በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንድሜ ወይም እህቴ ሕይወታቸውን ቢያጠፉስ?

ወንድሜ ወይም እህቴ ሕይወታቸውን ቢያጠፉስ?

የወጣቶች ጥያቄ

ወንድሜ ወይም እህቴ ሕይወታቸውን ቢያጠፉስ?

ካረን አባቷ የሚከተለውን መርዶ በነገራት ቀን ሕይወቷ ተለወጠ። አባቷ ሲቃ እየተናነቀው “ሺላ አረፈች” አላት። ካረንና አባቷ ተቃቅፈው እርስ በርስ ለመጽናናት ሞከሩ፤ ሁለቱም ለመረዳት አዳጋች የሆነውን ይህን ሁኔታ መቀበል ከብዷቸው ነበር። የካረን እህት ሕይወቷን አጥፍታ ነበር። *

አንድ ወጣት ሲሞት አሳቢ የሆኑ አጽናኞች ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩት በወላጆቹ ላይ ነው። የሟቹን ወንድሞች ወይም እህቶች ሲያገኟቸው “ወላጆቻችሁ ተጽናኑ?” ብለው ይጠይቋቸዋል። ይሁን እንጂ “እናንተስ እንዴት ናችሁ?” ብለው መጠየቅ ይረሳሉ። በመሆኑም፣ የሟቹ ወንድሞች ወይም እህቶች የተረሱ ሐዘንተኞች ተብለው የሚጠሩት ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

የወንድም ወይም የእህት መሞት በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቶች ያመለክታሉ። ጊል ዋይት የተባሉ አንዲት ዶክተር የወንድም ወይም የእህት ሞት ከሚያስከትለው ሐዘን መጽናናት (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “እንዲህ ዓይነቱ ከባድ ሐዘን በሕይወት ባሉት ልጆች እድገት፣ ጤንነት፣ ጠባይ፣ የትምህርት ውጤት ብሎም ለራሳቸው ባላቸው ግምት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።”

ትልልቅ ወጣቶችም ቢሆኑ በሐዘኑ ይጎዳሉ። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰችው ካረን ታናሽ እህቷ ሺላ ሕይወቷን ስታጠፋ የ22 ዓመት ወጣት ነበረች። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የሚሰማትን ሐዘን መቋቋም ከባድ ይሆንባት ነበር። “ከወላጆቼ በላይ ተጎድቻለሁ ማለቴ ባይሆንም የእነሱን ያህል ሥቃዩን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ግን አልነበረኝም” በማለት ትናገራለች።

አንተስ ልክ እንደ ካረን ወንድምህን ወይም እህትህን በሞት ተነጥቀሃል? ከሆነ “ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤ ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ” በማለት እንደጻፈው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ይሰማህ ይሆናል። (መዝሙር 38:6) ታዲያ ሐዘንህን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

“ቢሆን ኖሮ” እያሉ መጸጸት

ወንድምህ ወይም እህትህ ሕይወታቸውን ማጥፋታቸው በጥፋተኝነት ስሜት እንድትሠቃይ ሊያደርግህ ይችላል። ‘እንዲህ ባደርግ ኖሮ ወንድሜ ወይም እህቴ አይሞቱም ነበር’ እያልክ ታስብ ይሆናል። እንዲህ ብለህ እንድታስብ የሚያደርግ ነገርም ያለ ሊመስልህ ይችላል። አሥራ ስምንት ዓመት የሆነው ታናሽ ወንድሙ ራሱን ባጠፋበት ወቅት የ21 ዓመት ወጣት የነበረው ክሪስ ‘እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር’ የሚል አስተሳሰብ ነበረው። “ወንድሜ ከመሞቱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያነጋገርኩት እኔ ስለነበርኩ አንድ ችግር እንዳለ ማወቅ እንደነበረብኝ ተሰማኝ። ይበልጥ የምቀረብ ዓይነት ሰው ብሆን ኖሮ ችግሩን ገልጦ ይነግረኝ ነበር ብዬ አሰብኩ” በማለት ይናገራል።

