ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ድረ ገጽ (www.watchtower.org) መረጃዎቹን በ314 ቋንቋዎች ያቀርባል። ባለፈው ዓመት ድረ ገጹ ከ22 ሚሊዮን ለሚበልጥ ጊዜ ያህል ተጎብኝቷል፤ ይህም ሲባል በየቀኑ በአማካይ ከ60,000 ጊዜ በላይ ተጎብኝቷል ማለት ነው።
▪ “ዓለም ከተደቀነባት እልህ አስጨራሽ ችግሮች ሁሉ የከፋው ለሰው ሁሉ ንጽሕናው የተጠበቀ በቂ ውኃ ማቅረብ ነው። . . . ብዙውን ጊዜ ውኃ በሚያስፈልገን ቦታ የምናገኘው ጠመንጃ ነው።” —ባን ኪሙን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ
ደስታና ጤንነት
ውጥረት ካለባቸው፣ በጥላቻ ከተሞሉ ወይም አሉታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ይልቅ ደስተኛ የሆኑና አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው የተሻለ ጤንነት እንዳላቸው ከረዥም ጊዜ በፊት ሲታመን ቆይቷል። በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት፣ በሰውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ በዝቶ ከቆየ ለተለያዩ ሕመሞች ሊዳርግ የሚችለው ኮርቲሶል የሚባለው በውጥረት የሚመጣ ሆርሞን “የደስተኝነት መንፈስ” ባላቸው ሰዎች ውስጥ በአነስተኛ መጠን እንደሚገኝ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። በተጨማሪም “በሰውነት ውስጥ በስፋት የተሰራጨ ኢንፌክሽን መኖሩን የሚጠቁሙት ሁለት የፕሮቲን ዓይነቶች” እንደነዚህ ባሉት ሰዎች ውስጥ በዝቅተኛ መጠን እንደሚገኙ ተደርሶበታል። በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር አንድሩ ስቴፕቶ እንደሚሉት ከሆነ “ጠባያችን በዘር ውርስ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነትና በሕይወታችን ውስጥ በምናገኘው ስኬት ላይ የተመካ ነው።”
ጨረቃን በተራቀቁ መሣሪያዎች ማየት
ለብዙ መቶ ዓመታት ሙስሊሞች የረመዳን ወር አብቅቶ ጾም የሚፈታበትን ቀን የምታበስረውን አዲስ ጨረቃ ለማየት ሰማዩን በትኩረት ሲመለከቱ ኖረዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች አዲሷን ጨረቃ ለማየት የሚሞከረው በዓይን ብቻ ነበር፤ ከዚያ በኋላ አንድ የሃይማኖት መሪ ለእምነቱ ተከታዮች ሁኔታውን ያስታውቃል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ጨረቃን ለማየት በዘመናዊ መሣሪያዎች ለመጠቀም ተስማምተዋል። በአሁኑ ጊዜ ኢራናውያን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች፣ ያዩት ነገር ትክክል መሆኑን በሚያረጋግጡላቸው የሃይማኖት መሪዎች እየታገዙ እጅግ ዘመናዊ ቴሌስኮፖችን፣ በሌሊት መመልከት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን አልፎ ተርፎም የተራቀቁ የመመልከቻ መሣሪያዎች የጫኑ አውሮፕላኖችን ይጠቀማሉ። ጨረቃዋ ቶሎ ታየች ማለት በዓሉ ቀደም ብሎ ይከበራል ማለት ነው።
ጨቅላ ሕፃናት ሰውን መገምገም ይችላሉ?
ከተወለዱ ገና ስድስት ወር የሆናቸው ሕፃናት “መናገር ከመቻላቸው በፊት የሰዎችን ባሕርይ የመገምገም ችሎታ” እንደሚያዳብሩ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የዬል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ዕድሜያቸው ከስድስት እስከ አሥር ወር የሆናቸው ሕፃናት ትልልቅ ዓይኖች ያሉት አንድ አሻንጉሊት ተራራ ለመውጣት በሚሞክርበት ጊዜ አንዳንድ አሻንጉሊቶች ሲረዱት ሌሎቹ ደግሞ ወደኋላ ሲጎትቱት ተመለከቱ። ከዚያም ሕፃናቱ “በየትኞቹ ለመጫወት እንደሚመርጡ ለማየት ሲባል አሻንጉሊቶቹ ተሰጧቸው” በማለት ሂዩስተን ክሮኒክል ይገልጻል። “ሁሉም ሕፃናቶች ለማለት ይቻላል መጥፎውን አሻንጉሊት ትተው ለመርዳት ይጣጣር የነበረውን አሻንጉሊት መረጡ።” ስለዚህ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን “ሕፃናትም እንኳ ሳይቀሩ ተንኮለኛውን ከጥሩው በመለየት የትኛውን ጓደኛ መምረጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ” በማለት ጋዜጣው ይናገራል።
“አሜሪካውያን ለታሸገ ውኃ ያላቸው ጥም”
“አሜሪካውያን ለታሸገ ውኃ ያላቸው ጥም የሚቆርጥላቸው አይመስልም። ምክንያቱም ለዓመት የሚያስፈልጋቸው ውኃ 30 ቢሊዮን ጠርሙስ ሊደርስ ተቃርቧል” በማለት ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት ይናገራል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የታሸገ ውኃ ተጠቃሚዎች አብዛኛው የታሸገ ውኃ ከቧንቧ የተቀዳ መሆኑን አይገነዘቡም፤ በመሆኑም “ለጤናው ብሎ ከማዘጋጃ ቤት ውኃ ይልቅ የታሸገ ውኃን የሚመርጥ ሰው ተሳስቷል” በማለት መጽሔቱ ይናገራል። በብዙ አገሮች በቧንቧ የሚመጣው ውኃ የንጽሕና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል። ደግሞም “እጅግ በጣም ውድ ከሆነው” የታሸገ ውኃ ጋር ሲነጻጸር ከቧንቧ የሚገኘው ውኃ “በነፃ የሚገኝ ነው ለማለት ያስደፍራል።”