በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤት የምገባበትን ሰዓት በተመለከተ የተሰጠኝን መመሪያ እንዴት ልመለከተው ይገባል?

ቤት የምገባበትን ሰዓት በተመለከተ የተሰጠኝን መመሪያ እንዴት ልመለከተው ይገባል?

የወጣቶች ጥያቄ

ቤት የምገባበትን ሰዓት በተመለከተ የተሰጠኝን መመሪያ እንዴት ልመለከተው ይገባል?

ከጓደኞችህ ጋር አምሽተህ ቤት ስትደርስ በጣም መሽቷል። ቤት መግባት ያለብህን ሰዓት ስላሳለፍክ የቆየህበትን ምክንያት ለወላጆችህ ማስረዳት ይጠበቅብሃል። ወደ ቤት ከመግባትህ በፊት ቆም ብለህ አመነታህ። ‘አባባና እማማ ተኝተው ሊሆን ይችላል’ ብለህ በማሰብ በሩን በቀስታ ስትከፍት ወላጆችህ ሰዓቱን እያዩ ሲጠብቁህ አገኘሃቸው። ያመሸህበትን ምክንያት እንድታስረዳቸው ይጠብቁብሃል።

እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ቤት የምትገባበትን ሰዓት በተመለከተ ከወላጆችህ ጋር ሳትስማሙ የቀራችሁበት ጊዜ አለ? የ17 ዓመቷ ዲቦራ “ሠፈራችን ሰላማዊ ነው ማለት ይቻላል፤ እንደዚያም ሆኖ ቤት ሳልገባ በጣም ከመሸ ወላጆቼ መጨነቅ ይጀምራሉ” ብላለች። *

ልጆች ቤት የሚገቡበትን ሰዓት በተመለከተ ወላጆች የሚያወጡትን መመሪያ ማክበር ይህን ያህል የሚከብደው ለምንድን ነው? የበለጠ ነፃነት ለማግኘት መፈለግ ስህተት ነው? ወላጆችህ ቤት እንድትገባ በሚጠብቁብህ ሰዓት ረገድ በጣም ጥብቅ ከሆኑ ምን ማድረግ ትችላለህ?

መመሪያውን መታዘዝ አስቸጋሪ የሚሆንበት ምክንያት

ወላጆችህ የሚያወጡት የሰዓት ገደብ በተለይ ከጓደኞችህ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ እንደገደበብህ ከተሰማህ በጣም ሊያበሳጭህ ይችላል። የ17 ዓመቷ ናታሻ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ቤት የምገባበትን ሰዓት በተመለከተ ያወጡት መመሪያ በጣም ያበሳጨኛል። አንድ ቀን በአቅራቢያችን ባለች ጓደኛዬ ቤት ሆነን ፊልም እያየን ነበር። ወላጆቼ ይህንን ቢያውቁም ቤት መግባት ካለብኝ ሰዓት ሁለት ደቂቃ ሲያልፍ ስልክ ደውለው ለምን ቤት እንዳልተመለስኩ ጠየቁኝ!”

ስቴሲ የተባለች ወጣት ደግሞ ሌላውን ችግር ስትጠቅስ እንዲህ ብላለች፦ “እማማና አባባ ከመተኛታቸው በፊት ቤት እንድገባ ይጠበቅብኝ ነበር። ወላጆቼ እኔን ሲጠብቁ ሳይተኙ ከቆዩ ቤት ስመጣ በጣም ደክሟቸውና ተበሳጭተው አገኛቸዋለሁ።” ይህ ምን ያስከትላል? ስቴሲ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጉኛል። ይህ ደግሞ ያበሳጨኛል። ለምን ትተውኝ እንደማይተኙ አይገባኝም።” ከወላጆችህ ጋር እንዲህ ዓይነት ግጭት መፈጠሩ የ18 ዓመቷ ኬቲ የተሰማት ዓይነት ስሜት እንዲያድርብህ ሊያደርግ ይችላል፤ ኬቲ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡኝ ጫና እንዳደረግኩባቸው ሳይሰማኝ የበለጠ ነፃነት ቢሰጡኝ ደስ ይለኝ ነበር።”

አንተም እንደ እነዚህ ወጣቶች የሚሰማህ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦

ከቤት ውጭ ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስተኝ ለምንድን ነው? (አንዱ ላይ ምልክት አድርግ።)

□ ነፃነት እንዲሰማኝ ያደርገኛል።

□ ያለብኝን ውጥረት ይቀንስልኛል።

□ ከጓደኞቼ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ያስችለኛል።

እነዚህ የተለመዱ ምክንያቶች ናቸው። እያደግህ ስትሄድ የበለጠ ነፃነት ለማግኘት መፈለግህ ያለ ነገር ነው፤ ደግሞም ጊዜህን ከወትሮው በተለየ መንገድ ማሳለፍህ ዘና እንድትል ሊያደርግህ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ጓደኞች እንድታፈራ ያበረታታሃል። (መዝሙር 119:63፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22) ፈጽሞ ከቤት የማትወጣ ከሆነ ደግሞ ይህን ማድረግ አዳጋች ሊሆን ይችላል!

ይሁን እንጂ ወላጆችህ ቤት እንድትገባ የሚጠብቁብህ ሰዓት የማያፈናፍን ከሆነብህ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ለማከናወን የሚያስችል ነፃነት እንዴት ማግኘት ትችላለህ? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

አንደኛው ፈተና፦ ወላጆችህ ቤት እንድትገባ የወሰኑልህ ሰዓት ልጅ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደርግሃል። አሁን የ21 ዓመት ወጣት የሆነችው አንድሪያ “በጊዜ ቤት የሚያደርሰኝ ሰው ለማግኘት ስል አብረውኝ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፕሮግራም ማበላሸቴ ሕፃን እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል” ብላለች።

ምን ማድረግ ትችላለህ? መንጃ ፈቃድ ስታወጣ የሚኖረውን ሁኔታ አስብ። በአንዳንድ አገሮች ቢያንስ የተወሰነ ዕድሜ ላይ እስክትደርስ ድረስ የምትነዳበትን አካባቢና ሰዓት የሚገድብ እንዲሁም ከማን ጋር መንዳት እንደምትችል የሚገልጽ ሕግ አለ። እንዲህ ዓይነት ሕግ ባለበት አገር የምትኖር ከሆነ “ያለ ምንም ገደብ እንድነዳ ካልተፈቀደልኝ እስከ ጭራሹ ባልነዳ ይሻለኛል” ብለህ መንጃ ፈቃድ ላለማውጣት ትወስናለህ? በፍጹም እንዲህ አታደርግም! መንጃ ፈቃድ ማግኘትህ በራሱ ትልቅ እድገት እንደሆነ ይሰማሃል።

በተመሳሳይም ወላጆችህ ያስቀመጡት የሰዓት ገደብ በትክክለኛው አቅጣጫ አንድ እርምጃ እንደሄድክ የሚያሳይ የእድገት ምልክት እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። በተጣለብህ እገዳ ላይ ሳይሆን በሚያስገኝልህ ነፃነት ላይ ትኩረት አድርግ። ልጅ ከነበርክበት ጊዜ ይልቅ አሁን የበለጠ ነፃነት አልተሰጠህም?

እንዲህ ማድረግህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ቤት የምትገባበትን ሰዓት በተመለከተ ወላጆችህ ያወጡትን መመሪያ እንደ እንቅፋት ሳይሆን እምነት የሚጣልብህ ሰው መሆንህን ለማሳየት እንደሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አድርገህ መመልከትህ ሁኔታውን ቀላል ያደርግልሃል። ወላጆችህ በዚህ ረገድ ያወጡትን መመሪያ ከታዘዝክ ወደፊት ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡህ ይችላሉ።—ሉቃስ 16:10

ሁለተኛው ፈተና፦ ወላጆችህ በጊዜ ቤት እንድትገባ የሚጠብቁብህ ለምን እንደሆነ ሊገባህ አልቻለም። እናቷ ያወጣችላትን የሰዓት ገደብ ማክበር ይከብዳት የነበረችው ኒኪ “እማማ ሕግ የምታወጣው ሕግ ማውጣት ስለምትወድ ብቻ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” ብላለች።

