በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀድሞውንም ቢሆን የተፈሩት “አጥፊ መሣሪያዎች”

ቀድሞውንም ቢሆን የተፈሩት “አጥፊ መሣሪያዎች”

ቀድሞውንም ቢሆን የተፈሩት “አጥፊ መሣሪያዎች”

“የሰው ክፉ አእምሮ፣ በሥራው ውጤት መሰሎቹ የሆኑትን የሰው ዘሮች እንዴት አድርጎ እንደሚጨቁን፣ እንደሚያጠፋ ወይም እንደሚያታልል ሲያውጠነጥን ውሎ ያድራል።” —ሆራስ ዎልፖል፣ የ18ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ጸሐፊ

የበረራ ጥበብ ለሰው ልጆች በርካታ ጥቅሞች አስገኝቷል። ይሁን እንጂ ሆራስ ዎልፖል የተናገራቸው ከላይ ያሉት ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! የሰው ልጅ በአየር ላይ የመብረር ሕልሙ እውን ከመሆኑ በፊትም እንኳ ሰዎች በራሪ ማሽኖችን እንዴት አድርገው ለጦር መሣሪያነት እንደሚጠቀሙባቸው ሲያስቡ ቆይተዋል።

ሰዎች በባሉን አየር ላይ መንሳፈፍ ከመጀመራቸው ከመቶ ዓመት በፊት ማለትም በ1670 ፍራንቼስኮ ላና የተባሉ ጣሊያናዊ ቄስ “አምላክ ተራውን ሕዝብም ሆነ መንግሥታትን ሊያውኩ የሚችሉ በርካታ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ሲል እንዲህ ያለ መሣሪያ እንዲሠራ በፍጹም አይፈቅድም” በማለት ግምታዊ ሐሳብ ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ችግር አስመልክተው እንዲህ በማለት አክለው ተናግረዋል:- “አውሮፕላኑ በማንኛውም ሰዓት ቀጥታ ወደ ገበያ ቦታ መጥቶ ሰዎችን ሊያራግፍ ስለሚችል የትኛዋም ከተማ ብትሆን ከድንገተኛ ጥቃት ልታመልጥ እንደማትችል [የማይታየው] ማን ነው? የግለሰቦች ግቢም ሆነ ባሕር በማቋረጥ ላይ ያሉ መርከቦች ተመሳሳይ ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል . . . እዚያው አየር ላይ እንዳለ ብረታ ብረቶችን ሊጥልና መርከብ ሊያሰምጥ ብሎም ሰዎችን ሊገድል ይችላል። በተጨማሪም መርከቦች እሳት የሚያስነሳ ነገርና ቦምብ ተወርውሮባቸው ሊጋዩ ይችላሉ።”

በ18ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ በሞቃት አየርና በሃይድሮጅን የተሞሉ ባሉኖች ከተፈለሰፉ በኋላ፣ ዎልፖል እነዚህ ተንሳፋፊ ነገሮች ብዙም ሳይቆይ ‘የሰውን ዘር የሚያጠፉ መሣሪያዎች’ እንደሚሆኑ ስጋት አድሮበት ነበር። እንደተፈራውም በ1794 ማብቂያ አካባቢ የፈረንሳይ የጦር ጄኔራሎች የጠላት ጦር ሰፈሮችን ለመሰለልና ወታደሮቻቸውን ወደዚያ በዘዴ ለማስገባት በሃይድሮጅን የተሞሉ ባሉኖችን ተጠቅመዋል። ባሉኖች በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅትም ሆነ በ1870ዎቹ ዓመታት በፈረንሳይና በጀርመን መካከል በተደረገው ጦርነት ጥቅም ላይ ውለው ነበር። ባለፈው መቶ ዘመን በተደረጉት በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ላይም የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይና የጀርመን ወታደሮች የጠላትን ክልል ለመቃኘት ባሉኖችን በሰፊው ተጠቅመውባቸዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓን የጦር ኃይል ቦምብ የጫኑ 9,000 ሰው አልባ ባሉኖችን ወደ አሜሪካ በላከ ጊዜ በእርግጥም ባሉኖች የጥፋት መሣሪያ መሆናቸው ግልጽ ሆነ። ከ280 በላይ የሚሆኑ ቦምብ የጫኑ ባሉኖች እስከ ሰሜን አሜሪካ ደርሰው ነበር።

