ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ ፈሳሽ
ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ ፈሳሽ
ውኃ ተአምራዊ ፈሳሽ ነው። ቀላል የሚመስል ሆኖም ውስብስብ የሆነ ውሕድ ነው። እያንዳንዱ ሞለኪውል ሦስት አቶሞች ብቻ ማለትም ሁለት ሃይድሮጂንና አንድ ኦክስጅን ይዟል። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች፣ የውኃ ሞለኪውሎች እንዴት እንደሚሠሩ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። ሁላችንም የምናውቀው ነገር ቢኖር ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ ፈሳሽ እንደሆነና ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከሰውነታቸው ክብደት 80 በመቶው ውኃ መሆኑን ነው። ይህ አስደናቂ ንጥረ ነገር ካሉት ባሕርያት መካከል አምስቱን ብቻ እስቲ እንመልከት።
1. ውኃ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት እያለም እንኳ ከፍተኛ መጠን ያለው ሙቀት በውስጡ አምቆ መያዝ ይችላል፤ ይህ ደግሞ የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ያስችላል።
2. ውኃ ወደ በረዶነት በሚቀየርበት ጊዜ የመስፋት ባሕርይ አለው፤ ይህ ደግሞ በረዶው እንዲንሳፈፍና ከታች ላለው ውኃ እንደ ሽፋን እንዲሆን ያደርጋል። ውኃ እንደ ሌሎች ንጥረ ነገሮች በሚቀዘቅዝበት ጊዜ ክብደቱ የሚጨምር ቢሆን ኖሮ ሐይቆች፣ ወንዞችና ባሕሮች ከታች ጀምሮ ወደ በረዶነት ይቀየሩ ነበር። ይህ ደግሞ በውኃ ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ በበረዶ እንዲቀበሩ ያደርግ ነበር!
3. ውኃ በከፍተኛ መጠን ብርሃን አስተላላፊ ነው፤ ይህም ለመኖር የግድ ብርሃን የሚያስፈልጋቸው በተወሰነ ጥልቀት በባሕር ውስጥ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሕይወት እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል።
4. የውኃ ሞለኪውሎች እርስ በርሳቸው ስለሚሳሳቡ ስስ “ሽፋን” የሚመስል ነገር ይፈጥራሉ። ይህ ደግሞ ጥቃቅን ነፍሳት በኩሬ ውኃ ላይ እንዲሄዱ፣ የውኃ ጠብታዎች እንዲፈጠሩና ሌላው ቀርቶ በጣም ረጃጅም ተክሎች እንኳ ውኃን ከመሬት ወደ ላይ መሳብ እንዲችሉ ረድቷል።
5. ውኃ ከየትኛውም ፈሳሽ ይበልጥ ልዩ የማሟሟት ችሎታ ያለው ፈሳሽ ነው። ውኃ አንድን ነገር እንዲሟሟ በሚያደርግበት ጊዜ በውስጡ ኦክስጅን፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ጨው፣ ማዕድናትንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መያዝ ይችላል።
የምድር የአየር ንብረት የተስተካከለ እንዲሆን ያደርጋል
ውቅያኖሶች የምድርን 70 በመቶ ስለሚሸፍኑ የአየር ንብረትን በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ውቅያኖስና ከባቢ አየር ሙቀትን፣ ውኃን፣ ጋዝን እንዲሁም ነፋስንና ሞገድን ያለማቋረጥ እርስ በርስ በመለዋወጥ አንድ ላይ ተቀናጅተው ይሠራሉ። እንዲሁም የፀሐይን ሙቀት፣ ሞቃታማ ከሆነው ክልል ወደ ዋልታዎች በመውሰድ የተስተካከለ የአየር ንብረት
እንዲኖር ተባብረው ይሠራሉ። አብዛኞቹ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሕይወት እንዲኖሩ የምድር ሙቀት መጠን ውኃ በፈሳሽ መልክ እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆን ይኖርበታል። ሬር ኧርዝ—ኋይ ኮምፕሌክስ ላይፍ ኢዝ አንኮመን ኢን ዚ ዩኒቨርስ የተባለው መጽሐፍ “የምድር ሁኔታ ፍጹም የተስተካከለ ነው” በማለት ዘግቧል።ምድር በአንድ ሌላ ኃይል የተገኘች እንጂ በራሷ የመጣች አይደለችም። ምድርን እንድትገኝ ያስቻለው ኃይል በአጋጣሚ የተገኘ ነው ወይስ ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ አንድ ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ አለ? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ እንደሠራት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 14:15-17) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምድር ንጹሕና ለመኖር ተስማሚ ፕላኔት እንድትሆን ያስቻላትን ዑደት በምንመለከትበት ጊዜ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ እናገኛለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ነው
ምድር በጠፈር ውስጥ ተንጠልጥላለች። “የሰሜንን ሰማይ በሕዋው ላይ ዘረጋው፤ ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት።”—ኢዮብ 26:7፣ በ1613 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተነገረ
ምድር ክብ ናት። “እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል።”—ኢሳይያስ 40:22፣ በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈ
የውኃ ዑደት። “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ . . . ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።”—መክብብ 1:7፣ በ1000 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈ
አጽናፈ ዓለም በሕጎች ይመራል። “የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት [ወይም ሕጎች] ያጸናሁ እኔ [ይሖዋ ነኝ።]”—ኤርምያስ 33:25፣ በ580 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ማግኔቶስፌር፦ NASA/Steele Hill; አውሮራ፦ Collection of Dr. Herbert Kroehl, NGDC; ሪፍ፦ Stockbyte/Getty Images