በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕላኔቷ ምድራችን አደጋ ተደቅኖባታል?

ፕላኔቷ ምድራችን አደጋ ተደቅኖባታል?

ፕላኔቷ ምድራችን አደጋ ተደቅኖባታል?

የምድር ሙቀት መጨመር፣ በሰው ልጆች ላይ ከተደቀኑት አደጋዎች ሁሉ እጅግ የከፋው እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል። ሳይንስ የተሰኘው መጽሔት እንደሚናገረው ተመራማሪዎችን የሚያስጨንቃቸው “በአዝጋሚ ሁኔታ የጀመርነው ለውጥ ተፋፍሞ የሚቀጥል መሆኑ ነው።” አንዳንዶች የዚህን አባባል እውነተኝነት ይጠራጠራሉ። እውነት ነው፣ ብዙዎች የምድር ሙቀት እየጨመረ ነው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ፤ ይሁን እንጂ መንስኤው ምን እንደሆነና ምን መዘዝ እንደሚያስከትል የሚያውቁት ነገር የለም። የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ቢያምኑም ዋነኛው መንስኤ እንዳልሆነ ይናገራሉ። እንዲህ ያለ የሐሳብ ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?

መጀመሪያ ነገር፣ ለምድር አየር ንብረት መንስኤ የሆኑት ተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስብስብ ከመሆናቸውም በላይ እነዚህን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መረዳት አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም በመስኩ የተሠማሩ ሰዎች፣ የምድር ሙቀት እየጨመረ እንዲመጣ ካደረጉት ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች ሳይንሳዊ መረጃዎችን የሚተረጉሙት እንደፈለጉ ነው።

የምድር ሙቀት በእርግጥ እየጨመረ ነው?

ኢንተርገቨርንመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ (IPCC) የተባለ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት የምድር ከባቢ አየር ሙቀት መጨመሩ “አሌ የማይባል ሐቅ” ሲሆን ለዚህም ተጠያቂው ሰው መሆኑ “እሙን ነው።” በዚህ መደምደሚያ በተለይም ተጠያቂው ሰው ነው በሚለው ሐሳብ የማይስማሙ አንዳንድ ሰዎች፣ ከተሞች እየሰፉ በመሄዳቸው ምክንያት ሙቀታቸው እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ይናገራሉ። ከዚህም በላይ አርማታና ብረቶች የፀሐይን ሙቀት አምቀው ስለሚይዙ ከመሸ በኋላም እንኳ ቶሎ አይቀዘቅዙም። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በከተሞች የሚመዘገበው የሙቀት መጠን የገጠሩን እንደማይወክልና ዓለም አቀፉን አኃዛዊ መረጃ ሊያዛባው እንደሚችል ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ግን አላስካ አካባቢ በሚገኝ ደሴት ላይ የሚኖሩ ክሊፎርድ የሚባሉ የአገር ሽማግሌ እየተከሰቱ ያሉትን ለውጦች በገዛ ዓይናቸው እንደተመለከቱ ተናግረዋል። የመንደራቸው ሰዎች የተለያዩ የአጋዘን ዝርያዎችን ለማደን ወደ አላስካ የሚሻገሩት ባሕሩ ላይ በተጋገረው በረዶ ላይ ተጉዘው ነበር። ይሁንና የአካባቢው ሙቀት መጨመሩ እንዲህ ያለውን ሁኔታ አዳጋች አድርጎታል። ክሊፎርድ እንዲህ ብለዋል:- “የባሕሩ ሞገድ ተለውጧል፣ የበረዶው ሁኔታ ተለውጧል፣ በረዶው በቸክቺ ባሕር ላይ የሚጋገርበት ጊዜም . . . ተለውጧል።” እሳቸው እንደሚሉት ድሮ ድሮ በረዶው ባሕሩ ላይ የሚጋገረው ጥቅምት መጨረሻ ላይ ነበር፤ አሁን ግን እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ ድረስ ይቆያል።

