በተደጋጋሚ ጊዜያት የተሠራው ድልድይ
በተደጋጋሚ ጊዜያት የተሠራው ድልድይ
ቡልጋሪያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ማዕከላዊ ሰሜን ቡልጋሪያን በሚያቋርጠው የኦሰም ወንዝ ላይ ባለ ጣሪያው የሎቬች ድልድይ ይገኛል። ይህ አስደናቂ ድልድይ፣ ከሚገለገሉበት ሰዎች ጋር በጣም የሚመሳሰል አስገራሚ ታሪክ አለው።
ለዚህ ድልድይ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገው የመጀመሪያው ሰው በ19ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሎቬችን የጎበኘው አሚ በዋ የተባለ ኦስትሪያዊ የጂኦሎጂ ባለሞያ ነበር። ይህ ሰው “በትንንሽ ሱቆች ስላጌጠ ባለጣሪያ የድንጋይ ድልድይ” ጽፏል። በእርግጥም፣ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ድልድይ ከወንዙ ማዶና ማዶ ያሉትን የከተማውን ክፍሎች የሚያገናኝ የሎቬች የመጓጓዣ አውታር ከመሆኑም በላይ ገበያም ሆኖ አገልግሏል! በዚህም ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ ድልድይ ሆኗል።
መጀመሪያ ላይ ይህ ባለ ጣሪያ የሎቬች ድልድይ የተሠራው ከድንጋይ ሳይሆን ከእንጨት ነበር። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ድልድዩ በተደጋጋሚ ጊዜ በጎርፍ ጉዳት ስለደረሰበት እንደገና መሠራት ያስፈልገው ነበር። በመጨረሻም በ1872 ድልድዩን ጎርፍ ጠራርጎ ስለወሰደው ማዶ ለማዶ ያለው የከተማው ሕዝብ የሚያገናኘውን በጣም አስፈላጊ የመገናኛ መሥመር አጣ።
ድልድዩን እንደገና መልሶ መሥራት ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ስመ ጥር ግንበኛ የነበረው ቡልጋሪያዊው ኮልዮ ፊቼቶ አዲስና የተሻለ ጥንካሬ ያለው ድልድይ ንድፍ አውጥቶ እንዲገነባ ተቀጠረ።
ፈጠራ የተንጸባረቀበት ንድፍ
ፊቼቶ የቀድሞውን አሠራር ለመከተል በመወሰን ጣሪያ ያለውና ዳርና ዳሩ ላይ ትንንሽ ሱቆች የተደረደሩበት ድልድይ ለመሥራት ንድፍ አወጣ። ርዝመቱ 84 ሜትር ወርዱ ደግሞ 10 ሜትር የሆነውን ድልድይ ደግፎ ለማቆም ሞላላ ቅርጽ ያላቸው ቋሚዎችን ተጠቀመ። እነዚህ 5 ሜትር ርዝመት ያላቸውና ወደጫፋቸው እየቀጠኑ የሚሄዱ ሾጣጣ ቋሚዎች አዲስ ገጽታ ነበራቸው። ቋሚዎቹ ከቁመታቸው መሃል ጀምሮ ወደላይ እስከ ጫፋቸው ድረስ የጎርፍ ውኃ በመሃል እንዲያልፍ የሚያስችሉ ክፍተቶች አሏቸው። ከዚያም ፊቼቶ በቋሚዎቹ አናት ላይ ጠንካራ የባሉጥ ወጋግራዎችንና ሳንቃዎችን ረበረበ። በድልድዩ ዳርና ዳር የተደረደሩትን 64 ሱቆች ጨምሮ የድልድዩ ቀሪ ክፍል ጠንካራ በሆነ እንጨት ተሠራ። ጣሪያውም በተመሳሳይ በእንጨት ተሠርቶ በቆርቆሮ ተከደነ።
ትኩረት የሚስበው ሌላው የፊቼቶ ንድፍ አወጣጥ ደግሞ ድልድዩን የደገፉትን ወጋግራዎች ለማገናኘት የተጠቀመው በብረትና በምስማር ሳይሆን በሚሰካኩ እንጨቶች መሆኑ ነበር። ፊቼቶ በእንጨት በተሠራው ድልድይ ላይ ድንጋይ በማንጠፍና በላዩ ላይ ኮረት በማፍሰስ አጠናቀቀው። ትንንሽ የጎን መስኮቶችና በጣሪያው ላይ ያሉ ክፍተቶች ድልድዩ ቀን ቀን የተፈጥሮ ብርሃን እንዲያገኝ ያስችሉታል። በምሽት ደግሞ በጋዝ የሚሠሩ ፋኖሶች ይበራሉ። አዲሱ ድልድይ ንድፉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በጠቅላላው ሦስት ዓመታት ገደማ ወስዷል [1]።
በድልድዩ ላይ የሚካሄደው እንቅስቃሴ
በድልድዩ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር? አንድ የዓይን ምሥክር የሰጠውን ገለጻ ልብ በል:- “በድልድዩ ላይ መኪና፣ በፈረስ የሚጎተት ጋሪ ወይም ጭነት የተሸከሙ አህዮች እምብዛም ስለማያልፉ ሻጮች፣ አላፊ አግዳሚዎችና በአካባቢው የሚቆሙ ሰዎች በእንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች አይረበሹም፤ እነዚህ ሰዎች የሚያሰሙት ድምፅ ከቀጥቃጮቹ ሱቅ ከሚወጣው ጩኸት . . . እና ዕቃቸውን ከሚያስተዋውቁት ቸርቻሪዎች ጫጫታ ጋር ተቀላቅሎ ውካታ ይፈጥራል። በድልድዩ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ የራሱ
የሆነ የተለየ ገጽታ ነበረው። ከሱፍ በተሠሩ ክሮች፣ በዶቃዎችና በልዩ ልዩ ዓይነት ሸቀጦች እስከ አፍ ገደፋቸው ጢም ብለው የሞሉት በቀለማት ያሸበረቁ በርካታ ትንንሽ ሱቆች ለየት የሚያደርጋቸው ሁኔታና ባሕል ነበራቸው።”በባለ ጣሪያው ድልድይ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ ባለ ሱቆች ሙዚቀኞችም ስለነበሩ ሰዎች ወደዚያ የሚመጡት ለገበያ ብቻ ሳይሆን ለመዝናናትም ጭምር ነበር። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሰው አክሎ እንዲህ ብሏል:- “በፀጉር ማስተካከያ ቤቶች ውስጥ ከፀጉር አስተካካይነት በተጨማሪ በተለይ እንደ ጊታር ያሉ የአውታር የሙዚቃ መሣሪያዎችን ጥሩ አድርገው የሚጫወቱ አምስት ወይም ስድስት ሰዎች ነበሩ። እነሱም ብዙውን ጊዜ ሙዚቃቸውን ለመጫወት ነፃ ጊዜ የሚያገኙ ሲሆን ደንበኞቻቸውም እስኪጨርሱ በደስታ ይጠብቋቸው ነበር።” ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አንዳንዶቹ ፀጉር አስተካካዮች የፀጉር አስተካካዮች ኦርኬስትራ በመባል የሚታወቀው ቡድን መሥራቾች ሆኑ።
አሳዛኝ ክስተት
ፊቼቶ የሠራው ባለ ጣሪያ ድልድይ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ጎርፉን፣ ጦርነቱንና ሌሎቹንም አደጋዎች ተቋቁሞ ቆየ። በ1925 ነሐሴ 2/3 ሌሊት ላይ ግን በድልድዩ ላይ የተነሳው ኃይለኛ ቃጠሎ ውብ የሆነው የከተማዋን ድልድይ አመድ አደረገው፤ ድልድዩ በእሳት ሲጋይ በሎቬች አካባቢ ሁሉ ይታይ ነበር። ቃጠሎው እንዴት ተነሳ? የእሳቱ መነሾ የጥንቃቄ ጉድለት ይሁን ወይም ሆን ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት እስከ ዛሬ ድረስ ማንም በእርግጠኝነት አያውቅም። ያም ሆነ ይህ ሎቬች እንደገና ያለ ድልድይ ስለቀረች በወንዙ ማዶና ማዶ ያሉት ሁለቱ የከተማው ክፍሎች መገናኘት አልቻሉም።
በ1931 አንድ አዲስ ባለ ጣሪያ ድልድይ የተሠራ ሲሆን በድልድዩ ዳርና ዳር ትንንሽ ሱቆችና የጥገና ክፍሎች ነበሩት [2]። አዲሱን ድልድይ የሠራው ሰው ግን የተጠቀመው በእንጨትና በድንጋይ ሳይሆን በብረትና በሲሚንቶ ነበር። ጠቅላላ ንድፉም ከፊቼቶ ንድፍ በጣም የተለየ ነበር። ጣሪያዎቹ በመስታወት የተሠሩ ሲሆን ድልድዩ መሃል አካባቢ ላይ የተወሰነው ክፍል ግድግዳ አልተሠራለትም። በ1981/82 ድልድዩ ኮልዮ ፊቼቶ ባወጣው የቀድሞው ንድፍ መሠረት እንደገና ተሠራ [3]።
የሎቬች ባለ ጣሪያ ድልድይ የከተማዋ መለያ እንዲሁም ጥሩ ችሎታ ያለው የእጅ ባለሙያ ድንቅ የሥራ ውጤት ነው። ዛሬም ቢሆን የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆኑ ጎብኚዎች በዳርና በዳር ሱቆች በተደረደሩበት በዚህ ድልድይ ላይ በእግር መጓዝ ያስደስታቸዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቡልጋሪያ
ሶፊያ
ሎቬች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ፎቶ 2:- From the book Lovech and the Area of Lovech