ወጣቶች ችግሩን እንዲቋቋሙ መርዳት
ወጣቶች ችግሩን እንዲቋቋሙ መርዳት
የዓለም ሁኔታ፣ የአኗኗር ዘይቤው እንዲሁም ፋሽኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለዋወጣል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ሲሆን ለውጥ የዘመናችን ዓይነተኛ መለያ ሆኗል። ትናንት ፋሽን የነበረው ነገር ዛሬ ጊዜ ያለፈበት ይሆናል፤ እንዲሁም ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ነገር ነገ እንደ ተራ ነገር ይታያል። እንዲህ ያለው ፈጣን ለውጥ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ማኅበራዊ አብዮት
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቴክኖሎጂው በወጣቶች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ ለውጥ አስከትሏል። ለምሳሌ ያህል፣ በብዙ አገሮች ሞባይልና ኮምፒውተር ወጣቶች እርስ በርስ ለሚያደርጉት ግንኙነት የደም ሥር ሆኗል ለማለት ይቻላል። ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ድረ ገጾች በርካታ አዳዲስ አጋጣሚዎችን ከፍተዋል። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት የ19 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “በአካባቢያችሁ ምንም ዓይነት ጓደኛ አይኖራችሁ ይሆናል፤ ሆኖም በኢንተርኔት አማካኝነት በአንድ ጀንበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ጓደኞች ልታፈሩ ትችላላችሁ።”
ብዙ ሰዎች የሞባይል ስልክም ሆነ ኢንተርኔት በርካታ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይስማማሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ መሣሪያዎች ለብዙ ሰዎች ሱስ ሆነውባቸዋል። የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶናልድ ሮበርትስ አንዳንድ ተማሪዎች “ከ4 እስከ 5 ሰዓት ባለው የዕረፍት ጊዜያቸው በሞባይል ሳያወሩ ትንሽ ደቂቃ እንኳ ማሳለፍ አይችሉም። ይህን አለማድረጋቸው እረፍት የሚነሳቸው ይመስለኛል፤ እንዲያውም ‘ጭር ሲል አልወድም’ የሚል ዓይነት ስሜት ያላቸው ይመስላል።”
አንዳንድ ወጣቶችም ራሳቸው እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ እንደሆነባቸው በግልጽ ይናገራሉ። የ16 ዓመቷ ስቴፋኒ እንዲህ ትላለች:- “ኢንተርኔትና ሞባይል ሱስ ሆነውብኛል። ምክንያቱም ከጓደኞቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ማድረግ የምችለው በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት ነው። እቤት እንደደረስኩ በቀጥታ ኢንተርኔት እከፍትና . . . አንዳንዴ እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ስጠቀም እቆያለሁ።” ስቴፋኒ ለስልክ በየወሩ ከ100 እስከ 500 የአሜሪካ ዶላር ታወጣለች። ስቴፋኒ አክላ እንደሚከተለው ብላለች:- “እስከ አሁን ወላጆቼን ለስልክ ተጨማሪ 2,000 የአሜሪካ ዶላር አስወጥቻቸዋለሁ። ያም ሆኖ ሞባይሌ ተለይቶኝ ስለማያውቅ ካለ እርሱ መኖር የምችል አይመስለኝም።”
ችግሩ ከወጪ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ኤሊኖር ኦክስ የተባሉ አንዲት አንትሮፖሎጂስት በቤተሰብ ሕይወት ዙሪያ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዳሉት ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ሚስትም ሆነች ልጆች በሚያደርጉት ነገር በጣም ከመመሰጣቸው የተነሳ ባል ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ ከ3 ቀናት ውስጥ በ2ቱ ‘እንደምን ዋልክ’ እንኳ አይሉትም! ትኩረታቸው ሙሉ በሙሉ የሚያርፈው በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎቻቸው ላይ ነው። ኦክስ “ወላጆች ልጆቻቸው ስለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በቅጡ ማወቅ እንኳ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ማስተዋል ችለናል” ብለዋል። አክለውም በጥናቱ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸው በሚያደርጓቸው ነገሮች ተመስጠው ሲያዩአቸው ተመልሰው ሲሄዱ ማየታቸውን ተናግረዋል።
በኢንተርኔት የሚደረገው ማኅበራዊ ግንኙነት ምንም ጉዳት የለውም?
ወጣቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ድረ ገጾችን በመጠቀም የሚያሳልፉት ጊዜ ብዙ ወላጆችንና መምህራንን ያሳስባቸዋል። እነዚህ የኢንተርኔት ገጾች አንድ ሰው ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን የሚያስገባበት ብሎም የዕለት ውሎውን የሚመዘግብበትን የራሱን ድረ ገጽ እንዲፈጥር ያስችሉታል።
እንዲህ ያሉትን የኢንተርኔት ገጾች ማራኪ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ ተጠቃሚዎቹ ከጓደኞቻቸው ጋር በቀላሉ መገናኘት መቻላቸው ነው። ሌላው ደግሞ አንድ ወጣት የራሱን ድረ ገጽ መፍጠሩ ማንነቱን ይኸውም “ሐሳቡን ለመግለጽ” የሚያስችለው መሆኑ ነው። የጉርምስና ዕድሜ አንድ ወጣት ስለ ራሱ የማወቅ እንዲሁም ሌሎችን ሊማርክና ሊቀሰቅስ በሚችል መልኩ ስሜቱን የመግለጽ ፍላጎቱ የሚያይልበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን፣ ይህ ገጽ ወጣቶችን መሳቡ ያን ያህል አያስደንቅም።
ይሁንና ችግሩ፣ አንዳንድ ሰዎች በድረ ገጻቸው ላይ የሚገልጹት እውነተኛውን ማንነታቸውን ሳይሆን ለመሆን የሚፈልጉትን መሆኑ ነው። አንድ የ15 ዓመት ልጅ “በምማርበት ክፍል ውስጥ ያለ አንድ ልጅ ዕድሜው 21 እንደሆነና በላስ ቬጋስ እንደሚኖር አድርጎ ራሱን አስተዋውቋል” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ልጆች የሚኖሩት ከላስ ቬጋስ 1,600 ኪሎ ሜትር ርቀው ነው።
እንዲህ ያለው ውሸት የተለመደ ነው። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት የ18 ዓመት ወጣት እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ተናግራለች:- “በኢንተርኔት የፈለጋችሁትን ነገር ማድረግ ትችላላችሁ። ማንም ስለማያውቃችሁ ራሳችሁን ሙሉ ለሙሉ ለውጣችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉም አትፈሩም። ራሳችሁን ማራኪ አድርጋችሁ ለማቅረብ የፈጠራ ሐሳብ ልትናገሩ ትችላላችሁ። በሕይወታችሁ ለብሳችሁት የማታውቁትን ልብስ እንደለበሳችሁ ወይም ሰርታችሁት የማታውቁትን ሥራ በመሥራት ላይ እንዳላችሁ አድርጎ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ማስገባት ትችላላችሁ። በአካል ተገናኝታችሁ ቢሆን የማትናገሯቸውን ነገሮች ለመጻፍ ትደፍራላችሁ። ማንነታችሁ ስለማይታወቅ የምታደርጓቸው ነገሮች ለችግር እንደማይዳርጓችሁ ሆኖ ይሰማችኋል። ማንም ቢሆን እውነተኛውን ማንነታችሁን አያውቅም።”
እንደማንኛውም የመገናኛ መሣሪያ ሁሉ ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ድረ ገጾችም የራሳቸው የሆነ ጥቅምም ሆነ ጉዳት አላቸው። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ በኢንተርኔት ምን እንደሚያደርጉ ታውቃላችሁ? ልጆቻችሁ ጊዜያቸውን በጥበብ እየተጠቀሙበት ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ትችላላችሁ? * (ኤፌሶን 5:15, 16) ከዚህም በላይ ተገቢ ያልሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀም ወጣቶችን ለበርካታ አደጋዎች ያጋልጣቸዋል። ከእነዚህ አደጋዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ኢንተርኔት ያለው መጥፎ ገጽታ
የተጠቃሚዎቹ ማንነት ተለይቶ የማይታወቅ በመሆኑ ኢንተርኔት በልጆች ላይ የጾታ ጥቃት ለሚያደርሱ ሰዎች ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል። ወጣቶች በኢንተርኔት ለተዋወቁት ሰው የግል መረጃዎቻቸውን ከሰጡና ከግለሰቡ ጋር በአካል ለመገናኘት