በ2007 ኖርዝዌስት ፓሴጅ የሚባለው መተላለፊያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመርከብ ጉዞ ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑ የምድር ሙቀት ለመጨመሩ ግልጽ ማስረጃ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ናሽናል ስኖው ኤንድ አይስ ዴታ ሴንተር በተባለው ማዕከል ውስጥ ለረጅም ዓመት የሠሩ አንድ ሳይንቲስት “በዚህ ዓመት [በ2007] ያየነው ነገር በረዶ የሚቆይባቸው ወቅቶች እያጠሩ መምጣታቸውን የሚገልጹትን መረጃዎች የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።

ግሪንሃውስ ኢፌክት —ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ክስተት

እንዲህ ላለው ለውጥ መንስኤ ተደርገው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ በምድር ላይ ላለው ሕይወት ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ግሪንሃውስ ኢፌክት የሚባለው ተፈጥሯዊ ክስተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ነው። ከፀሐይ የሚመጣው ሙቀት ምድር ላይ ሲደርስ 70 በመቶ የሚያህለው ተውጦ ስለሚቀር አየሩን፣ መሬቱንና ባሕሩን ያሞቀዋል። እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ባይኖር ኖሮ የምድር አማካይ የሙቀት መጠን ከዜሮ በታች 18 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይሆን ነበር። ይህ ሙቀት በጨረር መልክ ቀስ በቀስ ወደ ሕዋ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህ ደግሞ ምድር ከመጠን በላይ እንዳትሞቅ ያደርጋል። ነገር ግን በአየር ብክለት ምክንያት የከባቢ አየር ይዘት ሲቀየር ወደ ሕዋ የሚመለሰው ሙቀት መጠን እየቀነሰ መጣ። ይህም ለምድር ሙቀት መጨመር ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ግሪንሃውስ ኢፌክት ለተባለው ክስተት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ጋዞች መካከል ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ናይትረስ ኦክሳይድ፣ ሚቴን እንዲሁም የውኃ ተን ይገኙበታል። የኢንዱስትሪው አብዮት ከፈነዳበት እንዲሁም እንደ ከሰል ድንጋይና ነዳጅ ዘይት ባሉት ነገሮች መጠቀም እየጨመረ ከመጣበት ከ250 ዓመታት ወዲህ በከባቢ አየር ውስጥ ያሉት የእነዚህ ጋዞች መጠን በጣም ጨምሯል። ለእነዚህ ጋዞች መጨመር እንደ መንስኤ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሌላው ምክንያት ሚቴን እና ናይትረስ ኦክሳይድ የሚያመነጭ የምግብ መፍጫ ሥርዓት ያላቸው የርቢ እንስሳት ቁጥር መጨመር ነው። አንዳንድ ተመራማሪዎች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሙቀት የጨመረው የሰው ልጆች በአየር ንብረቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ከመጀመራቸው በፊት ተከስተዋል በሚሏቸው ነገሮች ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

የአየር ንብረት መለወጡ የተለመደ ነገር ነው?

ለሙቀት መጨመር ተጠያቂዎቹ ሰዎች ናቸው የሚለውን ሐሳብ የሚቃወሙ ግለሰቦች የምድር ሙቀት ድሮም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ ይለዋወጥ እንደነበረ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች፣ አንዳንዶች ምድር ከአሁኑ ይልቅ በጣም ቀዝቃዛ ነበረች እያሉ የሚናገሩለትን የበረዶ ዘመን ታሪክ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፤ የአካባቢ ሙቀት መጨመር የተለመደ መሆኑን ለማስረዳት እንደ ግሪንላንድ ያሉ እጅግ ቀዝቃዛ አካባቢዎች በአንድ ወቅት የቆላ ዕፅዋት ይበቅሉባቸው የነበረ መሆኑንም ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ። እርግጥ ነው፣ የሳይንስ ሊቃውንት የታሪክን ገጽ ወደኋላ በገለጡ ቁጥር ስለ አየሩ ሁኔታ ያላቸው እርግጠኝነት እየቀነሰ እንደሚመጣ ያምናሉ።

የሰው ልጅ ለምድር ሙቀት መጨመር አስተዋዕኦ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት የአየር ንብረቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲለዋወጥ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት ክስተቶች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ መካከል ፀሐይ ከምታመነጨው የሙቀት መጠን መለዋወጥ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነቁጠ ፀሐይ (sunspots) እና በፀሐይ ላይ የሚከሰተው ድንገተኛ የሃይድሮጅን ፍንዳታ (solar flares) ይገኙበታል። በተጨማሪም ምድር ፀሐይን ለመዞር የምትከተለው ምሕዋር በብዙ ሺህ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሊጠብ ወይም ሊሰፋ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ፕላኔታችን ከፀሐይ ባላት ርቀት ላይ ለውጥ ያመጣል። እሳተ ገሞራ የሚተፋው አመድና የባሕር ሞገዶች መለዋወጥም የራሳቸው ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።

የአየር ንብረት ሞዴል

መንስኤው ምንም ይሁን ምን የምድር ሙቀት እየጨመረ ነው። ታዲያ ይህ በእኛም ሆነ በተፈጥሮ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ወደፊት ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነገሮች ትክክለኛ ትንቢት መናገር አዳጋች ነው። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት የአየር ንብረቱ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ የሚረዷቸው የተራቀቁ ኮምፒውተሮች አሏቸው። በኮምፒውተሮቻቸው ላይ በሠሯቸው ሞዴሎች ውስጥ የፊዚክስ ሕጎችን፣ የአየር ንብረትን የሚጠቁሙ አኃዛዊ መረጃዎችን እንዲሁም በአየር ንብረቱ ላይ ተጽዕኖ የሚኖራቸው ተፈጥሯዊ ክስተቶችን አካትተዋል።

እነዚህ ሞዴሎች፣ የሳይንስ ሊቃውንቱ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ቃል በቃል ሊፈጽሟቸው የማይችሏቸውን ነገሮች እንዲሞክሩ አስችለዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ የምታመነጨው ኃይል በዋልታ በረዶ፣ በአየሩና በባሕሩ ሙቀት፣ በትነት መጠን፣ በደመና አፈጣጠር፣ በነፋስና በዝናብ እንዲሁም በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለማየት በመጠኑ ላይ “ለውጥ” ያደርጋሉ። የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችን “ይፈጥሩና” ከዚያ የሚወጣው አመድ በአየር ንብረቱ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያስከትል ይመረምራሉ። ከዚህም በላይ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የደን መጨፍጨፍ፣ የመሬት አጠቃቀም፣ ከባቢ አየር ውስጥ ያሉት ጋዞች መብዛት እንዲሁም የመሳሰሉት ነገሮች የሚያስከትሉትን ውጤት መመርመር ይችላሉ። የሳይንስ ሊቃውንቱ ሞዴሎቻቸው በጊዜ ሂደት ይበልጥ ትክክለኛና አስተማማኝ እንደሚሆኑ ተስፋ ያደርጋሉ።

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሞዴሎች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? ይህ በአብዛኛው የተመካው በአኃዛዊ መረጃዎቹ ትክክለኝነትና ለኮምፒውተሮቹ በምንሰጠው መረጃ መጠን ላይ ነው። በመሆኑም በውጤቱ ላይ የሚኖረው ለውጥ መጠነኛ አሊያም በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን ሳይንስ መጽሔት እንደሚናገረው “[በተፈጥሯዊው] የአየር ንብረት ላይ ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰት ይችላል።” አሁንም እንኳ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን በእጅጉ ያስገረሙ ፈጽሞ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች እየተከሰቱ ነው፤ ከእነዚህም መካከል የአርክቲክ በረዶ ባልተጠበቀ ፍጥነት መቅለጡ ይገኝበታል። ፖሊሲ አውጪዎች በአሁኑ ጊዜ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ወይም አለመውሰድ ስለሚያስከትለው ውጤት ያላቸው ግንዛቤ መጠነኛ ቢሆንም ነገ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ ዛሬ አንዳንድ ውሳኔዎችን ማድረግ ይችላሉ።

ኢንተርገቨርንመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ (IPCC) የተባለው የተመራማሪዎች ቡድን ከዚህ በመነሳት በስድስት ሞዴሎች ላይ ምርምር እያደረገ ነው። ከእነዚህም መካከል በተወሰኑት ሞዴሎች ላይ ወደ ከባቢ አየሩ የሚለቀቀው ጋዝ ምንም ቁጥጥር የማይደረግበት ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ልክ በአሁኑ ጊዜ እንዳለው መጠነኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፤ በተቀሩት ላይ ደግሞ የከባቢ አየር ጋዞች መጠን እንዳይበዛ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ሞዴል የሚኖረው የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሁኔታ የተለያየ ነው። ተንታኞች ትንበያዎቹን መሠረት በማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል። ከእነዚህ መካከል የነዳጅ ዘይትን አጠቃቀም በሚመለከት ሕግ ማውጣት፣ ደንብ ተላላፊዎችን መቅጣት፣ ተጨማሪ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎችን መገንባትና በከባቢ አየሩ ላይ ጉዳት የማያደርሱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማስተዋወቅ ይገኙበታል።

ሞዴሎቹ አስተማማኝ ናቸው?

ተቺዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የሚሠራባቸው የትንበያ ዘዴዎች “መሠረት የሌለው ነገር ይዘው በመነሳት ውስብስብ የሆነውን የአየር ንብረት ሥርዓት አቃልለው ያቀርባሉ፤” እንዲሁም “አንዳንድ [የተፈጥሮ] ሂደቶችን ችላ ብለው ያልፋሉ።” ከዚህም ሌላ ተቺዎች ከሞዴሎቹ የሚገኘው ውጤት ወጥነት እንደሚጎድለው ይናገራሉ። ኢንተርገቨርንመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ (IPCC) የተባለው የተመራማሪዎች ቡድን አባል የሆኑ አንድ ሳይንቲስት እንዲህ ብለዋል:- “እጅግ ውስብስብ የሆነውን የአየር ንብረት ሥርዓት የመለካቱና አጠቃላይ ሁኔታውን የመረዳቱ ሥራ ፈጽሞ ከአቅማችን በላይ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶቻችን ስለ አሠራሩ የማወቅ ችሎታችንን እስከ መጠራጠር ደርሰናል።” *

የችግሩ መንስኤ በእርግጠኝነት ስለማይታወቅ ምንም እርምጃ መውሰድ አያስፈልግም የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን ሰበብ አድርጎ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን በመጪው ትውልድ ሕልውና ላይ ቁማር ከመጫወት ተለይቶ እንደማይታይ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች “የተፈራው ነገር ቢደርስ ለልጆቻችን ምን ብለን እናስረዳቸዋለን?” ይላሉ። የአየር ንብረት ሞዴሉ ትክክለኛ ሆነም አልሆነ፣ ምድር ከባድ ችግር የተደቀነባት ለመሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሕይወትን ለማቆየት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ተፈጥሮ በብክለት፣ በደን ጭፍጨፋ፣ በከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የተለያዩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ከምድር ገጽ በመጥፋታቸው ሳቢያ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት ነው። በምድር ላይ እየደረሱ ካሉት የማይካዱ ችግሮች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።

