እያንዳንዱን ወላጅ የሚያሳስብ አደጋ
ሄዘርና ስኮት ተጫዋችና ደስተኛ ባልና ሚስት ሲሆኑ ብልህና ጤነኛ የሆነ የሦስት ዓመት ልጅ አላቸው። * እነዚህ ባልና ሚስት ለልጃቸው ጥሩ እንክብካቤ ያደርጉለታል። ሆኖም ባለንበት ዓለም ውስጥ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። በርካታ ኃላፊነቶችን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ወላጆችን የሚያስጨንቋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ልጆች መማር የሚያስፈልጋቸው ብዙ ነገር አለ! ከእነዚህ መካከል ሄዘርንና ስኮትን ይበልጥ የሚያሳስባቸው ልጃቸውን ከፆታ ጥቃት የመጠበቁ ጉዳይ ነው። ለምን?
ሄዘር “አባቴ ጨካኝና ቁጡ የሆነ ሰካራም ሰው ነበር” በማለት ትናገራለች። “በኃይል ይደበድበኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ እኔንና እህቶቼን በፆታ ያስነውረን ነበር።” * እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት ጥልቅ የሆነ የስሜት ጠባሳ እንደሚያስከትል ብዙዎች ይስማማሉ። ሄዘር ወንድ ልጇን ከጥቃት ለመጠበቅ ቆርጣ መነሳቷ ምንም አያስገርምም! ስኮትም ቢሆን ልጃቸውን ከጥቃት ስለ መጠበቅ ተመሳሳይ ስሜት አለው።
ብዙ ወላጆች በልጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በጣም ያሳስባቸዋል። ምናልባት አንተም ይህ ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል። ከሄዘርና ከስኮት በተለየ መልኩ የፆታ ጥቃት አልደረሰብህ ይሆናል፤ እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የሚያስከትለውን ተጽዕኖም አታውቀው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ርኩስ ተግባር ምን ያህል እንደተስፋፋ የሚገልጹ ዘግናኝ ዘገባዎችን እንደሰማህ ጥርጥር የለውም። በዓለም ዙሪያ ያሉ አፍቃሪ ወላጆች በአካባቢያቸው በልጆች ላይ የሚደርሰውን ነገር ማወቁ ይዘገንናቸዋል።
በመስኩ ጥናት ያካሄዱ አንድ ሰው በልጆች ላይ የሚደርሰውን የፆታ ጥቃት መጠን ሲገልጹ “በዘመናችን ከሚታዩት በጣም ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች አንዱ” እንደሆነ መናገራቸው የሚያስገርም አይደለም። ይህ በእርግጥም አሳዛኝ ዜና ነው፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት መስፋፋቱ ያስደንቃል? ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አስደናቂ አይደለም። የአምላክ ቃል የምንኖረው ‘የመጨረሻ ዘመን’ ተብሎ በሚጠራ በመከራ በተሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሆነና ሰዎች “ጨካኞች፣” “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ይገልጻል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
የፆታ ጥቃት የሚዘገንን ጉዳይ ነው። አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆችን በፆታ ለማስነወር ስለሚፈልጉ ሰዎች ክፋት ማሰቡ እንኳ ይዘገንናቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ችግር ከወላጆች አቅም በላይ ነው? ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ከፆታ ጥቃት ለመጠበቅ ሊወስዷቸው የሚችሏቸው ተግባራዊ እርምጃዎች አሉ? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እነዚህን ጥያቄዎች ይዳስሳል።
^ አን.2 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ ያሉት ስሞች ተለውጠዋል።
^ አን.3 አንድ ልጅ በፆታ ተነወረ የሚባለው አንድ አዋቂ ወንድ (ሴትም ልትሆን ትችላለች) የፆታ ፍላጎቱን ለማርካት ልጆችን መጠቀሚያ ሲያደርጋቸው ነው። ይህ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት (በግሪክኛ ፖርኒያ) ብሎ የሚጠራውን ድርጊት የሚያጠቃልል ሲሆን ይህም የሌላውን የፆታ ብልት ማሻሸትን፣ የፆታ ግንኙነትንና በአፍ ወይም በፊንጢጣ ወሲብ መፈጸምን የመሳሰሉ ተግባሮችን ይጨምራል። ጡትን ማሻሸት፣ ቀጥተኛ የብልግና ጥያቄዎች ማቅረብ፣ ለልጅ የብልግና ሥዕል ማሳየት፣ ዕርቃናቸውን የሆኑ ወይም የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎችን በማየት እርካታ ለማግኘት መሞከርና ጨዋነት በጎደለው መልኩ ሰውነትን ማጋለጥ የመሳሰሉት አንዳንድ አስነዋሪ ድርጊቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማይረካ ምኞትና ርኵሰት’ ወይም ‘ቅጥ የሌለው ብልግና’ በማለት ካወገዛቸው ድርጊቶች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።—ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 4:19