ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
ከአልኮል መጠጥ ባርነት ነፃ መውጣት (ግንቦት 2007) የይሖዋ ምሥክሮች መጽሔቶቻችሁን ሲሰጡኝ አነባለሁ። በመጽሔቶቻችሁ ላይ የሚገኙት ሐሳቦች በቴሌቪዥን ከሚታዩትና በጋዜጦች ላይ ከሚወጡት የሚያስጨንቁ ዜናዎች ጋር ሲወዳደሩ በጣም የሚያበረታቱ ናቸው። የአልኮል ሱሰኛ ባልሆንም በርካታ የቤተሰቤ አባላትና ጓደኞቼ በዚህ ችግር ይሠቃያሉ። በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ከአልኮል ሱሰኝነቱ የተላቀቀው ከሦስት ወር በኋላ እንደሆነ ገልጿል። ግለሰቡ ይህን ለውጥ ያደረገው ለበርካታ ዓመታት በአልኮል ሱስ ከተሠቃየ በኋላ ነው። ያደረገው ለውጥ ቢያስገርመኝም ከሱሱ ለመላቀቅ የወሰደበት ጊዜ ግን ከእውነታው የራቀ እንደሆነና ይህን ችግር ለማሸነፍ የሚታገሉ ሰዎችን ተስፋ እንደሚያስቆርጣቸው ይሰማኛል። ከአልኮል ሱሱ ለመላቀቅ ጥረት የሚያደርግ አንድ ሰው ይህ ችግሩ በተደጋጋሚ ሊያገረሽበት ይችላል።
ጂ. ኤ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ፦ ከአልኮል ሱስ መላቀቅ ቀላል ነው ማለታችን አይደለም። ይህን ሱስ ለማሸነፍ ጥረት የሚያደርጉ በርካታ ሰዎች ችግሩ በተደጋጋሚ ሊያገረሽባቸውና ተስፋ ሊቆርጡ እንደሚችሉ እናምናለን። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአልኮል ሱስ የተላቀቁ ሰዎችም እንኳ ችግሩ እንዳያገረሽባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በመሆኑም በርዕሱ ላይ እንደተገለጸው፣ ቀደም ሲል ‘የአልኮል መጠጥ ባሪያ’ የነበረውና ለአሥር ዓመታት ያህል አልኮል የሚባል ነገር ያልቀመሰው ይህ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች ከዚህ ቀደም ያደረግኩትን ብርቱ ትግል እንዲሁም አንድ ብርጭቆ እንኳ መጠጣቴ ወደነበርኩበት ሕይወት ሊመልሰኝ እንደሚችል አያውቁም። የአልኮል መጠጥ አምሮት አሁንም ያስቸግረኛል። ይሁን እንጂ አልጠጣም ለማለት ከልቤ መጸለይና ባደረግኩት ውሳኔ ቆራጥ መሆን ይጠይቅብኛል።” ብዙ ሰዎች በጸሎት አማካኝነት አምላክ እንዲረዳቸው በመጠየቅ የአልኮል መጠጥ ባሪያ ከመሆን ነፃ ወጥተዋል።—መዝሙር 55:22
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ? (ኅዳር 2007) የ12 ዓመት ልጅ ነኝ፤ በዚህ የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም ላይ ለወጡት ማራኪና ትምህርት ሰጪ ሐሳቦች ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በተለይ ደግሞ በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ እርስ በርሱ የሚስማማ ስለመሆኑ የሚናገረውን ርዕስ ወድጄዋለሁ። ይህ ርዕስ ከዚህ በፊት አስቤባቸው የማላውቃቸውን አንዳንድ ነጥቦች ይዟል። ቀጣዩን የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም በጉጉት እየጠበቅሁ ነው!
ዲ. ኤፍ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች በንቁ! መጽሔት ይዘት ላይ ስለተደረገው ለውጥ ላመሰግናቸሁ እፈልጋለሁ። በአንዳንድ ርዕሶች መጨረሻ ላይ የሚቀርቡት ጥያቄዎች በጣም ጠቅመውኛል። ጥያቄዎቹ በዚያ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች እንዳስታውስና እንዳሰላስልባቸው ረድተውኛል። በዛሬው ጊዜ ሕይወታችን ሩጫ የበዛበት ስለሆነ መጽሔቶችን ስናነብ አስፈላጊና አበረታች የሆኑ አንዳንድ ሐሳቦችን ሳናስተውል ልናልፍ እንችላለን።
ኤም. ኤ. ኤስ.፣ ብራዚል
ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው? (ታኅሣሥ 2007) ከስድስት ወራት በፊት እናቴ አሳዛኝ በሆነ አደጋ ሞተች። ይህን ርዕስ ማንበቤ በጣም ያበረታታኝ ሲሆን እናቴን በትንሣኤ እንደማገኛት ያለኝን ተስፋ አጠናክሮልኛል። ከልብ አመሰግናችኋለሁ።
ኤል. ኤል. አር.፣ ብራዚል
የወጣቶች ጥያቄ . . . የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ያለብኝ ለምንድን ነው? (ኅዳር 2007) ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እስካልፈጸምኩ ድረስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር ምንም ችግር እንደሌለው አስብ ነበር። ሆኖም ከወንድ ጓደኛዬ ጋር እንዲሁ ጊዜ ማሳለፍ ብቻ ደስታ አላስገኘልኝም። በመሆኑም ተገቢ ያልሆነ ምኞት አደረብኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ይህን ትምህርት ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው ወጣቶች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ በማቅረባችሁ በጣም አመሰግናችኋለሁ።
ኢ. ኤፍ.፣ ጃፓን