ምን ማድረግ ትችላለህ? በምሳሌ 15:22 ላይ የሚገኘውን “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” የሚለውን መመሪያ በተግባር ለማዋል ጥረት አድርግ። ስለ ሁኔታው ከወላጆችህ ጋር በረጋ መንፈስ ተወያይ። በዛ ሰዓት ቤት እንድትገባ የወሰኑት ለምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። *

እንዲህ ማድረግህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ወላጆችህ የሚያቀርቡትን ምክንያት መስማትህ ሐሳባቸውን ለመረዳት ያስችልሃል። ስቴቨን እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ በሰላም ቤት መግባቴን ካላየች እንቅልፍ እንደማይወስዳት አባቴ ነገረኝ። ፈጽሞ እንደዚያ አስቤ አላውቅም ነበር።”

መቆጣት ወይም መከራከር መጥፎ ውጤት ማስከተሉ ስለማይቀር ምንጊዜም ነገሮችን በረጋ መንፈስ መወያየቱ የተሻለ መሆኑን አስታውስ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ናታሻ “በአብዛኛው ወላጆቼን ተናድጄ ከተናገርኳቸው በሚቀጥለው ጊዜ ላደርግ የምፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮች እንደምከለከል አውቃለሁ” ብላለች።

ሦስተኛው ፈተና፦ ወላጆችህ ነፃነት እንዳሳጡህ ይሰማሃል። አንዳንድ ጊዜ ወላጆችህ ቤት የምትገባበትን ሰዓት መወሰንን ጨምሮ ሌሎች ሕጎችን የሚያወጡት ለራስህ ጥቅም እንደሆነ ይነግሩሃል። የ20 ዓመቷ ብራንዲ “ወላጆቼ እንዲህ ሲሉኝ የራሴን ምርጫ እንዳደርግ ወይም ሐሳቤን እንድገልጽ እንደማይፈልጉ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ተናግራለች።

ምን ማድረግ ትችላለህ? “አንድ [ባለሥልጣን] አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ” የሚለውን በማቴዎስ 5:41 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ልታደርግ ትችላለህ። አሽሊ እና ወንድሟ ይህንን ምክር ሠርተውበታል። “አብዛኛውን ጊዜ ወላጆቻችን ከወሰኑልን ሰዓት 15 ደቂቃ ቀደም ብለን ቤት ለመድረስ ጥረት እናደርጋለን” ብላለች። አንተስ ተመሳሳይ ግብ ማውጣት ትችላለህ?

እንዲህ ማድረግህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? አንድን ነገር፣ ማድረግ ስላለብን ብቻ ሳይሆን በራሳችን ፍላጎት ተነሳስተን ስናደርገው የበለጠ ደስታ ያስገኝልናል! እንዲሁም ወላጆችህ ከወሰኑልህ ሰዓት ቀደም ብለህ ቤት ለመድረስ ከሞከርክ ጊዜህን የምትቆጣጠረው አንተ ራስህ ትሆናለህ። በተጨማሪም ‘የምታደርገው መልካም ነገር ሁሉ በውዴታ እንጂ በግዴታ አይሁን’ የሚለውን መሠረታዊ መመሪያ አስታውስ።—ፊልሞና 14

ከዚህም በላይ በጊዜ ቤት መግባትህ ወላጆችህ እንዲተማመኑብህ ስለሚያደርግ ብዙውን ጊዜ የበለጠ ነፃነት እንዲሰጡህ ያነሳሳቸዋል። የ18 ዓመቱ ዌድ “የወላጆችህን አመኔታ ካተረፍክ ተጨማሪ ነፃነት ይሰጡሃል” በማለት ተናግሯል።

ወላጆችህ ቤት የምትገባበትን ሰዓት በተመለከተ ያወጡትን መመሪያ ማክበር ፈታኝ እንዲሆንብህ የሚያደርግ ሌላ ምክንያት ካለህ ጻፍ።

․․․․․

ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላለህ?

․․․․․

እንዲህ ማድረግህ ጠቃሚ የሆነው ለምን ይመስልሃል?

․․․․․

ከወላጆችህ ቤት ወጥተህ ራስህን ችለህ የምትኖርበትና ሰፊ ነፃነት የምታገኝበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ግን ትዕግሥተኛ ሁን። አሁን የ20 ዓመት ወጣት የሆነችው ቲፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “የምትፈልገውን ያህል ነፃነት አታገኝ ይሆናል፤ ሆኖም ወላጆችህ የሚያወጧቸውን ገደቦች ማክበርን ከተማርክ የወጣትነት ዕድሜህን በሙሉ በመማረር አታሳልፍም።”

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.21 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በታኅሣሥ 2006 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ወላጆችህ ቤት የምትገባበትን ሰዓት በተመለከተ ያወጡት መመሪያ እንደሚያስቡልህ የሚያሳየው እንዴት ነው?

▪ ቤት መግባት ካለብህ ሰዓት ዘግይተህ ከመጣህ እንደገና የወላጆችህን አመኔታ ማትረፍ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዳንድ እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“ወላጆቼ ቤት እንድገባ የሚፈልጉበት ሰዓት ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማኛል፤ በቂ እንቅልፍ ካላገኘሁ ያነጫንጨኛል!” —የ17 ዓመቱ ጌብ

“ወላጆቼ በወሰኑልኝ ሰዓት ቤት መግባቴ ብዙ ጊዜ ከችግር ጠብቆኛል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ግብዣ ላይ እያለን የተወሰኑ ልጆች የአልኮል መጠጥ ይዘው መጡ። እኔና ጓደኛዬ ይህን ስናይ ቤት መግባት ያለብን ሰዓት መድረሱን ምክንያት አድርገን ከግብዣው ቦታ ወጣን።”—የ18 ዓመቷ ኬቲ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ግልጽ የሆነ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሞክሩ

ወላጆችህ ቤት እንድትገባ ስለሚፈልጉበት ሰዓት ተወያይታችሁ ከዚህ በታች ባሉት ነጥቦች ረገድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ለምን አትሞክሩም?

▪ ․․․․․ [ቀኖቹን ጻፍ] በ․․․․․ ሰዓት ቤት እገባለሁ፤ ․․․․․ [ቀኖቹን ጻፍ] ደግሞ በ․․․․․ ሰዓት እገባለሁ።

▪ ወላጆቼ በወሰኑት ሰዓት ቤት ሳልገባ ከቀረሁ ቢያንስ ለ․․․․․ ሳምንት በ․․․․․ ሰዓት እንድገባ ቅጣት ይወሰንብኛል።

▪ ቢያንስ ለ․․․․․ ወራት ሰዓቴን አክብሬ ቤት ከገባሁ ቤት እንድገባ በሚጠበቅብኝ ሰዓት ላይ ማሻሻያ ይደረግልኛል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቤት የምትገባበት ሰዓት ገፋ እንዲደረግልህ ከፈለግህ . . .

▪ ተስማሚ ጊዜ መርጠህ ጉዳዩን ለወላጆችህ አንሳላቸው። —መክብብ 3:1, 7

▪ ሁልጊዜ በተወሰነልህ ሰዓት ቤት በመግባት ጥሩ ስም አትርፍ።ማቴዎስ 5:37

▪ ወላጆችህ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ማየት እንዲችሉ አንዳንድ ቀናት ከወትሮው አምሽተህ እንድትገባ እንዲፈቅዱልህ ጠይቃቸው።—ማቴዎስ 25:23

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

▪ በሩ በቀስታ ሲከፈት ሰዓታችሁን ትመለከታላችሁ። ልጃችሁ ቤት መግባት ከነበረበት ሰዓት 30 ደቂቃ አሳልፏል። ‘ይሄን ጊዜ የተኛን መስሎታል’ ብላችሁ ታስባላችሁ። እናንተ ግን አልተኛችሁም። እንዲያውም ልጃችሁ ሰዓቱን ማሳለፉን ስታዩ በሩ ሥር ቁጭ ብላችሁ እየጠበቃችሁት ነው። በሩ ወለል ብሎ ሲከፈት ከልጃችሁ ጋር ዓይን ለዓይን ተፋጠጣችሁ። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? ልጃችሁን ምን ትሉታላችሁ?