ከተስማሙ ሳያውቁት ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ። ፓረንቲንግ 911 የተባለው መጽሐፍ አንዳንድ ሰዎች ምን አመለካከት እንዳላቸው ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ልጆች ለዓመጽ ድርጊት ወይም ለጥቃት ይበልጥ የሚጋለጡት በቤታቸው አሊያም በሚጫወቱበት ሥፍራ ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ወላጆች ይበልጥ አደገኛ እንደሆነ የሚሰማቸው የጾታ ጥቃት ፈጻሚዎች በኮምፒውተር አማካኝነት ቤታቸው ድረስ ገብተው ልጆቻቸውን ሊያበላሹ የሚችሉ መሆኑ ነው።”ኢንተርኔት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። አንዳንድ ወጣቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ሌሎችን ያለማቋረጥ ይዘልፋሉ፣ ያጥላላሉ፣ ያዋርዳሉ ወይም ያስፋራራሉ። አንድን ግለሰብ ለማዋረድ ብቻ ታስበው የሚዘጋጁ ድረ ገጾች ያሉ ሲሆን ኢ-ሜይል፣ ቻት ሩሞችና እነዚህን የመሳሰሉት ሌሎች መልእክት መለዋወጫ መንገዶችም የሰዎችን ስም የሚያጠፉ ወሬዎችን ለማናፈስ ይውላሉ። በኢንተርኔት በሚላኩ መልእክቶች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ አንድ ቡድን ዳይሬክተር የሆኑ አንዲት ሴት፣ ከ10 እስከ 14 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው ይሰማቸዋል።
እርግጥ ነው፣ ሰዎች በሌሎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው አዲስ አይደለም። ይሁንና በዛሬው ጊዜ እንዲህ የሚደረገው በኢንተርኔት አማካኝነት ሲሆን የሰውን ስም ለማጥፋት ተብሎ የሚናፈሰው ወሬና ሐሜት በከፍተኛ ፍጥነት ሊዛመት ይችላል። አብዛኞቹ ወሬዎች ደግሞ እጅግ አስጸያፊ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ካሜራ ያላቸው ሞባይሎች መጥፎና አሳፋሪ የሆኑ ፎቶዎችን ለማንሳት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ምናልባትም ፎቶዎቹ የተነሱት በተማሪዎች የልብስ መቀየሪያ አሊያም የመታጠቢያ ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ፎቶዎቹ ለማየት ለሚፈልግ ለማንኛውም የኢንተርኔት ተጠቃሚ ይላካሉ።
እየተባባሰ የመጣ አሳሳቢ ጉዳይ
በኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ዲፓርትመንት ኦቭ ሎው ኤንድ ፐብሊክ ሴፍቲ የተባለ ድርጅት “ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ ለሚያደርጉት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ ለመጣው ተገቢ ያልሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀም መፍትሔ መስጠት እንድንችል የእናንተን እርዳታ እንሻለን” የሚል ደብዳቤ ለወላጆችና ለአሳዳጊዎች ለመላክ ተገድዷል። ደብዳቤው ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ልጆች የግል መረጃዎቻቸውንና ፎቶአቸውን በኢንተርኔት ላይ ማውጣታቸው እንደሆነም ጠቅሷል። እነዚህን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን የያዙ ድረ ገጾች አብዛኛውን ጊዜ የመጥፎ ወጣቶችንና ጎልማሶችን ትኩረት ይስባሉ። ደብዳቤው እንዲህ ይላል:- “ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን፣ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባችኋል፤ እንዲሁም ስለ ሁኔታው ያላችሁን እውቀት በማዳበርና የልጆቻችሁን የኢንተርኔት አጠቃቀም በመቆጣጠር ደኅንነታቸውን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት ትችላላችሁ።”
ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በኢንተርኔት አማካኝነት ምን ዓይነት መረጃዎችን እንደሚለዋወጡ እምብዛም አያውቁም ማለት ይቻላል። የ16 ዓመት ልጇን የኢንተርኔት አጠቃቀም በጥብቅ የምትከታተል አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “ወላጆች፣ ልጆቻቸው በኢንተርኔት አማካኝነት ምን እንደሚልኩና ስለምን ጉዳዮች እንደሚወያዩ ቢያውቁ መደንገጣቸውና ማፈራቸው አይቀርም።” በኢንተርኔት በሚላኩ መልእክቶች ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ አንዲት ባለሙያ፣ አንዳንድ ወጣቶች የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ፎቶዎችን እንደሚያወጡ ተናግረዋል።
መጥፎ ውጤቶች
ይህ ሁሉ ሐሳብ የወጣትነት ጊዜያቸውን እንዴት እንዳሳለፉ የዘነጉ አዋቂዎች ከልክ ያለፈ ስጋት የወለደው ማስጠንቀቂያ ነው? አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። እስቲ የሚከተለውን ተመልከት:- በአንዳንድ ቦታዎች ከ15 እስከ 17 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል። ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 19 ከሚሆኑ
ወጣቶች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአፍ የሚደረግ ወሲብ ፈጽመዋል።ለዚህ አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠር ቴክኖሎጂ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጎ ይሆን? ምን ጥያቄ አለው። ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን እንዲህ የሚል ሪፖርት አውጥቷል:- “ሞባይል ስልክም ሆነ ኢንተርኔት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነጻነት ያስገኘላቸው መሆኑ ብዙም ከማያውቁት ሰው ጋር በቀላሉ የጾታ ግንኙት እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል።” እንደ እውነቱ ከሆነ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር በድብቅ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዝ ጥቂት የኮምፒውተር ቁልፎችን ከመጫን የበለጠ ነገር አይጠይቅም። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከአምስት ልጃገረዶች መካከል አራቱ ኢንተርኔት በሚጠቀሙበት ጊዜ ያን ያህል ጥንቃቄ እንደማያደርጉ አምነዋል።
በኢንተርኔት አማካኝነት ተቃራኒ ጾታ ያለው ጓደኛ ወይም ለአንድ ቀን አብሯቸው የሚያድር ሰው የሚፈልጉ ሰዎች ይህን ግባቸውን ለማሳካት ብዙም ውጣ ውረድ አልገጠማቸውም። በካሊፎርኒያ ግዛት የኖቫቶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባልደረባ የሆኑት ጄኒፈር ዌልች ‘የጾታ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ተመልክተናል’ በማለት ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ እኚህ ሴት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ብዙ ሰዎች ጥቃት ከፈጸመባቸው ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት በኢንተርኔት መሆኑንና በኋላም በአካል ለመገናኘት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
‘ከዓለም ጥበብ’ ተጠበቁ!
ለወጣቶች የሚሆን ምክር ይዘው የሚወጡ የመጽሔትና የጋዜጣ አምዶች ወጣቶች የጾታ ግንኙነት እንዳይፈጽሙ በመምከር ረገድ የለዘብተኝነት አቋም ይታይባቸዋል። እነዚህ መጽሔቶችና ጋዜጦች መታቀብንና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ቢደግፉም ዋነኛው ግባቸው ከመታቀብ ይልቅ “በኮንዶም መጠቀምን” ማበረታታት ነው። ይህን አቋማቸውን ለማስተባበልም ‘ወጣቶችን የጾታ ግንኙነት እንዳይፈጽሙ ልንከለክላቸው አንችልም፤ ስለሆነም ቢያንስ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ልናስተምራቸው እንችላለን’ የሚል ሰበብ ይሰጣሉ።
ለወጣቶች በተዘጋጀና በጥሩነቱ አድናቆት በሚቸረው አንድ ድረ ገጽ ላይ የወጣ ጽሑፍ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት መፈጸም አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለውን ጉዳይ ባነሳበት ወቅት ግምት ውስጥ ያስገባው ሦስት ነጥቦችን ብቻ ነበር። እነርሱም:- (1) እርግዝና ሊከሰት መቻሉ (2) በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች የመጋለጥ አደጋ መኖሩ እና (3) ሁለቱ ግለሰቦች የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ከስሜት አንጻር ዝግጁ የመሆናቸው አስፈላጊነት ናቸው። ድረ ገጹ መጨረሻ ላይ “እንግዲህ ውሳኔው ለእናንተ የተተወ ነው” ይላል። ይህ ድረ ገጽ ጉዳዩን በተመለከተ ከወላጆች ጋር የመወያየቱን አስፈላጊነት ያነሳው እንዲያው እንዳይቀር ያህል ነው። በዚህ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች የጾታ ግንኙነት መፈጸማቸው ትክክል ወይም ስህተት ስለመሆኑ የጠቀሰው ነገር የለም።
ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ አስተማማኝነት ከሌለውና ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ‘የዓለም ጥበብ’ በተሻለ መመሪያ እንዲመሩ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:20) ልጆችህ በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት አደጋዎች እንዲርቁና የጉርምስና ዕድሜያቸውን በተሳካ ሁኔታ ማሳለፍ እንዲችሉ ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ኮምፒውተርን የመዝጋትን ወይም ሞባይሎቻቸውን የመንጠቅን ያህል ቀላል አይደለም። ሳይታሰብባቸው የሚወሰዱት የመፍትሔ እርምጃዎች ልብን የመንካታቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። (ምሳሌ 4:23) ልጆቻችሁ ሞባይል ስልኮችንና ኢንተርኔትን የመሳሰሉ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙት እናንተ ወላጆች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልታሟሉላቸው ለምትችሏቸው አንዳንድ ፍላጎቶቻቸው መፍትሔ ለማግኘት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይኖርባችኋል። ለመሆኑ እነዚህ ፍላጎቶቻቸው ምንድን ናቸው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 ወላጆች ኢንተርኔትን እንዲሁ በደፈናው ከማውገዝ ይልቅ ልጆቻቸው በአብዛኛው የሚመለከቷቸውን ድረ ገጾች በደንብ ቢያውቁ ጥሩ ነው። ይህም ወላጆች ልጆቻቸውን ‘መልካሙን ከክፉው መለየት’ እንዲችሉ ለመርዳት ያስችላቸዋል። (ዕብራውያን 5:14) ወላጆች የሚሰጡት እንዲህ ያለው ሥልጠና ልጆች ጎልማሳ በሚሆኑበት ጊዜም ጭምር ይረዳቸዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እቤት እንደደረስኩ በቀጥታ ኢንተርኔት እከፍትና . . . አንዳንዴ እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ስጠቀም እቆያለሁ”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በኢንተርኔት የፈለጋችሁትን ነገር ማድረግ ትችላላችሁ። ማንም ስለማያውቃችሁ ራሳችሁን ሙሉ ለሙሉ ለውጣችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ወላጆች፣ ልጆቻቸው በኢንተርኔት አማካኝነት ምን እንደሚልኩና ስለምን ጉዳዮች እንደሚወያዩ ቢያውቁ መደንገጣቸውና ማፈራቸው አይቀርም”
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በኢንተርኔት የሚደረግ ማኅበራዊ ግንኙነት የአንዲት ወጣት ተሞክሮ
“አብረውኝ ከሚማሩ ተማሪዎችና ከመምህራኖቼ ጋር በትምህርት ቤታችን ድረ ገጽ አማካኝነት መልእክት እለዋወጥ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ይህን የማደርገው በሳምንት ለአንድ ሰዓት ያህል ብቻ ነበር። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በየዕለቱ ኢንተርኔት ላይ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ። ሱስ የሆነብኝ ከመሆኑ የተነሳ ኢንተርኔት ሳልጠቀም ስቀር ስለዚያ አስብ ነበር። በሌሎች ነገሮች ላይ ማተኮር ተሳነኝ። በትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎቼ ሁሉ ወደኋላ ቀረሁ። በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ በትኩረት ማዳመጥ አቃተኝ። እንዲያውም ጓደኞቼን ሳይቀር ማነጋገር አቆምኩ። በመጨረሻም ወላጆቼ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደገባሁ በማወቃቸው በኢንተርኔት አጠቃቀሜ ላይ ገደብ አደረጉብኝ። ይህ ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በጣም ተበሳጨሁ። ነገር ግን አሁን ወላጆቼ ያን እርምጃ በመውሰዳቸው ደስተኛ ነኝ። አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ። በዚህ ሱስ በድጋሚ መያዝ ፈጽሞ አልፈልግም!”—ቢያንካ