መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መራቅ ያለብህ ለምንድን ነው?
በአንዲት የእስያ አገር፣ ሕዝቡ ለመናፍስት ክብር ለመስጠት የሚዘጋጅ በዓል ለማክበር ይሰበሰባል። ዋናው የአከባበር ሥነ ሥርዓት የሚፈጸመው መናፍስት የሚገቡባቸውን ሁለት ሴቶች በመምረጥ ነው። ከዚያም ሴቶቹ ዓይናቸውን ግልብጥብጥ ያደርጉትና ኃይለኛ ንዝረት ያለው ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው መላ ሰውነታቸው መንዘፍዘፍ ይጀምራል።
በፖርቶ ሪኮ፣ አንድ መናፍስት ጠሪ (ሳንቴሮ) የመብረቅ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ከሚታመን ቻንጎ ከሚባል መንፈስ ጋር ለመገናኘት ይሞክራል። መናፍስት ጠሪው በራእይ ስለሚታዩት ነገሮች ሲናገር በክፍሉ ውስጥ ያሉት ሁሉ መናፍስት የገቡባቸው ይመስል መንዘፍዘፍ ይጀምራሉ።
በብዙ አገሮች ውስጥ ምትሐታዊ ድርጊቶችን መፈጸም በጣም የተለመደ ተግባር ነው። ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች ማመን ይበልጥ ተወዳጅ እየሆነ ከመምጣቱም በላይ ሰዎች እንዲህ ስላለው ሁኔታ ማወቅ ያጓጓቸዋል። በአጋንንት፣ በአስማትና ከተፈጥሮ ውጪ በሆኑ ክስተቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተበራከቱ መጥተዋል።
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምትሐታዊ ኃይል ካለው ከማንኛውም ነገር ጋር ግንኙነት መፍጠር መናፍስታዊ ድርጊት እንደሆነ ያስተምራል። መናፍስታዊ ድርጊት ችግር የማያስከትል ወይም ጉዳት የሌለው ጨዋታ አይደለም። የማያውቁትን ነገር ለማወቅ የሚደረግ ምርምር እንደሆነ ተደርጎም መታየት አይኖርበትም። መናፍስታዊ ድርጊት፣ ከአጋንንት ማለትም በአምላክ ላይ ካመፁ ክፉ መላእክት ጋር የሚደረግ ግንኙነት ነው።—ራእይ 12:9, 12
እንደ እውነቱ ከሆነ አጋንንት መናፍስታዊ ድርጊትን የሚጠቀሙበት መንገድ ዓሣ አጥማጆች ዓሣን ለመያዝ ከሚጠቀሙበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ነው። አንድ ዓሣ አጥማጅ እንደ ዓሣው ዓይነት የተለያዩ የማታለያ ምግቦችን በመንጠቆው ላይ ያስቀምጣል። በተመሳሳይም ክፉ መናፍስት ሁሉንም ዓይነት ሰዎች በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ የተለያዩ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይጠቀማሉ። የአጋንንት መሪ “የዚህ [ክፉ] ዓለም አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። ይህ መሪ የማያምኑ ሰዎችን አእምሮ በማሳወር ማለትም የአምላክ ዓላማም ሆነ በቃሉ ውስጥ የሚገኘው እውነት እንዳይታያቸው በማድረግ ረገድ ተሳክቶለታል።—2 ቆሮንቶስ 4:4
የመናፍስታዊ ድርጊት መጨረሻ ምንድን ነው?
የክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ዓላማ ትኩረታችንን በመከፋፈልና እኛን በማሳሳት ከፈጣሪያችን ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዳንመሠርት ማድረግ ነው። እነዚህ መናፍስት፣ ሰዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች እንዳይታዘዙ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። ስለሆነም መናፍስታዊ ድርጊት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናጣ፣ ተስፋ ቢስ እንድንሆን በመጨረሻም ለጥፋት እንድንዳረግ ያደርገናል።—ራእይ 21:8
በፖርቶ ሪኮ የሚኖረው ሉዊስ እንዲህ ይላል:- “ሕፃን ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ ቤተሰቦቼ በመናፍስታዊ ድርጊቶች የተጠላለፉ ነበሩ። መናፍስታዊ ድርጊት የቤተሰባችን ሃይማኖትና የሕይወታችን ክፍል ነበር። ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጠንቆል መቻሌም ሆነ ለጥንቆላ የሚያገለግል ሥዕል ያለባቸውን ካርታዎች ማንበቤ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ሰዎች ሎተሪ እንዲወጣላቸው ለመርዳት ለማሸነፍ የሚያስችሉ ቁጥሮችን እመርጥላቸው ነበር። ሆኖም እንደ ተሰጥኦ አድርጌ የማያቸው እነዚህ ችሎታዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት እንዳላገኝ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ዝምድና እንዳልመሠርት ትኩረቴን ከመስረቅ ውጪ ምንም የፈየዱልኝ ነገር አልነበረም።”—ብዙ ሰዎች ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ምንም ጉዳት እንደሌለው አልፎ ተርፎም ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ጥሩ የሆኑ መናፍስት እንዳሉ ወይም ደግሞ መናፍስታዊ ድርጊቶችን መፈጸማቸው እውቀት እንደሚጨምርላቸው፣ ሀብት ወይም ደስታ እንደሚያስገኝላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። ሉዊስ እንደተናገረው እንዲህ ያለው ሁኔታ “ሁልጊዜ የሚያስከፍለው ነገር አለ።”
ቻድ የሚባል አንድ ወጣት በተኛ ቁጥር በሕልሙ አስፈሪ ነገሮች ይታዩትና ከእንቅልፉ ያባንኑት ነበር። ሁኔታውን አስመልክቶ ሲናገር “አጋንንት ሁልጊዜ ማታ ማታ ያስፈራሩኝና ያሠቃዩኝ ነበር” ብሏል። እንዲህ ካለው የአጋንንት ጥቃት ጥበቃ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
ጥበቃ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ራሳችንን ከጥቃት ለመጠበቅ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገድ ያስፈልገናል። (ገላትያ 5:19-21) በመሆኑም ይሖዋ አምላክ፣ አገልጋዮቹ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ተግባሮች ከመፈጸም እንዲቆጠቡ መመሪያ ሰጥቷቸዋል:- “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።”—ዘዳግም 18:10-12
ብዙዎች ከእነዚህ ቃላት ጋር በመስማማት ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ዝምድና ያላቸውን መጻሕፍት ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች ማስወገዳቸው ራሳቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ አስችሏቸዋል። ከመናፍስታዊ ድርጊት የተላቀቀው ኬን “ዕቃዎቼን በሙሉ በርብሬ መጥፎ እንደሆነ የተሰማኝን ሁሉ አስወገድኩ” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20ን ተመልከት።
ከሁሉ የሚበልጠው መከላከያ ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት ነው። በያዕቆብ 4:7, 8 ላይ የተገለጸውን ልናደርገው የሚገባንን ነገር ልብ በል:- “ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።”
ይሖዋ አምላክ ወደ እሱ የሚቀርቡትን ሰዎች ያስተምራቸዋል፤ እንዲሁም ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ የሚያስተምራቸው ሰዎች ‘የሰይጣንን ዕቅዶች አይስቱም’ ወይም ራሱን ለመለወጥ ቢሞክር አይታለሉም። (2 ቆሮንቶስ 2:11፤ 11:14) በተጨማሪም ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። ሰዎች ይሖዋን በእምነት መጥራታቸው ከክፉ መናፍስት ጥቃት ነፃ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቻድ “እንዲህ ያለውን ሥቃይ የሚያደርሱብኝ እነማን መሆናቸውን ማወቄና ከጥቃታቸው እንዲጠብቀኝ ይሖዋ አምላክን መጥራቴ ከችግሩ እንድገላገል አስችሎኛል” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 91:1, 2
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች፣ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ጥበቃ በማግኘታቸው በቅርቡ ደግሞ አጋንንትም ሆኑ ለእነሱ ተጽዕኖ የሚገዙ ሰዎች እንደሚጠፉ በማወቃቸው ሊደሰቱ ይችላሉ። የሰው ዘር መናፍስታዊ ድርጊት ከሚያስከትላቸው ውጤቶች ነፃ በሚሆንበት ጊዜ በምድር ላይ የሚሰፍነው ደስታና ሰላም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ!—ኢሳይያስ 11:9፤ ራእይ 22:15