በመላው ዓለም የሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀት
በመላው ዓለም የሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀት
በቅርቡ ለንባብ የበቃውን ዘ ቺቲንግ ካልቸር የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉት ዴቪድ ካላሃን “ማጭበርበር የሌለበት ቦታ የለም” ብለዋል። እኚህ ደራሲ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚፈጸሙት የማጭበርበር ድርጊቶች መካከል “የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የኮሌጅ ተማሪዎች የሚፈጽሙት ማታለል፣” ሙዚቃና ፊልም “በሕገወጥ መንገድ ማባዛት፣” “የሥራ ሰዓትን አለማክበርና የመሥሪያ ቤትን ንብረት መስረቅ፣” በሕገወጥ መንገድ ለመክበር ሲባል “በሕክምናው መስክ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም” እንዲሁም በስፖርቱ ዓለም ስቴሮይድ የሚባል አበረታች መድኃኒት መውሰድ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። ሲደመድሙም “ከግብረ ገብና ከሕግ አንጻር የሚፈጸሙትን የተለያዩ ጥፋቶች አንድ ላይ ስትደምሯቸው የሥነ ምግባር ውድቀቱ አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ መድረሱን ትገነዘባላችሁ” ብለዋል።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በ2005 መገባደጃ ላይ ዩናይትድ ስቴትስን የመታችው ካትሪና የተባለችው አውሎ ነፋስ “በዘመናችን ታይቶ የማይታወቅ የማጭበርበርና የማታለል ድርጊት እንዲፈጸም እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ አሠራሩ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆናለች።” የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑ አንዲት ሴት “ዓይን ያወጣው ማጭበርበር፣ ድፍረት የተሞላው ማታለልም ሆነ የሚባክነው ንብረት ብዛት እጅግ አስገራሚ ነው” በማለት ሪፖርት አድርገዋል።
እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ሰብዓዊ ርኅራኄ የሚያሳዩ ሰዎች አሉ። (የሐዋርያት ሥራ 27:3፤ 28:2) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ “ምን ጥቅም አገኝበታለሁ?” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን መስማት የተለመደ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ እኔ ልቅደም፣ ከራስ በላይ ነፋስ የሚለው አመለካከት የብዙኃኑ ፈሊጥ እየሆነ የመጣ ይመስላል።
ባለፉት ዘመናት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውና ዓይን ያወጡ የሥነ ምግባር ብልግና ድርጊቶች እንደ ሮማ ላሉ ግዛቶች ሥልጣኔ መውደቅ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆኑ ይነገራል። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉት ነገሮች ከዚያ የሚበልጥ ውድቀት መቃረቡን የሚያመላክቱ ይሆኑ? መጽሐፍ ቅዱስ የጠቅላላው ሥርዓት ፍጻሜ ምልክት እንደሆነ አድርጎ የሚናገረለት ‘እየገነነ የመጣው ክፋት’ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው?—ማቴዎስ 24:3-8, 12-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
በመላው ዓለም የሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀት
አፍሪካ ኒውስ በሰኔ 22, 2006 እትሙ ላይ በአንድ የኡጋንዳ ጎስቋላ መንደር ውስጥ ከሚፈጸመው “የጾታ ጥቃትና ከወሲባዊ ፊልሞች ስርጭት ጋር በተያያዘ የተደረገውን ጥናት” አስመልክቶ ሲዘግብ “በአካባቢው ዝሙት አዳሪዎችና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች እንዲበራከቱ ያደረገው የወላጆች ቸልተኝነት” ነው ብሏል። ጽሑፉ አክሎ “በካዌምፔ ፖሊስ ጣቢያ የሕፃናትና ቤተሰብ ደኅንነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሚስተር ዳባንጄ ሳሎንጎ ሕፃናትን በጾታ ማስነወርና በቤት ውስጥ የሚፈጸም የኃይል ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ተናግረዋል” ብሏል።
በሕንድ የሚገኙ አንድ ሐኪም “ኅብረተሰቡ ሥነ ምግባሩን እንዲጠብቅ የሚያደርጉትን ባሕላዊ እሴቶች እያጣ ነው” በማለት ተናግረዋል። አንዲት የፊልም ዳይሬክተር “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትና ልቅ የጾታ ግንኙነት ሕንድ ‘የምዕራቡ ዓለም ስድነት’ እየተጋባባት መሆኑን የሚያሳይ ሌላው ምልክት ነው” ብለዋል።
ቤጂንግ የሚገኘው የቻይና የሥነ ጾታ ማኅበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሁ ፓቼንግ “ቀደም ሲል በኅብረተሰባችን ውስጥ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ነበረ። አሁን ግን ያላንዳች ገደብ ያሻንን ማድረግ እንችላለን” ብለዋል። ቻይና ቱዴይ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ሁኔታውን እንደሚከተለው ገልጾታል:- “ኅብረተሰቡ ከጋብቻ ውጪ ለሚፈጸሙ የጾታ ግንኙነቶች ግዴለሽ እየሆነ መጥቷል።”
የእንግሊዙ ዮርክሺር ፖስት በቅርቡ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል:- “ሰው ሁሉ ሸቀጡን ለመሸጥ ሲል ልብሱን ማውለቅና ወሲብን መሣሪያ አድርጎ መጠቀም የሚፈልግ ይመስላል። ቀደም ባሉት ዓመታት እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች መፈጸም እንደ ነውር ይታይ ስለነበር ሕዝቡን ያስቆጣ ነበር። ዛሬ ግን ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምስሎች ከየአቅጣጫው የሚዥጎደጎዱብን ሲሆን ይህ ሁኔታ . . . ሥር ሰዶ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል።” ጋዜጣው አክሎ “በአንድ ወቅት ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ይፈቀዱ የነበሩ መጽሐፎች፣ መጽሔቶችና ፊልሞች አሁን በቤተሰብ ደረጃ የሚታዩ ሆነዋል፤ ፀረ ወሲባዊ ምስል ዘመቻዎችን
የሚያካሂዱ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ የብልግና ሥዕሎችና ፊልሞች ብዙውን ጊዜ በልጆች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው” ብሏል።ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት “[በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች] ምግብ ቤት ገብተው ስለ ምግቡ ዝርዝር ሲነጋገሩ ምንም ዓይነት የሃፍረት ስሜት እንደማይሰማቸው ሁሉ [ከወሲብ ጋር በተያያዘ ስላጋጠሟቸው ነገሮች] ሲወያዩም ምንም አይሸማቀቁም” ብሏል። “ከ8 እስከ 12 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ላሏቸው ወላጆች የሚጠቅም መመሪያ” የያዘ ትዊንስ ኒውስ የተሰኘ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “አንዲት ልጃገረድ ሕፃን ልጅ የሞነጫጨረው በሚመስል የእጅ ጽሑፍ የሚከተለውን ቅስም የሚሰብር መልእክት ጻፈች:- ‘እናቴ የወንድ ጓደኛ እንድይዝና ወሲብ እንድፈጽም ትገፋፋኛለች። እኔ ገና 12 ዓመቴ ነው። . . . እባካችሁ እርዱኝ!’”
ጊዜው ምንኛ ተለውጧል! የካናዳው ቶሮንቶ ስታር ከቅርብ ጊዜ በፊት “ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶች ወይም ሴቶች በግልጽ አብረው መኖራቸው እንደ ነውር ስለሚታይ ኃይለኛ ቁጣ ይቀሰቅስ ነበር” በማለት ገልጿል። ሆኖም ኦታዋ በሚገኘው ካርልተን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኅብረተሰብ ታሪክ አስተማሪ የሆኑት ባርባራ ፍሪማን አሁን ያለውን ዝንባሌ በሚመለከት “ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ‘የግል ሕይወት የግል ነው፤ ማንም ጣልቃ እንዲገባብን አንፈልግም’ ይላሉ” በማለት ተናግረዋል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በመላው ዓለም የሰዎች ሥነ ምግባር በፍጥነት አሽቆልቁሏል። ለእነዚህ ሥር ነቀል ለውጦች መከሰት ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? አንተ በግልህ ስለ እነዚህ ለውጦች ምን ይሰማሃል? ለውጦቹ ስለወደፊቱ ጊዜ ምን ያመላክታሉ?