በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች
3. በውስጡ የያዘው ሐሳብ እርስ በርስ ያለው ስምምነት
የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው 40 ሰዎች እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ምዕራፍ እየጻፉ በኅብረት አንድ መጽሐፍ እንዲያወጡ ኃላፊነት ሰጠሃቸው እንበል። ጸሐፊዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ከመሆኑም ሌላ አንዳቸው ከሌላው ጋር አይተዋወቁም። አንዳንዶቹ ደግሞ ሌሎቹ ምን እንደጻፉ እንኳ አያውቁም። በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀ መጽሐፍ እርስ በርሱ የሚስማማ ሐሳብ ይኖረዋል ብለህ ትጠብቃለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ባለ ሁኔታ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። * እንዲያውም ጸሐፊዎቹ ከላይ ከተገለጸውም እጅግ በባሰ ሁኔታ ሥር ሆነው የጻፉት ቢሆንም በውስጡ የያዘው ሐሳብ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነው።
የኢየሱስ ልብስ ሐምራዊ ነበር ወይስ ቀይ?
የተለዩ ሁኔታዎች።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ እስከ 98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ባሉት 1,600 ዓመታት ውስጥ ነው። በመሆኑም 40 ከሚያህሉት ጸሐፊዎቹ መካከል አብዛኞቹ የኖሩበት ዘመን በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ይራራቃል። የተሰማሩበት ሥራም የተለያየ ነበር። አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጆች፣ በግ ጠባቂዎች ወይም ነገሥታት ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ሐኪም ነበር።
እርስ በርሱ የሚስማማ መልእክት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አምላክ የሰው ልጆችን ለመግዛት ያለው መብት ስለመረጋገጡ እንዲሁም ጠቅላላውን ዓለም በሚያስተዳድርበት በሰማይ ባለው መንግሥቱ አማካኝነት ዓላማውን ከግብ የሚያደርስ ስለመሆኑ የሚናገር አንድ ማዕከላዊ ጭብጥ አላቸው። ይህ ጭብጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ሲሆን ቀጣዮቹ መጻሕፍት ይበልጥ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ካብራሩት በኋላ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተቋጭቷል።—በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ዝርዝር በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ያለው ስምምነት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች ረገድ እንኳ ሳይቀር እርስ በርሱ የሚስማማ ሐሳብ ጽፈዋል፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የሐሳብ ስምምነት ሊኖር የቻለው ታስቦበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ የሆነው ዮሐንስ ኢየሱስን ለማዳመጥ ብዙ ሕዝብ በመጣበት ወቅት ኢየሱስ ለሕዝቡ የሚሆን ጥቂት እንጀራ ከየት መግዛት እንደሚቻል ፊልጶስን እንደጠየቀው ይነግረናል። (ዮሐንስ 6:1-5) ሉቃስ በጻፈው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ይህ ሁኔታ የተፈጸመው በቤተሳይዳ ከተማ አቅራቢያ እንደነበረ ተናግሯል። ከዚያ ቀደም ሲል ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ ፊልጶስ የቤተሳይዳ ከተማ ሰው እንደነበረ ገልጿል። (ሉቃስ 9:10፤ ዮሐንስ 1:44) ስለዚህ ኢየሱስ ጥያቄውን ሊያቀርብ የሚችለው በአካባቢው ለኖረ ሰው ነው። ይህን ጉዳይ በሚመለከት የቀረቡት ዝርዝር ሐሳቦች እርስ በርስ ይስማማሉ፤ ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን የቻለው ታስቦበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። *
ምክንያታዊ የሆኑ ልዩነቶች።
በአንዳንድ ዘገባዎች መካከል ጥቂት ልዩነቶች አሉ፤ ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ የሚጠበቅ ነገር አይደለም? ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ወንጀል ሲፈጸም ተመለከቱ እንበል። እያንዳንዳቸው የተደረገውን እያንዳንዱን ነገር ቅደም ተከተሉን ጠብቀው በአንድ ዓይነት ቃላት ቢያስረዱ ይህን ያደረጉት ተመካክረው ነው ብለህ አትጠረጥርም? እያንዳንዱ ሰው ስለተፈጸመው ሁኔታ የሚሰጠው ምሥክርነት እንደየአመለካከቱ በተወሰነ መጠን የተለያየ መሆኑ ምክንያታዊ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።
እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ በሞተበት ዕለት የለበሰው ልብስ ምን ዓይነት ነበር? ዮሐንስ እንዳለው ሐምራዊ ነበር? (ዮሐንስ 19:2) ወይስ ማቴዎስና ማርቆስ እንደተናገሩት ቀይ ነበር? (ማቴዎስ 27:28፤ ማርቆስ 15:17) እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ሐምራዊ በውስጡ ቀይ ቀለም አለው። ስለዚህ ተመልካቹ ከቆመበት አቅጣጫ እንዲሁም ከብርሃኑ ነጸብራቅና ከበስተ ጀርባው ካሉት ነገሮች አንጻር የልብሱ መልክ ሊቀያየር ይችላል። *
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች፣ አስበውት ባይሆንም እንኳ እርስ በርሱ የሚስማማ ሐሳብ ማስፈራቸው የጻፏቸው ጽሑፎች እምነት የሚጣልባቸው ለመሆናቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው።
^ አን.4 መጽሐፍ ቅዱስ የ66 ትንንሽ መጻሕፍት ስብስብ ሲሆን በዘፍጥረት ተጀምሮ በራእይ መጽሐፍ ይደመደማል።
^ አን.7 እንዲህ ያለውን ስምምነት በሚመለከት ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ከገጽ 16-17 ተመልከት።
^ አን.9 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? በተሰኘው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።