ከአልኮል መጠጥ ባርነት ነጻ መውጣት
ከአልኮል መጠጥ ባርነት ነጻ መውጣት
የአልኮል መጠጥን በልክ ማቅረብ በምግብ ሰዓት ገበታን የተሟላ ሊያደርግ ወይም ለአንድ ሥነ ሥርዓት ድምቀት ሊጨምር ይችላል። አንዳንዶችን ግን የአልኮል መጠጥ መጠጣት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይከታቸዋል። እስቲ ከአልኮል መጠጥ ሱስ መላቀቅ ስለቻለ ሰው የሚናገረውን የሚከተለውን ታሪክ ተመልከት።
በቤታችን ነግሦ ስለነበረው ውጥረት መናገር አሁን ድረስ የስሜት ሥቃይ ያስከትልብኛል። አባባና እማማ መጠጣት ይጀምራሉ፤ ከዚያም አባባ እማማን ይደበድባታል። ብዙውን ጊዜ እኔም ቡጢ አይቀርልኝም ነበር። ለመለያየት በወሰኑበት ወቅት እኔ ገና የአራት ዓመት ልጅ ነበርኩ። አያቴ ቤት እንድኖር ሲወስዱኝ የነበረው ሁኔታ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል።
ፍጹም እንደማልፈለግ ተሰማኝ። የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ድምፅ ሳላሰማ ወደ ምድር ቤት እሄድና ቤት የተጠመቀ ወይን ጠጅ እጠጣ ነበር። እንዲህ የማደርገው ሐዘኔን የሚያስታግስልኝ ስለሚመስለኝ ነበር። አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላኝ እናቴና አያቴ በእኔ የተነሳ ተበጣበጡ። እናቴ በጣም ከመናደዷ የተነሳ መንሽ ወረወረችብኝ። ይሁንና እንደምንም ብዬ አመለጥኳት! እንዲህ ያለ አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ይህ የመጀመሪያዬ አልነበረም። ያም ሆኖ ሰውነቴን የወረሰው ጠባሳ በውስጤ ተቀብሮ የሚገኘውን የስሜት ጠባሳ ያህል የከፋ አልነበረም።
አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ የወጣልኝ ጠጪ ሆንኩ። በመጨረሻም በ17 ዓመቴ ከቤት ጠፍቼ ወጣሁ። መጠጥ፣ ነጻ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ስለነበር በጣም ጠበኛ ሆንኩ፤ በመሆኑም በአካባቢው በሚገኙ መጠጥ ቤቶች እየገባሁ ችግር መፍጠር ጀመርኩ። በሕይወቴ ውስጥ የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር መጠጥ ብቻ ነበር። በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ አምስት ሊትር ወይን ጠጅ፣ ጥቂት ጠርሙስ ቢራና ኃይለኛ አረቄ እጠጣ ነበር።
ትዳር ከመሠረትኩ በኋላ ደግሞ ባለቤቴ በዚህ አመሌ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ላይ ወደቀች። ብስጭቴና ምሬቴ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመጨመሩ ባለቤቴንም ሆነ ልጆቼን እደበድባቸው ነበር። በመሆኑም የቤተሰባችን ሁኔታ እኔ ካደግሁበት ቤት የማይሻል ሆነ። የማገኘውን ገንዘብ በሙሉ እጠጣበት ነበር ለማለት ይቻላል። ምንም የቤት ዕቃ ስላልነበረን እኔና ባለቤቴ የምንተኛው መሬት ላይ ነበር። የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ ስለማላውቅ ሁኔታውን ለማሻሻል ምንም ያደረግኩት ጥረት የለም።
አንድ ቀን ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተወያየሁ። ሥቃይና መከራ የበዛው ለምን እንደሆነ ስጠይቀው አምላክ ከችግር ነጻ የሆነ ዓለም ለማምጣት የገባውን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየኝ። ያቀረበልኝ አሳማኝ ማስረጃ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንድጀምር አነሳሳኝ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል ስጀምርና የምወስደውን የመጠጥ መጠን ስቀንስ የቤተሰባችን ሁኔታ በጣም እየተሻሻለ ሄደ። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል ከፈለግሁ በአልኮል
መጠጥ ረገድ ያለብኝን ችግር ማሸነፍ እንዳለብኝ ተገንዝቤ ነበር። ከሦስት ወራት ብርቱ ትግል በኋላ ከአልኮል መጠጥ ሱስ ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆንኩ። ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ራሴን ለአምላክ ወስኜ ተጠመቅሁ።የአልኮል መጠጥ ባሪያ ከመሆን ስለተላቀቅሁኝ ያሉብኝን የገንዘብ ዕዳዎች በሙሉ መክፈል ቻልኩ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ቤትና መኪና የገዛሁ ሲሆን መኪናውን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ላይ ለመካፈል እንጠቀምበታለን። ይህን ሁሉ ካደረግኩ በኋላ ለራሴ አክብሮት ይሰማኝ ጀመር።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ስገኝ የአልኮል መጠጥ እንድጠጣ ይጋብዙኛል። ብዙ ሰዎች ከዚህ ቀደም ያደረግኩትን ብርቱ ትግል እንዲሁም አንድ ብርጭቆ እንኳ መጠጣቴ ወደነበርኩበት ሕይወት ሊመልሰኝ እንደሚችል አያውቁም። የአልኮል መጠጥ አምሮት አሁንም ያስቸግረኛል። ይሁን እንጂ አልጠጣም ለማለት ከልቤ መጸለይና ባደረግኩት ውሳኔ ቆራጥ መሆን ይጠይቅብኛል። ውኃ ሲጠማኝ አልኮልነት የሌላቸውን መጠጦች የቻልኩትን ያህል እጠጣለሁ። አልኮል የሚባል ነገር ከቀመስኩ አሁን አሥር ዓመት ሆኖኛል።
ይሖዋ ከሰው አቅም በላይ የሆነውን ነገር ማድረግ ይችላል። አገኘዋለሁ ብዬ አስቤው የማላውቀውን ነጻነት እንዳገኝ ረድቶኛል! አሁንም ቢሆን የልጅነት ሕይወቴ ያስከተለብኝ የስሜት ጠባሳ ስላልሻረልኝ ወደ አእምሮዬ ከሚመጡብኝ አሉታዊ አስተሳሰቦች ጋር ያልተቋረጠ ትግል አደርጋለሁ። በሌላ በኩል ግን ከአምላክ፣ እውነተኛ ጓደኞችን ማፍራት ከቻልኩበት ጉባኤና እምነቴን ከሚጋራው ግሩም ቤተሰብ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ባለቤቴና ልጆቼ ከአልኮል መጠጥ ጋር በማደርገው ትግል በሙሉ ልባቸው ይደግፉኛል። ባለቤቴ “ከዚህ በፊት ሕይወቴ ሥቃይ የበዛበት ነበር። አሁን ግን ከባለቤቴና ከሁለት ልጆቼ ጋር ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ስላለኝ ይሖዋን በጣም አመሰግናለሁ” ብላለች።—ተጽፎ የተላከልን።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ የወጣለት ጠጪ ሆንኩ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ ከሰው አቅም በላይ የሆነውን ነገር ማድረግ ይችላል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስ እና የአልኮል መጠጥ
▪ መጽሐፍ ቅዱስ አልኮል መጠጣትን አያወግዝም። እንዲያውም ‘የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኘው ወይን’ ሰዎች ከአምላክ በስጦታ ያገኙት እንደሆነ ይገልጻል። (መዝሙር 104:14, 15) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ወይንን የብልጽግናና የደኅንነት ተምሳሌት እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (ሚክያስ 4:4) እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጸማቸው ተአምራት የመጀመሪያው በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ነበር። (ዮሐንስ 2:7-9) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ‘ደጋግሞ በሚነሣበት ሕመም’ እንደሚሠቃይ ሲሰማ “ጥቂት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ ሐሳብ አቅርቦለት ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:23
▪ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣትን ያወግዛል:-
“ሰካራሞች . . . በፍጹም የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮንቶስ 6:9-11፣ “ዘ ጀሩሳሌም ባይብል”
“በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።”—ኤፌሶን 5:18
“ዋይታ የማን ነው? ሐዘንስ የማን ነው? ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው? በከንቱ መቍሰል የማን ነው? የዐይን ቅላትስ የማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤ እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው። መልኩ ቀይ ሆኖ፣ በብርጭቆ ውስጥ ሲያንጸባርቅ፣ ሰተት ብሎ በሚወርድበትም ጊዜ፣ ወደ ወይን ጠጅ ትክ ብለህ አትመልከት። በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል። ዐይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤ አእምሮህም ይቀባዥራል።”—ምሳሌ 23:29-33
ከላይ ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው አልኮል የመጠጣት ችግር የነበረባቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከዚህ በመታቀብ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ አድርገዋል።—ማቴዎስ 5:29