በክሪስና በወንድሙ መካከል አለመግባባት የነበረ መሆኑ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜቱን ይበልጥ አባብሶበታል። “ወንድሜ ሲሞት በተወው ማስታወሻ ላይ ከዚያ የተሻልኩ ወንድም መሆን እችል እንደነበረ ተናግሯል” በማለት ክሪስ በታላቅ ሐዘን ያስታውሳል። “ይህን በጻፈበት ወቅት ስሜቱ ተረብሾ እንደነበረ ባውቅም አሁንም ድረስ ስለ ሁኔታው ሳስብ እሠቃያለሁ።” ወንድምህ ወይም እህትህ ከመሞታቸው በፊት ጥሩ ያልሆኑ ቃላትን ተነጋግራችሁ ከነበረ ይህን ማስታወሱ ብዙውን ጊዜ የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ያባብሰዋል። “ሐዘን የገጠማቸው በርካታ ወጣቶች ከወራት ወይም ከዓመታትም በፊትም እንኳን ሳይቀር ከሟች ወንድማቸው ወይም እህታቸው ጋር የተጣሉበትን ጊዜ እያስታወሱ በጥፋተኝነት ስሜት እንደሚሠቃዩ ነግረውኛል” በማለት ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ዋይት ለንቁ! ዘጋቢ ተናግረዋል።

አንተም ወንድምህ ወይም እህትህ ሕይወታቸውን በማጥፋታቸው ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት እያሠቃየህ ከሆነ ‘የሌላውን ሰው ድርጊት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የሚችል ሰው ይኖራል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ካረን እንዲህ ብላለች:- “ሟቹ ሊሸሸው የፈለገውን እየደረሰበት የነበረውን ሥቃይና ሥቃዩን ለማስቆም የተጠቀመበትን አሰቃቂ መንገድ የመከላከል ችሎታ የላችሁም።”

ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ወንድምህን ወይም እህትህን የተናገርካቸውን አሳቢነት የጎደላቸው ሐሳቦች መርሳት እንደማትችል ቢሰማህስ? መጽሐፍ ቅዱስ ለነገሮች ተገቢ አመለካከት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ይላል:- “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2፤ መዝሙር 130:3) በእርግጥም ወንድምህን ወይም እህትህን በጥሩ መንገድ አለመያዝህን አሊያም የሚያስከፋቸውን ቃል መናገርህን እያሰብክ መብከንከን ሐዘንህን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም። እነዚህ ትዝታዎች የስሜት ሥቃይ ሊፈጥሩብህ ቢችሉም ለወንድምህ ወይም ለእህትህ ሞት ምክንያቱ አንተ አይደለህም። *

ሐዘንን መቋቋም

ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገለጹበት መንገድ ይለያያል። አንዳንዶች በሰዎች ፊት እንባ አውጥተው የሚያለቅሱ ሲሆን እንዲህ ማድረግም ምንም ስህተት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳዊት ልጁ አምኖን ሲሞት ‘እጅግ እንዳለቀሰ’ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 13:36) ኢየሱስም እንኳ የወዳጁ የአልዓዛር ሞት ያስከተለውን መሪር ሐዘን በተመለከተ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’—ዮሐንስ 11:33-35

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች፣ በተለይም ሞቱ የደረሰው በድንገት ከሆነ ወዲያውኑ አያለቅሱም። ካረን ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “በድን የሆንኩ መሰለኝ። ለተወሰነ ጊዜ የተለመደ ተግባሬን ማከናወን አልቻልኩም።” ወንድማቸውን ወይም እህታቸውን በሞት ባጡ ሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ መከሰቱ በጣም የተለመደ ነገር ነው። ዶክተር ዋይት ይህን አስመልክተው ለንቁ! ዘጋቢ እንዲህ ብለዋል:- “ሕይወትን ማጥፋት እጅግ አሰቃቂ ገጠመኝ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ከማዘኑ በፊት ድንጋጤውን መቋቋም ይኖርበታል። እንደዚህ ዓይነት ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች በመንከባከብ ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሙያዎች፣ የሟቹን ወንድሞች ወይም እህቶች ድንጋጤው ሳይለቃቸው እንዲያለቅሱ ለማድረግ ይሞክራሉ። እነሱ ግን ገና በድንጋጤ እንደደነዘዙ ናቸው።”

