ከሀብት ይልቅ ብልጫ ያላቸው በረከቶች
ከሀብት ይልቅ ብልጫ ያላቸው በረከቶች
በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ጆን አማካሪ ሆኖ ስለሚሠራ ጥሩ ገንዘብ ይከፈለዋል። ገና በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በመላው ዓለም የተዘዋወረ ሲሆን ብዙ ገንዘብም ማግኘት ችሎ ነበር። እሱና ሚስቱ በጣም ቆንጆ ቤት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ የተንደላቀቀ ሕይወት ይመሩ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት በብዙዎች ዓይን ሲታዩ በጣም የተባረኩ ይመስላሉ።
የአንድ ሌላ ሰው ሁኔታ ደግሞ ተመልከት። ኮስታስ * ከ5,000 ከሚበልጡ አመልካቾች መካከል በአውሮፓ በሚገኝ አንድ የታወቀ ባንክ ውስጥ የሥራ ልምድ እንዲያገኙ ከተመረጡ 80 ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። በጥቂት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ እድገት አድርጎ በመጨረሻ በሌላ ባንክ ውስጥ የአንድ ትልቅ የሥራ ክፍል ኃላፊ ለመሆን በቃ። ይህን ሥራ አቁሞ የራሱን ድርጅት ለመክፈት በሚያስብበት ወቅት የነበረው ዓመታዊ ገቢ ብዙ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ከሚያገኙት ገንዘብ ይበልጣል። ይህ ሰው አምላክ እንደባረከው ይሰማው ነበር።
ይሁንና እነዚህ ሁለት ሰዎች ከቁሳዊ ሀብት ይልቅ ብልጫ ያላቸው በረከቶች እንዳሉ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ፣ በዛሬው ጊዜ ጆን ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት በፈቃደኝነት ተነሳስቶ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራል። ጆን እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ቁሳዊ ብልጽግና ደስታ እንደማያስገኝ ከራሴ ሕይወት ማየትና መማር ችያለሁ። ቁሳዊ ብልጽግና ለማግኘትም ሆነ ያንን ላለማጣት የሚደረገው ትግል ለሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ያሳጣችኋል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት የላቀ ደስታ የሰፈነበት የትዳር ሕይወት፣ የአእምሮ ሰላምና
ጥሩ ሕሊናን የመሳሰሉ ብዙ በረከቶች ያስገኝላችኋል።”ኮስታስ በተመሳሳይ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ የቅንጦት ሕይወት እንድንኖር አይፈልግም። አምላክ ለዕለታዊ ሕይወታችን ከሚያስፈልገን በላይ የሚሰጠንን ማንኛውንም ነገር ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የመጠቀም ግዴታ እንዳለብን በጥብቅ አምናለሁ።” በቅርቡ፣ ኮስታስና ቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለብዙ ሰዎች ለማስተማር ሲሉ ሌላ ቋንቋ መማር ጀምረዋል። ኮስታስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝልን ተገንዝበናል” ሲል ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
በእርግጥም ጆን እና ኮስታስ ከቁሳዊ ብልጽግና ይልቅ መንፈሳዊ በረከቶች እጅግ የላቀ ዋጋ እንዳላቸው ተገንዝበዋል። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳንኤል ጊልበርት እንዲህ ብለዋል፦ “[የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች] በሀብትና በደስታ መካከል ያለውን ዝምድና ለማወቅ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጥናት ካካሄዱ በኋላ በጥቅሉ ሲታይ ሀብት ሰዎች ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያስችለው ከከፋ ድህነት ተላቅቀው ወደ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ እንዲሸጋገሩ የሚረዳቸው ሲሆን ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።” አክለውም “ከዚያ የበለጠ ሀብት ግን ተጨማሪ ደስታ የማስገኘቱ አጋጣሚ የመነመነ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ከመከራ የሚገኝ ትምህርት
ጉዳዩን በማስተዋል የተመለከቱ አንድ ምሑር “አንድ ሰው ከድህነት ከተላቀቀ በኋላ ገቢው መጨመሩ ሊያገኘው ከሚችለው ደስታ ጋር ያለው ዝምድና በጣም ውስን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ባለፈው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ ጋዜጠኛ በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም ከነበሩትና በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ መስክ ቀደምት አምራች ከሆኑት ከአንድሩ ካርኒጊ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት ፈጽሞ የማይረሳ አንድ ትምህርት አግኝቷል። ካርኒጊ እንዲህ ብለውት ነበር፦ “ሰዎች በእኔ ሊቀኑብኝ አይገባም። ያካበትኩት ሀብት ምን ሊረዳኝ ይችላል? አሁን ስልሳ ዓመቴ ነው፤ የምበላው ምግብ እንኳ አይፈጭልኝም። ወጣትነትንና ጤንነትን ማግኘት ብችል ያለኝን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሙሉ እሰጥ ነበር።”
ጋዜጠኛው ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “ሚስተር ካርኒጊ በድንገት ዞር ብለው ዝግ ባለ ድምፅና በቁጭት እንዲሁም
ስሜታቸውን ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታ እንዲህ ብለዋል፦ ‘እንደገና መኖር ብችል ማንኛውንም ነገር በደስታ እሰጥ ነበር።’” በነዳጅ ሽያጭ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያካበተው ጂን ፖል ጌቲ ይህንኑ ሐሳብ በመደገፍ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ገንዘብ ምናልባት ከደስታ ማጣት ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆናል እንጂ ከደስታ ጋር የግድ ግንኙነት አለው ብለን ማሰብ የለብንም።”አንተም እንደሚከተለው ሲል ጥያቄ ካቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ጋር ትስማማ ይሆናል፦ “ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤ ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ። ያለዚያ ግን ያለ ልክ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ‘እግዚአብሔር ማን ነው?’ እላለሁ፤ ወይም ድኻ እሆንና እሰርቃለሁ፤ የአምላኬንም ስም አሰድባለሁ።”—ምሳሌ 30:8, 9
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን “ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ” ሲል ገልጿል። ይሁንና አክሎ “ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር” ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ሰለሞን “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” በማለት ተናግሯል።—መክብብ 2:9-11፤ 5:12, 13፤ ምሳሌ 10:22
ዘላለማዊ በረከቶችን የምናገኝበት መንገድ
ከዚህ በግልጽ እንደምናየው እውነተኛና ዘላቂ ደስታ ማግኘት የምንችለው መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን በሚገባ ካረካን ብቻ ነው። ለአምላክ የመጀመሪያውን ቦታ ከሰጠን በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሁም ደስተኞች እንሆናለን።
ደስ የሚለው ነገር ገንዘብ ለጭንቀት መንስኤ መሆኑ የሚያበቃበት ጊዜ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ስግብግብና በዝባዥ የሆነው የንግዱ ዓለም ለዘለቄታው የሚወገድበት ጊዜ እንደሚመጣ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ከዚያ በኋላ አምላክ የሚያመጣው አዲስ ሥርዓት በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ይሆናል። በዚያ ጊዜ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ምድር ላይ እንዲኖሩ ባደረገበት ወቅት የነበረው የመጀመሪያው ዓላማ ስለሚፈጸም ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። በመላዋ ምድር ላይ ደስታ፣ ሰላምና ፍቅር ሰፍኖ ማየት እንዴት ያለ በረከት ነው!—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ 1 ዮሐንስ 4:8-11
ለአምላክ የመጀመሪያውን ቦታ ከሰጠን ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች ሊሆን ይችላል
በዚያ ጊዜ ሕይወት የማይጥም ወይም አሰልቺ አይሆንም። አምላክ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ያወጣውን የመጀመሪያ ዓላማ ስለሚፈጽም ከመንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ ቁሳዊ በረከቶችም ይኖራሉ። ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ፣ መጠለያና ትርጉም ያለው ሥራ እንደሚኖረው ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። እንዲሁም ድህነት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል።—መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 65:21-23፤ ሚክያስ 4:4
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ፣ በይሖዋ ላይ ልባዊ እምነት ያለው ሰው ሁሉ ለእፍረት አይዳረግም። (ሮም 10:11-13) በመሆኑም ከሀብት ይልቅ ብልጫ ያላቸውን በረከቶች ለማግኘት በአሁኑ ጊዜ ጥረት ማድረጋችን የጥበብ አካሄድ ነው!—1 ጢሞቴዎስ 6:6-10
^ አን.3 ስሙ ተለውጧል።