የአየር ላይ የጦር መሣሪያዎች

አውሮፕላን ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጦር መሣሪያነት ለመጠቀም ይታሰብ ነበር። አሌክሳንደር ግራሃም ቤል በ1907 እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አሁን ባለንበት ሁኔታ አሜሪካ በመላው ዓለም በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ግኝት ላይ ልትደርስ በጣም እንደተቃረበች የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው። ይህንን ስል ውጤታማ የሆኑ የአየር ላይ የጦር መሣሪያዎችን ልትገነባ ትንሽ ቀርቷታል ማለቴ ነው።” በዚያው ዓመት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ካፒቴን ቶማስ ላቭሌስ የተባሉትን የባሉን አብራሪ ጠቅሶ እንዲህ ብሏል:- “ከሁለት እስከ ሦስት ባሉት ዓመታት ውስጥ ሁሉም ታላላቅ አገራት ቶርፒዶ [የተባለውን ቦምብ] ወንጫፊ ጀልባዎችና ፀረ ቶርፒዶ ወንጫፊ ጀልባዎች ያሏቸውን ያህል የጦር አውሮፕላኖችና የአየር መቃወሚያም ይኖራቸዋል።”

ከሦስት ዓመታት በኋላ ዊልበር እና ኦርቪል ራይት የተባሉ ወንድማማቾች የመጀመሪያውን የጦር አውሮፕላን ለመሥራት ከአሜሪካ የጦር ኃይል ጋር ተዋዋሉ። መስከረም 13, 1908 በወጣው ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የቀረበ አንድ ጽሑፍ የጦር ኃይሉ አውሮፕላን ማሠራት የፈለገበትን ምክንያት ሲገልጽ “በጦር መርከቡ እንፋሎት ማውጫ በኩል ፈንጂ በመጣል ሞተሩን የሚያንቀሳቅሰውን ውኃ ማፍያ ጋን በማበላሸት መርከቡን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ነበር” ብሏል።

ግራሃም ቤል እንዳለው አውሮፕላን ‘በዓለም በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል።’ በ1915 የአውሮፕላን አምራቾች የአውሮፕላኑን ውልብልቢት ሳይነካ ፊት ለፊት የሚተኩስ መትረየስ የተገጠመለት አውሮፕላን መሥራት ቻሉ። ብዙም ሳይቆይ ተዋጊ አውሮፕላኖች በቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ይታገዙ ጀመር፤ እነዚህ አውሮፕላኖች እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድረስ መጠናቸው እየገዘፈ ከመምጣቱም በላይ ይበልጥ ኃይለኞች ሆኑ። ነሐሴ 6, 1945 B-29 የተባለው እጅግ ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ላይ የዋለውን አውቶሚክ ቦምብ ጥሎ ሂሮሺማ የተባለችውን የጃፓን ከተማ ሙሉ በሙሉ ያወደመ ከመሆኑም በላይ 100,000 የሚያክሉ ነዋሪዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ማለትም በ1943 ኦርቪል ራይት በግሉ በሰጠው አስተያየት አውሮፕላኑን መፈልሰፉ እንዳሳዘነው ተናግሯል። በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት በእርግጥም ከባድ ውድመት ያደረሰ የጦር መሣሪያ መሆኑን አስተውሎ ነበር። እንዲሁም ‘መንግሥት በመንግሥት ላይ በተነሳበት’ በዚህ ዘመን በጨረር እየታገዙ ዒላማቸውን የሚመቱ እጅግ የተራቀቁ ሚሳይሎችና ቦምቦች መመረታቸው አውሮፕላንን ይበልጥ አውዳሚ እንዲሆን አድርጎታል።—ማቴዎስ 24:7

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. ቦምብ የጫነ ሰው አልባ ባሉን

2. ባራዥ ባሉን

[ምንጭ]

Library of Congress, Prints & Photographs Division, FSA/OWI Collection, LC-USE6-D-004722

3. B-29 የተባለ እጅግ ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን

[ምንጭ]

USAF photo

4. F/A-18C ሆርኔት የተባለ ተዋጊና ቦምብ ጣይ አውሮፕላን

5. ከጠላት ራዳር እይታ ውጭ የመብረር ችሎታ ያለው F-117A

[ምንጭ]

U.S. Department of Defense