የተለያዩ አማራጮች አሏችሁ። ‘የልጅ ነገር ይኸው ነው’ ብላችሁ ነገሩን ቀለል አድርጋችሁ በማየት ልታልፉት ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ ወደ ሌላው ጽንፍ በመሄድ ‘ከአሁን በኋላ ከዚች ቤት እግርህ አይወጣም’ ልትሉት ትችላላችሁ። በስሜት ገንፍላችሁ ከመናገራችሁ በፊት ልጁ ዘግይቶ የመጣበት በቂ ምክንያት ሊኖረው ስለሚችል አዳምጡት። ከዚያም በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ለልጃችሁ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ልትሰጡት ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ይህን አማራጭ ሞክሩ፦ ስለዚህ ጉዳይ በማግስቱ እንደምትነጋገሩበት ንገሩት። ከዚያም አመቺ ጊዜ ምረጡና ምን ልታደርጉ እንዳሰባችሁ አወያዩት። አንዳንድ ወላጆች ከዚህ ቀጥሎ የቀረበውን ዘዴ ሞክረዋል፦ ልጃቸው ቤት መግባት ካለበት ሰዓት ዘግይቶ ከመጣ በሚቀጥለው ጊዜ ከወትሮው 30 ደቂቃ ቀደም ብሎ እንዲመለስ እንደሚጠበቅበት ይነግሩታል። በሌላ በኩል ደግሞ ልጁ ሁልጊዜ ሰዓቱን ጠብቆ በመምጣት እምነት የሚጣልበት መሆኑን ካሳየ በአንዳንድ ወቅቶች የተወሰነ ነፃነት ልትሰጡት ምናልባትም ቤት እንዲገባ የሚጠበቅበትን ሰዓት ገፋ ልታደርጉለት ታስቡ ይሆናል። ልጃችሁ በስንት ሰዓት ቤት እንዲገባ እንደሚጠበቅበት እንዲሁም ይህንን ካላደረገ ምን ቅጣት እንደሚጠብቀው በግልጽ ማወቁ አስፈላጊ ነው። ከዚያም መመሪያውን ከጣሰ ያላችሁትን ከመፈጸም ወደኋላ አትበሉ።

ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባ ነገር፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) ልጃችሁ ቤት እንዲገባ የምትፈልጉበትን ጊዜ ከመወሰናችሁ በፊት እሱ የሚመርጠውን ሰዓትና ይህንን ሰዓት የመረጠበትን ምክንያት እንዲናገር አጋጣሚ በመስጠት ስለ ጉዳዩ አወያዩት። ልጁ የሚያቀርበውን ሐሳብ ከግምት ለማስገባት ሞክሩ። ከዚህ ቀደም እምነት የሚጣልበት መሆኑን ካስመሠከረ የጠየቀው ነገር ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ እሱ የፈለገው እንዲሆን ልትስማሙ ትችሉ ይሆናል።

ሰዓት ማክበር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። በመሆኑም ልጃችሁ ቤት እንዲገባ የምትፈልጉበትን ሰዓት መወሰን ልጃችሁን ከችግር የመጠበቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንዲህ ስታደርጉ፣ ልጁ ራሱን ችሎ መኖር ከጀመረ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ የሚጠቅመው ጥሩ ልማድ እንዲያዳብር እያስተማራችሁት ነው።—ምሳሌ 22:6

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንጃ ፈቃድ ማውጣትህ እድገት ማድረግህን እንደሚጠቁም ሁሉ ቤት የምትገባበትን ሰዓት በተመለከተ ወላጆችህ መመሪያ ማውጣታቸውም እድገት እንዳደረግህ የሚያሳይ ነው