ከዚህ በመነሳት እኛንም ሆነ ውብ የሆነችውን ምድራችንን ከጥፋት ለመታደግ መላው የሰው ዘር የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርግ መጠበቅ እንችላለን? ከዚህም ሌላ፣ ለምድር ሙቀት መጨመር መንስኤው የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሆነ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ የቀረን ጊዜ በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ሳይሆኑ ጥቂት ዓመታት ናቸው። እነዚህን ለውጦች ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ የችግሩን ዋና ዋና መንስኤዎች ማለትም ስግብግብነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ድንቁርናን፣ ብቃት የጎደለው መስተዳድርንና ግዴለሽነትን በአፋጣኝ ማስወገድ ይኖርብናል። በእርግጥ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው ወይስ እንዲያው ምኞት ብቻ ነው? እንዲሁ ምኞት ብቻ ከሆነ ምንም ተስፋ የለንም ማለት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 ኅዳር 1, 2007 ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ የወጣውን ይህን ሐሳብ የተናገሩት ሀንትስቪል፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው የአላባማ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሥርዓት ሳይንስ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጆን አር ክሪስቲ ናቸው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የምድርን ሙቀት መለካት የምትችለው እንዴት ነው?

ይህን ማድረግ ምን ያህል ተፈታታኝ መሆኑን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። የአንድን ትልቅ ክፍል የሙቀት መጠን መለካት የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል ቴርሞሜትሩን የት ታስቀምጠዋለህ? ሙቀቱ ከፍ ሲል በወለሉ አካባቢ ካለው አየር ይልቅ በጣራው አካባቢ ያለው አየር ይሞቃል። በተጨማሪም ቴርሞሜትሩ መስኮት አጠገብ፣ ፀሐይ ላይ፣ ወይም ጥላ ሥር መቀመጡ በውጤቱ ላይ ለውጥ ያመጣል። ጠቆር ያሉ ነገሮች ሙቀት ስለሚስቡ የሙቀቱ መጠን እንደ ቀለሙ ዓይነትም ሊለያይ ይችላል።

ስለዚህ ትክክለኛውን የሙቀት መጠን ለማግኘት አንድ ጊዜ ብቻ መለካቱ በቂ ላይሆን ይችላል። በክፍሉ ውስጥ በተለያየ ቦታ ላይ ሙቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ለክተህ አማካይ ማውጣት ይኖርብሃል። እንዲሁም የሙቀቱ መጠን ከቀን ቀን ብሎም ከወቅት ወቅት ሊለያይ ይችላል። ስለዚህ ትክክለኛውን አማካይ ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ በተደጋጋሚ መለካት ይኖርብሃል። የአንድን ክፍል የሙቀት መጠን መለካት ይህን ያክል አስቸጋሪ ከሆነ የመሬቱን፣ የአየሩንና የውቅያኖሱን አጠቃላይ የሙቀት መጠን መለካት ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ያም ሆኖ በአየር ንብረት ላይ የሚከሰተውን ለውጥ በትክክል ለማወቅ እንዲህ ያሉ አኃዛዊ መረጃዎችን ማሰባሰቡ እጅግ አስፈላጊ ነው።

[ምንጭ]

NASA photo

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መፍትሔው የኑክሌር ኃይል ነው?

በመላው ዓለም የኃይል ፍጆታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ነዳጅ ዘይትንና የከሰል ድንጋይን መጠቀም በከባቢ አየር ውስጥ ያሉትን ጋዞች መጠን ስለሚጨምር አንዳንድ መንግሥታት አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማግኘት በሚገባ እያሰቡበት ነው፤ ብክለት የማያስከትል ሆኖ ያገኙትም የኑክሌር ኃይል ነው። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን የራሱ ችግር አለው።

ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከፍተኛ የኑክሌር ተጠቃሚ ከሆኑት አገሮች አንዷ የሆነችው ፈረንሳይ የኑክሌር ማብለያዎችን ለማቀዝቀዝ በየዓመቱ 19 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ያስፈልጋታል። ከባድ ሙቀት አጋጥሞ በነበረበት በ2003 ከፈረንሳይ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች በየጊዜው ይወጣ የነበረው የፈላ ውኃ የወንዞቹን የሙቀት መጠን እጅግ ከፍ አድርጎት ነበር፤ ይህም በወንዞቹ ውስጥ የሚኖሩትን ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን መዝጋት ግድ ሆኗል። የዓለም አቀፉ የሙቀት መጠን እየጨመረ ከሄደ ይህ ሁኔታ እንደሚባባስ ይጠበቃል።

