ሐሜቱን እንዴት ማስቆም እችላለሁ?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ሐሜቱን እንዴት ማስቆም እችላለሁ?
“በአንድ ወቅት በአንድ የጭፈራ ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ነበር። በማግስቱ፣ በግብዣው ላይ ከነበሩት ወንዶች መካከል ከአንዱ ጋር የጾታ ግንኙነት እንደፈጸምኩ ተወራ። ይህ ፍጹም ከእውነት የራቀ ነበር!”—ሊንዳ *
“አንዳንድ ጊዜ ከአንዲት ልጅ ጋር ጓደኝነት እንደመሠረትኩ ሲወራ እሰማለሁ። እውነቱን ለመናገር ልጅቷን ጭራሽ አላውቃትም! ሐሜተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች የሚያወሩት ነገር እውነት ይሁን አይሁን ብዙም አይጨነቁም።”—ማይክ
ሐሜት ከአንድ ፊልም የበለጠ ቀልብህን ሊስብ ይችላል። የ19 ዓመቷ አምበር እንዲህ ብላለች:- “ብዙ ጊዜ መጥፎ ነገር ይወራብኛል። እንዳረገዝኩ፣ እንዳስወረድኩ፣ ዕፅ እንደማዘዋውርና እንደምወስድ በተለያዩ ጊዜያት ተወርቶብኛል። ሰዎች እንዲህ ያለ ነገር የሚያወሩብኝ ለምንድን ነው? እውነቱን ለመናገር ምክንያቱን አላውቅም!”
በረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚሠራጭ ሐሜት
ወላጆችህ ወጣት በነበሩበት ወቅት ወሬ የሚሠራጨው በአፍ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን ሐሜት የሚዛመተው በረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሆኗል። አንድ ልጅ በተንኮል ተነሳስቶ ኢንተርኔትና ሌሎች ፈጣን የመልእክት መለዋወጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ምንም ቃል ሳይተነፍስ ስምህን ማጥፋት ይችላል። ሐሜት ለሚወዱ ሰዎች መጥፎ ወሬዎችን ለመላክ የሚያስፈልገው ጥቂት ፊደላትን መምታት ብቻ ነው።
አንዳንዶች እንደሚሉት ወሬን በፍጥነት በማሰራጨት ረገድ ከስልክ ይልቅ ኢንተርኔት ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። እንዲያውም አንድን ሰው ለማዋረድ ሲባል አንድ ራሱን የቻለ ድረ ገጽ የሚከፈትበት ጊዜ አለ። አብዛኛውን ጊዜ የግል መረጃዎችን ለማሰራጨት ተብለው የሚዘጋጁ ድረ ገጾች ፊት ለፊት ቢሆን ኖሮ በማይነገሩ ወሬዎች የተሞሉ ናቸው። በእርግጥም አንድ ጥናት እንዳመለከተው 58 በመቶ የሚያህሉ ወጣቶች በኢንተርኔት አማካኝነት መጥፎ ወሬ እንደተወራባቸው ተናግረዋል።
ሐሜት ይህን ያህል የተለመደ የሆነው ለምንድን ነው?
ስለ ሌሎች ማውራት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
ለሚከተለው ጥያቄ መልስ ስጥ።
ስለ ሌሎች ማውራት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። □ እውነት □ ሐሰት
ፊልጵስዩስ 2:4 ኒው ሴንቸሪ ቨርዥን) ይህ ሲባል ግን በማይመለከተን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንገባለን ማለት አይደለም። (1 ጴጥሮስ 4:15) ይሁንና እገሌ አገባ፣ እገሌ ልጅ ወለደ፣ እገሌ እኮ እንዲህ ያለ ችግር አጋጠመው እንደሚሉት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተን መጨዋወታችን ስለዚያ ሰው ጠቃሚ መረጃዎችን እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል። ደግሞም ስለ ሌሎች ሰዎች አንስተን ካላወራን ስለ እነሱ እናስባለን ማለት አንችልም።
ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ምንድን ነው? ወሬው ተራ ጭውውት ከሆነ ተገቢ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የሌሎች ሰዎች ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ሁኑ” በማለት ይነግረናል። (ይሁን እንጂ ተራው ጭውውት ሳይታወቅ ወደ ሐሜት ሊለወጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል “ቶማስና ሊዲያ ቢጋቡ ጥሩ ባልና ሚስት ይወጣቸዋል” የሚለው ተራ ወሬ ዞሮ ዞሮ “ቶማስና ሊዲያ ባልና ሚስት ናቸው” ተብሎ ይወራ ይሆናል። ይሁንና እነዚህ ሁለት ሰዎች በመካከላቸው ምንም ዓይነት ግንኙነት ላይኖር ይችላል። ምናልባት ይህ ወሬ የተወራው በአንተ ላይ እስካልሆነ ድረስ ምን ችግር አለው ትል ይሆናል!
የ18 ዓመቷ ጁሊ እንዲህ ያለው ሐሜት ተወርቶባት ስሜቷ ተጎድቷል። “ሁኔታው በጣም ነው ያናደደኝ። ሰውን ሁሉ እንድጠራጠር አድርጎኛል” በማለት ተናግራለች። የ19 ዓመቷ ጄንም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች:- “ጓደኝነት እንደመሠረትን የተወራብኝን ልጅ ዘጋሁት። ይሁንና ስለተወራብኝ ብዬ ከእሱ ጋር የነበረኝን ቅርርብ ሙሉ በሙሉ ማቋረጤ ትክክል አልነበረም።”
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሐሜት ከዚህም የከፋ ጉዳት አለው። ይሁን እንጂ በሐሜት ምክንያት የተጎዱ ሰዎች እነሱም በአንድ ወቅት ሌሎችን እንዳሙ ተናግረዋል። አንድ ሰው በክፉ ሲነሳ እኛም ስለ ግለሰቡ የሚሰማንን ለመናገር ልንፈተን እንችላለን። ለምን? የ18 ዓመቱ ፊሊፕ “ይህ ከችግር ማምለጫ ዘዴ ነው፤ ሰዎች ከራሳቸው ይልቅ በሌሎች ሰዎች ችግር ላይ ማተኮር ይቀናቸዋል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ይሁንና ተራው ጭውውት ወደ ሐሜት ቢቀየር ምን ማድረግ ትችላለህ?
ርዕሱን በዘዴ ቀይር!
መኪና በሚበዛበት መንገድ ላይ ማሽከርከር ጥሩ ችሎታ ይጠይቃል። እንዲህ ባለ መንገድ ላይ ስታሽከረክር ድንገት መስመርህን እንድትቀይር፣ ፍጥነትህን እንድትቀንስ አሊያም ከናካቴው እንድታቆም የሚያስገድድ ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል። ንቁና ጠንቃቃ አሽከርካሪ ከሆንክ ምን ነገር ሊከሰት እንደሚችል አስቀድመህ በማስተዋል አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለህ።
ጭውውት ማድረግን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጭውውቱ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ሐሜት መቀየሩን በቀላሉ ማስተዋል ትችላለህ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ከላይ እንዳየነው አሽከርካሪ መስመርህን በዘዴ መቀየር ትችላለህ? ምን ሊከሰት እንደሚችል አስተውለህ እንዲህ ያለ እርምጃ ካልወሰድህ ሐሜቱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ማይክ እንዲህ ብሏል:- “ስለ አንዲት ልጅ ‘ያየችው ወንድ ሁሉ አይለፈኝ ትላለች’ በማለት መጥፎ ነገር ተናግሬ ነበር። ይህ ወሬ ልጅቷ ጆሮ ደረሰ። አሳቢነት በጎደለው አነጋገሬ በጣም ተጎድታ መጥታ ስታነጋግረኝ የነበራት የጽምፅ ቃና ከአእምሮዬ አይጠፋም። በወቅቱ ተነጋግረን ችግሩን ፈታነው፤ ሆኖም በዚህ መንገድ ሰውን መጉዳቴን ሳስበው በጣም ይሰማኛል!”
ተራው ጭውውት አቅጣጫውን ስቶ ወደ ሐሜት መቀየሩን ስናስተውል ርዕሱን መለወጥ ድፍረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። የሆነ ሆኖ ሁኔታው የ17 ዓመቷ ካሮሊን እንደገለጸችው ነው። እንዲህ ብላለች:- “ስለምትናገረው ነገር መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ወሬውን የሰማኸው ከታመነ ምንጭ ካልሆነ ውሸት ልታዛምት ትችላለህ።”
ከሐሜት ለመቆጠብ ቀጥሎ በተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን ምክሮች ተከተል:-
“ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።” (ምሳሌ 10:19) ብዙ ባወራህ መጠን በኋላ የምትቆጭበትን ነገር መናገርህ አይቀርም። ለፍላፊ ነው ከመባል ይልቅ ጥሩ አዳማጭ ነው የሚል ስም ማትረፍ የተሻለ ነው!
“የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤ የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል።” (ምሳሌ 15:28) ከመናገርህ በፊት አስብ!
“ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌሶን 4:25) ስለ አንድ ጉዳይ ከማውራትህ በፊት እውነት መሆኑን አረጋግጥ።
“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ሉቃስ 6:31) ነገሩ እውነት ቢሆንም እንኳ ስለ አንድ ሰው ከመናገርህ በፊት እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘እኔ በዚያ ሰው ቦታ ብሆንና አንድ ሰው ስለ እነዚህ ነገሮች በግልጽ ቢያወራብኝ ምን ይሰማኛል?’
“ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ።” (ሮሜ 14:19) አንድ ሐሳብ እውነት ቢሆንም እንኳ የሚያንጽ እስካልሆነ ድረስ ጎጂ ሊሆን ይችላል።
“በገዛ እጃችሁ ሥሩ፤ በጸጥታ ኑሩ፤ በራሳችሁ ጒዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ።” (1 ተሰሎንቄ 4:11) በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ከልክ በላይ አትጠመድ። ጊዜህን በተሻለ መንገድ ልትጠቀምበት ትችላለህ።
ሐሜቱ የተወራው በአንተ ላይ ቢሆንስ?
አንድ ሰው አንደበቱን መቆጣጠርና ሌሎችን ከማማት መቆጠብ አለበት ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። ይሁንና ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት የምትሰጠው የታማኸው አንተ በምትሆንበት ጊዜ ነው። ሐሜት የተወራባት የ16 ዓመቷ ጆአን እንዲህ ብላለች:- “ከዚያ በኋላ ጓደኛ የሚባል ነገር እንደማይኖረኝ ተሰምቶኝ ነበር። አንዳንዴ እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ አለቅስ ነበር። ስሜ ሙሉ በሙሉ እንደጠፋ ተሰማኝ!”
መሠረተ ቢስ ወሬ ተወርቶብህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
▪ ምክንያቱን ለመረዳት ሞክር። ሰዎች ሐሜት እንዲናገሩ የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርግ። አንዳንዶች እንዲህ የሚያደርጉት ስለ ጉዳዩ የተሻለ እውቀት እንዳላቸው ለማሳየት ነው። የ14 ዓመቷ ካረን “አንዳንዶች ስለ ሌሎች በማውራት ሰዎች ብዙ እውቀት አላቸው ብለው ስለ እነሱ እንዲያስቡ ማድረግ ይፈልጋሉ” በማለት ተናግራለች። አንዳንድ ወጣቶች ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ሲሉ ሌሎችን ያጣጥላሉ። የ17 ዓመቷ ረኔ ደግሞ ሌላውን ምክንያት ስትጠቅስ “ሰዎች ስለሚሰላቹ አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ ያልሆነ ታሪክ ይፈጥራሉ” ብላለች።
▪ ስሜትህን ተቆጣጠር። በሐሜት የተጎዳና የተሰማውን የሃፍረት ብሎም የብስጭት ስሜት መቆጣጠር ያልቻለ ሰው የኋላ ኋላ የሚጸጸትበትን አንድ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ምሳሌ 14:17 “ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል” ይላል። ስሜትን መቆጣጠር የመናገሩን ያህል ቀላል ባይሆንም እንዲህ ባለው ወቅት መታገስ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግህ ያማህ ግለሰብ በተያዘበት ወጥመድ ውስጥ ከመግባት ትድናለህ።
▪ ለማለት የተፈለገውን ለመረዳት ጣር። እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘የሰማሁት ነገር በእርግጥ ስለ እኔ የተወራ ነው? ሐሜት ነው ወይስ እኔ በተሳሳተ መንገድ ተረድቼው ነው? በቀላሉ የምጎዳ ሰው ሆኜ ይሆን?’ እርግጥ ነው፣ ሐሜት ምንጊዜም ቢሆን ተገቢ አይደለም። ቢሆንም ከመጠን በላይ መቆጣትህ ሐሜቱ ካደረሰብህ የበለጠ ጉዳት ሊያስከትልብህ ይችላል። የረኔ ዓይነት አስተሳሰብ ቢኖርህ ጥሩ ነው። እንዲህ ብላለች:- “አንድ ሰው ስለ እኔ መጥፎ ነገር ሲናገር በጣም አዝናለሁ፤ ሆኖም ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት እሞክራለሁ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ስለ ሌላ ሰው ወይም ስለ ሌላ ነገር ያወሩ ይሆናል።” *
ከሁሉ የተሻለው መከላከያ
መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ይላል። (ያዕቆብ 3:2) በመሆኑም ስለ እኛ የሚነገረውን እያንዳንዱን ወሬ አክብደን መመልከት ጥቅም የለውም። መክብብ 7:22 “ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና” ይላል።
የተወራብህ ሐሜት እውነትነት እንደሌለው ማሳየት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ መልካም ባሕርይህ ነው። ኢየሱስ “ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19) በመሆኑም ምንጊዜም ተግባቢና አፍቃሪ ለመሆን ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ ሐሜቱን በፍጥነት ለማስቆም አሊያም የሚያስከትለውን ውጤት በጽናት ለመቋቋም እንደሚያስችልህ ስታይ ትገረም ይሆናል።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.33 አንዳንድ ጊዜ ሐሜተኛውን ቀርቦ ማነጋገሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ‘ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ስለሚሸፍን’ እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 4:8
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ ሐሜት ከማዛመት መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው?
▪ አንድ ሰው ቢያማህ ምን ታደርጋለህ?