ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
የወጣቶች ጥያቄ . . . ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ይኖርብኝ ይሆን? (ጥቅምት 2006) ይህንን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ በጣም ተጨንቄአለሁ። ሕይወቴን በሙሉ ሥር ከሰደደ የአመጋገብ ችግር ጋር ስታገል ኖሬአለሁ። በጽሑፉ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ይህን ችግር “ማስወገድ” የነበረብኝ ወጣት በነበርኩበት ወቅት እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርጓል። እስካሁን ድረስ ከዚህ ችግር ጋር ስታገል ቆይቻለሁ፤ አሁን ግን ተስፋ ቆርጫለሁ። ይህ ርዕስ አንድ ሰው ይህንን ችግር ማሸነፍ የሚችለው ጠንካራ እምነት ካለው ብቻ እንደሆነ ይናገራል።
ጄ. ጄ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው አምድ ሥር የሚወጡት ትምህርቶች በዋነኝነት የተዘጋጁት ለወጣቶች ቢሆንም በትምህርቶቹ ላይ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚሠሩ ናቸው። ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር፣ ለማሸነፍ ከፍተኛ ትግል ከሚጠይቁ ችግሮች መካከል አንዱ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህ ጽሑፍ ከአመጋገብ ችግር ጋር የሚታገሉ ሰዎች እምነት አንሷቸዋል አይልም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ችግር የሚሠቃዩ ሰዎች ችግሩን ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ እንዲጸልዩ ሐሳብ ያቀርባል። ከአምላክ እርዳታ ከመጠየቅ በተጨማሪ እነዚህ ሰዎች ‘ከወላጅ ወይም ሊረዳቸው ከሚችል ሰው’ እርዳታ እንዲጠይቁ ያበረታታል። ከዚህም በላይ ጽሑፉ “ከዚህ ችግር ለመላቀቅ የሚደረገው ትግል ቀላል እንዳልሆነ” እና ሊያገረሽ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል። ከበርካታ ዓመታት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አመጋገብን በተመለከተ ካለብሽ ችግር ጋር ትግል ማድረግሽ ተስፋ እንዳልቆረጥሽ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
የወጣቶች ጥያቄ . . . ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል? (ሐምሌ 2006) መደበኛ ትምህርቴን በቅርቡ ስለምጨርስ የምከተለውን የሕይወት አቅጣጫ በሚመለከት ዕቅድ የማወጣበት ትክክለኛ ወቅት ላይ እገኛለሁ። ይህ ርዕስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር የነበረኝን ግብ ይበልጥ እንዳጠናክር ረድቶኛል። ከዚህ ሌላ ጠቃሚና ደስታ የሚያስገኝልኝ ሥራ የለም።
ኤች. ደብሊው.፣ ሆንግ ኮንግ
ይህ ርዕስ፣ ቁሳዊ ሀብትን በሚያሳድደው በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ እኔ ላሉ ወጣቶች ለመንፈሳዊ ግቦች ቅድሚያ ከመስጠት የተሻለ ጠቃሚ ነገር አለመኖሩን እንዳስተውል ስለረዳኝ በጣም አመሰግናለሁ።
ኤ. ኤስ.፣ ብራዚል
በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ተወጥሬ ስለምውል ብዙውን ጊዜ ስለ ግቦቼ አስቤ አላውቅም። ይህን ርዕስ ማንበቤ ይሖዋን ለማገልገል የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ የነበረኝን ቁርጥ ውሳኔ እንዳጠናክር ረድቶኛል። ለእኛ ለወጣቶች ስለምታስቡልን በጣም አመሰግናችኋለሁ።
ኢ. ኤም.፣ ጃፓን
ደስታ የሰፈነበት ትዳር መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው? (ሐምሌ 2006) እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች በጣም ድንቅ ናቸው። የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ሌላውን እንዴት መያዝ እንደሚኖርባቸው ለማስረዳት ኢየሱስንና እርሱ ሐዋርያቱን የያዘበትን መንገድ እንደ ምሳሌ አድርገው ተጠቅመዋል። እባካችሁ በዚሁ ግፉበት። በየወሩ መጽሔቶቻችንን የምናገኝበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።
ኤስ. ኬ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ተስፋ ቢስ የነበርኩ ቢሆንም አሁን ደስተኛ ሆኛለሁ። (ሐምሌ 2006) እንደ ወንድም ጎንዛሌዝ ሁሉ እኔም ከሚሰማኝ የዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር እታገላለሁ። ‘ይሖዋ ከዚህ በፊት ባሳለፍኩት በኃጢአት የተሞላ ሕይወት ምክንያት ሊወደኝ አይችልም’ ብዬ አስብ ነበር። ይሖዋ በእርግጥም ደግ፣ መሐሪና አፍቃሪ መሆኑን ማወቅ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ከጉባኤው ባገኘሁት ምክርና ፍቅራዊ ድጋፍ እንዲሁም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ችያለሁ። ወቅታዊ ለሆነው ለዚህ መንፈሳዊ ምግብ አመሰግናችኋለሁ።
ቲ. ኤ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