ዩኒየን ኦቭ ኮንሰርንድ ሳይንቲስትስ የተባለው ድርጅት አባልና የኑክሌር መሐንዲስ የሆኑት ዴቪድ ሎችባውም፣ “የኑክሌር ኃይል እንዲኖረን ከተፈለገ በመጀመሪያ የአየር ንብረት መለወጡ ያስከተለውን ችግር መፍታት አለብን” ብለዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ካርታ]

ከአየር መዛባት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ አደጋዎች በ2007

ከአየር መዛባት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ አደጋዎችን በማስተናገድ ረገድ 2007ን የሚወዳደር የለም። የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ በዚህ ዓመት 14 የድንገተኛ አደጋ ጥሪዎችን አስተላልፏል። ይህ አኃዝ በ2005 ከተመዘገበው በ4 ይበልጣል። በ2007 ከደረሱት አደጋዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። ዝርዝሩ እያንዳንዱ አደጋ ያስከተለውን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ችግር እንደማይጨምር አስታውስ።

▪ ብሪታንያ:- ከ60 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ከደረሱት ሁሉ እጅግ የከፋ በሆነው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ350,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል። በእንግሊዝና በዌልስ ከግንቦት እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተመዝግቧል፤ አኃዛዊ መረጃዎች መያዝ ከተጀመረበት ከ1766 ወዲህ በእነዚህ ወራት ይህን ያህል መጠን ያለው ዝናብ ጥሎ አያውቅም።

▪ ምዕራብ አፍሪካ:- በ14 አገሮች ውስጥ በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት 800,000 ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል።

▪ ሌሶቶ:- ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ ሰብል አወደመ። ወደ 553,000 የሚጠጉ ሰዎች የምግብ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

▪ ሱዳን:- ኃይለኛ ዝናብ 150,000 ሰዎችን ያለ መጠለያ አስቀርቷል። ቢያንስ 500,000 የሚሆኑ እርዳታ ተደርጎላቸዋል።

▪ ማዳጋስካር:- ደሴቲቱን የመታው ኃይለኛ አውሎ ነፋስና የጣለው ከባድ ዝናብ 33,000 ሰዎችን ከማፈናቀሉም በላይ የ260,000 ገበሬዎችን ሰብል አውድሟል።

▪ ሰሜን ኮሪያ:- በብዙ ቦታዎች ላይ በደረሰ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የጭቃ ናዳ ሳቢያ በግምት 960,000 የሚሆኑ ሰዎች ለከባድ ችግር ተዳርገዋል።

▪ ባንግላዴሽ:- የጎርፍ መጥለቅለቅ በ8.5 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ከ3,000 የሚበልጡ ሰዎችንና 1.25 ሚሊዮን ከብቶችን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርጓል። ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶች ደግሞ አንድም ጉዳት ደርሶባቸዋል አሊያም ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል።

▪ ሕንድ:- የጎርፍ መጥለቅለቅ በ30 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

▪ ፓኪስታን:- አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ 377,000 ሰዎችን ያለ መጠለያ አስቀርቶ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

▪ ቦሊቪያ:- ከ350,000 የሚበልጡ ሰዎች በጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ ችግር ላይ የወደቁ ሲሆን 25,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።

▪ ሜክሲኮ:- የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያንስ 500,000 ሰዎችን ያለ መጠለያ ያስቀረ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለችግር ዳርጓል።

▪ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ:- ለረዥም ሰዓት የጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ያስከተለ ከመሆኑም በላይ 65,000 ሰዎችን አፈናቅሏል።

▪ ዩናይትድ ስቴትስ:- ድርቅ ባጠቃው የደቡባዊ ካሊፎርኒያ ደን ላይ በተነሳው ሰደድ እሳት ሳቢያ 500,000 ነዋሪዎች ከቤታቸው ለመሸሽ ተገድደዋል።

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery