በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበቆሎ አስደናቂነት

የበቆሎ አስደናቂነት

የበቆሎ አስደናቂነት

ሃርሊን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ኒው ዮርክ ግዛት በሚገኙት የፊንገር ሐይቆች አካባቢ የበቆሎ ገበሬ ነበር። ሃርሊን በቆሎን አስደናቂ ስለሚያደርጉት ነገሮች ለወዳጆቹና ሊጠይቁት ለሚመጡ እንግዶች መናገር ያስደስተዋል። ንቁ! መጽሔት ሃርሊን እውቀቱን ለአንባቢዎች እንዲያካፍል ጋብዞት ነበር። በተጨማሪም የዚህን አስደናቂ ተክል ሌሎች ገጽታዎች እንቃኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ በቆሎ የተገኘው የት እንደሆነ፣ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንዴት እንደተሰራጨና ምን ጥቅሞች እንዳሉት እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን በቆሎን አስደናቂ የሚያደርጉትን አንዳንድ ገጽታዎች በተመለከተ ሃርሊን የሰጠውን ሐሳብ እንመልከት።

‘የሚያወራ’ ተክል

“እኔ በቆሎን የምመለከተው የሥነ ጥበብና የረቀቀ የሂሣብ ውጤት እንደሆነ አድርጌ ነው። ከቅጠሉ አንስቶ እስከ ፍሬው ድረስ እያንዳንዱ ነገር የተቀመጠው ለዓይን በሚማርክና ሥርዓት ባለው መንገድ ነው። ከዚህም በላይ ተክሉ እያደገ ሲሄድ ‘ያወራችኋል።’ በቂ ውኃ ወይም ንጥረ ነገር አጥቶ ከሆነ ይነግራችኋል። አንድ ሕፃን ልጅ የሚያስፈልገው ነገር ሲኖር ያለቅሳል። እንደ ሌሎች በርካታ ተክሎች ሁሉ በቡቃያነት ደረጃ ላይ ያለ የበቆሎ ተክልም የቅጠሉን ቀለምና ቅርጽ በመቀየር ወይም በሌላ መንገድ ምን እንደሚያስፈልገው ይናገራል። ዋናው ነገር እነዚህን ምልክቶች መረዳቱ ላይ ነው።

“ቅጠሉ ሐምራዊ ከሆነ ፎስፎረስ አጥቷል ማለት ሊሆን ይችላል። ማግኒዝየም፣ ናይትሮጅን ወይም ፖታሽ ካጣ ደግሞ ሌሎች ምልክቶችን ያሳያል። በተጨማሪም አንድ ገበሬ የበቆሎ ሰብሉ በበሽታ መጠቃቱን ወይም በኬሚካል መጎዳቱን ቅጠሉን በማየት ብቻ ማወቅ ይችላል።

“እንደማንኛውም የበቆሎ ገበሬ ሁሉ ዘር የምዘራው አፈሩ ዘር እንዲበቀል የሚያስችል ሙቀት በሚያገኝበት የጸደይ ወራት ነው። ሰብሌ ከአራት ወይም ከስድስት ወር በኋላ እድገቱን ሲጨርስ 2 ሜትር የሚደርስ ቁመት ይኖረዋል።

“የበቆሎ ተክል የተለያየ የእድገት ደረጃ ያለው ሲሆን ቅጠሎቹን በመቁጠር በየትኛው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ ይቻላል። አምስት ቅጠል የሚያወጣበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ‘የኬሚስትሪ’ እና ‘የሂሣብ’ እውቀቱን በሚገባ እንደሚጠቀም ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። በመጀመሪያ ሥሮቹ አጠቃላይ የሆነ የአፈር ምርመራ ያካሂዳሉ። የዚህ ምርመራ ውጤት የበቆሎው ራስ ምን ያህል ውፍረት እንደሚኖረው ይወስናል፤ ይህም የሚለካው ፍሬዎቹ በሚደረደሩበት ረድፍ ብዛት ነው። ከ12 እስከ 17 ቅጠል የሚያወጣበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ሌላ የአፈር ምርመራ ያደርጋል፤ የዚህ ምርመራ ውጤት እያንዳንዱ ራስ ምን ያክል ፍሬ ማብቀል እንደሚኖርበት ይወስናል። በአጭሩ እያንዳንዱ ተክል ከአፈሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያገኝበትን መንገድ ያሰላል ማለት ይቻላል። የበቆሎን ተክል አስደናቂ የሚያደርገው ሌላው ነገር የሚራባበት መንገድ ነው።”

የበቆሎ አበባ፣ ብናኝ አቃፊና ፀጉር

“እያንዳንዱ የበቆሎ ተክል ወንዴና ሴቴ አለው። ከተክሉ አናት ላይ የሚወጣው አበባ የሚመስለው ነገር ወንዴው ነው። እያንዳንዱ ወንዴ አበባ 6,000 የሚያክሉ ብናኝ አቃፊዎች (anthers) አሉት። እነዚህ አቃፊዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወንዴ ዘር ብናኞችን ይለቃሉ። ብናኞቹ በነፋስ ኃይል ተወስደው በአካባቢው ባሉ የበቆሎ እምቡጦች ላይ በማረፍ እንቁላሎቹን ያዳብራሉ። እንቁላሎቹ በበቆሎው ራስ ሽልቃቂ ስለሚሸፈኑ ጉዳት አያገኛቸውም።

“ታዲያ ብናኙ ሽፋኑን አልፎ ወደ እንቁላሎቹ የሚደርሰው እንዴት ነው? በበቆሎው ፀጉር አማካኝነት ብላችሁ ትመልሱ ይሆናል። ፀጉር የሚባለው ከተሸፈነው የበቆሎ ራስ ጫፍ ላይ ተንዘርፍፎ የሚታየው ነጣ ያለ፣ ለስላሳና ቃጫ መሳይ ነገር ነው። እያንዳንዱ የበቆሎ ራስ በመቶ የሚቆጠሩ ፀጉሮች ይኖሩታል። እያንዳንዱን ፀጉር ተከትላችሁ ወደ ውስጥ ብትገቡ እንቁላሉ ወደሚገኝበት አንድ የሴቴ አበባ ክፍል ትደርሳላችሁ። አንድ እንቁላል አንድ ፀጉር ያለው ሲሆን እያንዳንዱ እንቁላል አንድ የበቆሎ ፍሬ ያስገኛል።

“ከበቆሎው ሽፋን ውጪ አየር ላይ የሚወዛወዘው ፀጉር የወንዴውን ዘር አጣብቆ የሚይዝበት ጥቃቅን ቃጫዎች ወይም ስቲግማዎች አሉት። አንድ ብናኝ ከውጪ በሚገኘው በዚህ ፀጉር ላይ ካረፈ በኋላ ያጎነቁልና እንደ ሥር ያለ ነገር አበጅቶ ወደ ውስጥ በመግባት እንቁላሉን ያዳብራል።

“አንዳንድ የበቆሎ ራሶች በተወሰነ ቦታ ላይ ፍሬ የማይኖራቸው ፀጉራቸው ቶሎ ባለማደጉ ምክንያት ብናኝ ሳያገኝ በመቅረቱ ሊሆን ይችላል። አፈሩ ሲደርቅ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ገበሬው የችግሮቹን ምልክት ከተረዳ አብዛኛውን ጊዜ የተሻለ ምርት ሊያስገኝለት የሚችለውን እርምጃ ሊወስድ ይችላል፤ በወቅቱ ምንም ለውጥ ማምጣት ባይችል እንኳ በቀጣዩ የምርት ወቅት ላይ የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላል። ምርቴን ለማሻሻል ካደረግኳቸው ነገሮች አንዱ በቆሎና አኩሪ አተር እያፈራረቁ መዝራት ነው። አኩሪ አተር፣ ኮርን ቦረር በተባለ ትል የማይጠቃና ለአፈሩ ናይትሮጅን የሚጨምር ተክል ነው። *

“ባዶ የነበረው ማሳ ቀስ በቀስ አረንጓዴ ሲሆንና ብዙ ምርት ሲያስገኝ ማየት በጣም ያስደስተኛል፤ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ምንም ዓይነት ድምፅ ሳያሰማ፣ አካባቢ ሳይበክልና ውበትን በተላበሰ መንገድ ነው። እንደማንኛውም ተክል ሁሉ በቆሎም አስደናቂ ፍጥረት እንደሆነ አምናለሁ። በቆሎ ካሉት አስደናቂ ነገሮች ውስጥ እኔ የማውቀው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው።”

ሃርሊን የሰጠው ሐሳብ ስለዚህ አስደናቂ ተክል ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ጉጉት እንዲያድርባችሁ አድርጓል? እስቲ የበቆሎን ታሪክና ያለውን ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንመልከት።

ከሜክሲኮ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ተሰራጨ!

በቆሎ መመረት የጀመረው ከአሜሪካ አገሮች በአንዱ ምናልባትም በሜክሲኮ ሲሆን ከዚያም ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰራጨ። ከኢንካዎች በፊት ይኖሩ የነበሩ ፔሩያውያን አናቷ ላይ በሚደረጉ የበቆሎ ራሶች የምታጌጥ የበቆሎ ሴት አምላክ ያመልኩ ነበር። ተፈጥሮን አስመልክቶ የሚጽፉት ጆሴፍ ካስትነር እንደተናገሩት የአሜሪካ ሕንዶች “[በቆሎን] አማልክት የሠሩት ነገር እንደሆነ አድርገው በመመልከት እንዲሁም ሰው የተሠራው ከበቆሎ እንደሆነ በማመን ያመልኩት ነበር። . . . ይህን ተክል በቀላሉ ማምረት ይቻል ነበር፤ አንዱ የበቆሎ ተክል የአንድን ሰው የዕለት ጉርስ መሸፈን ይችል ነበር።” ይሁን እንጂ የአሜሪካ ሕንዶች በቆሎን የሚመገቡት ከባቄላ ጋር ቀላቅለው ነበር። እንዲህ ያለው አመጋገብ ዛሬም ቢሆን በላቲን አሜሪካውያን ዘንድ የተለመደ ነው።

አውሮፓውያን ስለ በቆሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁት በ1492 ማለትም ክርስቶፎር ኮሎምቦስ የካሪቢያን ደሴቶችን ከረገጠ በኋላ ነው። የኮሎምቦስ ልጅ የሆነው ፈርዲናንድ፣ አባቱ ‘ሰዎች በቆሎ ብለው የሚጠሩትን ከምንም በላይ ጣፋጭ የሆነ ጥራጥሬ እንዳየና ይህ ጥራጥሬ እንደሚቀቀል፣ እንደሚጠበስ ወይም ተፈጭቶ ዱቄት እንደሚሆን’ ጽፏል። ኮሎምቦስ የዚህን ተክል ዘር ይዞ ወደ አገሩ ሄደ። ካስትነር እንደጻፉት “በ1500ዎቹ አጋማሽ ላይ [በቆሎ] በስፔን ብቻ ሳይሆን በቡልጋሪያና በቱርክ ጭምር መብቀል ጀምሮ ነበር። የባሪያ ነጋዴዎች በቆሎን ወደ አፍሪካ ወሰዱ። . . . [በፖርቹጋል የተወለደው የስፔናዊው የፈርዲናንድ] ማጂላን ሰዎች ደግሞ ከሜክሲኮ የተገኘውን ዘር ወደ ፊሊፒንስና እስያ ወሰዱ።” በዚህ መንገድ በቆሎ በሰፊው ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ።

በአሁኑ ጊዜ በቆሎ በመላው ዓለም በሰፊው ጥቅም ላይ በመዋል ረገድ ከስንዴ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል። የሦስተኛነቱን ደረጃ የያዘው ሩዝ ነው። እነዚህ ሦስት ዋና ዋና ሰብሎች ከብቶችን ሳይጨምር ለአብዛኛው የሰው ዘር በምግብነት ያገለግላሉ።

እንደ ሌሎቹ የሣር ዝርያዎች ሁሉ የተለያዩ የበቆሎ ዓይነቶች አሉ። የተዳቀሉ ዝርያዎችን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ1,000 የሚበልጡ የራሳቸው ስም ያላቸው የበቆሎ ዓይነቶች አሉ። የተክሎቹ ቁመት ከ60 ሴንቲ ሜትር እስከ 6 ሜትር ይደርሳል! የበቆሎዎቹ ራስ ቁመትም የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ከ5 ሴንቲ ሜትር ያላለፈ ቁመት ሲኖራቸው እስከ 60 ሴንቲ ሜትር የሚደርሱ የበቆሎ ራሶችም አሉ። ላቲን አሜሪካን ኩኪንግ የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው “በዛሬው ጊዜ በደቡብ አሜሪካ ከሚዘሩት የበቆሎ ዓይነቶች አንዳንዶቹ አንድ ኢንች በአንድ ኢንች የሆኑ ሰፋፊ ፍሬዎች ያሏቸው የአሜሪካውያንን የእግር ኳሶች የሚያክሉ ትልልቅ የበቆሎ ራሶች ያፈራሉ።”

ከዚህም በላይ በቆሎ የተለያየ ቀለም አለው። ከቢጫ በተጨማሪ ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ሮዝ ወይም ጥቁር ቀለም ያላቸው የበቆሎ ራሶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የበቆሎው ራስ ነጠብጣብ ወይም ሸንተረር ያለው አሊያም ቡራቡሬ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉት የተዋቡ የበቆሎ ራሶች ከድስት አፍ ተርፈው ለጌጥነት የሚያገለግሉበት ጊዜ አለ።

ፈርጀ ብዙ ጥቅም ያለው እህል

በዓይነታቸው እጅግ ብዙ የሆኑት እነዚህ የበቆሎ ዝርያዎች በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ። እነሱም ዴንት ኮርን፣ ፍሊንት ኮርን፣ ፍሎር ኮርን፣ ስዊት ኮርን (ጣፋጭ በቆሎ)፣ ዋክሲ ኮርን እና ፖፕኮርን (ፈንድሻ) ይባላሉ። ከሌሎቹ የበቆሎ ዝርያዎች ሁሉ በአነስተኛ መጠን የሚመረተው ስዊት ኮርን ነው። ይህ የበቆሎ ዓይነት ጣፋጭ ሊሆን የቻለው ወደ ስታርችነት የሚለወጠው የስኳር መጠን አነስተኛ በመሆኑ ነው። በመላው ዓለም ከ60 በመቶ የሚበልጠው የበቆሎ ምርት የሚውለው ለከብት መኖነት ሲሆን ለሰው ቀለብ የሚውለው ከ20 በመቶ ያነሰ ነው። ቀሪው ለኢንዱስትሪዎች አገልግሎትና ለዘር ይውላል። እርግጥ ይህ አኃዝ ከአገር አገር ይለያያል።

በቆሎ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ይህ እህል ወይም የዚህ እህል ተዋጽኦዎች ማጣበቂያ፣ ማዮኒዝ፣ ቢራና የሕፃናት ዳይፐር የመሳሰሉ ነገሮችን ለመሥራት ያገለግላሉ። ብዙ ውዝግብ ያስከተለ ቢሆንም በቆሎ በነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥም ትልቅ ቦታ አግኝቷል። ከበቆሎ ኢታኖል የተባለው ነዳጅ ይዘጋጃል። ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የዚህ አስደናቂ ተክል ታሪክ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በገጽ 25 ላይ የሚገኘውን “ንድፍ አውጪ አለው? በአፈር ውስጥ የሚደረግ አስደናቂ ትብብር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምርጥ የበቆሎ ዘር

በብዙ አገሮች የበቆሎ ገበሬዎች በአብዛኛው የሚዘሩት ምርጥ ዘር ነው። ይህ የሆነው ምርጥ ዘር ብዙ ምርት ስለሚያስገኝ ነው። የዴንት ኮርን ምርጥ ዘሮች አብዛኛውን ጊዜ የሚገኙት የተለያዩ ዝርያዎችን በማዳቀልና ተፈላጊ ባሕርይ ያላቸውን ዘሮች ደጋግሞ በማራባት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ገበሬዎች ለእያንዳንዱ ሰብል አዲስ ዘር እንዲገዙ ያስገድዳቸዋል። ለምን? ያለፈውን የምርጥ ዘር ምርት እንደ ዘር መጠቀም ጥራቱን የሚቀንሰው ከመሆኑም በላይ ምርቱም አነስተኛ ስለሚሆን ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በቆሎ በመላው ዓለም የሚገኝ በርካታ ዝርያዎች ያሉት ተክል ነው

[ምንጮች]

Courtesy Sam Fentress

Courtesy Jenny Mealing/flickr.com