በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ማወቅ የሚገባቸው ነገር

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ማወቅ የሚገባቸው ነገር

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ማወቅ የሚገባቸው ነገር

ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ልጆች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ኮምፒውተሩን ሁሉም ሰው ሊያየው በሚችልበት ቦታ ማስቀመጥ በቂ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። እንዲህ ማድረጉ ልጆች አደገኛ የሆኑ ወይም ተገቢ ያልሆኑ ድረ ገጾችን ከመመልከት እንዲቆጠቡ እንደሚረዳቸው ይታመናል። አሁንም ቢሆን ልጆች መኝታ ቤታቸው ሆነው ብቻቸውን ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ መፍቀድ የጥበብ አካሄድ ባይሆንም ልጆችን ከአደጋ ለመጠበቅ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ሽቦ አልባ የመገናኛ ቴክኖሎጂ በመኖሩ ወጣቶች በየትኛውም ቦታ ሆነው ኢንተርኔት መጠቀም ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ በርካታ ሞባይል ስልኮችም የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት በሚያስችል መንገድ ተሠርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች በኢንተርኔት ካፌዎች፣ በቤተ መጻሕፍት እንዲሁም በጓደኛቸው ቤት ሆነው ኢንተርኔት መጠቀም ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ አማራጮች ስላሉ ወላጆች የልጆቻቸውን የኢንተርኔት አጠቃቀም ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው እንደሚችል ለመረዳት አያዳግትም።

ብዙ ወጣቶችን የሚማርኳቸውን አንዳንድ የኢንተርኔት አገልግሎቶችና እነዚህ ነገሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ እስቲ እንመልከት።

ኢ-ሜይል

ኢ-ሜይል ምንድን ነው? በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አማካኝነት የሚላክ በጽሑፍ የሰፈረ መልእክት ነው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? ኢ-ሜይል ከጓደኞችና ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ፈጣንና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ የመገናኛ ዘዴ ነው።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ ከማታውቋቸው ሰዎች የሚላኩ ብዙውን ጊዜ ስፓም ተብለው የሚጠሩ የኢ-ሜይል መልእክቶች የሚያበሳጩ ከመሆናቸውም ሌላ በአብዛኛው አስጸያፊ የሆኑ የብልግና ሐሳቦችን የያዙ ናቸው። እነዚህ መልእክቶች ተጠቃሚው (ልጅም ሊሆን ይችላል) የግል መረጃዎችን እንዲሰጥ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ የግለሰቡን መረጃ በመጠቀም ለሚፈጸም ወንጀል ሊያጋልጥ ይችላል። እንደዚህ ያሉ መልእክቶች በፍጹም እንዲላኩላችሁ እንደማትፈልጉ ለመግለጽ ብላችሁ ቢሆንም እንኳ ምላሽ መስጠታችሁ የኢ-ሜይል አድራሻችሁን እንደምትጠቀሙበት ስለሚጠቁም ከማታውቋቸው ሰዎች ተጨማሪ መልእክቶች እንዲደርሷችሁ ሊያደርግ ይችላል።

ድረ ገጽ

ድረ ገጽ ምንድን ነው? ድርጅቶች፣ የትምህርትና የንግድ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የሚያዘጋጁትና በየጊዜው ተጨማሪ ሐሳቦችን የሚያስገቡበት የተለያዩ መረጃዎችን የያዘ ገጽ ነው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድረ ገጾች ስላሉ ወጣቶች ለመገብየት፣ ምርምር ለማድረግ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ ለመጫወት ወይም ሙዚቃ ለማዳመጥ አሊያም እነዚህን ነገሮች ወደራሳቸው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ለመጫን ሰፊ አጋጣሚ ያገኛሉ።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ብዙ ሰዎች ድረ ገጽን ለመጥፎ ዓላማ ይጠቀሙበታል። በርካታ ድረ ገጾች ሰዎች የጾታ ብልግና ሲፈጽሙ በግልጽ የሚያሳዩ ሲሆን አንድ ሰው ካልተጠነቀቀ እነዚህን ድረ ገጾች ሳያውቅ ሊከፍት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከ8 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ወጣቶች ላይ በተደረገው ጥናት፣ 90 በመቶ የሚሆኑት ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ሳያስቡት የብልግና ምስሎችን ማየታቸውን ተናግረዋል፤ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸው የትምህርት ቤት ሥራቸውን በመሥራት ላይ ሳሉ ነው!