ወንድምህ ወይም እህትህ መሞታቸውን አምኖ መቀበል ጊዜ ይጠይቃል፤ ከደረሰው ነገር አንፃር ሲታይ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ክሪስ እንዲህ ይላል:- “ቤተሰባችን፣ ከተሰበረ በኋላ በድጋሚ እንዲጣበቅ ከተደረገ የአበባ ማስቀመጫ ጋር ይመሳሰል ነበር። ትንሽ ውጥረት ሲያጋጥም በቀላሉ ‘የምንሰነጣጠቅ’ እንመስል ነበር።” ከታች የተዘረዘሩት ሐሳቦች ይህን ሁኔታ እንድትቋቋም ሊረዱህ ስለሚችሉ በሥራ ላይ ለማዋል ሞክር:-

የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መዝግበህ በመያዝ በየቀኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ አንብባቸው።—መዝሙር 94:19

▪ ርኅሩኅ ለሆነ ጓደኛህ ስሜትህን ተናገር። የልብህን አውጥተህ መናገርህ ሐዘንህ እንዲቀንስልህ ሊረዳህ ይችላል።—ምሳሌ 17:17

▪ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ አሰላስል።—ዮሐንስ 5:28, 29

በተጨማሪም፣ ለጊዜውም ቢሆን የሚሰማህን ነገር በየዕለቱ በማስታወሻ ላይ መጻፍህ ሐዘንህ ከቁጥጥርህ ውጭ እንዳይሆን ይረዳሃል። ለሙከራ ያህል ከታች ያለውን ሣጥን ለምን አትጠቀምበትም?

‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ መሆኑንና ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ’ እርግጠኛ ሁን። (1 ዮሐንስ 3:20) አምላክ፣ ወንድምህ ወይም እህትህ እንዲጨነቁ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ከማንኛውም ሰው በላይ ያውቃል። እንዲሁም፣ አምላክ ራስህን ከምታውቀው በላይ ያውቅሃል። (መዝሙር 139:1-3) ሐዘንህን መሸከም እንዳቃተህ ሆኖ ሲሰማህ በመዝሙር 55:22 ላይ ያለውን የሚከተለውን ሐሳብ አስታውስ:- “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።”

ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን ማጽናኛ

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን ለመቋቋም የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የምትወዱት ሰው ሲሞት የሚል ርዕስ ያለው ብሮሹር ተመልከት።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.12 ወንድምህ አሊያም እህትህ የሞቱት በሕመም ወይም በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት በሚሆንበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ወንድምህን ወይም እህትህን የቱንም ያህል ብትወዳቸው “ጊዜና አጋጣሚ” የሚያመጡትን ነገር ማስቀረት አትችልም።—መክብብ 9:11 NW

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ሐዘንህ ልትቋቋመው ከምትችለው በላይ እንደሆነ ሲሰማህ ስሜትህን ለማን መናገር ትችላለህ?

▪ ሐዘን የደረሰበትን ወጣት መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሐሳብህን በጽሑፍ ማስፈርህ ሐዘንህን ለመቋቋም ትልቅ እገዛ ሊያደርግልህ ይችላል። ይህን በአእምሮህ በመያዝ ቀጥሎ የቀረቡትን ዓረፍተ ነገሮች አሟላ፤ ለጥያቄዎቹም መልስ ስጥ።

ከወንድሜ ወይም ከእህቴ ጋር ካሳለፍኳቸው አስደሳች ትዝታዎች መካከል ሦስቱ:-

1 ․․․․․

2 ․․․․․

3 ․․․․․

ወንድሜ ወይም እህቴ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ብነግራቸው ደስ ይለኝ የነበሩ ነገሮች:-

․․․․․

ለታላቅ ወንድሙ ወይም ለእህቱ ሞት ራሱን ተጠያቂ የሚያደርግን ልጅ ምን ብለህ ታጽናናዋለህ?

․․․․․

ከሚከተሉት ጥቅሶች መካከል ይበልጥ ያጽናናህ የትኛው ነው? ለምንስ?

□ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።”—መዝሙር 34:18

□ “እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣ አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው።”—መዝሙር 22:24

□ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል።”—ዮሐንስ 5:28, 29