ ካጋጠሟቸው ተፈታታኝ ችግሮች መካከል አንዱ የመሬቱን የመክዳት ባሕርይ ለመቀነስ ሲባል ሐዲዱ የሚያርፍበት መሠረት ሙሉውን ዓመት ቀዝቃዛ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ነበር። ከዚህም በላይ ሐዲዱ የተሠራበት ከፍታ በመሣሪያ አማካኝነት አየር ወደ ባቡሩ ፉርጎዎች ማስገባት አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ፉርጎዎቹ እያንዳንዱ መንገደኛ የሚጠቀምበት ኦክስጅን ተሟልቶላቸዋል።
“የውሸት ተማሪዎች”
በአንድ የፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሥነ ጽሑፍ ለመማር ከተመዘገቡት የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች መካከል ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት “ትምህርት በሚሰጥባቸው ክፍሎች ተገኝተው አያውቁም” በማለት ለ ፊጋሮ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። አንዳንዶቹ የተማሪ መታወቂያቸውን የሚጠቀሙበት መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማ ለመውሰድ እንዲሁም በአውሮፕላን ወይም በሕዝብ መጓጓዣ ሲጠቀሙ፣ በሆቴሎች ውስጥ ሲስተናገዱ ብሎም ፊልም ቤት ሲገቡ የአገልግሎት ዋጋ ቅናሽ ለማግኘት ነው። “የውሸት ተማሪዎቹ” እነዚህን ጥቅማ ጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ እንደ ቤላሩሲያን፣ ፊኒሽና ስዋሂሊ ያሉትን ብዙ ተማሪዎች የማይመርጧቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለመማር ይፈርማሉ። ተማሪዎቹ ክፍል መግባታቸውን ለማረጋገጥ ስም ጥሪ ስለማይካሄድ በውሸት መመዝገብ በጣም የተለመደ ነው። “ተማሪዎች” በኢንተርኔት አማካኝነት ተመዝግበው በጥቂት ቀናት ውስጥ የተማሪ መታወቂያ ካርድ እንደሚያገኙ ሪፖርቱ ገልጿል።
‘ከዓለም ተሰውሮ የቆየ’ ዋሻ
እስራኤላውያን የሳይንስ ሊቃውንት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው መቶ ዘመናት “ከውጪው ዓለም ተሰውሮ በቆየ” አንድ ዋሻ ውስጥ የጀርባ አጥንት የሌላቸው ስምንት ዓይነት አዳዲስ የእንስሳት ዝርያዎችን ማግኘታቸውን እንደተናገሩ ዘ ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል። ካባ ውስጥ የሚሠሩ ቆፋሪዎች ጠቅላላ ርዝመቱ 2.5 ኪሎ ሜትር ወደሆነ ዋሻ የሚያስገባ አንድ ትንሽ ቀዳዳ አገኙ። በዚህ ዋሻ ውስጥ አንድ ትንሽ ሐይቅ ያለበት ክፍል አለ። አዲስ ከተገኙት ከእነዚህ ዝርያዎች መካከል አንዳንዶቹ ጊንጥ ይመስላሉ። ሁለቱ የባሕር ውስጥ ፍጥረታት ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ጨው አልባ በሆነ ውኃ ውስጥ የሚገኙ ሸርጣኖች ናቸው፤ አራቱ ግን የየብስ እንስሳት ናቸው።