ወጣቶች ቁማር መጫወት የሚችሉባቸው አንዳንድ ድረ ገጾችም አሉ። ካናዳ ውስጥ ጥናት ከተደረገባቸው የ10ኛ እና የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ወንዶች መካከል 23 በመቶ የሚሆኑት ቁማር መጫወት የሚቻልባቸው ድረ ገጾች ውስጥ ገብተው እንደሚያውቁ ተናግረዋል። በኢንተርኔት አማካኝነት ቁማር መጫወት ከባድ ሱስ ሊሆን ስለሚችል ባለሙያዎች ሁኔታው ቢያሳስባቸው ምንም አያስገርምም። “የተዛባ የአመጋገብ ልማድን” የሚያበረታቱ ፕሮ አኖሬክሲያ የሚባሉ ድረ ገጾችም አሉ። * ከዚህም ሌላ አነስተኛ በሆኑ ጎሳዎችና የሃይማኖት ቡድኖች ላይ ጥላቻ የሚያነሳሱ ድረ ገጾች አሉ። አንዳንድ ድረ ገጾች ደግሞ ቦምብ መሥራት፣ መርዝ መቀመም እንዲሁም የሽብር ተግባር መፈጸም የሚቻልበትን መንገድ ያስተምራሉ። በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ ጨዋታዎች አሰቃቂ ዓመፅና ደም መፋሰስ በግልጽ ይታይባቸዋል።

ቻት ሩም

ቻት ሩም ምንድን ነው? ሰዎች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ መልእክት በመጻጻፍ ውይይት የሚያደርጉበት መድረክ ነው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? ልጃችሁ ከእሱ ጋር የሚመሳሰል ፍላጎት ካላቸውና ከዚህ ቀደም በአካል አግኝቷቸው ከማያውቃቸው በርካታ ግለሰቦች ጋር ሊወያይ ይችላል።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ በኢንተርኔት አማካኝነት ወይም በአካል ተገናኝተው ከልጆች ጋር የጾታ ብልግና መፈጸም የሚፈልጉ ምግባረ ብልሹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በቻት ሩም ይጠቀማሉ። ልጆቻችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ምን እንደሚያደርጉ ታውቃላችሁ? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ካዘጋጁት ሴቶች መካከል አንደኛዋ ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ስለ መከላከል ምርምር ስታደርግ ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ለመጽሐፉ እንዲረዳት በማሰብ በኢንተርኔት ላይ የ12 ዓመት ልጅ እንደሆነች አድርጋ ራሷን አስተዋወቀች። መጽሐፉ ሴትየዋ ምን እንዳጋጠማት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ወዲያውኑ ማለት ይቻላል አንድ ሰው በግል ቻት ሩም እንዲወያዩ ጠየቃት። እሷም ወደዚህ ቻት ሩም መግባት የሚቻልበትን መንገድ እንደማታውቅ ነገረችው፤ በዚህ ጊዜ አሳቢ የሆነው አዲሱ ጓደኛዋ ማድረግ ያለባትን ነገር ደረጃ በደረጃ ነገራት። ከዚያም [በኢንተርኔት አማካኝነት] የጾታ ግንኙነት መፈጸም ትፈልግ እንደሆነ ጠየቃት።”

ፈጣን መልእክቶች

ፈጣን መልእክቶች ምንድን ናቸው? ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መልእክት መጻጻፍ የሚችሉበት መንገድ ነው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? አንድ ሰው የኢንተርኔት አድራሻቸውን ከሚያውቃቸው ጓደኞቹ መካከል ከመረጣቸው ጋር ፈጣን መልእክቶችን መለዋወጥ ይችላል። በካናዳ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በ16ና በ17 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት በቀን ውስጥ ከአንድ ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ ከጓደኞቻቸው ጋር ፈጣን መልእክቶችን የሚላላኩ መሆኑ አያስገርምም።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ ልጃችሁ እያጠና ወይም ትኩረት የሚያሻው ሌላ ሥራ እያከናወነ ከሆነ እንዲህ ዓይነት መልእክት መለዋወጡ ሐሳቡን ሊሰርቅበት ይችላል። ከዚህም ሌላ ልጃችሁ ከማን ጋር እየተጻጻፈ እንዳለ ምን ታውቃላችሁ? ምክንያቱም ውይይታቸውን መስማት አትችሉም።

ብሎግ

ብሎግ ምንድን ነው? የዕለት ውሎን ለማስፈር የሚያስችል ድረ ገጽ ነው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? ሐሳባቸውን እንዲሁም የሚያስደስቷቸውንና ያከናወኗቸውን ነገሮች በጽሑፍ ለማስፈር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። እንደነዚህ ያሉት አብዛኞቹ ድረ ገጾች፣ አንባቢዎች አስተያየታቸውን ማስፈር የሚችሉበት ቦታ አላቸው፤ ብዙ ወጣቶች ደግሞ እነሱ የጻፉትን ነገር ሌላ ሰው አንብቦት ሐሳብ እንደሰጠበት ማወቅ ያስደስታቸዋል።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ እነዚህን ድረ ገጾች ማንም ሰው ሊያነባቸው ይችላል። አንዳንድ ግድየለሽ ወጣቶች የቤተሰባቸውን ማንነት ብሎም የትምህርት ቤታቸውን ወይም የቤታቸውን አድራሻ የሚጠቁም መረጃ ይሰጣሉ። ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር አለ፦ አንድ ሰው በእነዚህ ድረ ገጾች ላይ ያሰፈረው ሐሳብ የራሱንም ሆነ የሌሎችን መልካም ስም ሊያጎድፍ ይችላል። ለምሳሌ፣ ሠራተኛ መቅጠር የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ተቀጣሪው የዕለት ውሎውን የሚያሰፍርበትን ድረ ገጽ ይመለከታሉ።

ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትባቸው ድረ ገጾች

ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትባቸው ድረ ገጾች ምንድን ናቸው? ወጣቶች የራሳቸውን ድረ ገጽ መፍጠርና በዚህ ድረ ገጽ ላይ ፎቶግራፎችን፣ የቪዲዮ ምስሎችንና የዕለት ውሏቸውን ማስገባት የሚችሉባቸው ገጾች ናቸው።

ወጣቶችን የሚማርካቸው ለምንድን ነው? አንድ ወጣት ድረ ገጽ መፍጠሩና በዚህም ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ማስገባቱ ማንነቱን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጠዋል። ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትባቸው ድረ ገጾች፣ ወጣቶች በርካታ አዳዲስ “ጓደኞችን” እንዲያፈሩ ያስችሏቸዋል።

ወላጆች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር፦ ጆአና የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትበት ድረ ገጽ በኢንተርኔት ላይ እንደተዘጋጀ ግብዣ ነው። አንዳንድ አስፈሪ ሰዎች ወደ ግብዣው ሊመጡ ይችላሉ።” ምግባረ ብልሹ የሆኑ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ማኅበራዊ ግንኙነት በሚመሠረትበት ድረ ገጽ ላይ የሰፈሩትን መረጃዎች ለመጥፎ ዓላማ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ኢንተርኔት የሚያስከትለውን አደጋ ስለመከላከል የሚያጠኑ ፔር አፍታብ የተባሉ ባለሙያ እንዲህ ዓይነቶቹን ድረ ገጾች “የጾታ ጥቃት መፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉንም ነገር የሚያገኙበት የገበያ አዳራሽ” በማለት ገልጸዋቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኢንተርኔት የሚመሠረተው ወዳጅነት እውነተኛ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ወጣቶች ብዙ ጓደኞች ያሏቸው ለመምሰል ሲሉ በአካል አግኝተዋቸው የማያውቋቸውን ሰዎች አድራሻ ዝርዝር በድረ ገጻቸው ላይ ያሰፍራሉ። ካንዲስ ኬልሲ፣ ጀነሬሽን ማይስፔስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ ‘ወጣቶች አንድ ሰው ጥሩ ጓደኛ መሆን አለመሆኑን የሚገመግሙት ግለሰቡ በምን ያህል ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆኑን በማየት ነው።’ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ ‘የሰዎችን ጥሩነት በሌሎች ዘንድ ባላቸው ተወዳጅነት መገምገም ልጆቻችን እንደ ዕቃ እንዲቆጠሩ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጓደኞች ለማግኘት ሲሉ ማንኛውንም ነገር እንዲያደርጉ ጫና ይፈጥርባቸዋል።’ ልጆቻችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ምን እንደሚያደርጉ ታውቃላችሁ? የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን ተገቢ ጥያቄ ያነሳል፦ “[የኢንተርኔቱ] ዓለም ወጣቶች ከተለያዩ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቁና ለሰዎቹ አሳቢነት ሳያሳዩ ዋጋ እንደሌለው ዕቃ ቆጥረው እንዲተዉአቸው እያበረታታ እያለ ልጆቻችሁ አዘኔታና ርኅራኄ ማዳበር እንዳለባቸው እንዴት ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ?”

እነዚህ ስድስት ምሳሌዎች በዛሬው ጊዜ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ወጣቶችን ከሚማርኳቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ወላጆች ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አደጋዎችን ለማስቀረት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 እንደነዚህ ያሉት አብዛኞቹ ድረ ገጾችና ድርጅቶች የተዛባ የአመጋገብ ልማድ መከተልን እንደማያበረታቱ ይገልጻሉ። ሆኖም ከእነዚህ አንዳንዶቹ አኖሬክሲያ ሕመም ሳይሆን በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመሠረተ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ። እነዚህ ድረ ገጾች አንድ ወጣት የሰውነቱን ትክክለኛ ክብደት መደበቅ እንዲሁም ወላጆቹ የአመጋገብ ልማዱ የተዛባ መሆኑን እንዳያውቁበት ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ መረጃዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችል የውይይት መድረክ አላቸው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሕንድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 54 በመቶ የጨመረ ሲሆን ለዚህም በአብዛኛው ምክንያት የሆኑት ወጣቶች ናቸው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንድ ወላጅ፣ በኮምፒውተር ላይ የተገጠመ የቪዲዮ ካሜራ ልጁ ከጓደኞቹና ከዘመዶቹ ጋር ለመገናኘት የሚችልበት ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ የመገናኛ መሥመር እንደሆነ ሊያስብ ይችላል፤ ልጆችን ለማጥቃት ለሚፈልጉ ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነቱ ካሜራ ወደ አንድ ልጅ መኝታ ክፍል ለመግባት የሚያስችል ክፍት መስኮት ይሆንላቸዋል።”—ሣልሳዊ ሮበርት ሙለር፣ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር