“በእርግጥ ስንፈልገው የነበረ ነው!”
“በእርግጥ ስንፈልገው የነበረ ነው!”
ይህ በጣሊያን የምትኖር አንዲት እናት ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ በደረሳት ጊዜ የተናገረችው የአድናቆት ቃል ነው። ይህቺ እናት “እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም” በማለት ተናግራለች። ትንሽ ልጇን አስመልክታ ስትናገርም እንዲህ ብላለች:- “ልጄ ማንበብ ባትችልም ሥዕሎቹን በመመልከት ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ማስታወስ ችላለች። መጽሐፉ የተጻፈው አንባቢው ስሜቱን እንዲገልጽ በሚገፋፋ መንገድ በመሆኑ ልጄ ጥናቱን በጣም በጉጉት ትከታተላለች፤ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ተሳትፎ ታደርጋለች። ከዚህ የተሻለ ስጦታ አግኝተን አናውቅም።”
በጣሊያን የሚኖር አንድ አባት እርሱና ባለቤቱ የጾታ ግንኙነትን በተመለከተ ትንሹ ልጃቸውን እንዴት እንደሚያስረዱት ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። እንዲህ ብለዋል:- “ይህ አዲስ ጽሑፍ ሲወጣ አምላክ ጭንቀታችንን የተረዳልን ያህል ተሰማን። ጽሑፉን ካነበብነው በኋላ ይህ አዲስ መጽሐፍ ልጃችን ጥሩ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖረው በእጅጉ ሊረዳው እንደሚችል ተነጋገርን።”
በልጅነቷ ጾታዊ ትንኮሳ ተፈጽሞባት የነበረች በጃፓን የምትኖር አንዲት ወጣት ለመጽሐፉ ያላትን አድናቆት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩ ከመሆኑም በላይ ደግሜ ደጋግሜ ይሖዋን አመስግኜዋለሁ። መጽሐፉ በዚህ ክፉ ዘመን ልጆች ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ነገሮች በግልጽና በትክክል ይናገራል። ጥያቄዎቹ አንድ ልጅ ውስጣዊ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር የሚያበረታቱ ናቸው። ምዕራፍ 32 ልጆችን ከክፉ ሰዎች ለመጠበቅ በጣም ጠቃሚ ነው! ከ20 ዓመት በፊት እንዲህ ያለ ግልጽ ሐሳብ የያዘ የማስተማሪያ መሣሪያ አግኝቼ ቢሆን ኖሮ ሕይወቴን ከዚህ በተሻለ ሁኔታ መምራት በቻልኩ ነበር።”
እርስዎም ውብ ሥዕሎችን የያዘውና ከዚህ መጽሔት ጋር ተመሳሳይ መጠን ያለው ይህ ባለ 256 ገጽ መጽሐፍ እንዲላክልዎት መጠየቅ ይችላሉ። ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።